ኢትዮጵያውያን በኦሎምፒክ

0
259

የ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ከአራት ቀናት በኋላ ይጀመራል:: በኦሎምፒክ ድግሱ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክም ወደ ቦታው አምርቷል:: ሀገራችን በኦሎምፒክ መድረክ ዘግይተው መሳተፍ ከጀመሩ ሀገራት መካከል አንዷ ነች:: ከግብጽ፣ ከናይጀሪያ፣ ከጋና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከመሳሰሉት ሌሎች ሀገራት ዘግይታ መጀመሯን ታሪክ ያስረዳል::

ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችውም በ16ኛው ኦሎምፒያድ ነው:: በአውስትራሊያ ሜልቦርን በተደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ሀገራችን በሁለት የስፖርት ዘርፎች መሳተፏን መረጃዎች ያመለክታሉ:: በአትሌቲክስ እና በብስክሌት ስፖርት ብቻ ተሳትፋለች:: በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከመቶ እስከ አንድ ሺህ 500 ሜትር ርቀት፣ በ4X100 እና 4X400 ዱላ ቅብብል እንዲሁም በማራቶን ውድድር ማሞ ወልዴን ጨምሮ ስምንት አትሌቶች ተካፍለዋል::

በብስክሌት ውድድር ደግሞ ገረመው ደንበቦን እና ሌሎች ሦስት አትሌቶች መሳተፋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ:: በዚህ የሜልቦርኑ  መድረክ ሁሉም ኢትዮጵያውያን  ማጣሪያውን ማለፍ ባለመቻላቸው ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም:: ይሁን እንጂ አሁን ደረስ እየተመዘገበ ላለው ውጤት መሰረት የተጣለበት መሆኑ ይነገራል::

በአትሌቲክሱ ዘርፍ የታሪክ ተቀናቃኝ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኬኒያ እና ዩጋንዳም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1956ቱ የሜልቦርን ኦሎምፒክ መሳተፋቸው በታሪክ ማህደራቸው ተመዝግቧል:: እ.አ.አ በ1960 በተካሄደው የሮም ኦሎምፒክ ደግሞ አትሌት አበበ ቢቂላ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ወደ አፍሪካ ምድር በማምጣት ለአፍሪካውያን አዲስ የብርሃን መንገድ ከፍቷል::

በ17ኛው የኦሎምፒክ ድግስ ሀገራችን 83 ተሳታፊዎችን ነበር ወድ ጣሊያን የላከችው:: በመቶ፣ 400፣ 800፤ አምስት ሺህ፣ ዐስር ሺህ እና ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተካፈሉባቸው ርቀቶች ነበሩ:: በብስክሌት ስፖርትም አምስት ተወዳዳሪዎች ወደ ቦታው ማቅናታቸውን ታሪክ ያወሳል:: በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ አብዛኞቹ ትወዳዳሪዎች ማጣሪያውን እንኳ አላለፉም::

አበበ ቢቂላ ግን ማንም ሳይጠብቀው በወቅቱ ታዋቂ የነበሩትን የማራቶን አትሌቶች ራሒም ቢን አብዱሳላምን እና ሰርጊ ፖፖቭን በባዶ እግሩ በመሮጥ አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል::  ይህም በኦሎምፒክ ታሪክ  የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አድርጎታል:: ድሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ አፍሪካውያን ጭምር የድል ብስራት ተደርጎ ተወስዷል::  በርካታ የጣሊያን ጋዜጦችም “አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮምን ወረረ” በማለት በስፋት ዜናውን አስነብበዋል::

የአበበ የባዶ እግር ገድል ለብዙ ኢትዮጵያውያን እና አፍሪካውያን ስፖርተኞች መነቃቃትን ፈጥሯል:: ከአበበ ቢቂላ ጋር በማራቶን ውድድር አብሮ የተካፈለው አበበ ዋቅጅራ ደግሞ ሰባተኛ ሆኖ ነበር ያጠናቀቀው:: ከዚያ ወዲህ ኢትዮጵያ በተወዳደረችበት የኦሎምፒክ መድረክ አንድም ጊዜ ያለ ሜዳሊያ ተመልሳ አታውቅም::

በ1964 እ.አ.አ በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው ኦሎምፒክም የአበበ ቢቂላ ጀብድ ቀጥሏል:: ሻምበል አበበ ቢቂላ በማራቶን ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አምጥቷል:: በወቅቱ ኢትዮጵያ ከቶኪዮ አዲስ አበባ ይዛው የገባችው ብቸኛው ሜዳሊያም ነበር:: ከ60 ዓመታት በፊት በሩቅ ምስራቋ ሀገር በተደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ እና ከብስክሌት በተጨማሪ ለመጀመሪያ ግዜ በቡጢ ስፖርትም የተሳተፈችበት ጊዜ ነበር::

ኢትዮጵያ አሁን በኦሎምፒክ ውድድሩ ልምድ እያካበትች በመሆኑ በአትሌቲክሱ ዘርፍ የዓለምን ትኩረት መሳብ ጀምራለች:: ውጤቱም በሥራ እንጂ በአጋጣሚ የመጣ አለመሆኑን ሁሉም መመስከር ጀምረዋል:: በ1968ቱ የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ደግሞ ማሞ ወልዴ የደመቀበት እንደነበር ያስመዘገበው ውጤት ያሳያል:: በአውስትራሊያ ሜልቦርን፣ በጣሊያን ሮማ እና በጃፓን ቶኪዮ በተከታታይ በመሳተፍ ልምድ ያካበተው ማሞ ወልዴ በማራቶን ወርቅ እና በዐስር ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ማሸነፍ ችሏል::

የሻምበል አበበ ቢቂላን እና የማሞ ወልዴን እግር በመከተል በሁለት ኦሎምፒኮች ሁለት ወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያ አምጥቷል- ማርሽ ቀያሪው  ምሩጽ ይፍጠር:: ምሩጽ እ.አ.አ በ1972ቱ የሙኒክ ኦሎምፒክ በዐስር ሺህ ሜትር ርቀት የብር ሜዳሊያ በማምጣት በድል ጀምሯል:: እ.አ.አ በ1980 የሞስኮ ኦሎምፒክ ደግሞ በአምስት ሺህ እና በዐስር ሺህ ሜትር ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል:: ማርሽ ቀያሪው በአንድ የኦሎምፒክ መድረክ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊም መሆን ችሏል::

በወቅቱ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት አትሌቶችን ያሳተፈችበት ጊዜ እንደነበረም ታሪክ ያወሳል:: ወደ ሞስኮ ከተላኩት 41 ስፖርተኞች መካከል ሁለቱ ሴቶች እንደነበሩ የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ:: ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በሦስት መድረኮች ብቻ ነው ያልተሳተፈችው:: እ.አ.አ በ1976 በካናዳ ሞንትሪያል፣ በ1980 በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ እና በ1984 በደቡብ ኮሪያ ሲኦል በተደረገው ኦሎምፒክ ሀገራችን አልመሳተፏን የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ድረ ገጽ ያስነብባል::

ያልተሳተፈችበትን ምክንያት ድረ ገጽ ድረ ገጹ ሲያብራራ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ ስርዓት በመቃወም እንደሆነ ያስረዳል:: ከ12 ዓመታት ተቃውሞ በኋላ ግን በ1992ቱ የባርሴሎና ኦሎምፒክ ተመልሳለች:: በ25ኛው የባርሴሎና ኦሎምፒያድ ደራርቱ ቱሉ በዐስር ሺህ ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ አይዘነጋም:: ኮማንደር ደራርቱ በኦሎምፒኩ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት በመሆን ስሟ በክብር መዝገብ ሰፍሯል::

በስፔን ባርሴሎና አትሌት አዲስ አበበ በዐስር ሺህ እና ፊጣ ባይሳ በአምስት ሺህ ሜትር ርቀቶች ተጨማሪ የነሐስ ሜዳሊያዎችን አምጥተዋል:: በጣሊያን ሮም በአበበ ቢቂላ የተጀመረው ገድል በየጊዜው ታላላቆችን አፍርቷል፤ እያፈራም ይገኛል:: በማሞ ወልዴ እና ምሩጽ ይፍጠር የትውልድ ቅብብሎሽ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ዘንድ ደርሷል:: በስፔን ባርሴሎና “ሀ” ተብሎ በደራርቱ ቱሉ የተገኝው ድል ለፋጡማ ሮባ፣ መሰረት ደፋር እና ጥሩነሽ ዲባባ መፈጠር ምክንያት ሆኗል:: ፋጡማ ሮባ በኦሎምፒክ በማራቶን ውድድር ወርቅ ያሸነፈች የመጀመሪያው አትሌት መሆኗ ይታወሳል::

ካለፉት 14 የኦሎምፒክ መድረኮች ሀገራችን የተሻለ ውጤት ያስመዘገበችው ከፈረንጆች ሚሊኒየም ወዲህ ባለው ውድድር ነው::  በፈረንጆች 2000 በሲድኒ እና በ2008 በቤጂንግ በተደረጉ ኦሎምፒኮች ነው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻለችው:: በፈረንጆች ሚሊኒየም በአውስትራሊያ ሲዲኒ በተደረገው የኦሎምፒክ ድግስ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስምንት ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ የራሷን ክብረወሰን አሻሽላለች:: ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የወርቅ ሜዳሊያ ነው:: ይህም እስካሁን ድረስ ትልቁ የኦሎምፒክ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡  ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ እ.አ.አ ከ1996ቱ የአትላንታ ኦሎምፒክ በኋላ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በዐስር ሺህ ሜትር ያሸነፈበት ጭምር ነው::

በተመሳሳይ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉም በዐስር ሺህ ሜትር፣ ሚሊዮን ወልዴ በአምስት ሺህ ሜትር እና ገዛኸኝ አበራ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያዎችን አምጥተዋል:: ጌጤ ዋሜ በዐስር ሺህ ሜትር ብር እና በአምስት ሺህ ሜትር ርቀት የነሐስ ሜዳሊያ ለሀገሯ አስገኝታለች:: እንዲሁም አሰፋ መዝገቡ በዐስር ሺህ ሜትር እና ተስፋዬ ቶሎሳ በማራቶን ተጨማሪ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች ናቸው:: በተመሳሳይ በቤጂንግ ኦሎምፒክም የኢትዮጵያ ልዑክ አባላት ከአራት የወርቅ ሜዳሊያ ጋር  አዲስ አበባ እንደገቡ አይዘነጋም::

በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ቀነኒሳ በቀለ በአምስት ሺህ እና ዐስር ሺህ ሜትር ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ድርብ ድል ማስመዝገብ ችለዋል:: አትሌት ቀነኒሳ በሁለትም ርቀቶች ክብረወሰን በማስመዝገብ ጭምር ነው ያሸነፈው:: ስለሺ ስህን እና መሰረት ደፋር ደግሞ የብር ሜዳሊያ ሲያመጡ፤ ፀጋዬ ከበደ በማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ይዞ አዲስ አበባ ገብቷል::

ከፈረንጆች ሚሊኒየም ወዲህ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድርከ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበችበት ወቅት የ2020ው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ነው:: በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አንድ ዓመት ተገፍቶ በተደረገው ውድድር ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የተባለውን ውጤት ነበር ያስመዘገበችው:: በወቅቱም በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን አስነስቶ እንደነበር አይዘነጋም:: በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴው መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ አልፏል::

በቶኪዮ ኦሎምፒክ ብቸኛው የወርቅ ሜዳሊያ ያገኝችው በአትሌት ሰለሞን ባረጋ አማካኝነት ነው:: በለሜቻ ግርማ ብር፣ በለተሰንበት ግደይ እና ጉዳፍ ፀጋዬ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ መገኝቱ የሚታወስ ነው:: በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እና ኦሎምፒክ ኮሚቴው አለመግባባት ምክንያት፤ የአትሌቶች ምርጫ እንደነበር አይዘነጋም:: አትሌቶች ለኦሎምፒክ የሚመረጡበት መስፈርት ወረቀት ላይ ቢሰፍርም ሁለቱ ተቋማት ግን ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ውዝግቦችን አስነስቷል:: በውጤቱ ላይም ተጽዕኖ አሳድሮ አልፏል::

ኢትዮጵያ እስካሁን በተሳተፈችባቸው 14 የኦሎምፒክ መድረኮች 58 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች:: ከእነዚህ ውስጥ 23ቱ የወርቅ ሜዳሊያ ነው:: 12 የብር እና 23 የነሐስ ሜዳሊያዎች አሏት:: ይህ የሜዳሊያ ብዛትም ከአህጉራችን፤  ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አስችሏታል:: ደቡብ አፍሪካ በ27 ወርቅ፣ 33 ብር እና 29 ነሐስ በድምሩ በ89 ሜዳሊያዎች ከፍሪካ በርካታ ሜዳሊያ በመያዝ ቀዳሚ ሀገር ናት::

በ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ በአትሌቲክስ እና ወኃ ዋና ስፖርት ዘርፍ 34 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚካፈሉ ይሆናል:: ምን ዐይነት ውጤት ይመዘገባል የሚለውን ከአራት ቀን በኋላ በሚጀመረው ውድድር አብረን የምናየው ይሆናል:: አሚኮ በኩር ዝግጅት ክፍል ለተሳታፊ ስፖርተኞቻችን መልካም ምኞቱን ይገልጻል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here