አጓጊዉ  የኤንቢኤ ፉክክር

0
5

የአሜሪካ ኤንቢኤ (ቅርጫት ኳስ ) የአዲሱ  የውድድር  ዘመን  ፉክክር ተጀምሯል:: በሊጉ 30 ቡድኖች የሚፎካከሩ ሲሆን በአጠቃላይም 82 ጨዋታዎች ይደረግበታል:: ኤንቢኤ ካለፈው ዓመት ፍጹም የተለየ ገጽታ እንደሚኖረውም ይገመታል። ኮከብ ተጫዋቾች እና ተስፋ የተጣለባቸው አዲስ ተጫዋቾች ወደ ሊጉ መምጣት የውድድር ዘመኑን ከምንጊዜውም በላይ አጓጊ እና የማይገመት አድርጎታል።

የኤንቢኤ ኮከቡ ኬቨን ዱራንት የሂዩስተን ሮኬትስ ማሊያን ለብሶ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ ሲገባ ታይቷል፤ ዴሚየን ሊላርድ በበኩሉ ከጉዳት አገግሞ ወደ ቀድሞ ክለቡ ፖርትላንድ ትሬል ብሌዘርስ ተመልሷል:: በሌላ በኩል የምሥራቁ ኮንፈረንስ ቦስተን ሴልቲክስ እና ኢንዲያና ፔሰርስ በከባድ ጉዳት ምክንያት የኃይል ሚዛኑ የሚቀየር ይመስላል። ይህ ሁኔታ እንደ ኒው ዮርክ ኒክስ እና ክሊቭላንድ ካቫሊየርስ ላሉ ቡድኖች ወርቃማ ዕድል ይዞ መጥቷል። አንጋፋው የኤንቢኤ ኮከብ ለብሮን ጄምስ በ23 ዓመታት የቅርጫት ኳስ ስፖርት ህይወቱ ለአምስተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን ተዘጋጅቷል። ሊብሮን ጄምስ ከነርቭ ጋር የተያያዘ ችግር እያጋጠመው እንደሆነ እና የ2025-26 የNBA መደበኛ የውድድር ዘመን የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ሳምንታት እንደሚያመልጠው የኤንቢኤ ዶት ኮም መረጃ አስነብቧል:: የአምናው ሻምፒዮን ኦክላሆማ ሲቲ ተንደር በኤንቢኤ (NBA) ታሪክ ሁለተኛው ወጣት ሻምፒዮን ቡድን በመሆን ታሪክ ሠርቷል። ቡድኑ ዘንድሮም የአምናውን ገድል ለመድገም የባለፈው ዓመት የሊጉን ኮከብ ተጫዋች ሻይ ጊልጀስ አሌክሳንደርን እንዲሁም ቁልፍ ተጫዋቾች የሆኑትን ጄለን ዊሊያምስን እና ቼት ሆልምግሬንን በረጅም ጊዜ የውል ስምምነት በማስፈረም ቡድኑን አጠናክሯል።

የምዕራብ ኮንፍረንስ ተሳታፊው የቡድን ትልቁ ጥንካሬ ጠንካራ የተከላካይ ክፍሉ መሆኑን የያሆ ስፖርት መረጃ አስነብቧል:: ዘንድሮም ለዋንጫ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል:: ኦክላሆማ ሲቲ ባለፈው ዓመት 68 ጨዋታዎችን አሸንፏል፤ ቡድኑ በዚህ ዓመትም ድልን የተጠሙ ወጣት እና ጥልቅ የተጫዋቾች ስብስብ ያለው በመሆኑ የዘንድሮው ብቃቱ ከበፊቱ የተሻለ ሆኖ 70 ጨዋታዎችን በማሸነፍ በኤንቢኤ ታሪክ ሦስተኛው ቡድን ሊሆን እንደሚችል የኤስፒኤን መረጃ አመልክቷል።

በምዕራቡ ኮንፈረንስ ዘንድሮ ከፍተኛ ፉክክር ለማድረግ የተዘጋጁ በርካታ ጠንካራ ቡድኖች እንዳሉ የኤስፒኤን መረጃ ያስነብባል። ከእነዚህ ክለቦች መካከል ዴንቨር ነጌትስ አንዱ ነው:: ክለቡ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ይጨረሳል በሚል የኤንቢኤ ዶት ኮም መረጃ  አስነብቧል:: ኒኮላ ዮኪች ለዓመታት የዴንቨር ነጌትስ የልብ ምት ሆኖ መቆየቱ አይዘነጋም። ሦስት ጊዜ የሊጉ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተሸላሚ የሆነው ዮኪች እንደ ብርጭቆ በቀላሉ ተሰባሪ መሆኑ ግን ቡድኑ ወስጥ ስጋትን  ፈጥሯል:: ዘንድሮ ግን ቡድኑ በዙሪያው የገነባው የተጫዋቾች ስብስብ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል።

የነጌትስ ዋነኛ ድክመት ሁልጊዜም የኋላ ክፍሉ ላይ ነው። ባለፈው የውድድር ዘመን በጥሎ ማለፉ ውድድር ከተሳተፉ ቡድኖች ውስጥ ደካማ የኋላ ክፍል ከነበራቸው መካከል ነጌትስ ቀዳሚው ነበር:: ይህንን ድክመት ማሻሻል ካልቻሉ ግን ለሻምፒዮና መፎካከር ይከብዳቸዋል። እንደ ኤስፒኤን መረጃ ቡድኑ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ዓመቱን ይጨርሳል:: በምዕራብ ኮንፍረንስ የሚገኘው እና በአዲሱ የውድድር ዘመን ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ቡድን ሂዩስተን ሮኬትስ ነው:: የኬቨን ዱራንት ወደ ሂዩስተን ሮኬትስ ማምራት የቡድኑን ተስፋ ከፍ አድርጎታል። ልምድ ያለው ተከላካይ ፍሬድ ቫንቭሊት በጉዳት ምክንያት ከሜዳ መራቁ የዱራንት ሚና በቡድኑ ውስጥ የበለጠ ወሳኝ እንዲሆን አስችሎታል። ዱራንት በሊጉ ውስጥ ካሉ ገዳይ ነጥብ አስቆጣሪዎች አንዱ መሆኑ ቡድን እየመራ ለሻምፒዮና እንዲበቃ ከፍተኛ ጫና ይጠብቀዋል።  ቡድኑ በወጣት ኮከቦች የተሞላ  እና ድል የተራበ መሆኑም ሰፊ ግምት ተሰጥቶታል::

የቡድኑ ትልቁ ጥንካሬ የተጫዋቾች አካላዊ ግዙፍነታቸው ሲሆን እንደ አሜን ቶምፕሰን ፣ ዱራንት ፣ ጃባሪ ስሚዝ ጁኒየር ፣ አልፔረን ሴንጉን  እና ስቲቨን አዳምስ  ያሉ ረዣዥም ተጫዋቾችን ይዘዋል::  ሂዩስተን ሮኬትስ ሦሰተኛ ደረጃ ይዞ እንደሚጨርስ ከወዲሁ ግምት አግኝቷል::

ባለፉት ዓመታት ከምሥራቅ ኮንፈረንስ የበላይነት በጥቂት ቡድኖች መዳፍ ነበር። ነገር ግን የቦስተን ሴልቲክሱ ጄይሰን ቴተም እና የኢንዲያና ፔሰርሱ ታይሪስ ሃሊበርተን በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት የዘንድሮው የኃይል ሚዛን ሙሉ በሙሉ ይለወጣል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ አጋጣሚ ለዓመታት ከፍተኛ ፉክክር ሲያደረጉ ለነበሩ እንደ ክሊቭላንድ ካቫሊየርስ እና ኒው ዮርክ ኒክስ ላሉ ቡድኖች ወደ በጥሎ ማለፉ ፍጻሜ ለመድረስ ወርቃማ ዕድል ይሆናቸዋል::ለክሊቭላንድ ካቫሊየርስ እና ለኮከቡ ዶኖቫን ሚቼል የዘንድሮው የውድድር ዘመን ትርጉም ያለው እንደሚሆን የኤስፒኤን ዘገባ ያስነብባል:: ቡድኑ ባለፈው የውድድር ዘመን 64 ጨዋታዎችን በማሸነፍ አስደናቂ ብቃት ማሳየቱ አይዘነጋም:: ዘንድሮ ደግሞ አራተኛ ደረጃን ይዞ ይጨረሳል የሚል እምነት ተጥሎበታል::

የካቫሊየርስ የማጥቃት አቅም ጠንካራ ቢሆንም የቡድኑ እውነተኛ መሠረት ግን የመከላከሉ ጥንካሬ ነው። እንደ ኤቫን ሞብሊ (የዓመቱ ምርጥ ተከላካይ) እና ጃሬት አለን ያሉ ሁለት ምርጥ እና ጉዳት የማይበግራቸው ታላላቅ ተጫዋቾች መኖራቸው ቡድኑ በ82 ጨዋታዎች  ጠንካራ መከላከል እንዲኖረው ያስችለዋል። ካቫሊየርስ ጥልቅ የተጫዋቾች ስብስብ ቢኖረውም በቀላሉ ከፍተኛ የጉዳት ሰለባ የሚሆን ቡድን ጭምር ነው።

የዘንድሮው የውድድር ዘመን በሁሉም መልኩ ልዩ ሆኖ እንደሚዘልቅ ይጠበቃል:: ኦክላሆማ ሲቲ ተንደር ወጣትነቱን እና ጥልቀቱን ተጠቅሞ ሻምፒዮናውን ማስጠበቅ ይችል ይሆን? ወይስ እንደ ዴንቨር ነጌትስ ያሉ ተፎካካሪዎች ዙፋኑን ይነጥቁታል? በጉዳት የታመሰው የምሥራቅ ኮንፈረንስ ሻምፒዮን ቡድን ዘንድሮ  ያሳየን ይሆን? ኒክስ እና ካቫሊየርስ ይህንን ታሪካዊ ዕድል መጠቀም ይችላሉ? ወይስ አጋጣሚውን አሳልፈው ለሌሎች ቡድኖች ይሰጣሉ?

እንደ ሊብሮን ጄምስ እና ኬቨን ዱራንት ያሉ አንጋፋ ኮከቦች አሁንም በሊጉ ላይ ያላቸውን የበላይነት እና ተጽዕኖ ማሳየት ይችሉ ይሆን? እንዲሁም ኩፐር ፍላግ እና ዲላን ሃርፐር ያሉ ወጣት ተጫዋቾች በሊጉ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ያሳድራሉ? የሚለው  ጥያቄ በግንቦት ወር መጨረሻ ምላሽ ያገኛል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here