አፍሪካዊው አቦ ሸማኔ

0
184

የወቅቱ የአፍሪካ ፈጣኑ የመቶ ሜትር ሯጭ ነው:: እንደ ሮኬት ይፈጥናል፤ በወጣቶቹ መድረክ የክብረ ወሰን ባለቤት ጭምር ነው፤ ጥረቱ፣ ጥንካሬው፣ ከእድሜው በላይ የበሰለ አትሌት ነው- ቦትስዋናዊዉ የአጭር ርቀት ሯጩ ሌቲሲል ቴቦጎ። በመጪዎቹ ዓመታት በአትሌቲክሱ ዘርፍ በአጭር ርቀት የአቦ ሸማኔውን ዩዜን ቦልት ተተኪ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል ይህ የ20 ዓመቱ ወጣት አንዱ ነው።
ሌቲሲል ቴቦጎ በ2023ቱ የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከአሜሪካዊው ኖህ ሎየልስ በመተናነቅ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ከወጣት አትሌት ወደ ዓለም አቀፍ አትሌትነት የተሻገረበት እንደነበር በርካቶቹ መስክረውለታል። ቴቦጎ ግንቦት 10 1997 እ.አ.አ ከቦትስዋና ዋና ከተማ ጋቦሮኒ በ83 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ ካኒ ነው የተወለደው።
የአካል ብቃት አስፈላጊነትን ከተገነዘበ ቤተሰብ የተወለደው አትሌት የአትሌቲክሱን ዘርፍ ለመቀላቀል ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል:: ተሰጥኦው እና ፍጥነቱም ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ነው የመጪው ዘመን የአጭር ርቀት ንጉስ ሊሆን እንደሚችል ያመላከተው።
ገና በስድስት ዓመቱ እግር ኳስ ሲጫወት ፈጣን እና ጎበዝ ባለተሰጥኦ ተጫዋች እንደነበረም የታሪክ ማህደሩ ያስረዳል። ነገር ግን የሚያጋጥመው ተደጋጋሚ ጉዳት ከእግር ኳስ ይልቅ የአትሌቲክስ ስፖርትን እንዲመርጥ አስገድዶታል።
“ሰውን አልፌ እሮጥ ነበር እና ሜዳሊያዎችን እወስድ ነበር።በእግር ኳስም ፈጣን እና ጥሩ ተጫዋች ነበርኩ። ይሁን እንጂ በእግር ኳስ ተደጋጋሚ ጉዳት ሲደርስብኝ ተስፋ ቆርጬ ሩጫው ላይ አተኮርኩኝ” ይላል ቶቦጎ::
በ2016 እ.አ.አ የቦትስዋና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስፖርት ማህበር ሻምፒዮና ላይ በመቶ ሜትር ፣በሁለት መቶ ሜትር ፣በአራት በመቶ የዱላ ቅብብል ሩጫን አሸንፏል። በዚህ አስደናቂ ውጤት የተደነቁት የቦትስዋና አትሌቲክስ ፌደሬሽንም ሳይውል ሳያድር ለብሄራዊ ቡድኑ በ13 ዓመቱ ጥሪ አድርጎለታል። ታዳጊው ቴቦጎ በናሚቢያ በተካሄደው የደቡብ አፍሪካ የትምህርት ቤቶች ሻምፒዮና ለሀገሩ በሁለት መቶ ሜትር ፣በአራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል በቅደም ተከተል የነሐስ እና የብር ሜዳሊያን አስገኝቷል።
አትሌት ሌቲሲል ቴቦጎ ምንም እንኳ በሚሳተፍባቸው ሁሉም መድረኮች ውጤታማ ቢሆንም እስከ 2019 እ.አ.አ ድረስ የሩጫ ውድ ድርን እንደ ቁም ነገር እና ዋና ሙያው አድርጎ አይመለከተውም ነበር።
እንደ ቦትስዋና ጋዜጣ መረጃ ፣እ.አ.አ 2020 በኬኒያ ናይሮቢ የተደረገው የዓለም ሻምፒዮና ግን የወጣቱን ድንቅ አትሌት አመለካከት ቀይሮታል።
በተወዳደረበት መቶ ሜትር በማሸነፍ ተፈጥሮ የሰጠችውን ፀጋ በመጠቀም ራሱን ለሌላ ፈተና ማዘጋጀት ጀመረ። ጠንክሮ በመሥራትም በዓለም አቀፍ መድረክ በመቶ ሜትር ርቀት ሜዳሊያ ለሀገሩ ያስገኘ ብቸኛው ቦትስዋናዊ መሆን ችሏል::
እ.አ.አ ከ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ኒጄል አሞስ ቀጥሎ በርቀቱ ለቦትስዋና ሜዳሊያ የወሰደ ሁለተኛው አትሌትም ነው- ቴቦጎ።
በ2022 እ.አ.አ በኮሎምቢያ ካሊ በተደረገው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዩና ላይም በመቶ ሜትር ርቀት ማሽነፉም ይታወሳል። ዓለም በጉጉት በሚጠብቀው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ፣መቶ ሜትሩን ርቀት ዘጠኝ ሰከንድ ከሰማንያ አራት ማይክሮ ሰከንድ በመሮጥ ለቦትስዋና ታሪካዊውን የብር ሜዳሊያ በማስገኝት በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርጓል።
በጃፓን ቶኪዮ የፈፀመው ገድልም ለበርካታ አትሌቶች በትጋት እና በቁርጠኝነት ህልማቸውን እንዲያሳኩ አነሳስቷል። በተለያዩ የዲያመንድ ሊግ ውድድሮችም ከርቀቱ ታላላቅ አትሌቶች አንድሬ ግሬሲ እና ክርስቲያን ኮማን ከፍተኛ ትንቅንቅ በማድረግ የአትሌቲክስ ቤተሰቡን “አጃኢብ” አሰኝቷል። ቴቦጎ በቅርብ ዓመታት ውስጥም የፕላኔታችን ፈጣኑ ሰው ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ታታሪነቱ ፣ጥንካሬው፣ ተሰጥኦው ፣ለሙያው ያለው ክብር እና ወጣትነቱ በበርካታ የአትሌቲክስ ተንታኞች ዘንድ ከፍተኛ ግምት እንዲሰጠው አድርጎታል። በርካቶችም የዩዜን ቦልትን የወጣትነት ዘመን በማስታወስ ከእርሱ ጋር እያነፃፀሩት ይገኛሉ።
አቦ ሸማኔው ዩዜን ቦልት እ.አ.አ በ2008 በቤጂንግ የዓለም ሻምፒዮና አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ የምድራችን የአጭር ርቀት ንጉስ መሆኑን አስመስክሯል። በዚህ ርቀት ላለፉት 14 ዓመታት የጃማይካዊውን የቀድሞ አትሌት ክብረ ወሰን የሚያሻሽል አትሌት እስካሁን አልተገኝም።
አትሌት ቴቦጎ ከመቶ ሜትር ይልቅ በሁለት መቶ ሜትር ርቀት መወዳደርን ምርጫው ያደርጋል።በ2022 በፈረንጆቹ የጊዜ አቆጣጠር በሞሪሺየስ ሴንትፔር በተደረገው የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ በተፎካከረበት ሁለት መቶ ሜትር ያሸነፈ በእድሜ ትንሹ አትሌት ለመሆን በቅቷል።በ2023 የዲያመንድ ሊግ የዙር ውድድር በተለይ በለንደን የተደረገውን ውድድር ፈጣን ስዓት በማስመዝገብ አሸንፏል።
የተወዳደረበትን ሁለት መቶ ሜትሩን አስራ ዘጠኝ ሰከንድ ከሃምሳ ማይክሮ ሰከንድ በመሮጥ በሀገሩ ልጅ ፍራንኪ ፍሬድሪክሰን ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ጭምር በማሻሻል ነው ያሸነፈው።
ቴቦጎ በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከልም አንዱ ሆኗል። አፍሪካውያን ከሚታወቁባቸው የረዥም እና የመካከለኛ ርቀት ሩጫ በተጨማሪ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአጭር ርቀትም ከተሳትፎ በዘለለ ውጤታማ ስለመሆናቸው የቴቦጎ ውጤት ትልቅ ማሳያ ነው።
በእርግጥ ደቡብ አፍሪካ፣ናሚቢያ፣ናይጀሪያን የመሳሰሉት ሀገራት በአጭር ርቀት ከአፍሪካ የተሻለ ስም ያላቸው ሀገራት ናቸው።
የደቡብ አፍሪካውያኖቹን ኢካኒ ሲምባኒ እና የፈርዲናንድ ኦማንዶላን ፣ የናይጀሪያዊው ኦዶዶ ቹዲን በአጭር ርቀት በተለይ ደግሞ ሁለት መቶ ሜትር ተስፋ የተጣለባቸው አትሌቶች ናቸው። ሌቲሲል ቴቦጎም በዚህ ርቀት ከእነዚህ አፍሪካውያን አትሌቶች ጋር የአፍሪካን ስም ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በዓለም አቀፍ መድረክ የቴቦጎ አንፀባራቂ ድል በቦትስዋና ምድር ሌሎችን ተወርዋሪ ኮከብ አትሌቶች ለማፍራት በር ከፍቷል። ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቃቱ እየጨመረ የመጣው ሌቲሲል ቴቦጎ በርቀቱ የዩዜን ቦልትን ክብረ ወሰን ሊያሻሽል ይችላል ወይ? የሚለው በብዙዎቹ አዕምሮ የሚመላለስ ጥያቄ ነው።
ቦትስዋናዊው የአትሌቲክስ ኮከቡ ግን ያንን ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም ተአምር እንደሚሰራ ይናገራል።
በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክም ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ መሆን ችሏል::

ቦትስዋና እንዴት በአጭር ርቀት ስኬታማ ሆነች?
ቦትስዋና በደቡቡ የአፍሪካ ክፍል የምትገኝ ሀገር ስትሆን ከዚምባቡዌ ፣ከዛምቢያ ፣ከአንጎላ፣ ከናሚቢያ እና ከደቡብ አፍሪካ በድንበር የምትዋሰን ሀገር ናት።አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላትም ይገመታል። ሀገሪቱ በፈረንጆቹ ሚሊኒየም መንግስት አዲስ የስፖርት ፖሊስ በማፅደቅ ውጤታማ መሆን ችላለች።
ቦስትስዋና አሁን እየሰራችበት ያለችው የስፖርት ፖሊሲዋም ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ እንደሚሆን የኦሎምፒክ ዶት ኮም (Olympic .Com) መረጃ ያመለክታል።ይህ ሁሉ አስደናቂ ተግባር እና ውጤት ቦትስዋና በቀላሉ እንዳላገኘችውም ድረ ገጹ ያስነብባል።
ቦትስዋናውያን ለአትሌቲክስ ስፖርት ያላቸው አነስተኛ ግንዛቤ፣የገንዘብ እና የባለሙያ እጥረት፣ በቂ የስፖርት መሰረተ ልማት አለመኖር፣ መንግሥት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅት ደካማ መሆን፣ሴቶችን ጨምሮ ህዝቡ ለአትሌቲክስ ስፖርት ያለው ተሳትፎ አነስተኛ መሆን አትሌቲክስን በቦትስዋና ምድር ለማስፋፋት መሰናክል የነበሩ ናቸው። እነዚህን ሁሉ ችግሮች በመስበር የቦትስዋና ስፖርት ሚኒስቴር ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ጋር በመቀናጀት የአጭር እና የረዥም ጊዜ እቅድ በመንደፍ ውጤታማ መሆን ችለዋል።
የስልጠና ሂደቱን በማዘመን፣ከአልኮል ድርጅቶች ጋር በአጋርነት በመሥራት ሰፊ የሚዲያ ሽፋን በመስጠት በተለያየ የእድሜ እርከን ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት፣ በትምህር ቤቶች ደረጃ የአትሌቲክስ ስፖርት በሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ እንዲሰጥ በማድረግ ውጤታማ ማድረግ ችለዋል።
በኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የተለያዩ መድረኮች የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ የሚያደርጉ አትሌቶች በየ ጊዜው እየወጡ ቢሆንም ያለውን እምቅ አቅም እና ተሰጥኦ ግን በሚገባ እየተጠቀንምበት እንዳልሆነ የዘርፉ አሰልጣኞች እና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት ውጤታማ ልትሆን የምትችልባቸው ፍንጮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታይተዋል። ይህንን ተሰማሚ የአየር ንብረት በመጠቀም በዘርፉ በሁሉም ርቀት በምን መልኩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል በኩር ጋዜጣ ዝግጅት ከአትሌቲክስ ባለሙያ ጋር ቆይታ በማድረግ በሌላ እትሟ ለአንባቢያን ይዛ የምትቀርብ ይሆናል:: የመረጃ ምንጮቻችን ኦሎምፒክ ዶት ኮም እና ወርልድ አትሌቲክስ ቦትስዋና ጋዜጣ ናቸው።

(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here