መካከለኛው ምስራቅ ከባድ አለመረጋጋት የተፈጠረበት ክልል ነው። በዚህ ታሪካዊ ክልል በታሪክ ውስጥ እንደተመለከተው መደበኛ ያልሆነ በኢራናውያን የሚመራ ወይም የሚደገፍ የወታደራዊ እና ፖለቲካዊ የትግል ጥምረት አለ፥ አክሲስ ኦፍ ረዚስታንስ ይሉታል።
ይህ ጥምረት ኦክቶበር 7 ቀን 2023 ቀን ሃማስ ባደረገው ጥቃት ላይ የአለማቀፉን ማህበረሰብ የሳበ የተለያዩ በቀጣናው የተነሱ ቡድኖች ለአንድ አላማ ሲታገሉ ታይቶ ነበር። ይህ ህብረትም ዛሬ የታየ ሳይሆን ለተመሳሳይ አላማ የተመሰረተ ጥምረት ነው። ይህ ጥምረት በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የአሜሪካን እና የእስራኤልን ተፅእኖ ለመመከት ተሳታፊ አካላትን ያጣመረ በኢራን የተደራጀ ነው። ጥምረቱ በዋናነት የሊባኖሱን ሂዝቦላህ፣ የኢራቅ እስላማዊ ረዚስታንስ፣ እንዲሁም የየመኑ ሃውቲ ይካተቱበታል። አንዳንዴ ደግሞ ሃማስን እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን ያካትታል።
አክሲስ ኦፍ ረዚስታንስ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው አል ዛፍ በተባለ ሊቢያ እለታዊ ጋዜጣ ነበር። ይህም የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆርጅ ዳብሊው ቡሽ 1995 ዓ.ም ላይ ኢራን፣ ኢራቅ እና ሰሜን ኮሪያ ‘የክፉዎች ጥምረት’ እንደፈጠሩ ይፋ ለማድረጋቸው ምላሽ የተሰጠ ነበር። የአሜሪካን የበላይነት ለመገዳደር የፈጠሩትን ይህንኑ ጥምረት አረቡ አለም አርበኝነት ሲለው ምእራቡ ደግሞ ክፋት አድርጎ ነበር የቆጠረው።
ጥምረቱ በጊዜ ሂደት ለዘብተኛ የሆነውን አሜሪካን መሩን አለማቀፋዊ ስርአት በመቃወም የተወለደው ጥምረት እየጠበቀ እና እየተጠናከረ መቀጠል ችሏል።
እነዚህ ቡድኖች ከኢራን የውጭ ፖሊሲ ግቦች ጋር በመዋሃድ እና አንዳንዴም የኢራንን በቀጣናው ያላትን አቅም እንድታሳድግ በማገዝ ረገድ የጎለበተ ጥምረት ነው። የጥምረቱ ጅማሮ ከሂዝቦላ እና ኢራን ግንኙነት ጋር የጀመረ ነው። ሂዝቦላ እንዴት ተጀመረ?
ሂዝቦላ መሰረቱን በሊባኖስ ላይ ያደረገ ታጣቂ ሚሊሻ እና የፖለቲካ ፓርቲ ነው። በ1974 ዓ.ም በአስራ አምስት ዓመታቱ የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነቱ መካከል የተወለደው ሂዝቦላ “የአምላክ ፓርቲ” የሚል ትርጓሜ አለው። የድርጅቱ ዋና ዓላማ የምእራባውያን ኃይሎችን ከመካከለኛው ምስራቅ ማስወገድ እና የእስራኤልን የመኖር መብት መቃወም ነው።
እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ባሉ ፍልስጤማውያን ለደረሰባት ጥቃት ለበቀል የከፈተችውን ጦርነት ተከትሎ ነበር ሂዝቦላ የተመሰረተው። እናም ሂዝቦላ ሌባኖስን ከእስራኤል ነፃ ለማውጣት በሚል አላማ እስራኤል በ1992 ዓም ከሊባኖስ እስከወጣችበት ጊዜ ድረስ የሽምቅ ውጊያ አካሂዷል።
በ1998 ዓ.ም ላይ ሂዝቦላ ለአምስት ሳምንታት ያህል ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ የነበረ ሲሆን ይህም ፍልስጤምን ነፃ ለማውጣት ያለመ ሳይሆን አቅሙን ለመፈተሽ ነበር።
ሀማስን ለመደገፍ በሚል ሽፋን በሊባኖስ አዲስ የግጭት ግንባር ከፍቶ የሮኬት፣ የሚሳይሎች እና የድሮን ጥቃት በእስራኤል ላይ እየሰነዘረ ይገኛል። በአነስተኛ የጦርነት ግጭት ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሂዝቦላ የኢራንን ድጋፍ ካገኘ ወደ ሙሉጦርነት እንደሚገባ እና ይህም ሁኔታውን ወደ ቀጣናዊ ጦርነት እንደሚቀይረው አስግቷል።ሂዝቦላ እንደሀማስ አለመሆኑን የሚገልፁት ወታደራዊ ተንታኞች በአሁኑ ወቅት ቡድኑ በሺዎች የሚገመት የረጅም ርቀት ባልስቲክ ሚሳየሎች፣ ሮኬቶች እና ድሮኖች ባለቤት ሲሆን ከ250-300 ኪሎ ሜትሮ ርቀት መምታት የሚችል አቅም እንዳላቸው እየተነገረ ይገኛል።
ሂዝቦላ ቃሉ አረብኛ ነው። “የጌታ ፓርቲ” እንደማለት ነው በጥሬው ሲተረጎም።
ዛሬም ድረስ በኢራን ይደገፋል። ያዋለደችውም ኢራን ናት። በትጥቅም፣ በስንቅም ደግፋ ለዚህ ያበቃቸው ኢራን ናት። ይህ የጀመረው ከፈረንጆቹ 1980ዎቹ መባቻ ነው።
ሂዝቦላ ከደካማ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የወጣ ጠንካራ የሚባል ድርጅት ነው። ሕዝብ የሚታደገው ሲሻ፣ መንግሥት ባጣ ጊዜ ሂዝቦላ ደርሶ ነው ‘ሕዝባዊ’ መሆን የቻለው።
እስራኤል ሊባኖስን መውረሯን ተከትሎ ደካማ ውክልና የነበራቸው የደቡባዊ ሊባኖስ ሺአ ሙስሊሞችን ለመታደግ የተመሠረተ ቢሆንም፣ አሁን ግን ፖለቲካዊ ፍላጎቱ እና ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ቀጣናዊ ለመሆን በቅቷል።
ፓርቲውን ከ1992 ጀምሮ እስከ ዛሬ የሚመሩት ሐሰን ናስራላህ ናቸው። በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ተደማጭነታቸው ከፍ ያለ ነው።
ሄዝቦላህ ርዕዮተ ዓለማዊ እሳቤው ከምሥረታው ዘመንም ራቅ ይላል። በሊባኖስ የሺአ ኢስላም ማንሰራራትን ተከትሎ ወደ 60ዎቹ ዘመን ይሳባል።
ሂዝቦላ በሊባኖስ ፖሊቲካ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብሎ ማለፍ የድርጅቱን ሚና ማሳነስ ይሆናል። በዚያች አገር ፈላጭ ቆራጭ ነው።
የሂዝቦላ የፖለቲካ ክንፍ ‘ሎያሊቲ ቱ ሬዝስታንስ ብሎክ’ በተባለ ፓርቲ በሊባኖስ ፓርላማ ውስጥ ይወከላል።
ሂዝቦላ በሊባኖስ ካቢኔ ውስጥ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን አለው።
ሂዝቦላ ባለፉት አሥርታት በርካታ ጥቃቶችን ሲፈጽም እና ግድያዎችን ሲያቀነባብር ቆይቷል። በብዛት ዒላማ የሚያደርገው ደግሞ የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቅሞች ላይ ነው።
ሂዝቦላ በአሜሪካ፣ በእስራኤል፣ እና በሌሎች የምዕራብ አገራት እንዲሁም በአረብ ሊግ የሽብር ቡድን በሚል ተፈርጇል።
ሂዝቦላ ድርጅት የሶሪያ ፕሬዝዳንት የባሻር አል አሳድ ቀኝ እጅ እና የማያወላዳ ደጋፊ ነው።
የ2003 ዓ.ም የሶሪያን አመጽ ተከትሎ ሂዝቦላ ከአሳድ ጎን ሆኖ ተፋልሟል። በአማጺዎች የተወሰዱ ቦታዎችን ከመንግሥት ኃይሎች አብሮ እና ተባብሮ አስመልሷል።
በተለይም ከሊባኖስ ኩታ ገጠም የሆኑ ቀበሌዎችን ሂዝቦላ ለአሳድ አስረክቦ አመኔታን አትርፏል።
እስራኤል በሰላሙ ጊዜ ሳይቀር እጅግ በተደጋጋሚ በሶሪያ የሚገኙ የሂዝቦላን እና የኢራንን ወታደራዊ ዒላማዎች ታጠቃለች። ሆኖም ግን ጥቃት ፈጸምኩ አትልም።
ጥቃቶቹ ግን ሂዝቦላን አዳክመውት ይሆናል እንጂ አላጠፉትም።
የሂዝቦላ በሶሪያ የውስጥ ጉዳይ መግባቱን ተከትሎ በሊባኖስ የሃይማኖት መስመርን የተከተለ የእምነት ግጭት እንዳይቀሰቅስ ስጋት ነበር። በቀጣይ ክፍል በኢራቅ እና በየመን ስለሚንቀሳቀሱት የአክሲሱ አባላት እናነሳለን።
ይቀጥላል።
(መሠት ቸኮል)
በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም