አፈርን የሚያክመዉ

0
21

አርሶ አደር ምንባለ ታየ ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ወይንማ አምባየ ቀበሌ ነው። አርሶ አደሩ እንደ ሀገር እያጋጠመ ያለውን  የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እጥረት እና የዋጋ ንረት በመኸር እና በበጋ ልማታቸው ላይ ተጽኖ አሳርፎባቸዋል:: ችግሩን ግን እጆቻቸውን አጣጥፈው አልተቀበሉትም፤  በራስ አቅም ለመፍታት በጓሯቸው በቀላሉ ከሚያገኟቸው  ሊበሰብሱ ከሚችሉ ፍራፍሬዎች፣ ተክሎች፣ አረሞች፣ ቅጠላቅጠሎች፣ ማሳ ላይ ከሚቀር ገለባ እንዲሁም ከሳር በል እንስሳቶች ጽዳጅ /ፍግ/ እና ከሌሎች እያዘጋጁ ጥቅም ላይ ማዋል ከጀመሩ ቆይተዋል:: ለአብነት በ2015/16 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ከቀድሞው በባሰ እጥረት በተከሰተበት ወቅት  ችግሩን መሻገር እንደቻሉ ለበኵር ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት የተፈጥሮ ማዳበሪያ   በመጠቀማቸው ወጫቸውን በግማሽ መቀነስ ችለዋል:: የመሬታቸው የአፈር ለምነት በመሻሻሉም ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ተጠቅመው ያገኙት ከነበረው ምርት  በሄክታር እስከ አምስት ኩንታል ተጨማሪ ምርት ማግኘታቸውንም መስክረዋል::

ለምነቱ በቀነሰ ማሳ ላይ በበቂ መጠን እና በጥራት የተዘጋጀ  የተፈጥሮ ማዳበሪያ  አንዴ ከተጨመረ ሦስት ዓመት እና ከዚያ በላይ የተሻለ ምርት እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት እንዳገኙ የሚናገሩት አርሶ አደሩ፤ ጥቅሙን በመረዳታቸውም ኮምፖስትን ከዓመት ዓመት በተሻለ መንገድ በብዛት እና በጥራት እያዘጋጁ መጠቀም ከጀመሩ ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። አርሶ አደር ምንባለ አሁን ላይ ለ2018/19 የምርት ዘመን የሚሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ላይ ናቸው:: በዓመት እስከ 20 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ቢያንስ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ጥቅም ላይ ያውላሉ::

አርሶ አደሩ  በግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት በሚደረግላቸው ሙያዊ ድጋፍ (በዋናነት ግንዛቤ ፈጠራ) በቆሎ፣ ስንዴ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ  ኮምፖስት ተጠቅመው አምርተዋል። ወደ ፊትም የመሬታቸውን የአፈር ለምነት በሚጠብቀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመጠቀም ተግተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የአርሶ አደር ምንባለን  ሀሳብ መነሻ አድርገን  ለምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ በዞኑ  የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት እየተሠራ ያለውን ተግባር፣ የመሬትን ለምነት በመጠበቅ፣ ወጭን በመቀነስ…ያለው የጎላ ጥቅም ምንድን ነው? ስንል ጥያቄ አንስተን ነበር:: የመምሪያው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ባለሙያ አቶ በላይነህ ጌትነት ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የአፈርን ተፈጥሯዊ ይዘት ለማሻሻል ያለመ መጠነ-ሰፊ የኮምፖስት ዝግጅት ንቅናቄ ቀደም ብሎ ተጀምሯል።  ንቅናቄው እየተመናመነ የመጣውን የአፈር ለምነት በማሻሻል አርሶ አደሩ ከኬሚካል ማዳበሪያ ጥገኝነት ወጥቶ በተፈጥሯዊ መንገድ ምርቱን እንዲያሳድግ ለማስቻል ያለመ ነው። የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለተክሎች አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ለመስጠት፣ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል፣ የውኃ መያዝ ችሎታን እንዲሁም የሰብል እና ፍራፍሬ ምርቶችን ለመጨመርም  ያስችላል::

የሰብል ልማት ባለሙያው እንዳሉት በተያዘው በጀት  ዓመት በመደበኛ ኮምፖስት አምስት ሚሊዮን 217 ሺህ 380 ሜትር ኪዩብ  ኮምፖስት ለማዘጋጀት ታቅዶ  አምስት ሚሊዮን 164 ሺህ 710 ሜትር ኪዩብ ማዘጋጀት ተችሏል። ይህም 131 ሺህ 344 ሄክታር መሬት ላይ ጥቅም ላይ ለማዋል ነው:: ሌላው ቨርሚ ኮምፖስት ሲሆን 60 ሺህ 270 ኩንታል በማዘጋጀት ሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጥቅም ላይ ለማዋል ታቅዶ እስከ ኅዳር 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 30 ሺህ 238 ኩንታል ማዘጋጀት ተችሏል።

በተጨማሪም 18 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ ባዮ- ሳላሪ ኮምፖስት በማዘጋጀት ሁለት ሺህ 313 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 16 ሺህ 162 ሜትር ኪዩብ ኮምፖስት  ተዘጋጅቷል። እስከ ኅዳር 30 ቀን 2018 ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካትም ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሰብል እድገት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በተመጣጠነ ሁኔታ የያዘ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ለምርት እድገት እና የአፈር ለምነትን ለመጨመር ወሳኝ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል:: ኮምፖስትን ለማዘጋጀትም የሚያስፈልጉ ቁስ አካላት እርጥበት፣ የአየር ሁኔታ፣ ጥሩ የማብላላት ሂደት ናቸው:: በመሆኑም አርሶ አደሩ በተለይ የርጥበት ጊዜው ሳያልፍ ፈጥኖ ማዘጋጀት እንዳለበት መክረዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሚያዘጋጁበት ጊዜ ሁለት አይነት  ዘዴዎች መኖራቸውንም ባለሙያው  አመላክተዋል:: በአብዛኛው ቀዝቃዛ የአየር ንብረት እና ዝናብ በሚኖርበት አካባቢ ከመሬት በላይ በመከመር ማዘጋጀት አንዱ ዘዴ ነው:: ሌላው በጉድጓድ ውስጥ በመቅበር በሞቃታማ እና በደረቅ አካባቢ የሚዘጋጅ የኮምፖስት አይነት ነው::

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አቶ አጠቃ አይቸው በበኩላቸው ለበኵር እንደተናገሩት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ እና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደ ክልል በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በተለይ ከአፈር ለምነት ማሻሻያ ተግባራት ውስጥ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም አንዱ እና ዋነኛው ተግባር ሆኖ እየተተገበረ ነው።

ክልሉ አምራች ቢሆንም በተከታታይ ዓመታት በመታረሱ፣ በአንድ ማሳ ላይ በተከታታይ ዓመት ተመሳሳይ ሰብል መመረቱ እና  ያለባለሙያ ምክረ ሐሳብ ከፍተኛ የሆነ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉ በአፈሩ  ለምነት ላይ ከፍተኛ ችግር ተጋርጦበታል። ከችግሮቹ መካከልም  የአፈር አሲዳማነት ተጠቃሽ  እንደሆነ አቶ አጠቃ ጠቁመዋል:: ይህንን በአሲዳማነት  የተጠቃ እና የለምነት ችግር የገጠመውን መሬት ወደ ነበረበት ለመመለስ ባለፉት ዓመታት የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በመሠራቱ ሲናር ሲያበቅል የነበረው መሬት አሁን ላይ ስንዴ ማምረት መቻሉን በማሳያነት ጠቁመዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ በተለይ ከአፈር ለምነት ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ሰፊ አስተዋፅኦ እያስገኘ ነው።

ሌላው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ የሚለየው የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ምርት እና ምርታማነትን የሚጨምር ብቻ ሲሆን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ደግሞ የሰብል ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ የአፈርን ለምነት ይጨምራል። “ለዚህም ነው የተፈጥሮ ማዳበሪያን በዚህ መንገድ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለነው“በማለት የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቆሙት::

በክልሉ ለ2018  የመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል 76 ሚሊዮን 589 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (መደበኛ ኮምፖስት) ለማዘጋጀት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱንም ባለሙያው ገልጸዋል። መረጃውን እስካጠናቀርንበት ኅዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 76 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ጥራቱን የጠበቀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን ነው ባለሙያው ያስታወቁት።

አቶ አጠቃ አክለውም 599 ሺህ 450 ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት ለማምረት ታቅዶ እስካሁን 317 ሺህ 755  ኩንታል ተዘጋጅቷል። በተጨማሪም 216 ሺህ 170 ሜትር ኪዩብ በላይ ባዮሳላሪ ለማዘጋጀት ታቅዶ 153 ሺህ 347 ሜትር ኪዩብ ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል።

አርሶ አደሮች የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ መሬት ላይ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል እና አዋጭ በመሆኑ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያን የአርሶ አደሩን ወጪ የሚቆጥብ፣ ለጤና እና ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ፣ የአፈር ለምነትን ለረጅም ጊዜ የሚጠብቅ እና በቀላሉ የሚተገበር በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ የሚያዘጋጀውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥራቱን መሰረት ማድረግ እንዳለበትም አመላክተዋል። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአግባቡ በሚገባው ቦታ ተቀምጦ፣ በሚገባው ምክረ ሀሳብ መሰረት ከአፈር ጋር በተገቢው መንገድ ተቀላቅሎ የአፈርን እና የሰብልን ምርታማነት በመጨመር የታለመለትን ግብ እንዲመታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው:: የችግር ጊዜ መውጫ መንገድ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ መጠቀም በመሆኑ ሁሉም በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።

 

መረጃ

 

ኮምፖስት በሚዘጋጅበት ወቅት መካተት የሌለባቸው ግብዓቶች

 

ዘር ያፈሩ የአረም ተክሎች

የባህር ዛፍ ቅጠል

የተለያዩ ቀለማትን የያዙ ወረቀቶች

በበሽታ የተጠቁ እጽዋቶች

የማይበሰብሱ ልዩ ልዩ ቁሶች

የብረት ነክ ቁሶች እና የነዳጅ ውጤቶች

አጥንት፣ ስብ፣ ማናቸውም የዓሳ ግልፋፊዎች እና መሰል መካተት እንደሌለባቸው ከግብርና ሚኒሥትር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው  መረጃ  ያመለክታል፡፡

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር 22 ቀን 2018  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here