አፍላቶክሲን ምንድን ነው?

0
181

በሀገራችን የተኃሳስ ወር ዓመታዊው የበርበሬ ሰብል የሚደርስበት በመሆኑ አብዛኛው ሰው በዚህ ወር በርበሬ ያዘጋጃል:: እኛም ባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው በአቡነሀራ የገበያ ስፍራ ተገኝተናል:: አብዛኛው ሸማች ትኩረት አድርጎ የሚገዛው ስለዋጋው እንጅ ስለ በርበሬ ጥራቱ አልነበረም:: እኛም አንዳንድ ሸማቾችን ስለ አፍላቶክሲን የሚያውቁት ነገር ካለ በሚል ለጠይቅናቸው ጥያቄ ሁሉም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነግር ግን ሲያዩት ቀለሙ ጥቁር ደም የሚመስል ቀለም  ያለውን እና ያልተሰባበረ የበርበሬ ዛላ እንደሚገዙ አጫዎቱን:: ከዛ ውጭ ግን በርበሬ ጤና ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ግንዛቤው እንደሌላቸው ነው የተናገሩት::

እኛም በዛሬው የጤና አምድ ጽሑፋችን  ስለ አፍላቶክሲን ምንነት፣ የሚያስከትላቸው ጉዳቶች፣ መንስኤዎቹ እና መከላከያውን በተመለከተ በባሕር ዳር ዩኒቭርሲቲ  የኬሚካል እና ምህንድስና ፋኩልቲ የምግብ ደህንነትና ጥራት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና ስለ አፍላቶክሲን ጥናት ካደረጉት አድማሱ ፋንታ (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርገናል! መልካም ንባብ!

ዶክተር አድማሱ ፋንታ እንዳብራሩት አፍላቶክሲን (Aflatoxin) በአፈር፣ በበሰበሰ ቁስ እና በሰብል ውስጥ በሚገኙ ፈንገሶች (molds) የሚመረት እጅግ አደገኛ መርዝ ነው:: አስፐርጊለስ ፍላቨስ (Aspergillus flavus) እና አስፐርጊለስ ፓራሲቲከስ (Aspergillus parasiticus) የተባሉት ፈንገሶች ደግሞ መንስኤዎች ናቸው፤ በተለይ ሙቀት እና እርጥበት በሚበዛበት ቦታ የተቀመጡ ምግቦች ለአፍላቶክሲን የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው::

ሰብሎች በተገቢው መንገድ ተሰብስበው እና ደርቀው በተገቢ መንገድ ካልተከማቹ ለአፍላቶክሲን የመጋለጥ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው:: በተለይ ግን በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ አፍላቶክሲን በተደጋጋሚ የሚገኝባቸው ሰብሎች በቆሎ፣ በርበሬ፣ ለውዝ፣  የቅባት  እህሎች፣ የእንስሳት መኖ እና ተዋጽኦ ውስጥ ነው::

በሀገራችን አፍላቶክሲን የሚፈጠረው ሰብሉ ተሰብስቦ በሚከማችበት ወቅት እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ:: ለአብነትም በርበሬ ላይ አፍላቶክሲን እንዴት እንደሚፈጠር ሲያስረዱ::

አርሶ አደሩ በርበሬውን በሚፈለገው ደረጃ ሳያደርቅ በሚያከማችበት ጊዜ እና ለነጋዴው አስረክባለሁ ብሎ በሚያስብበት ጊዜ እንዳይሰባበር በሚል ውኃ በሚያርከፈክፍበት ወቅት ችግሩ መፈጠር ይጀምራል::

ነጋዴውም እስኪሸጥ በሚል እንዳይሰባበር እና ሚዛን እንዲያነሳ በሚል ድጋሚ የደረቀው በርበሬ ላይ ውኃ አርከፍክፈው በማዳበሪያ ወይም በጆንያ አፍነው ያስቀምጡታል:: በደረቅ እና በእርጥበት መካከል የሚገኘው በርበሬም አፍላቶክሲን ማመንጨት ይጀምራል::

ዶክተር አድማሱ እንዳስገነዘቡት ብዙ ጊዜ አፍላቶክሲን በዓይን የሚታይ አይደለም፤ ሆኖም ግን አንዳንድ የሻገቱ የበርበሬ ዛላዎች  ይኖራሉ:: እነዚህ ሻጋታዎችም በአፍላቶክሲን የተጠቁ ሊሆኑ ይችላሉ::

ባለሙያው እንዳብራሩት በርበሬ የእርጥበቱ ደረጃ 12 በመቶ እስኪሆን ድረስ መድረቅ አለበት:: ከዚያ በታች ከደረቀ ይሰባበራል:: እንዲሁም ከ12 በመቶ በላይ ከደረቀ ደግሞ ለአፍላቶክሲን ይጋለጣል:: ባለሙያው ጥናት ባካሄዱበት የበርበሬ አምራች ወረዳ አርሶ አደሮች ላይ ያገኙትን ውጤት ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት በርበሬን ከማሳቸው ላይ ሰብስበው በማዳበሪያ ጆንያ ካስቀመጡ በኋላ ለነጋዴዎች ለመሸጥ ሲያስቡ ከሦስት ቀናት በፊት ውኃ ያርከፈክፉታል:: ይህም ለጤና ጎጂ ነው:: አፍላቶክሲን በበርበሬው ቀለም ላይ ብዙ ተጽዕኖ ላይፈጥር እንደሚችል ልብ ይሏል::

አፍላቶክሲን የሚያስተከትለው ጉዳት

ዶክተር አድማሱ ፋንታ እንደሚናገሩት ሰዎች ለአፍላቶክሲን የሚጋለጡት  አፍላቶክሲን ያለባቸው ምግቦችን በቀጥታ በመመገብ ነው:: በተጨማሪም የተበከለ መኖ የተመገቡ የእንስሳት አስተዋጽኦን (ስጋ፣ ወተት) በመመገብ፣ በአፍላቶክሲን ከተጠቃ ሰብል የሚወጣ ብናኝን በአየር አማካኝነት ወደ ውስጥ በማስገባት ተጋላጭ ይሆናል::

አፍላቶክሲን ጉበትን ይጎዳል፤ የጉበት ካንሰርም (ሄፓቶሴሉላር ካንሰር) ያመጣል:: የሰውነት በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል፣ በልጆች ላይም የዕድገት ውስንነትን ወይም መቀንጨርን ያስከትላል:: አፍላቶክሲን ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ የሰብል ጥራት እንዲቀንስና የአርሶ አደሮች ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል:: በተጨማሪም ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ያሳጣል::

አፍላቶክሲንን ለመከላከል

አፍላቶክሲንን ለመከላከል ምን መደረግ አለበት? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም ዶክተር አድማሱ  ፋንታ በኢትዮጵያ ስለ አፍላቶክሲን እና ጤና ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት በቂ ግንዛቤ እንደሌለ አንስተዋል፤ መንግሥት አፍላቶክሲን በጤና ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ለአርሶ አደሮች፣ ለነጋዴው እና ለተጠቃሚው ግንዛቤ መፍጠር እንዳለበትም ጠቁመዋል:: ለአርሶ አደሮች  የበርበሬ እርጥበት መጠንን የሚለዩበት መሣሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ ቢቅርብላቸው እንዲሁም በሚያከማቹበት ጊዜም አየር የማያስገባ ከረጢት እንዲጠቀሙ እገዛ ቢያደርግ ችግሩ ይፈታል ነው ያሉት::

ምግብ ለማብሰል የምንጠቀመው የሙቀት ኃይል አፍላቶክሲንን ሙሉ በሙሉ አያጠፋም:: በመሆኑም ከአፍላቶክሲን የምንጠበቀው ከመጀመሪያው እንዳይፈጠር ስናደርግ ብቻ ነው:: አፍላቶክሲንን ለመከላከል በመጀመሪያ አርሶ አደሩ ገና ከማሳ ሲሰበስብ በትክክል ደርቋል ወይ የሚለውን ማረጋገጥ፣ ሲያሰጣም ደራርቦ አለማስጣት፣ በስሱ ማስጣት፣ በአንድ ማስጫ ብቻ አለማስጣት፣ እያገላበጡ ማስጣት፣ ባዶ መሬት ላይ አስጥቶ አለማድረቅ፣ እንዲሁም በትክክለኛው የመድረቅ ደረጃ ከደረሰ በኋላ አየር በማያስገባ ከረጢት ማስቀመጥ ተገቢ ነው::

ነጋዴውም ከአርሶ አደሩ የገዛውን በርበሬ ውኃ ሳያርከፈክፍ ለተጠቃሚው መሸጥ እንዳለበትም አስገንዝበዋል:: ሆኖም ተጠቃሚዎች ከቻሉ በርበሬ ሲገዙ ያልተሰባበረ፣ ቀለሙ ያልነጣ፣ ደረቅ የሆነን መርጠው ቢገዙ የተሻለ እንደሆነ እና ውስጡም ያልሻገተ መሆኑን ለመለየት እየሰነጠቁ ቢያዩ ሲሉ ነው ሙያዊ ምክረ ሐሳብ ያቀረቡት::

እያንዳንዱ የበርበሬ ዛላ ውስጡ ፈንገስ ያለው ነው ወይስ የሌለው የሚለውን ለይተው መግዛት እንዳለባቸውም አስረድተዋል:: የምግቦችን ደኅንነትን ለማረጋገጥ የቁጥጥር አካላት የአፍላቶክሲን መጠን ያላቸውን ምግቦችን በተለይም ገበያ ውስጥ ያሉ ምግቦችን መመርመር አስፈላጊ ነው ብለዋል::

በተጨማሪም የመከላከያ መንገዱ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ (farm–to–fork) መሆን አለበት ነው ያሉት:: በሽታን የሚቋቋም ዘር (resistant varieties) መጠቀም፣ ትክክለኛ የእርሻ አስተዳደር መተግበር (እርጥበትን መቆጣጠር)፣ ተባዮችን መቆጣጠር፣  እህልን ከማስፈጨት በፊት መፈተሽ አፍላቶክሲንን ለመከላከል ያስችላሉ ብለው ያቀረቧቸው ምክረ ሐሳቦች ናቸው::

በፖሊሲ እና በሕብረተሰብ ደረጃ የምግብ ደኅንነት መመሪያዎችን ማጠናከር፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለነጋዴዎች እና ለተጠቃሚዎች (ሸማቾች) ስለአፍላቶክሲን ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም የአፍላቶክሲን ምርመራ ቤተሙከራዎችን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ ነው ዶክተር አድማሱ ያስረዱት::

ጤና አዳም

 

ይህን ያቁ ኖሯል?

*አፍላቶክሲን በበቆሎ፣  በጥጥ ፍሬ፣ በለውዝ እና በቅባት እሕሎች ላይ ይገኛል፡፡

*ምግብን ማብሰል ወይም ማቀዝቀዝ አፍላቶክሲንን አያጠፋውም፡፡

* በአፍላቶክሲን የተመረዘ ምግብ የተመገቡ ሰዎች  ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የሆድ ህመም እና ሌሎች የከፍተኛ የጉበት ጉዳት ምልክቶችን ሊያሳዩ ይችላል፡፡

*ሰዎች የተበከሉ ሰብሎችን በመመገብ ወይም የተበከለ መኖን ከበሉ እንስሳት ሥጋ ወይም የወተት ተዋጽኦዎች ምክንያት  ለአፍላቶክሲን ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የግብርና ሠራተኞችም የተበከሉ ሰብሎችን እና መኖዎችን በሚሰበሰቡበት ጊዜ እና ወደ ምግብነት ለመለወጥ በሚደረገው የማቀነባበር ሂደት የሚፈጠረውን አቧራ ወደ ውስጥ በመተንፈስ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡

ምንጭ፡- https://www.cancer.gov/

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የታህሳስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here