ኢትዮጵያን ለአምላክ ሰጧት

0
233

“ኢትዮጵያ እማማ እናታችን

እጇን ዘርግታ ለአምላካችን፤

ቡራኬ አገኘች ለሠላም

ስሟ እንዲጠራ በዓለም”

ከላይ የጠቀስሁት ግጥም የታምራት ሞላ ዘፈን ውስጥ የተካተተ ነው። ስለ ኢትዮጵያ ከዘፈኑት ይልቅ ያልዘፈኑትን ድምጻዊያን መጥቀስ ቀላል እስኪሆንልን ድረስ በርካታ ድምጻዊያን ስለ ሀገራቸው ዘፍነዋል። ሁለት ሦስት ጊዜ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ድምጻዊያን አሉ። ሀገር፣ ሚስት እና እናት ሦስቱ አንድነት አላቸው።

ታምራት ሞላ ከቀደሙት አንጋፋ ድምጻዊያን መካከል በምድር ጦር ኦርኬስትራ በኩል የተገኘ ነው። አባቱ ዘፋኝ ለምን ሆንህ ብለው በሽጉጥ ሊያስመቱት ሰው ይልኩበት ነበር። ድምጻዊያን ሀገራቸውን በወቅቱ፣ በዘመኑ፣ በጊዜያዊ ስሜታቸው፣ በገጠማቸው፣ በተስፋቸው፣ በማግኘት ማጣታቸው እና በደስታም በሀዘንም ጊዜ ያነሷታል። የታምራት ሞላ ኢትዮጵያ ኃይሏ፣ መባረኳ ከላይ ከአምላኳ ነው። እሱም ይህችን ሀገር በቅዱስ ያሬድ ዜማ ተመስግናለችና እኔስ ለምን አላመሰግናትም ብሎ ያዜማል።

አለማየሁ እሸቴ፣ ጥላሁን ገሠሠ እና ግርማ ሞገስ ደግሞ ታምራት ሞላን በድምጽ በማጀብ የሚከተለውን ግጥም ያዜሙታል። እጃቸውን ወደ ሠማይ ከፍ አድርገው።

“ጠላት ሲወራት ሠላም ሲጠፋ

ያለ ፈጣሪ ማን አላት ተስፋ፤

ኢትዮጵያ እማማን አምላክ ወዷታል

ለዘላለሙ ይጠብቃታል”

ግርማ ሞገስ ደግሞ በበገና ደርዳሪነት ይመጣል። የኢትዮጵያን የሠላም ተስፋ እና መጠጊያነት ያንጎራጉራል።

“አንድ ቀን ክፉ ዘመን ሲመጣ ከዓለም ዙሪያ

ያንን ጊዜ ትሆኛለሽ የስደተኞች መሰብሰቢ

መሸሸጊያ እናት ዓለም ኢትዮጵያ”

ኢትዮጵያ የስልጣኔ አምባ ናት፣ የሰው ዘር መገኛም ጭምር፣ ሕዝቦቿ  ጠላትን ለመፋለም ነጻነታቸውን በተጋድሎ ያስከበሩ፣ ወግና ባህላቸውን ጠባቂ እንግዳን የሚቀበሉ ናቸው ይላል ታምራት ሞላ በዘፈኑ። በነካ እጄ ወደ ታምራት ደስታ ኢትዮጵያ ልሂድ።

“አንጠፋም አንበታተንም እኛ

ፍቅር ነው ያቆራኘን ዳኛ፤

ብዙ ታምር እናያለን ገና

የኢትዮጵያ አምላክ እሱ የት ሄደና”

አምላክ ኢትዮጵያን አንድ ሕዝብ አድርጎ ሠርቷል፤ በፍቅርና አንድነት አጽንቷታል። ከላይ ከሠማይ ሆኖ ልጆቼ ብሎ ይመለከተናል፤ አምላክ እንዳንጠፋ እየጠበቀን አለ። ሀገሬ ኢትዮጵያም አትፍሪ አይዞሽ፤ ሰንደቅሽ ከፍ እንዳለ ከፍ ብለሽ በማይደክመው የአምላክ ክንድ ጥበቃ ትኖሪያለሽ ይላታል።

ምንጊዜም አትጠፋም ይህች የተስፋ አገር

ህዝቡ በቃል ኪዳኑ  ታጥሯል በአንድ ማገር

እንክርዳድ የሚዘራ አልፎ አልፎ  ባይጠፋም

እኛን የሚጠብቅ ከቶ አያንቀላፋም

ታምራት ደስታ እጠፋለሁ አትበይ አበባ ሆነሽ ገና ትኖሪያለሽ የሚላት ኢትዮጵያ ተስፋዋና ኃይሏ አምላኳ ነው።  ስጋት ስለገጠማት አይዞሽ እያለ እያጽናናት ነው።

1991 ዓ.ም የወጣው የኃልዬ ታደሰ “ አንቺን ይዞ አልበም” የኢትዮጵያ አምላክ የሚል ዘፈንን አካቷል። ኃይልየም የተበደለች ሀገሩን እያሰበ ነው የሚያዜመው። ከሰው በሆነው ነገር ከሰው መፍትሔን አልጠበቀም። የኢትዮጵያ ጠላትና በደል አድራሽ አንድ ቀን ባንዲራዋ ስር፣ እግሯ ስር ወድቆ ይቅር በይኝ ይላታል ሲል ያዜማል።

“ሌት ከዶለተባት ቀን ቀን ከሚያድናት

ጉልበቷ እምነቷ  ነው ሁሌም የሚያድናት፤

እፍ ይሏታል እንጂ አያጠፏትም

ዝንተ ዓለም ህያው ነች ኢትዮጵያ አትሞትም”

በኃይልዬ ዘፈን ኢትዮጵያን ለመድፈር የታጠቀ፣ በቁጣ የተነሳ ጠላት ቢኖርም ጥላና መከታ የሚሆናት አምላክ አላት። ሁሉም ሀገር ርግጥ አምላክ አለው። ኃልዬ የኢትዮጵያ የሚለው አምላክ ሕዝቧ ፍትህን የያዘ በመሆኑ የሚያግዛት ነው።

“ነጻነት ተገፎ ድንበር አስቆርሶ

አያልፍም ለትውልድ ባርነት አውርሶ፤

ልጇም ለአንድነቱ እንደ አባት አያቱ

ባንዲራዋን አቅፎ ታልፋለች ሕይወቱ”

ኀይልዬ ቀደምት አባቶች ለነጻነት እንደተዋደቁት ሁሉ የዛሬውም ልጅሽ ክብርና አንድነትሽን ለማስጠበቅ ይዋደቅልሻል ሲል ነው ምንሰማው። ይህ ዘፈን በነገራችን ላይ  በሚዲያ እንዳይጋበዝ ካሴቱ ላይ ምልክት ተደግጎበት አንድ ሬዲዮ ጣቢያ በሄድሁበት ጊዜ ተመልክቻለሁ።

በዚህም ምክንያት ፋንታሁን ሸዋንቆጨው ኢትዮጵያ ዘላለማዊ ነሽ ሲል ያዜማል።አንቺ ውበትሽ ቀስት ደመና ፣ትውልዱ ጅረቱን የሚቀጥልብሽ፣ የአብሮ መኖር ምሳሌ፣ የተበታተኑትን የምትሰበስቢ ድንቅ ዘላለማዊት ሀገር ነሽ ይላል።

“የእምነትሽን ጽናት

የእውነትሽን ጥራት፤

በጊዜ መስታዎት እያደር ያዩታል

ዘላለምነትሽን ዘላለም ያውቁታል፤

አንገቴን አቅንቼ

ሽቅብ ተመልክቼ፤

ስትውለበለቢ ካንቺ ያነበብሁት

ነጻነት ነው ክብር ፍቅር   እውነት እምነት”

ኢትዮጵያን አይጥሉሽም ፣አይቆርጡሽም፣ አይክዱሽም አይፍቁሽም ለምን ቢባል በህይወት ዘርተውሻል። በደም አጽድቀው አብቅለውሻልና። ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ የምትቀጥል ዘላለማዊት ነሽ ይላል ፋንታሁን።

የፀሐዬ ዮሐንስ ኢትዮጵያ እጆቿን ለሠላም ዘርግታ የቆመች ናት። ፀሐዬ አምላክን እባክህ ሠላም ስጣት ብሎ የሚያማልድን ልጅ ይመስላል። ፍቅርና ሠላም ከሰው በራቀበት በዚህ ጊዜ አምላክ ሆይ እባክህ አንተ ስማን፣ ያንተ ቸርነት አይለየን ይላል።

“ሠላም ይደርባት

ፍቅር ይስፈንባት

ስምህ ይንገሥባት

ጸጋህ ይዝነብባት

ዘርተን እንቃምባት

ወልደን እንሳምባት

አምላኬ ሆይ

ባርክልን ኢትዮጵያን

ያላንተስ ማን አላት”

ኢትዮጵያ እኮ ኃያል፣ ገናና ነበረች ብሎ የሚጀምረው የፀሐዬ ዮሐንስ ሌላው ዘፈን ያ የጥንቱ ገናናው ስሟ ይመለሳል፤አምላኳ ቃል ገብቶላታል ሲል እንሰማዋለን ፀሀዬን።

“አላት የአምላክ ኪዳን ከሰማይ ያያታል

ቢዘገይም አይቀርም በዕጥፍ ይክሳታል፤

የኛ ኢትዮጵያ እንዲህ ሆና አትቀርም

ዝም አይልም እሱ

ያ ገናናው ውብ ስሟ ዳግም መመለሱ”

ኢትዮጵያ የዓለሙ ህዝብ መነጋገሪያ ሆናለች፣ ሕዝቧ ተሳቋል፣ አፍሯል፣ ርሀብና ስደት መገለጫዎቹ ሆነዋል። ይህ የሚሆነው ግን አምላክ ገናናውን ስሟን ለመመለስ ቃል ገብቶላታልና አንድ ቀን በቅርብ ይመለሳል በሚል ያንጎራጉራል።

የምስክር አወል ኢትዮጵያ ድህነትን አሸንፋ በዓለም ብርሀን የተጠቀሰውን ስሟን ለማደስ ባለመስራቷ የምታሳዝን ናት።ደሀ ሕዝቧ ስደትን ምርጫ አድርጎ በባዕዳን መንደሮች የሚያድር ሆኗል። ጠንክረን መስራት ሲገባን አላደረግነውም የሚል ቁጭትን ይዞ ምስክር አወል ያዜማል። የሀገራችን መጠሪያ ስም በጎ ይሁን፤ ረሀብና ስደት ይብቃ ይላል ፈጣሪንም “ጥረህ ግረህ ብላ” የሚል ትእዛዝህንስ አክብረን የለም ወይ፣ስራ ላይ ተሰማርተን አይደል ወይ፤ ሕዝባችን ደሀ፣ ስማችን ረሀብተኛ የሆነው ለምን  ነው በሚል ሙግት ያቀርባል።

“የሚወደውን ሰው አምላክ ይፈትናል

ቃሉም እውነት አለው ያንቺም ስቃይ በዝቷል፤

ኢትዮጵያ ሀገሬ ምድራዊ ገነት

ለበጎ ይሆን ያንቺ ስቃይ መብዛት”

ነገር ሁሉ ለበጎ ነው፣ፈተናዎችሽን አትፍሪ ምናልባት የተሻለ ነገር ተደግሶልሻል አይዞሽ ብሎ ይመለሳል። በፍቅር ሰላም ተስፋ እምነት ታንጸን ጠንክረን እንስራ ፤ ስንፍናን ከቤታችን እናስወጣው፤ ረሀብና ልመና በሀገራችን ታሪክ ይሆናል  በሚል ምስክር አወል ያዜማል።

ሚካኤል በላይነህ ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ምድር ናት፤ የሚጠብቃት አለና ነገም የተሻለ ይመጣል በሚል ሲያመሰግን እንሰማዋለን።

“ቢሸመት ቢሰፈር በእንቁላል ስባሪ

አማኝ ልጆቹን ጥሎ አያውቅ ፈጣሪ፤

ልቦናው ይልማ እንጂ የሰው ልጅ መንፈሱ

ሰማይና ምድር መስጠትን አልረሱ፤

እንቆጥራለን ጸጋ እያልን ተመስገን

ነን እና ከሚድኑት ወገን”

ኢትዮጵያ ተስፋ አላት። ገና እንደ ጥቢ አዝመራ አብባ ፍሬም ታፈራለች። አምላኳ የሚያምኑ ልጆቹን ጸሎትና ምህላ አይረሳም። በችግራችን ልክ እንዲያውም መጥፋት ይጠብቀን ነበር፣ ግን ፈጣሪ አድኖናል፤ በክፋታችን እና ከጥፋታችን ልክ ፍቅር ከጎናችን ዛሬም አለ፤ አልሸሸም ይላል።  ብዙ በደልና መከራዎች ባሉበት ዛሬም ተመስገን ነው፤ የፈጣሪ ምሕረቱ አልተለየንም ተመስገን ነው ይላል። ፍቅርን በየዕለት ኑሯችን ዳኛ እናድርግ፤ ፈጣሪ ጠባቂ ዓይኑን ከእኛ ላይ አላነሳም፤ የበለጠ ጥበቃ ከፈጣሪ እንድናገኝ ደግሞ ድካምና ልፋት፤ መውጣትና መውረድ ቢኖር  በፍቅር ይሁን ሲል ይመክራል። ያለ ፍቅር የሚደረግ ነገር ሁሉ ከንቱ ነው ይላል

“በኢትዮጵያ ድንኳኖች መታወክ እንዳይሆን

እኛን የሚበጀን አንድ ልብ መሆን”

ሲል ሚካኤል ሕዝቧ ከፈጣሪ ጥበቃ ባሻገር  አንድነትን ማጥበቅ አለበት በሚል ያዜማል። ጌትሽ ማሞ ኢትዮጵያን በዘር በቋንቋ በእምነት ለመከፋፈል የሚሞክሩ ሁሉ ህዝቧን አያውቁትምና ሁሉም ድካም ነው ይላል። ከፈጣሪ የተሰጠንን ኢትዮጵያዊነት፣ሰው አይነጥቀንም፣የሚጠብቃት እሱ ፈጣሪዋ በመሆኑ።

“እሷን ነክቶ ሰላም አግኝቶ

ማንም የለም የሚኖር ከቶ፤

ጠባቂዋ አለ ከላይ

በዙፋኑ ሁሉን የሚያይ”

በጌትሽ ዘፈን ኢትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ከፍ ብሎ ይጠቀሳል። የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች እያለን “ሰው በዘር አበደ ልቡን ሞላው ክፋት፣ አምላኬ አደራህን ኢትዮጵያን ጠብቃት” በማለት ለአምላክ ያመለክታል። ዘሩባቤል ሞላም ኢትዮጵያን የሚጠብቃት የማያንቀላፋው ፈጣሪዋ ነው ይላል። የክፋትና ተንኮል ደመናሽን ጸሎትሽ ይገፍልሻል አይዞሽ ይላል። አሁን በዘር በቋንቋ በሰፈር የሚያምኑት ልጆችሽ ሐሳብ ቀይረው፣ሰላም ይታይብሻል፣ቂምና ጥላቻ ጠፍቶ ኢትዮጵያ የሚሉ እንደ አሸዋ ይበዙልሻል፣እንደፀሀይም ይደምቃሉ ሲል ይመኛል።

የአስናቀ ገብረየስ ኢትዮጵያ በገጠር አኗኗር ብዙ ልጆች ያሏት እናትን ትመስላለች።ዙሪያዋን ልጆቿ ቤት ሰርተው ልጆች ወልደው አብረዋት በፍቅር የሚኖሩ፤ነገር ግን አንድ ዘመን ላይ በዘር፣በቋንቋ በእምነት ልዩነት ፈጥረው ከጋራ ነገራቸው ይልቅ የግል ማነታቸው ላይ አብዝተው በማተኮር የሚበጣበጡ ሆኑባት። የእናታቸው ርስት ላይ ቤት ሰርተው ከሚኖሩ ልጆች አንዱን የሚመስለው አስናቀ ገብረየስ “እምዬ ወዴት ነሽ ልጆችሽን በትነሽ ጎጇችን ዘሞ እያየች?” ብሎ በእንጉርጉሮ ይጠይቃታል። ይህ የእናቱ መሸሸጊያና መጠጊያ ቤት ፍቅርና ሕብረት ርቆት የደረሰበትን ችግር ያነሳል። ድህነት፣ ጉስቁልና፣ መለያየት ዘርና አከባቢ ማለት ቀርቶ አንድ ሕዝብ (አንድ ቤተሰብ) እንሁን ሲል ያንጎራጉራል። ቅይጥ ባሕል ያለው አንድ ሕዝብ ጠንካራ ሀገር እንሁን ብሎ ይሰብካል። መሬት አልጠበበንም፣ ፍቅርና ሕብረት ተቸገርን እንጂ ይላል። ለእናቱ የሆነውን ተናገረ፣ወንድሞቹን እባካችሁ አንድ እንሁን አለ።

“የሰማይ ደመና ርቋት የራብ አለንጋ ሲገርፋት

ሳታጣ ያጣች እምየን ከዚህ መከራ እናትርፋት፤

እግዚኦ ማረን ፈጣሪ ረድኤት ፍቅርህ አይራቀን

ተመጽዋች ሆነን ከመኖር አላቀን አንተው ጠብቀን”

አስናቀ አምላኩን ከጠየቀ በኋላ ወንድሞቹን እና እናቱን ይመርቃል።ፍቅር እንዲሰፍን፣አንድነት እንዲጸና፣ቸር ወሬ እንዲሰማ አንድ ሕዝብ አንድ ሀገር ይኑረን ሲል ይመርቃል።

ዳግማዊት ፀሐዬ ወርቅ በሚል አልበሟ ውስጥ “ንዑስ” የሚል ርእስ የሰጠችው ዘፈን ኢትዮጵያ ሆይ አይዞሽ ፣አምላክ ያስብሻል ስትል ተስፋዋን ታዜማለች።

“ቅር አለኝ  ዛሬ ኅዘንሽን ሳይ

ላይ ያለው ያስብሽ ከሰማይ፤

አርማዬ የስሜ መለያ

ይነጋል አይዞሽ ኢትዮጵያ”

ጨለማው ይገፈፋል፣ ዝናሽ ይመለሳል፣ ክብርሽ ዳግም ይመጣል ስትል ዳግማዊትን እንሰማታለን። ጠላትሽ ያፍራል አንቺ በኩራት ትቆሚያለሽ ትላለች። በዚህ ጽሑፍ  የጠቀስናቸውም  ይሁኑ ያልጠቀስናቸው ዘፋኞች ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የገጠሟትን ችግሮች የሚዳስሱ ናቸው። ብዙዎቹ ችግሮች ከውጪ የመጣ ወራሪ ያመጣውን ጫና ሳይሆን በራሳችን በኢትዮጵያዊያን መካከል የተፈጠሩ መሆናቸው የበለጠ ያስደነግጣል። ታሪካችን የውጪ ወራሪን በአንድነት አሳፍሮ መመለስ ሆኖ ሳለ፣በውስጣችን የጫርነው እሳት ግን አልጠፋ ብሎ ሰበብ ፈልጎ የሚነሳ አውዳሚ ጠላታችን ሆኗል። ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን አትንኩብን፣እባካችሁ የሚሉ ዘፈኖች እየወጡ መሆናቸው የውስጣችን ችግር ምንኛ ስር የሰደደ እንደሆነ ያሳያሉ። ሞት፣ስደት፣ ጦርነት፣ ርሀብ፣ መፈናቀል አሁናዊ የኢትዮጵያ መገለጫዎች ሆነዋል። አንዱን የጦርነት ምዕራፍ ዘግተን ሌላ የምንጀምር  ሽግግራችን ከሰይፍ ወደ ጠረጴዛ ሳይሆን ወደ መድፍ እና  ድሮን የሚያድግብን የዓለም መሳለቂያ ሆነናል።

ድምጻዊያን የሰላምና ድርድር፣ምክክርና መወቃቀሶች ታልፈው የሰላም አየር አለመንፈሱን አይተዋል። ባንዱ የብጥብጥ ወገን ተሰልፈው በለው ቁረጠው ለማለት አልወደዱም፤እባካችሁ ይቅርብን በሚል ሲመክሩ እንሰማቸዋለን። ሆኖም ጉዞው ጦርነትን ያላቆመ እና ሠላምን ያላመጣ በመሆኑ ፤ ከሰው ብቻ እንደማይሆን አይተው የፈጣሪን ጣልቃ ገብነት ሲለምኑ እንሰማለን።የውጪ ወራሪ በመጣበት ወቅት እንደ ነበረው ሰይፍ ስለው፣ጎራዴ ታጥቀው፣ስንቅ ቋጥረው ዘመቻ መውጣት አልቻሉም። “የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ” ነውና ነገሩ። ጉልበትና ኀይል ከመጠቀም ተቆጥበው  ወንድም በወንድሙ ላይ እንዳይነሳ እባክህ ፈጣሪ ይላሉ። እንድነትን ስጠን እያሉ፤ ሰላም ይስፈን ይላሉ። ኢትዮጵያን ለአምላክ ከመስጠት በቀር “ፈጣሪ ከጥልና ችግር ነጻ እንዲያወጣን እናግዘው ብለው፣ታግለን ነጻ እንውጣ” ማለት አልቻሉም።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here