ኢትዮጵያዊነት እንዲጎለብት …

0
156

የዓለም ሀገራትን ታሪክ ሰንዶ የሚያስነብበው ሂስትሪ ዶት ኮም (www.history.com) እንዳስነበበው የዓለም ሀገራት የሚበዛው ታሪካቸው በጦርነት የታጀበ ነው። የነዚህ ጦርነቶች መንስኤዎቹ የተለያዩ ቢሆኑም ብዙዎቹ እልባት ያገኙት ግን አስከፊ ውድመት ከደረሰ በኋላ በውይይተ እንደሆነ መረጃው ያስገነዝባል።

በተመሳሳይ የጦርነት መልካም ገጽታ ባይኖረውም በብሔር ምክንያት የሚከሰተው ግን እጅግ የከፋ እንደሆነ የመረጃ ምንጩ አክሏል፣ ለዚህ በአብነት የሚጠቀሱት ደግሞ ሩዋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ እና መሰል ሀገራት ይጠቀሳሉ። በተለይ እ.አ.አ በ1998 በሩዋንዳ የተካሄደው የዘር ተኮር ጭፍጨፋ በ24 ሰዓታት ውስጥ የአንድ ሚሊዮን ያህል ሩዋንዳዊያንን ህይወት በልቷል። ይህም በዓለማችን ታሪክ ውስጥ በከፋ ሰብዓዊ ጉዳቱ የሚታወስ ያደርገዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የገጠማቸውን ችግር እንደ መስፈንጠሪያ በመጠቀም ወደ ሁለንተናዊ ዕድገት የተሸጋገሩ ሀገራትንም ያነሳል፣ ለዚህ አብነትም ሩዋንዳ ናት የምትጠቀሰው። ሪሊፍ ዌብ የተሰኘው የመረጃ ምንጭ እንዳስነበበው ሩዋንዳ ከአስከፊው እልቂት ማግስት በተሻለ እድገት ላይ ትገኛለች። ስለ ብሔር ማውራትም እንደ ነውር የሚቆጠር ሆኗል። ከዚያ አለፍ ሲልም ስለ ብሔርተኝነት ማቀንቀን ጠበቅ ያለ እርምጃን ያስወስዳል። በአሁኑ ወቅት ታዲያ ካሳለፉት ብሔር የወለደው መከራ በመማር ሁሉም ፊቱን ወደ ልማት እና ሀገራዊ አንድነት እንዲያዞሩ አድርጓቸዋል።

በተመሳሳይ ናይጄሪያ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካም በዚህ የተሻለ ተሞክሮ እንዳላቸው መረጃው አክሏል። በሌላ በኩል ለዘመናት በተቀነቀነው ብሔርተኝነት ምክንያት ሀገራችንን ግጭት ውስጥ ካስገባት ውሎ አድሯል። ሁሉም በየብሔሩ አጥር በመከለሉም ትልቁ ስዕል ኢትዮጵያዊነት እንዲዋጥ አድርጎታል፤ በተመሳሳይ በሀገራችን ታሪክ ላይ ያለን የተለያዬ አረዳድ ችግሩን እንዳባባሰው ይነገራል።

ከዚህ ችግር ለመውጣት ታዲያ ሀገራዊ የወል ትርክትን ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል። ለዚህ ደግሞ በተለይ አንድ የሚያደርጉንን በማጉላት፣ ብዝኃነትን ደግሞ እንደ ጌጥ መጠቀም ተገቢ ነው ተብሏል።

ተመስገን በየነ (ዶ/ር) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት (ፎክሎር) ክፍል አባል እና የሂውማኒቲስ ፋኩልቲ ምክትል ዲን ናቸው፤ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ችግሮች በተመለከተ እና ከችግሮቹም ለመሻገር የጋራ ትርክትን እንዴት መገንባት እንደሚገባ ሙያዊ ሐሳባቸውን ሰጥተውናል፤ ዶክተር ተመስገን ኢትዮጵያ የብዝኃ ባሕል እና የብዙ ሀገር በቀል ዕውቀት ባለቤት መሆኗን በማንሳት እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ሀገራችንን የብዙ ዓመት የሀገረ መንግሥት ባለ ታሪክ አድርገዋታል ይላሉ::እነዚህ ዕሴቶች የኢትዮጵያ ጌጦች ናቸው ያሉት ምሁሩ በዘመናት ሂደትም የችግሮች መፍቻ (ችግሮች ሳይከሰቱም ከተከሰቱ በኋላም) ቁልፍ ሆነው ያገለገሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ሀገራችን ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ባለ ታሪክ ናት፤ ለዚህ ሁሉ መሠረቱ ደግሞ ሀገር በቀል ዕውቀታችን፣ ብዝኃ ባሕላችን፣ ወግ ልማዶቻችን፣ አብሮ የመኖር ዕሴቶቻችን እና መሰል ትውፊቶች ናቸው::እነዚህ ኢትዮጵያዊ ጸጋዎች እንደ ሀገር እንድንቀጥል ያስቻሉ መሆናቸውን ዶክተር ተመስገን አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ተመስገን እንዳስገነዘቡት ከሚዲያዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በርካታ መረጃዎች (የተጣሩም ያልተጣሩም) ይለቀቃሉ፤ መረጃዎች በማስረጃ ሳይደገፉ ሲለቀቁ ደግሞ አፍራሽ ይሆናሉ፤ ኢትዮጵያ የገጠማት ችግርም የዚህ ውጤት ነው::የብዙ ሺህ ዓመታት የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ፣ የችግሮች መፍቻ ሀገር በቀል ዕውቀት ያለን፣ የበዝኃ ባሕል እና አብሮ የመኖር የመቻቻል ተምሳሌት ሆነን ሳለ አሁን ሀገራችንን እየፈተናት ያለው ነገር ምንድን ነው? ሲሉ የሚጠይቁት ዶክተር ተመስገን እንደ ሀገር ያስተሳሰሩን በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

ምሁሩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት ከ98 በመቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን አማኝ ናቸው፤ ማናኛውም ሃይማኖት ደግሞ ሰውነትን በማስቀደም ተከባብሮ እና ተቻችሎ መኖርን የሚያስተምር በመሆኑ ሀገራችን ከገጠማት ችግር እንድትወጣ ሕዝቡ አማኝ መሆኑ ትልቅ ዕድል ነው::በተመሳሳይ ሀገራችን ያላት የረዥም ዘመን የንግድ ሥርዓት (በዋናነት የሲራራ ንግድ) የአብሮነት ማሳያችን መሆኑን በማንሳት በዚህም ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች ጋራ ሸንተረር እያቆራረጡ በየትኛውም አካባቢ ግብይት እንዲያከናውኑ አስችሏቸዋል፤ “ከዚህ በላይ የአብሮነት እና የመቻቻል ማሳያ የለም፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ብንኖርም የሚቀድመው እና የሚያስተሳስረን ኢትዮጵያዊነት ነው” የሚሉት ምሁሩ በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም ስለ ብሔሩ ከማውራቱ በተጨማሪ ክልል በሚል መታጠሩ የኢትዮጵያዊነትን ስዕል እንዲዋጥ ማድረጉን ነው የገለጹት፡፡

ሀገራችን የውጪ ወራሪዎችን አሳፍሮ በመመለስ እና በጭቆና ውስጥ ለነበሩ ሀገራትም ነጻነታቸውን እንዲያውጁ ብርሃን የፈነጠቀች ናት፤ ለዚህ ቁልፉ ደግሞ ጠላትን በኢትዮጵያዊ አንድነት አሳፍረን የመመለስ ታሪክ ስላለን ነው::ይህ የኢትዮጵያዊነት ጽናት ታዲያ ሀገራችን እንደ ሀገር እንድትቀጥል በማድረግ ለአሁኑ ትውልድ እንድትሸጋገር አድርጓታል፡፡

ሂስትሪ ዶት ኮም ላይ ያገኘነው መረጃ እንዳስነበበው ብሔርተኝነትን መሠረት አድርገው ሀገረ መንግሥታቸውን ያዋቀሩ ሀገራት በርካታ ችግሮችን አስተናግደዋል፣ ጦሱን ተረድተው ፈጥነው የወጡ እና ሀገራዊ አንድነትን አስቀድመው የሠሩ ሀገራትም ወደ ዕድገት ጎዳና ተመልሰዋል። ሩዋንዳ ደግሞ ለዚህ አብነት ተብላ ነው የምትጠቀሰው።

በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ሀገራዊ ታሪክን እና ሰላምን በተመለከተ ምሁራን የተሳተፉበት ምክክር ተካሂዶ ነበር። በምክክሩ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማሕበር ፕሬዘዳንት ባሕሩ ዘውዴ (ፕ/ር) ታሪክን የማያውቅ ዜጋ መሠረት እንደሌለው ተናግረዋል። በመሆኑም የወል ትርክትን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት ይህን በማድረግም  “ሀገርን ማሳደግ ይቻላል” ብለዋል።

የባሕል ጥናት ምሁሩ ዶክተር ተመስገን በየነ ኢትዮጵዊያን አንድ እንድንሆን የሚያደርጉንን በርካታ አብነቶች ያነሳሉ፤ የአድዋ የድል በዓል፣ አዲስ ዓመት አከባበራችን፣ አማኝነታችን፣ ከተሞችን የመመሥረት ልምዳችን (ከተሞችቻችን የተመሠረቱት ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ አካባቢዎች በመሰባሰብ መሆኑን ልብ ይሏል) እና መሰል ትውፊቶቻችንን ያነሳሉ፤

በተመሳሳይ ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓታችን ችግሮችን ለመፍታት የምንጠቀምበት የኢትዮጵዊያን ትውፊት መሆኑን ተናግረዋል፤ ይህ ደግሞ (አተገባበሩ እንደየ ቦታው ቢለያይም) የተለያዩ ማኅበረሰቦች እንዲተዋወቁ፣ ተቻችለው እንዲኖሩ፣ ከዚያም አለፍ ሲል በጋብቻ ኢትዮጵዊነትን በማጥበቅ ለመኖር አስቻይ ሀብታችን ነው::ከዚህ ባለፈም ለዘመናዊ ሕጉም አጋዥ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ዶክተር ተመስገን እንዳስገነዘቡት ኃያላን ሀገራት ኃያልነታቸውን ያመጡት በአንድነታቸው ነው፤ ለዚህ የምትጠቀሰው ደግሞ አሜሪካ ናት::ሀገሪቱን የገነቧት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ሕዝቦች ናቸው፤ በታሪካቸው፤ በአሜሪካዊነታቸው እና በመሰል ጉዳዮች ደግሞ አንድ ናቸው::ይህ መሆኑ ታዲያ ለሀገሪቱ ኃያልነት መሠረት መጣሉን አብራርተዋል፡፡

በአንድ እንድንተሳሰር እጅግ ብዙ መገለጫዎች ያሏት ሀገራችን ታዲያ (ከላይ ያነሷቸውን ትውፊቶቻችን በማስታወስ) ከገባችበት ችግር እንድትወጣ መሠረቶቿ ሊሆኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም በተለይ ምሁራን በማስረጃ የተደገፈ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ታሪክን በማሳወቅ የጋራ ትርክት እንድንገነባ   ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያሏትን ትውፊቶች በመዘርዘር “በእጅ የያዙት ወርቅ … ሆነውብናል” ያሉት ዶክተር ተመስገን ዋጋቸውን አጉልተን በማሳየት ከገጠሙን ችግሮች ለመውጣት እና የጋራ ትርክት ለመፍጠር መጠቀም እንደሚገባ ሙያዊ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል::በተመሳሳይ የሀገራችን ብዙኃን መገናኛ ተቋማት ለውጪ ሀገር ርእሰ ጉዳይ ብዙ ትኩረት እንደሚሰጡ በመጥቀስ የተቹት ምሁሩ ይህ መሆኑ ደግሞ “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር አውሮፓዊ ወጣትን ፈጥሯል” ነው ያሉት፤ በመሆኑም ሀገራዊ አንድነትን፣ የጋራ ትርክትን በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ እና በጋራ ዕሴቶቻችን ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሺ ዘመናት ጉዞዋ በመስዋዕትነት ነው ከዚህ የደረሰችው። ለዚህ ደግሞ ሕዝቧን ያስተሳሰሩ ብዝኃ ዕሴቶቿ መሠረት ናቸው። እነዚህ ጸጋዎች ታዲያ የማንነት መገለጫ ብቻ ሳይሆኑ ማሕበረሰብን በአንድ ያጋመዱ ናቸው። በመሆኑም ዕሴቶቹን ገዢ ትርክትን ለመገንባት መጠቀም እንደሚገባ የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ምክትል ፕሬዚዳንት ቹቹ አለባቸው (ዶ/ር) ተናግረዋል። ምሁሩ ለአሚኮ እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ዕሴቶች እየተሸረሸሩ ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ነጠላ ትርክት ላይ ሲቀነቀን መቆየቱ እና በአክራሪ ፖለቲከኞች (ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ዝቅ የማድረግ) ሆን ተብሎ ስለተሠራበት ነው።

የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ ታሪክ ማሳነስ ሆን ተብሎ ቢሠራበትም አሁንም ድረስ ያስተሳሰረን ዋናው ነገር ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊነት ዕሴት ነው ብለዋል።

እንደ ዶክተር ቹቹ ማብራሪያ በአንድነት አስተሳስረውን የቆዩ ዕሴቶቻችን ፈተና ውስጥ ቢገቡም መጠበቅ ይገባል።  በአሁኑ ወቅት ገዢ የጋራ ትርክት ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረትም እነዚህን ዕሴቶች ለማከም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። ገዢ ትርክትን ለመገንባት ታዲያ የኢትዮጵያዊነትን ብዝኃ ዕሴቶች መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ “ከፖለቲካ ታሪኮች ባለፈ ሌሎች የጋራ ታሪኮችን ማጉላት ይገባል” ማለታቸው ይታወሳል። ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁልጊዜም አንድ የሆነች ጠንካራ ሀገርን መገንባት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የጋራ፣ የወል የሆነ፣ የማይገፋ እና ሁሉን የሚያቅፍ ትርክት እንገንባ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ታሪክን በተመለከተም ለሙያተኞች መተው ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here