የምድር እምብርት በሚባልለት በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያሉ ግጭቶች በዓለማቀፍ የሚዲያ ሽፋን፣ በአካባቢያዊ ፅሁፎች እና በዓለማቀፍ ፖለቲካ ውስጥ በቋሚነት የሚነሳ ጉዳይ ነው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ልዩ ልዩ መልክ ያላቸው ግጭቶች የክልሉን መልክ ሰርተውታል። በተለይ በሱኒዎች እና በሻይቶች መካከል የሚደርግ ትግል፣ የአረብ እና የፐርሺያ ስልጣኔዎች ፍትጊያ፣ የእስራኤል በሙስሊሙ ዓለም ውስጥ የሀገርነት ተቀባይነት የማግኘት ጉዳይ እና በኢራንና እና በአሜሪካ መካከል ያለ የጋራ ጠላትነት ይጠቀሳሉ። እየታዩ ያሉ በርካታ አለመጣጣሞች ግጭቶችን በማወሳሰብ ብዙ አይነት ቅርፅ እንዲይዙ አድርገዋል። የዓመታት የተሞከሩ የሰላም ሂደቶችን እንዳይሳኩ በማድረግ በኩልም ሰፊ ድርሻ አላቸው።
የአረብ ፐርሺያ ባላንጣነት
ፐርሺያ በእስያ ከተነሱ ከጥንታዊ ኃያላን መካከል አንዱ ነበር። በአሁኑ ዘመን የኢራን ሀገረ መንግሥት የተመሰረተበትን አካባቢ የሚወክል ስፍራ ሲሆን በታሪክ ውስጥ በርካታ ከፍታ እና ዝቅታዎችን ያለፈ ስፍራ ነው። ነብዩ ሙሀመድ ከሞቱ ከሁለት አስርት ዓመት በኋላ ያለው 400 ዓመታት የፐርሺያ ስርወ መንግሥት በአረብ ሱኒ ሙስሊሞች ተወርሮ የነበረበት ነው። እናም በአብዛኛው የዞራስትራሊዝም እምነት ተከታይ የነበሩት ፐርሺያዎች ወደ እስልምና ተቀይረዋል። በዚህ ሁኔታ ነበር የአረቢያን ሰርጥ የመምራት የስልጣን ፍትጊያ በአረብ እና በፐርሺያ መካከል የተጧጧፈው።
ከ1492 እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ የገዙት አረብ ያልሆኑት የሻይት ዳይናስቲዎች መነሳት በፐርሺያ የነበረውን የሱኒዎች አገዛዝ እንዲያከትም አድርገውታል። ሻይቶች ደግሞ ከ1492 -1971 ዓ.ም ድረስ ፐርሽያን መርተዋል። የአረቦች እና የፐርሺያዎች ፉክክር ሲነሳ 1971 ዓ.ም በኢራን የእስላማዊ አብዮት የተቀጣጠለበት ዓመት አብሮ ይነሳል። ይህ ዓመት የአካባቢው የታሪክ መታጠፊያ ነው። ለአረብ ፐርሺያ ግንኙነትም የማዕዘን ድንጋይ ነበር። ከዚያ በኋላ ነበር በወቅቱ የሀገሪቱ መሪ በሆኑት አያቶላህ ሆሚኒ ስር የነበሩት “ሙላህ” የሚባሉት የሻይት ሀይማኖታዊ መሪዎች(clerics) ወደ ፖለቲካ ስልጣን እንዲመጡ የተደረገው። እናም በ1971 ዓ.ም የኢራንን እስላማዊ ሪፐብሊክን ከመሰረተው የሻይት ሙላህ አገዛዝ ጋር ተያይዞ የሱኒ ሻይቶች ፉክክር የተጠናከረበት፣ ቀጣይነት ባላቸው ሁከቶች እየተንፀባረቀ እና የተለያየ መልክ ያላቸው ግጭቶች (violence) የተፈጠረበት ነበር። ሳዑዲዓረቢያ፣ ካታር የሚመሩት እና ወኪሎቻቸው በሆኑ በአረብ ሱኒ መንግሥታት እና በኢራንና በዋናነት ሻይት በሆኑ ወኪሎቿ መካከል የተለያየ መልክ ያላቸው ግጭቶች ተደርገው ነበር። ማለትም እነ ሳውዲ፣ ካታር እና የእነርሱ ወኪል በሆኑ የአረብ ሱኒ መንግሥታት እና በአረብ ባልሆኑ ሻይቶች መካከል ግጭቶች በተለያየ መልኩ ይካሄዱ ነበር።
የኢራን እና የእስራኤል ግንነቶች
በ1971 ዓ.ም በኢራን የተካሄደው እስላማዊ አብዮት በአጠቃላይ በሀገሪቱ የውጭ ፖሊስ ላይ እና በተለየ ሁኔታ በኢራን እስራኤል ግንኙነት ላይ ለውጥ መደረጉን ያመለክታል። ነገር ግን በሻህ ስርወ መንግሥት ዘመን፣ በተለይ ከ1933-1971 ዓ.ም በነበረው በሻህ ሙሃመድ ሬዛ ፓህላቪ ዘመን፤ ኢራን እና እስራኤል ጥብቅ የሆነ ትስስር ፈጥረው ነበር። ጥብቅ የርቀት ጉርብትናም መስርተው ነበር። በአብዛኛው ሱኒዎች ሙስሊሞች በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ኢራን የሻይት ሙስሊም መንግሥት መሆኗ እና ከሙስሊም ጎረቤቶቿ ጋር በግጭት ከተሞላው ታሪኳ አንፃር እስራኤልን ተፈጥሯዊ ወዳጅ አድርጋ ትመለከት ነበር። በሌላ በኩል እስራኤል በሙስሊሙ ዓለም ውስጥ እውቅና ለማግኘት ትፈልግ ነበር። በመሆኑም ኢራንን የምናብ ጎረቤቷ አድርጋ ታይ ጀመራ ነበር። የእስራኤል የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ቤን ጉሪዮን እስራኤል በዙሪያዋ ከከበቧት ጎረቤቶቿ ጋር ግንኙነት ስላልነበራት ከእርሷ ጋር ወሰንተኛ ካልሆኑ ነገር ግን ከጎረቤቶቿ ጋር ከሚዋሰኑ ሀገራት ጋር የርቀት ጉርብትና የመፍጠርን ህሳቤ አጠናከሩ። ይህም የጠላት ጎረቤቶቿን ተፅኖ ለመከላከል ታሳቢነት ያደረገ ስትራቴጂ ነበር። ለአብነት ከኢራን እና ቱርክ ከ1971 ዓ.ምቱ እስላማዊ አብዮት በፊት ከእስራኤል ጋር ስትራቴጂያዊ ጥምረት መስርተው እንደነበር የአረብ እስራኤል ታሪክ ያስረዳል።
‘የጠላቴ ጠላት ወዳጄ’ በሚለው የርቀት ጉርብትና እሳቤ አንፃር እስራኤል ከኢራን ጋር በጋራ ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ፈጥራ ለአመታት በወዳጅነት ቆይታለች። እስራኤል በ1940 ዓ.ም እንደ ሀገር ስትመሰረት ከሙስሊሙ ዓለም እውቅና የሰጡ ብቸኛ ሀገራት ኢራን እና ግብፅ ነበሩ። ኢራን ምንም እንኳ ለእስራኤል የሰጠችው እውቅና ኢመደበኛ በሆነ መልኩ ቢሆንም በጋራ ቀጠናዊ ፖለቲካ የጋራ ጥቅማቸውን ያራመዱበትን ጥምረት አጠናክረው እስከ እስላማዊ አብዮት ድረስ አስቀጥለዋል።
የሻሆቹ አገዛዝ በነበረበት ዘመን የኢራን መንግሥት የበፊት ተቃውሞውን በመተው ለእስራኤል እውቅና የሰጠው በ1942 ዓ.ም ነበር። የእስራኤል አጋር መሆኑ ለእስራኤል ህልውና እውቅና መስጠቱን ተከትሎ ነበር። እስራኤልም የበለጠ ግልፅ ግንኙነት ከኢራን ያገኘችው ከ1949 ዓ.ም የስዊዝ ቦይ ጦርነት በኋላ ነበር። በስድስት ቀኑ ጦርነት ማለት ነው። በዚህ ወቅት ለነበረው ፓን አረባዊነት እና ለፍልስጥኤም ነፃነት የግብፁ ገማል አብድል ናስር ግንባር ቀደም ድምፅ የሆነበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ታዲያ ይህ ፓን አረባዊነት እና የሩሲያ ተፅእኖ እየተጠናከረ በቀጠናው መታየት አረብ ላልሆኑት እንደ እስራኤል፣ ኢራን፣ ቱርክ እና ኢትዮጵያ ላሉ የክልሉ ሀገራት የጋራ ስጋቶች ነበሩ። እናም የሩቅ ጉርብትና እውን እንዲሆን ጥርጊያውን እንዳመቻቸ የታሪክ አጥኚዎች ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ኢራን እና እስራኤል ኢራቅን የጋራ ስጋት አድርገው ይመለከቱ ነበር። ይህ ደግሞ ሌላ የትብብር ምክንያት ሆኖላቸዋል። በ1950ዎቹ እስራኤል ከኢራቅ ማእከላዊ መንግሥቱ ጋር ይፋለሙ የነበሩትን የኢራቅን ኩርዶች ትደግፍ ነበር። ኢራን በበኩሏ የኢራቅ ኩርዶች የኢራቅ ማእከላዊ መንግሥትን ለመጣል ዋነኛ አቅም እንደነበሩ ማመን ብቻ አይደለም ትደግፍ ነበር። በዚህ መሰረት የእስራኤሉ ሞሳድ እና የኢራኑ ሳቫክ የተባሉት የስለላ ድርጅቶች ሀይሎቻቸውን በማጣመር የኢራቅ ኩርዶችን ትግል ለማገዝ በትብብር ይሰሩ ነበር።
ሞሳድ የሚስጢር ስሙ “ትሪደንት” የተሰኘ የሶስትዮሽ የስለላ ጥምረት ከኢራን እና ከቱርክ ጋር መስርቶ ነበር። ሦስቱም ሀገራት በመሰረቱት የደህንነት ጥምረት መረጃዎችን በጋራ የመለዋወጥ እና የጋራ አፀፋዊ የደህንነት ዘመቻዎችን ያከናውኑ እንደነበር፤ ዳሊያ ዳሳኒ ካየ፣ አሊሬዛ ናድር እና ፓሪሳ ሮሻን በጋራ በፃፉት “እስራኤል እና ኢራን” በተባለው መፅሀፍ ላይ ያስረዳሉ።
ኢራን ከእስራኤል ጋር የመሰረተችው ግንኙነት በጋራ ፍርሀቶቻቸው ላይ የተመሰረተ ብቻ አይደለም። ይልቁንም ኢራን መንግሥቱን አጥብቆ ከሚነቅፍባት ፕሬዚደንት ኬኔዲ ከሚመሯት አሜሪካ ድጋፍ በማስገኘት ረገድ እስራኤል ያላት ከፍተኛ ተፅእኖ መሆኑን የሻህ መንግሥት የተጋነነ አመለካከት ነበረው። እናም ራሱን በእስራኤል በኩል ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ለማቀራረብ የኢራን ፍላጎት ከእስራኤል ጋር ትስስሯን ለማጠናከር በነበራት ውሳኔ ላይ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ የሻህ አስተዳደር የእስራኤል ተወካይ በኢራን እንዲኖር ፈቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ የሻህ መንግሥት ለእስራኤል የዲ ፋክቶ ኤምባሲ እንድትከፍት ከመፍቀድ ያለፈ እውቅና ያልሰጠ እና ከ1959 ዓ.ም የስድስት ቀኑ ጦርነት በኋላ እስራኤልን በተመለከተ በይፋ የሚያወጣቸው መግለጫዎቹ ይበልጥ ነቃፊነት የተላበሱ እየሆኑ ቀጥለው ነበር። ምንም እንኳ የኢራናውያን ተቃውሞ በእስራኤል ላይ እያደገ ቢመጣም የኢራን መንግሥት እስራኤል በዚህ ጦርነት በግብፅ፣ በሶሪያ እና በዮርዳኖስ መከላከያ ሀይሎች ላይ ድል መቀዳጀቷን በአደባባይ በመመስከር ግንኙነቱን በጥልቀት ለማስቀጠል ጥረት ሲያደርግ ይታይ ነበር። ምክንያቱም የእስራኤል በቀጠናው ጠንክሮ መውጣት የኢራንን አቅምም እንደሚያሳድገው የሻህ መንግሥት ያምን ነበር።
እስራኤል እና ኢራን ከጠበቀ ወዳጅነት ወደ ቀንደኛ ጠላትነት በዘለቀው ታሪካቸው ውስጥ የጋራ ስጋቶቻቸውን ለመታገል መሰረት ያደረገ ጥምረት ብቻ ሳይሆን በርካታ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችን ያደርጉ ነበር። የአሁኑን አያድርገውና እስራኤል እና ኢራን በእነዚህ ዘርፎችም ብዙ የትብብር ታሪክ አስመዝግበዋል።
….ይቀጥላል
(መሰረት ቸኮል)
በኲር ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም


