በማዳጋስካር ኢሆሮምቤ ክልል ፊያናራንሶዋ ግዛት ደቡብ ምእራብ ቀጣና ነው የሚገኘው:: የፓርኩ ስፋት 815 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለከቷል:: በፓርክነት እውቅና አግኘቶ የተመሰረተውም በ1962 እ.አ.አ ነው::
የፓርኩ ቀጣና ሰፋፊ ሜዳዎች፣ አለታማ ቋጥኞች ጥልቅ ሸለቆዎች እና የተራራ ላይ ሜዳዎች (ኘላቶ)ን አካቶ የያዘ ነው:: የመልካ ምድሩ የተለያየ መሆኑ እና አስደናቂ ገፅታው ባለፉት ዘመናት በዝናብ እና በነፋስ መፈራረቅ የተቀረፀ ለመሆኑ አብነት ነው::
ፓርኩ በደረቅ እና ሞቃት ክልል በመገኘቱ በአብዛኛው በቁጥቋጦ የተሸፈነ ነው:: አሽዋማ እና የተሸረሸሩ አለታማ ኮረብታዎች፣ ጅረት እና ምንጮች በሚፈሱበት ሸለቆ ለምለም ቁጥቋጦዎች እና አልፎ አልፎ በሚታዩ ዛፎች “ሊመር” የተሰኘው ዓይናማ ጦጣ መሰል በጥቁር እና ነጭ ዠንጉርጉር ጅራት የሚታወቀው እንስሳ ከአንዱ ወደ ሌላው ሲዘል ሲንጠላጠል ይስተዋላል፤ ይህም የጐብኚዎች ልዩ መስህብ ሆኖ ያገለግላል::
በፓርኩ 47 የተሳቢ እንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ:: ከዓዕዋፍም 80 ዝርያዎች በፓርኩ ቀጣና መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት በማዳጋስካር ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ ናቸው::
ከተሳቢ እንስሳት እስስት፣ እንሽላሊት፣ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ የእንቁራሪት ዝርያዎች እይታን ከሚስቡ መካከል ይጠቀሳሉ::
ለፓርክ በጣም ቅርብ የሆነ ነው ማረፊያ የራኖሂራ መንደር ሲሆን በቅርበት የሚገኙ ከተሞች ደግሞ ቶሊያራ እና አሆሲ መሆናቸውን ልብ ይላል::
ኢሳሎ ዝናባማ፣ ሞቃታማ እና ቀዝቃዛ ደረቅ ወቅቶች የፈራረቁበታል:: በእግር ተዘዋውሮ ለመጐብኘትም ከግንቦት እስከ ጥቅምት ያሉት ደረቅ ወራት ይመከራሉ::
ዓእዋፍን ለመመልከት ከመስከረም እስከ ህዳር ያሉት ተመራጭ ወራት ናቸው::
ፓርኩን በበላይነት የማዳጋስካር ብሔራዊ ፓርኮች ያስተዳድረዋል::
ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ሳፈሪ ዲል፣ ኦድሊ ትራቭል እንዲሁም ዋይልድ ላይፍ ወርልድ ዋይድ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


