ኢራን እና እስራኤል፤ ወዳጅም ጠላትም

0
217

ከወዳጅነት ወደ  ጠላትነት ያመራውን የእስራኤል እና የኢራን የግንኙነት ታሪክን በተመለከተ የነበረውን መልካም ግንኙነት ባለፈው ሳምንት ለማሳየት ሞክረን ለሳምንት በቀጠሮ ነበር የተለያየነው። ከዚያ የቀጠለውን ደግሞ እነሆ ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ።

የሻህ አስተዳደር ኢራንን እስካስተዳደረበት 1971ዱ አብዮት ድረስ የኢራን እና የእስራኤል ግንኙነት እየተጠናከረ ሰፊ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ወልዷል። የትብብር ዱካዎቻቸውን ለመደበቅ፣ ኢራን እና እስራኤል ትራንስ ኤዢያቲክ ኦይል በሚባል አንድ ማእከላዊ ሕጋዊ ሰውነት ባለው ድርጅት ስር ፓናማ እና ስዊዘርላንድ ውስጥ አዳዲስ ኩባንያዎችን መስርተው ነበር። የተመሰረተውም በ1960ዎቹ ማብቂያ ግድም በእስራኤል እና በኢራን ብሔራዊ ኦይል መካከል ያለውን ቁልፍ የሚስጢር ትብብር ማከናወኛ ማእከል በመሆን እንዲያገለግል ነበር። በጥቅሉ የእስራኤል ነዳጅ አቅራቢ ኢራን ነበረች።

በ1965 ዓ.ም የተደረገው የአረብ የነዳጅ አድማ፣ እስራኤልን ይደግፋሉ በሚል አሜሪካን እና አውሮፓን ለመቅጣት ቢደረግም የሻህ መንግሥቱን ደግሞ አጠናክሮታል። ኢራን አድማውን አልተቀላቀለችም ነበር፣ እናም በዚህ ምክንያት ዋና ተጠቃሚ ሆና ነበር፤ የተለመደ የነዳጅ ምርቷን በመቀጠል ገቢዋ በእጅጉ አሻቀበ። ኢራን እንዲሁም የነዳጅ ምርቷን ለወታደራዊ ፍላጎቷ ማጠናከሪያ ትጠቀምበትም ነበር። 1968 ዓ.ም ላይ የተሻለ ዘመናዊ የሚሳኤል ስርአት መገንባት ላይ ያተኮረ፣ ፕሮጀክት ፍላወር የሚባል አንድ ጥምር የኢራናውያን እስራኤላውያን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ነበረ። ይህ ነዳጅ ለጦር መሳሪያዎች ከሚል ሀገራቱ በ1960ዎቹ ማብቂያ ላይ ከፈረሟቸው፣ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ከሚገመቱት ስድስት ኮንትራክቶች መሀል አንዱ ነበር። እስራኤል 300 ሚሊዮን ዶላር በቀጥታ  እና 250 ሚሊዮን ዶላር በነዳጅ መልክ የምትከፍል ሲሆን ይህም ኢራንን እስራኤል መር ለሆኑ የምርምር እና የልማት ፕሮጀክቶች ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ያደርጋታል። እስራኤል ልማቱን ስትመራ፣ ኢራን የሚሳኤል መገጣጠሚያ እና መሞከሪያ መሰረተ ተቋም መገንባት ጀምራ እንደነበር ማሱድ ፋራንግ ባሳተመው ‘ኢራን-ኢስራኤሊ ኮኔክሽን’ በሚል ጆርናሉ ላይ አስነብቧል።

በእስራኤል እና በኢራን መካከል የነበረው ትብብር የተቀዛቀዘው በ1980ዎቹ ሲሆን፤ ነገር ግን ሁለቱም ሀገሮች እርስ በእርስ እንደ ቀጥተኛ ጠላት አይተያዩም ነበር። እስራኤል ትኩረቷን የያዘው ከባህረ ሰላጤው ጦርነት በኋላ የሳዳም ሁሴኗ ኢራቅ የጋረጠችባት የደህንነት ስጋት ነበር። ሆኖም በዚህ ወቅት የእስራኤል የደህንነት ተቋም ስለ ኢራን የሚሳኤል ግንባታ እና የኒኩሌር ፕሮጀትቶቿ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ቢሄድም፣ የኢራናውያን አስጊነት ብዙም  የሚራገብ አልነበረም። ይልቁንም በ1980ዎቹ ማብቂያ ላይ የእስራኤል የደህንነት ልሂቃን ኢራን በምንም መልኩ እስራኤልን ዋነኛ የደህንነት ስጋት እንደማትመለከት በማስረዳት ውጥረቱን እንዲለዘብ ማድረግ እንደሚቻል በመታወቁ እስራኤል ይህን በኢራን ላይ የነበራትን ስጋት እንደገና እንድትፈትሽ ሆና ነበር።

በዚህ ወቅት የኢራን መሪ የነበሩት ሙሃመድ ካታሚ በበኩላቸው ከእስራኤል ጋር የአርቅ ምልክት አሳይተው እንደነበር ይነገራል። ከአሜሪካ ጋር ሰላም የመውረድ ፖሊሲን እና ለእስራኤል ፍልስጤማውያን ግጭት የሁለት መንግሥት መፍትሄን ኢራናውያን እንደሚደግፉ አቋም በማሳየት መልካም ግንኙነት ለማስቀጠል ሞክረው ነበር።

ነገር ግን በመጀመሪያዎቹ ቀጣይ አስርት አመት የእስራኤል ኢራን ባላንጣነት በደንብ እየጠነከረ እና የሚታይ እየሆነ መጣ። በአፍጋኒስታን እና በኢራቅ የተደረጉት ጦርነቶች ታሊባንን እና ለሳዳም ሁሴን የመሰሉ ሁለት የረጅም ዘመን የኢራናውያን ጠላቶች ድል ነስቷል። ይህም የኢራውያንን የቀጠናዊ ተፅእኖ እንዲስፋፋ የማድረግ ውጤት አስከትሎ ነበር። እስራኤል በድንበሮቿ አለመረጋጋት እያስከተሉ ያሉ መንግስት ያልሆኑ እነ ሀማስ እና ሂዝቦላህ ያሉ ታጣቂዎች ድርጅቶች ጋር ያላት ትስስር እየጠበቀ መሄድ ኢራንን ለግጭቶች ሁሉ ዋና መፈልፈያ አድርጋ ትመለከታት ያዘች። በ1997 ዓ.ም  የአህመዲኒጃድ መመረጥ ካለው የፀረ እስራኤል ስብከቱ እና እስራኤል ላይ የዘር ማጥፋት አለመፈፀሙን መካዱ እስራኤል በኢራን ላይ ያላትን ፍራቻ አጠናከረው።

የአያቶላህ ኾሜኒ እስላማዊ አብዮት የሻህ መንግሥትን ገርስሶ ራሱን የጭቁኖች መሪ አድርጎ ብቅ አለ። የዚህ መንግሥት ዋነኛ መለያም የአሜሪካን እና የአጋሮቿን “ኢምፔሪያሊዝም” መቃወም ሆነ።

የአያቶላ አስተዳደር ኢራን ከእስራኤል ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠ። ለእስራኤል ፓስፖርትም እውቅና ነስቶ በቴህራን የነበረውን የእስራኤል ኤምባሲን፣ የእስራኤል መንግሥትን ሲዋጋ ለነበረው ለፍልስጤም ነጻነት ግንባር (ፒኤልኦ) አሳልፎ ሰጠ። እስራኤልን እንደ መንግሥት ማስተናገድ ከኃጢያት እንደሆነ እና ፂዮናዊቷን ሀገር ማጥፋት የሁሉም ሙስሊም ኃላፊነት እንደሆነ በይፋ አውጀው  ነበር።

በመላው ዓለም የሚካሄዱ ግጭቶችን የሚያጠናው ኢንተርናሽል ክራይሲስ ግሩፕ ዳይሬክተር የሆኑት አሊ ቫኤዝ የኢራን መሪዎች ጥላቻ የጀመረው ገና ከጠዋቱ ነው ይላሉ።

“እስራኤል ላይ ያመረረ ጥላቻ የአዲሱ የኢራን መንግሥት መገለጫ የሆነው፤ አብዛኞቹ የኢራን አመራሮች እንደ ሊባኖስ ባሉ አካባቢዎች ከፍልስጤም ታዋጊዎች ጋር ወታደራዊ ልምምድ እና የሽምቅ ውጊያ ሲያደርጉ ቅርበት ስለፈጠሩ ነው” ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም አዲስቷ ኢራን ራሷን የፍልስጤማውያን ጉዳይን በማጉላት የሙስሊሞች ተቆርቋሪ ሀገር ሆና ለመታየት ስለምትሻ ፀረ እስራኤል ሆና ብቃ ብላለች።

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ እና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ከእስራኤል ውጪ በቀጠናው ጠንካራ ሃገር የሆነችውን ሳዑዲ አረቢያን በጥርጣሬ ነው የምትመለከታት።

በአብዛኛው ሱኒ ሙስሊሞች በሚኖሩበት ቀጠና፣ የብዙኃን ሺዓ ሙስሊሞች መገኛ የሆነችው ኢራን ወደፊት ሊቃጣባት ከሚችል ጥቃት እራሷን ለመጠቅ ስትል በመረጠችው ስትራቴጂ ከተቀረው ዓለም ልትነጠል መቻሏን ቫዬዝ ይገልጻሉ።

በዚህም የኢራን መንግሥት ከአገራት ይልቅ በአካባቢው የተለያዩ ዓላማዎችን አንግበው ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር በማበር ፍላጎቷን ለማስጠበቅ ስትጥር ቆይታለች።

ኢራን “አክሲስ ኦፍ ሬዚዝታንስ’ ስትል የምትጠራው ስብስብ በሊባኖስ፣ በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በየመን ተንሰራፍቶ ይገኛል። ቴህራን በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን እና መቀመጫውን በሊባኖስ ያደረገውን ሂዝቦላህን ታስታጥቃለች። ጋዛን ለሚያስተዳድረው ሐማስ፣ በየመን ለሚንቀሳቀሱት ሁቲ አማጺያን ኢራን የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ በአካባቢው ተጽእኖ ስትፈጥር ቆይታለች።

እስራኤል ደግሞ ኢራን በዙሪያዋ ይህ ሁሉ ስታከናወን ዝም ባላ አልተመለከተችም። ኢራን ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎችን እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ አገራት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በቴህራን የሚደገፉ ቡድኖች ላይ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች።

ባለፉት ዓመታት በኢራን እና በእስራኤል መካከል የነበረው ጦርነት “ከመጋረጃ ጀርባ” ያለ ጦርነት ተብሎ ሲገለጽ ኖሯል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሁለቱ አገራት በሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ለሚፈጽሙት ጥቃት ኃላፊነት ሲወስዱ አይታይም።

በተለይ ኢራን እስራኤልን በቀጥታ ከመተንኮስ ይልቅ በምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖች በኩል በእጅ አዙር ስታጠቃት ኖራለች። በ1984 ዓ.ም የወቅቱ የሂዝቦላህ መሪ የነበሩት አባስ አል-ሙሳዊ ግድያን ተከትሎ ለኢራን ቅርበት ያለው እስላማዊ ጂሃድ ቡድን በቦነስ አይረስ የሚገኝ የእስራኤል ኤምባሲን በቦምብ አጋይቶ 29 ሰዎችን ገድሎ ነበር።

እስራኤል ለሂዝቦላህ መሪ ግድያ ኃላፊነት ባትወስድም የቴል አቪቭ የደኅንነት ተቋም የሆነው ሞሳድ ግድያውን መፈጸሙ ይታመናል። እስላማዊው የጂሃድ ቡድንም ቢሆን የእስራኤልን ኤምባሲ ያጋየው ያለ ኢራን እውቅና እንደማይሆን ግልጽ ነው።

እስራኤል የኢራን ጉዳይ አንገብጋቢ የሚሆንባት የአያቶላህ ቴህራን የኑክሌር ፕሮግራም ነው። ለዚህም ኢራን የኑክሌር ቦምብ ባለቤት እንዳትሆን እስራኤል የተቻላትን ስታደርግ ቆይታለች።

ኢራን ግን የኑክሌር ፕሮግራሟ ብቸኛው ዓላማ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚውል ሰላማዊ ዓላማ ያለው ነው እያለች ቆይታለች። ይህን ምክንያት ጨርሶ የማትቀበለው ኢራን በዲፕሎማሲ በኩል ኢራን ላይ ማዕቀብ ከማስጣል አልፋ ከአሜሪካ ጋር አብራ የኢራንን የኑክሌር ማብላያ ጣቢያን ‘ስቱአኔት’ በሚባል ኮምፒዩተር ቫይረስ አውካ ከፍተኛ ጉዳት አድርሳ ነበር።

እስራኤል የኢራን ኮምፒዩተሮችን ብቻ ሳይሆን ሳይንቲስቶቿንም ዒላማ እያደረገች በቴህራን ጎዳናዎች ላይ ገድላለች። በ2012 ዓ.ም በጉምቱው የኑክሌር ሳይንስ ተመራማው ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ላይ የተፈጸመው ግድያም ብዙ ያነጋገረ ነበር።

ኢራንም ብትሆን በእስራኤል ላይ ድሮኖችን እና ሮኬቶችን ስታስወነጭፍ እንዲሁም የእስራኤል ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ስትፈጽም ቆይታለች። እስራኤል እና ኢራን በየብስ ላይ “ከመጋረጃ ጀርባ” የሚያካሂዱት ጦርነት ወደ ባሕር ላይም ተሸጋግሮ በተለያዩ ጊዜያት በመርከብ የጉዞ መስመሮችም ላይ ስጋትን ሲደቅን ቆይቷል። አሁን ደግሞ ወደ ፊት ለፊት ፍልሚያ ተሸጋግሯል።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here