ባለፈው ሳምንት ዕትማችን ከዶ/ር ቹቹ አለባቸው ጋር ስለ ውልደት እና እድገታቸው፣ ስለትምህርት እና የሥራ ሁኔታቸው፣ “ዳገት ያበረታው የአማራ ፍኖት” በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ስላነሷቸው አንኳር ጉዳዮች፣ ከወሰን እና ማንነት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ችግሮች ምንጫቸው ምን እንደሆነ እና መፍትሔያቸው ምን መሆን እንዳለበት አንስተን በሰፊው ተወያይተናል:: በዚህ ክፍል ሁለት እና የመጨረሻው ዕትማችን ደግሞ ከዶ/ር ቹቹ አለባቸው ጋር የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ አድርገናል፤
መልካም ንባብ!
ሀገራችን ከጦርነት አዙሪት ውስጥ ልትወጣ ያልቻለችው ለምን ይሆን?
ሀገራችን እንደ ሀገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ታሪኳን ስንመለከት አብዛኛው ከጦርነት ጋር የተያያዘ ነው:: የጦርነት ምንጩ ደግሞ ውጫዊ እና ውስጣዊ ነው:: የውጭ የምንለው ጦርነት ኢትዮጵያን ለመውረር እና በቅኝ ግዛት ሥር ለማዋል በሚፈልጉ የውጭ አካላት ሀገራችን ላይ በተደጋጋሚ የተቃጣው ጦርነት ነው፤ ወይም ደግሞ ሀገራት ከኢትዮጵያ የሚፈልጉትን ልዩ ጥቅም በግድ ለማግኘት የሚፈፅሙት ጦርነት ነው:: ኢትዮጵያም የዚህ ዓይነት ጦርነቶችን ለመመከት በርካታ ዓመታትን አሳልፋለች::
ሀገራችን እና መሪዎቿ በውጭ ወራሪዎች ምክንያት በርከት ያሉ መስዋዕትነቶችን ከፍለዋል:: ለአብነት እናንሳ ካልን እንኳን ዐፄ ዮሐንስ የተገደሉት ከውጭ ወራሪዎች ጋር ባደረጉት ትግል ነው:: ዐፄ ቴዎድሮስ የተሰውት ከእንግሊዝ ጋር በተደረገው ውጊያ ነው:: በጣሊያን ወረራ ወቅት ብዙ ኢትዮጵያዊያን እና የጦር መሪዎቻቸው ለሀገራቸው ሉዓላዊነት መከበር ሲሉ የበዛ መስዋዕትነት ከፍለዋል:: ሀገራችን ከቱርክ፣ ከጣሊያን፣ ከእንግሊዝ፣ ከግብፅ፣ ከሶማሊያ እና ከሌሎችም አካባቢዎች ከመጡ የውጭ ወራሪዎች ጋር የተራዘሙ ጦርነቶችን አድርጋለች::
በዘመነ መሳፍንት ወቅትም ቢሆን ሀገራችን ለግዛት ማስፋፋት እና ለፖለቲካ የበላይነት በሚደረጉ ጦርነቶች ውስጥ ቆይታለች:: በዚህ ዓይነቱ የእርስ በርስ ጦርነት ምጣኔ ሀብታዊ የበላይነትን እና የስልጣን የበላይነትን ለማግኘት ሲባል በርካታ ዜጐች እርስ በራሳቸው ተገዳድለዋል:: የእነዚህ ጦርነቶች ዓላማ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ለግዛት እና ለስልጣን የበላይነት እንጂ ብሔርን ወይም ማንነትን መሰረት ያደረጉ አልነበሩም::
በኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት መልኩን እየቀየረ የመጣው ከ1960ዎቹ ወዲህ ነው:: ከ1960 ዎቹ ዓ.ም ወዲህ እየተደረጉ የመጡት ጦርነቶች በጣም አስቸጋሪ እና ውስብስቦች ናቸው:: ከዚያ በፊት ከነበሩት የእርስ በርስ ጦርነቶች በባህሪያቸው ፍፁም የተለዩም ናቸው:: ከ1960ዎቹ በኋላ በሀገራችን ውስጥ ይደረጉ የነበሩ ጦርነቶች ግን መነሻቸው አንድን ሕዝብ በተሳሳተ ትርክት በበላይነት መፈረጅ እና በዚያ ሕዝብ ላይ ሌላው ሕዝብ እንዲነሳበት የማድረግ ስልትን የተከተሉ ናቸው::
የደርግ ሥርዓት ብዙም በብሔር ፖለቲካ የሚታማ ባይሆንም ንጉሡን ከስልጣን ያወረደበት እና የተረከበውን ስልጣን ለማስተዳደር የሄደበት መንገድ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር:: ደርግ እንዲያውም በብሔር ከተደራጁ እንደ ሕወሓት፣ ኦነግ እና ሻኢቢያ ጋር ጦርነቶችን ሲያደርግ የብሔር አደረጃጀትን የሚቃወም የፖለቲካ መስመር የነበረው ነው:: ያም ቢሆን ግን በርከት ያሉ የብሔር ድርጅቶች ማበብ የጀመሩት በደርግ መንግሥት ወቅት ነው::
ደርግ የነገስታቱን ስርዓት በኃይል ካፈረሰ በኋላ እኩልነትን እና ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ብሎ ነበር፤ በተግባር የታየው ግን ይሄ አልነበረም:: በደርግ ስርዓት ወቅት በርካታ የብሔር ፖለቲከኞች መፈጠራቸው ብቻ ሳይሆን በርካታ አማራ ጠል የሆኑ ድርጅቶች ትግል የጀመሩበትም ወቅት ነው:: የደርግ ስርዓት ከስልጣኑ የተገለለውም በእርስ በርስ ጦርነት ነው:: የአንድነት ኃይሎች ተሸንፈው የብሔር ድርጅቶች ወደ ስልጣን የመጡትም በዚህ ወቅት ነው::
የደርግ ስርዓት የንጉሡን ስርዓት በኃይል ገለበጠ፤ እሱም በሌሎች ኃይሎች በኃይል ተገለበጠ:: እዚህ ጋር ያለው የሀገራችን ስብራት ስልጣንን በጦርነት እንጂ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መረካከብ አለመቻላችን ነው:: በጦርነት እና በመገዳደል ስልጣን መያዝን ባህላችን አድርገነዋል:: ከደርግ ስልጣንን የተረከበው ሕወሓት ይሄንን አምኖ ባለመቀበሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተገብቷል:: የበርካታ ዜጐችን ህይወት ከነጠቀው የሰሜኑ ጦርነት ትምህርት ባለመውሰዳችን አሁን ላይ ደግሞ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ለሌላ የከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ተዳርገን እንገኛለን:: በኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ስርዓት በአግባቡ ስላልሰፈነ ሀገራችንን በእርስ በርስ ጦርነት የምትታወቅ ሀገር እንድትሆን አድርገናታል::
ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ስርዓት አለመገንባታችን ሀገራችንን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው:: የፖለቲካ ባሕላችን ትልቁ ስብራትም ይሄው ነው:: ይህንን ስብራት መጠገን ባለመቻላችን ሀገራችንን ከጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳትወጣ አድርጓታል:: ስልጣን የሚነጠቅ አካል ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ ካላስረከበ እና ስልጣን ነጣቂውም በጉልበት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ማግኘት ካልቻለ ሀገሪቱ በጦርነት አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ የመፍረድ ያህል ነው::
ከዚህ ችግራችን መውጫ መንገዱ ምን ይሆን?
የዚህ ችግር መውጫ መንገዳችን የዴሞክራሲ ባሕልን ማዳበር ብቻ ነው:: ዴሞክራሲ የብዙዎችን ስሜት የሚገዛ በመሆኑ ዴሞክራሲን በመለማመድ እና በማዳበር ከእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መውጣት እንችላለን ብዬ አምናለሁ:: እስካሁን የመጣንበት ስልጣንን በጉልበት የመያዝ መንገድ እርስ በርስ አጠፋፋን እንጂ ጠቅሞናል ብዬ አላምንም:: የዴሞክራሲ ስርዓት አለመገንባታችን ይሄን ያህል ዋጋ ካስከፈለን እና ሀገራችንን ከጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳትወጣ ካደረጋት ይሄንን ማስተካከል ያስፈልጋል:: የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታችን የእርስ በርስ ጦርነታችን መቋጫ ምዕራፍ መሆን ይኖርበታል::
በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭትስ የዚሁ እሳቤ ነፀብራቅ ይሆን?
አሁን ላይ ነጥረው የወጡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፤ አንደኛው የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የወሰን እና የማንነት ጥያቄ ነው፤ ከክልሉ ውጪ የሚገኙ የአማራ ብሔር ተወላጆች መብት እና የፖለቲካ ተሳትፎ ሌላው ጥያቄ ነው፤ ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እና የሕግ መንግሥቱ ይሻሻልልኝ ጥያቄዎች በአማራ ሕዝብ ዘንድ ተደጋግመው የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው:: እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ ተጨባጭ ጉዳቶችን አድርሰዋል:: አብዛኛው የአማራ ሕዝብ የተበድያለሁ ስሜት እንዲኖረው ያደረጉትም እነዚሁ ጉዳዮች ናቸው:: ሕዝቡ ለህልውና ስጋት ተዳርጌያለሁ የሚለውም በእነዚሁ ምክንያቶች ነው::
እነዚህ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በክልሉ መንግሥት እና በፌደራሉ መንግሥትም እውቅና የተሰጣቸው ናቸው:: ጥያቄዎቹ መመለስ ያለባቸው ግን በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መሆን አለበት::
እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ እስካላገኙ ድረስ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚታየው ችግር በአጭር ጌዜ ይቋጫል የሚል እምነቱ የለኝም:: መንግሥትም የችግሮቹ ውስብስብነት፣ ጊዜ ፈላጊነት እና ሌሎችም ጉዳዮች ካላስቸገሩት በቀር ለችግሮቹ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይሠራል የሚል እምነቱ አለኝ::
የአማራ ሕዝብ አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች በሌሎቹ የሀገሪቱ ሕዝብ እጅ ላይም የወደቁ ናቸው:: ለአብነት ያህልም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ፣ የወሰን እና ማንነት ጉዳይ፣ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ አማራዎች እና ሌሎችም ጉዳዮች በተናጠል የሚፈቱ ችግሮች አይደሉም:: ችግሮቹ ሆን ተብለው የተፈጠሩ እና የተቆላለፉ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ለመፍታትም አስቸጋሪዎች ናቸው:: እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ተሳትፎ ይጠይቃል፤ የሌሎችን ተሳትፎ እና ትብብር ጠየቀ ማለት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች ወይም ምክክሮች ያስፈልጋሉ ማለት ነው::
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አንደኛው እና ሁነኛ አማራጭ ይመስለኛል:: የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በምክክር ኮሚሽኑም በኩል ሳይፈቱ የሚቀጥሉ ከሆነ የአማራ ሕዝብ ቅሬታም አብሮ የሚቀጥል ይሆናል:: የሕዝቡ ጥያቄዎች ወደ ፊት በትክክል ይመለሳሉ የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፤ የክልሉ መንግሥትም እዚህ ላይ ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን አውቃለሁ::
እንደኛ በችግር ውስጥ ያለፉ የውጭ ሀገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል?
በኛ ሀገር የተከሰቱ ችግሮች በኛ ሀገር ብቻ የተከሰቱ አይደሉም:: ብዙ ሀገራት በእውነተኛ ዴሞክራሲ እጦት ብዙ መከራዎችን አሳልፈዋል:: አንዳንዶቹም ችግሮቻቸውን በተገቢው መልኩ አክመው ለብዙዎቻችን ተምሳሌት ሆነዋል:: ለምሳሌ ሩዋንዳዎች በማንነት ወይም በጎሳ ፖለቲካ ብዙ ሕዝባቸውን በጦርነት ያጡ ናቸው፤ እነዚሁ ሩዋንዳዊያን ዛሬ ላይ ከስህተታቸው ተምረው ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን መንግሥት አፅንተዋል:: ደቡብ አፍሪካዊያንም በነጮች አገዛዝ ብዙ መከራ ያዩ ቢሆንም የመቻቻል ፖለቲካን ለዓለም ሕዝብ ያስተማሩ ሆነዋል::
ኢትዮጵያዊያንም ከሁለቱ የአፍሪካ ሀገራት ብዙ ትምህርቶችን መውሰድ እንችላለን:: የኛ ሀገር ችግር የማይፈታ አይደለም:: ችግራችንን ለመፍታት ግን በሁላችንም ዘንድ ቁርጠኝነት ያስፈልጋለ:: በተለይ የመሪዎች ቁርጠኝነት በጣም አስፈላጊው ነገር ነው:: ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንም የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፎች መሆን አለባቸው::
ከምንገኝበት ሁለንተናዊ ችግር በምን እንውጣ?
የአማራ ክልል እና ኢትዮጵያችን የሚገኙበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም:: ችግራችን የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጫናም ያለበት ነው:: ከሰላም ማጣታችን በተጨማሪ የኑሮ ውድነቱ የሀገራችንን ሕዝብ በእጅጉ እየፈተነው ነው:: በተለይም የአማራ ክልል ብዙ ውስብስብ ችግሮች ገጥመውታል:: በኦሮሚያም ተመሳሳይ ችግሮች እየታዩ ነው:: እነዚህን ችግሮች በተናጠል ሳይሆን በጋራ መፍታት ካልተቻለ የአንደኛው ክልል መታመም ለሌላውም ሕመም ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም:: የጋራ እሳቤ ከሌለን ሀገርን በጋራ ማዳን አንችልም::
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የገጠሟት ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች ናቸው:: የአማራ ክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ ይበልጥ ማተኮር ያለባቸው በውስጣዊ ችግሮቻችን ላይ ነው፤ ውስጣዊ ችግሮቻችንን መመልከት ከቻልን የውጭ ችግሮቻችንን ለመመከት አንቸገርም:: ከሁሉም በላይ ለሰላማችን የቅድሚያ ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅብናል:: መንግሥት ትጥቅ አንግበው ወደ ግጭት ከገቡ አካላት ጋር ሊያደርግ ያሰበውን ውይይት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል::
ከግጭት የሚያተርፍ አንድም አካል የለም:: ሰላማዊ ውይይት እና ድርድር ምርጫ የሌለው ምርጫችን ነው:: አብዛኛውን ጊዜ የሀገራችን ችግሮች መንስኤዎቹ ኤሊቶቹ ናቸው:: የሀገራችን ሕዝብ በኤሊቶቹ አስተሳሰብ ቢመሩ ኖሮ የዚች ሀገር ዕጣ ፈንታ መፈራረስ ብቻ በሆነ ነበር:: ደግነቱ ማኅበረሰቡ ያለው እሴት እና ኤሊቱ ያለው አስተሳሰብ የተለያዩ ናቸው::
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው እርስ በርስ የተጋባ እና የተዋለደ ነው:: አብዛኛው የጋራ የሆኑ እሴቶች ያሉት ነው:: የኤሊቱ የተዛባ እና የተሳሳተ አመለካከት ግን የማኅበረሰቡን የአንድነት ገመድ ለመበጠስ የሚጥር ነው::
የኤሊቱ የተሳሳተ እና ማኅበረሰብን አፍራሽ እሳቤ በጊዜ መፍትሔ ካልተበጀለት ማኅበረሰቡን የሚነጣጥል እና የሚጐዳው ነው፤ አሁን ላይ እየታየ ያለው አዝማሚያም ይሄው ነው:: በተለይም በአማራ እና በኦሮሞ፣ በአማራ እና በትግራይ፣ በትግራይ እና በኦሮሞ ኤሊቶች መካከል ያለው ልዩነት በኤሊቶቹ ዘንድ ብቻ ታጥሮ ቀርቷል ማለት አይቻልም::
የዚህች አገር የፖለቲካ ችግር መሰረታዊ ምንጩ የኤሊቱ የተበላሸ የፖለቲካ እይታ ነው፤ ይሄ እይታ በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት ባለመኖሩ ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብን አያያዥ ገመዶች ሙሉ በሙሉ አልተበጠሱም:: ይህ ማለት ግን ወደ ፊትም አይበጠሱም ማለት አይደለም እና ይህንን ማስቆም ያስፈልጋል::
መንግሥትም በዚህ ረገድ ሚናውን መወጣት ይኖርበታል:: ነጣጣይ ኤሊቶችም ሀገራቸውን ከማፍረስ የሚያገኙት ጥቅም ስለሌላቸው ወደ መግባባት ፖለቲካ መመለስ ይኖርባቸዋል እላለሁ::
ለሰጡን ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች ከልብ እናመሰግናለን!
እኔም በጋዜጣዋ ለተሰጠኝ ዕድል መሰግናለሁ!
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።