አጭሩ በረራ

0
129

በስኮትላንድ ስር በሚተዳደሩት ዌስትሬይ እና ፓፓ ዌስትሬይ በተሰኙ ደሴቶች መካከል ለመጓጓዝ ከሁለት ደቂቃ ያነሰ የጊዜ ምጣኔ የሚወስደው የዓየር ማጓጓዣ አጭር የንግድ የአውሮፕላን በረራ ክብረ ወሰን መያዙን ኦዳቲ ሴንትራል ድረ ገጽ  ለንባብ አብቅቶታል::

አብዛኛው ሰው ለአጭር ጉዞ ታክሲ ወይም አውቶቡስን ይገለገላል፤ ይመርጣል:: በሰሜናዊ ስኮትላንድ ደሴቶች ግን ያሉት አማራጮች ሁለት –  ጀልባች እና አውሮፕላን ብቻ ናቸው:: ከሁለቱ አማራጮች  ጀልባ ብዙ ጊዜ ማዕበል ስለሚበዛው አስፈሪ እና ለአደጋ የተጋለጠ ነው:: ቀሪው  እና የተሻለው ተመራጭ አውሮፕላን ብቻ ነው::

በዌስትሬይ እና ፓፓ ዌስትሬይ ደሴቶች መካከል ያለው ርቀት አንድ ነጥብ ሰባት ማይል ወይም ሁለት ነጥብ 27 ኪሎ ሜትር ነው:: ይህም በበርካታ አውሮፕላን ጣቢያዎች ከሚገኝ ማኮብኮቢያ ጋር ይመጣጠናል:: በመሆኑም በደሴቶቹ መካከል በመጓጓዣነት የንግድ አውሮፕላን መገልገል ግድ ነው:: የንግድ አውሮፕላኑ ስምንት ሰዎችን እና አብራሪውን ብቻ ነው የሚይዘው:: አስተናጋጅም ሆነ ረዳት አብራሪ የለውም::

በደሴቶቹ መካከል የሚደረገው የአውሮፕላን መጓጓዣ በረራ ከ90 እስከ 120 ሰኮንድ ወይም ከ2 ደቂቃ ያነሰ ጊዜን ነው የሚወስደው:: የአየር ሁኔታው ምቹ ከሆነ 53 ሰከንድ የአር ሁኔታው ወይም ግፊቱ አስቸጋሪ ከሆነ ሦስት ደቂቃ እንደሚወስድባቸው አብራሪዎቹ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል::

በዌስትሬይ እና በፓፓ ዌስትሬይ መካከል የሚደረገው በረራ የሚሸፍነው ርቀት አጭር በመሆኑ ለአካባቢው አስፈላጊ አይደለም ተብሎ እንደሚተች የድረ ገፁ ጽሑፍ አስነብቧል:: ሆኖም በዌስትሬይ ደሴት ለሚኖሩት 600 እና በፓፓ ዌስትሬይ ደሴት ለሚኖሩት 90 ነዋሪዎች በእጅጉ አስፈላጊ እና አንገብጋቢ መሆኑ ነው የተገለፀው::

ለአጭሩ የአውሮፕላን በረራ ለጐብኚዎች ከ17 እስከ 45 ፓውንድ መክፈል ግድ ይላቸዋል፤ የደሴቶቹ ነባር ነዋሪዎች የሚጓጓዙ ከሆነ ግን ወጪው በስኮትላንድ መንግሥት እንደሚደጐም ነው ድረ ገፁ በማጠቃለያነት ያስነበበው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሐምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here