የ23 ዓመቱ ህንዳዊ ጋኒሽ ባራያ በቁመቱ ማጠር መድሎ ቢደረስበትም የገጠሙትን መሰናክሎች በጽናት አልፎ በህክምና ሙያ ዲግሪውን ለማግኘት በማጠናቀቂያው የተግባር ልምምድ ላይ መድረሱን ኦዳቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
ጋኒሽ ባራያ በህንድ ጉጅራት ግዛት ታላጃ ታሉካ በተባለ ቦታ ነው የተወለደው::ከደሀ ቤተሰብ በመወለዱ መከራን ከልጅነቱ ጀምሮ ቀምሶታል::እድሜው አራት ዓመት ሲሞላው ወላጆቹ የራስ ቅሉ ከሌላው አካሉ ገዝፎ ማደጉን በማስተዋላቸው ወደ ሀኪም ቤት ይወስዱታል::ነገር ግን ሁነቱን በህክምና መግታት እንደማይቻል ይነገራቸዋል::
እኩዮቹ ቁመቱ በማጠሩ እና በራስ ቅሉ ማደግ ቢሳለቁበትም ትምህርቱን አጥብቆ መከታተሉን ይገፋበታል::
ከዕለታት አንድ ቀን በእርሻ ለሚተዳደሩ አባቱ ልጃቸው ጋኒሽ ባራያ በሰርከስ ቡድን ውስጥ ድንክ ገፀባህሪ እንዲተውን እና 1 ሺህ 200 ዶላር እንደሚከፍሏቸው ፈቃደኝነታቸውን ይጠይቋቸዋል::አባቱ እምቢተኛነታቸውን ይገልፁላቸዋል- ምክንያታቸው ደግሞ ልጃቸው በትርኢት ወቅት ተረጋግጦ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል የሚል ነበር::
ከዚያን ዕለት ወዲህ ልጃቸው ታፍኖ ሊወሰድ ይችላል በሚል ስጋት ወደ ትምህርት ቤት አጅበው ማመላለስ ይጀመራሉ::ከልጅነቱ ጀምሮ የህክምና ዶክተር መሆንን ያልም የነበረው ጋኒሽ ሙሉ አቅሙን ትምህርቱ ላይ ማዋልን ይገፋበታል::በዚሁም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል::
ጋኒሽ በውጤቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብቶ ያለመውን በህክምና ዶክተር ለመሆን ቅጽ ይሞላል::ነገር ግን ቁመቱ ከአንድ ሜትር ያነሰ /ሦስት ጫማ/ በመሆኑ ይከለከላል::
በክልከላው የተበሳጨው ጋኒሽ በህክምና ሙያ ዶክተር ለመሆን ሲያልመው ከነበረው ማንም ሊገታው እንደማይችል ራሱን አሳምኖ በየደረጃው ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ምኒስትሩ፣ አልፎም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ያመለክታል- ጆሮ የሰጠው አልነበረም::በመጨረሻም ተስፋ ሳይቆርጥ ለሀገሪቱ የበላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ማመልከቻ ተሰሚነት /ተቀባይነት/ አግኝቶ ፍትህ ይበየንለታል- በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገብቶ ሦስት ዓመታት ተምሮም ለተግባር ትምህርት ልምምድ ይበቃል::
ጋኒሽ ከሦስት ዓመታት በፊት ዶክተር መሆን አትችልም ተብሎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቢከለከልም ተስፋ ሳይቆርጥ ህልሙን ለመኖር ባደረገው ጥረት በሀገሪቱ የበላይ ፍርድ ቤት ባገኘው ውሳኔ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ጫፍ ላይ መድረሱ እንዳስደሰተው በድረ ገፁ የሰፈረው ጽሑፍ አመላክቷል::
በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ባለው ሦስት ጫማ ወይም 90 ሳንቲ ሜትር ቁመቱ ተመዝግቦ ባይረጋገጥለትም በርካታ ፈተናዎችን ያለፈ አጭሩ ዶክተር መባል እንደማይበዛበት ነው ድረ ገፁ በማጠቃለያነት ያስነበበው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም