አትዮጵያ የጥንታዊው ዘመን ኃያል ከሚባሉት ጥቂት መንግሥታት ተርታ ተደማሪ፣ የስልጣኔ ቀንዲል የሆነች፣ የተፈራና የተከበረ ሕዝብ እና ነገሥታት የገነቧት ትልቅ ሀገር ናት። መንግሥቷም በሁለት ዘመን ይከፈላል፤ የናፓታ እና የሜሮኢ ስርወ መንግሥት ዘመናት በመባል በተለያዩ ዘመናት ይጠራ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። የዚህ ስርወ መንግሥት ጥንታዊያን (የግሪክ እና የሮማዊያን) ፀሀፊዎች፣ የአሶራውያን ማስረጃዎች እንዲሁም መፅሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች እንደ ሰነዱት የናፓታውያን ግዛት መንግሥት አንዱ የኢትዮጵያውያን መንግሥት ተቀጥያ ነው። ይኸውም ቢያንስ ከሰሜኑ ጫፍ የቅዱስ ጀበል ባርካል ተራራ እስከ ደቡባዊው ክፍል ቴቤስን እና አስዋንን የሚያካትተውን የዓባይ ሸለቆን ይቆጣጠር የነበረ ሰፊ ግዛት ነው።
የጥንት ኢትዮጵያውያን (ኑባዊያን) ነገሥታት ከዓባይ ወንዝ ጎን ለጎን የተዘረጋን ሰፊ ግዛት ያስተዳድሩ ነበር። ነገር ግን ግብፅ በ8ኛው ክፍለ ዘመን ቅድመና ዓለም ላይ በውጭ ወራሪዎች አደጋ በተደቀነባት ወቅት ኑቢያውያን ደርሰው ታድገዋቸዋል። በዚያም 25ኛውን የግብፅ ዘረ መንግሥት መስርተው ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች በግብፅ ላይ ለመቶ ዓመታት ያህል ነግሰዋል። ከእነዚህ መካከል የካሽታ፣ ፒያንኮ እና ሻባካ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖችን ባለፈው ክፍል ተመልክተናል። ቀጣዩን እነሆ፤
ቲርሃቃ በ25ኛው የግብፃውያን ስርወ መንግሥት በጣም ከታወቁ የናፓታ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች መካከል አንዱ ነበር። ወደ ዙፋን የወጣው በ32 እድሜው ላይ ሲሆን ከ682 እስከ 663 ከክርስቶስ ልደት በፊት ቆይቷል። ፈርኦን ቲርሃቃ የሁለት ምድሮች ማለትም የኢትዮጵያ እና የግብፅ ገዥ እና ንጉሠ ነገሥት ነበር።
በእርሱ ግዛት ውስጥ ምጣኔ ሀብታዊ እና ባህላዊ ህይወትን ያሻሻለ አስተዋይ መሪ ነበር። በጥንታዊ የግብጽ እና ኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያ በርካታ ጥናት ያደረጉት ሰር ኢ. ኤ ዋሌስ በጅ እንደተናገሩት ቲርሃቃ አቅም ያለው እና ሀያል ንጉሥ ነበር። እንዲሁም እርሱ ከአሶራውያን ጋር በጦርነት ውስጥ ሆኖም እንኳ፣ በእርሱ የበቃ አመራር ስር የነበረችው ኢትዮጵያ ለሀያ አምስት ዓመታት ያህል የብልጽግና ዘመንን አጣጥማለች።” ይህ በተፈጥሮ ችሎታ የታደለ መሪ ሂታይታውያንን እና አሶራውያንን ወርሮ እንደነበር የሚያመላክት የድንጋይ ላይ ጽሁፍ ትቷል። የዓለም ንጉሠ ነገሥት እንደሆነ አድርጎ ራሱን ይቆጥርም ነበር። አንድ ታዋቂ ኢጂፒቶሎጂስት፣ “አስደናቂ የኔግሮ የበላይነት የነበረበት ዘመን” በማለት የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ፈርኦንን የስልጣን ዘመን ኃያልነት ገልፆታል። ዶ/ር ራንዳል ማክሌቨር የተባሉት የታሪክ ሊቅ እንደተናገሩትም፣ “አንድ አፍሪካዊ ጥቁር እንዲህ ራሱን የዓለም ንጉሠ ነገሥት አድርጎ ማየት መቻሉ በርግጥም አስደናቂ ነው” ብለዋል።
አገር ገንቢው ቲርሃቃ የፒያንኬ ልጅ ሲሆን በንጉሥ ሻባታካ እጅግ የተወደደ እና ከምርጥ ጄኔራሎቹ አንዱና ዋነኛው ነበር። ካዋ ውስጥ በሚገኙ የድንጋይ ላይ ጽሁፎች ላይ እንደተቀመጠው በምእራብ እስያ ላለበት ጦርነት እንዲያግዘው በሻባካ በኩል በተደረገለት ጥሪ መሰረት ቲርሃቃ ገና የሀያ ዓመት ወጣት እያለ የሚወዳትን እናቱን እና ኑቢያን ለቆ መሄዱን እንማራለን። ቲርሃቃ ከአጉቱ ጋር በተጠጋበት ሆኖ የወታደራዊና የመንግሥት ነክ ጉዳዮችን ሰልጥኗል። የእብራውያን እና የአሶራውያን ዜናዎች የአባቱ ጠላት ከነበረው ኤስራዶን ጋር ያደረጋቸውን ወታደራዊ ግጥሚያዎች ዘግበዋል። በ32 ዓመት እድሜው ወደ ስልጣን የወጣው ቲርሀቃ በወቅቱ የአሶራውያንን አደጋ ለመቋቋም ሙሉ ዝግጅት አልነበረውም። ቲርሀቃ አሶራውያን የኩሻውያን ግብፃውያንን ስርወ መንግሥት ትቢያ ለማድረግ ለጥቃት በሰፊው ሲዘጋጅ በተከታታይ ተግዳሮት ገጥሞት ነበር። በመጀመሪያ አስርት ዓመት የስልጣን ዘመኑ የተወሰኑ ድሎችን በሊቢያ እና በምእራብ እስያውያን ላይ ድል ቀንቶት የነበረ ከመሆኑም በላይ በፍልስጤም የፊንቃውያን ጠረፋማ ክፍልን ተቆጣጥሮ ነበር። እንዲሁም አሶራውያንን ወደ መጨረሻ የስልጣን ዘመኑ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራዎችን እስከፈፅሙበት የመጨረሻዎቹ የስልጣን ዘመኑ ድረስ በበርካታ ዘመቻዎች ድል ነስቷቸዋል።
እነዚህ ወታደራዊ ችግሮች የቲርሃቃን በሁለቱ የግዛት ወሰኖቹ ላይ ስርአት እና ፍትህን የማስፈን ግሩም ውሳኔውን እንዲሁም ቁርጠኝነቱን አላደናቀፉበትም። በእርሱ የአገዛዝ ዘመን ግብፃውያንን እና የኢትዮጵያ ግዛቶቹን እፎይታን ያጎናፀፈና በርካታ ሀውልቶችን እና ፒራሚዶችን መገንባት የቻለ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ፈርኦን እንደነበር ታሪኩን ያሳያል።
በመጨረሻም በ661 ቅድመ ዓለም፣ የአሶሩ ኤስራዶን ድል ማድረግ ቲርሃቃ ሰራዊቱን፣ ሚስቱን እና ልጆቹን በጠላት እጅ ትቶ ወደ ናፓታ ለመሠደድ ግድ ብሎታል። ቲርሃቃን ከሃዘን መብዛት የተነሳ በአምስት ዓመት ውስጥ ህይወቱ አልፏል። አስክሬኑም በሱዳን ካሉት ትልቁ በሆነው ፒራሚድ ውስጥ እንዳረፈ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ቲርሃቃ በአሶሪያውያን ተሸንፎ ኢትዮጵያውያን መንግሥታቸውን ለአያሌ ክፍለ ዘመናት ወዳስቀጠሉባት ናፓታ ከተማ ከተመለሰ በኋላ መዲናዋ በደቡብ በኩል ወደ ነበረችው ሜሮኤ የተዛወረ ሲሆን በዚህም ጠንካራ ወኔ የተላበሱት እና ቆነጃጅቱ ህንደኬዎቹ ስርወ መንግሥቱን ለረጅም ጊዜ መርተውበታል።
የመጨረሻው ግብፅን ያስተዳደረው ኢትዮጵያዊ ፈርኦን ታኑታሙን ነበር። ታኑታሙን የሻባካ ልጅ ሲሆን ከእርሱ በፊት በነበሩ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ኩነቶች የተነሳ በንጉሥነት የቆየው ለአጭር ጊዜ ሲሆን፣ ከ654 እስከ 648 ቅድመ ዓለም ድረስ ገዝቷል።
ኢትዮጵያዊው ፈርኦን ታኑታሙን የአሶራውያን የኔኮ ወራሪ ሰራዊት በማስወገድ፣ ግብፅን እንደገና ለመቆጣጠር፣ ባለ አንድ ሺህ በሮች ከተማ በመባል ወደ ምትታወቀው የግብፅ ትልቋ ከተማ ቴቤስ መሄዱን እና በመቀጠል ወደ ሌላኛዋ የግብፅ ከተማ ሜምፊስ እንደተመለሰ በሀውልቱ ላይ ተፅፎ ይገኛል።
የንጉሡ ሻባካ ልጅ እና የቲርሀቃ የወንድም ልጅ የነበረው ፈርኦን ታኑታሙን አሶራውያን በገጠማቸው ከባድ ሽንፈት ለማምለጥ ሲያፈገፍጉ ከኑብያ በመነሳት ዓባይን ተከትሎ ዘመተ እና መላ ግብፅን እንደገና ተቆጣጠረ። ምንም እንኳ የዴልታው ግብፃዊያን የጎሳ አለቆች እርሱን እንደ ንጉሣቸው በደስታ የተቀበሉት ቢሆንም በአሶራውያን ዘንድ ግን ተመሳሳይ አቀባበል አላገኘም። ቀዳማዊ ኔኮ ምንም እንኳ በጦርነቱ ቢገደልም ሰራዊቱን ግን መልሶ በመጠናከር ተጨማሪ ሀይል በማካተት ግብፅን እንደገና ለመያዝ ወደ ደልታው አካባቢ እንደተመለሱ ወደ ቴቤስ በመገስገስ ከተማዋን አወደሙ። ከአንድ ዓመት በኋላም የአሶሪያውያኑ አሱር ባኒፓል ሜምፊስን እንደገና በመቆጣጠሩ ነው ታኑታሙን ከሚስቶቹ ጋር ሰራዊቱን ይዞ ወደ ኩሽ የተሰደደው። ቴቤስም ሙሉ ለሙሉ በአሶራውያን እጅ ወደቀች።
የአሶራውያን ዳግም ወረራ ምንም እንኳ ኑባውያን በግብፅ ላይ የነበራቸው የበላይነት እንዲያከትም ቢያደርገውም የታኑታሙን ስልጣን ግን በላይኛው ግብፅ እስከ 648 ቅድመ ዓለም ድረስ እውቅና ነበረው። አሶራውያን አይለው ባይመጡ ኖሮ ኢትዮጵያ በምእራብ ሜዲትራኒያን አካባቢ ሀያል እንደሆነች ለተጨማሪ መቶ ዓመት ትቀጥል እንደነበር ይነገራል። ለዚህም እንደማሳያ የ25ኛው ስርወ መንግስት ትውልድ የሆነው ታኑታሙንን ተከትሎ በናፓታ የነገሰው ንጉሥ ናስታሰን የፋርሱን መሪ ካምቢሰስን ከግብፅ በማስወገድ ግብፅን ነፃ ለማውጣት መሞከሩን የታሪክ ሰዎች ያወሳሉ። ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያውያን ስርወ መንግስት ጨርሶ አበቃለት ማለት አይደለም። ምንም እንኳ የአሶራውያን በአካባቢው ይበልጥ እያጋነኑ በመሄድ የኩሻዊውን ስርወ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ከግብፅ የፈርኦኖች መንበር አራቁት። እናም ወደ ሁለተኛዋ ግዛታቸው ኑብያ በመመለስ መዲናቸውን በናፓታ ከዚያም በሜሮኤ እያደረጉ ግዛታቸውን አስከብረው ቀጥለዋል። በመጨረሻም ከሜሮኤ አክሱም ከትመው አዲስ የስልጣኔ አፈር ቀድደዋል።
ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች በግብፅ ለመቶ ዓመታት የዘለቀው 25ኛው ስርወ መንግሥት በግብፅ ስርወ መንግሥቶች ረጅሙ ነበር። ኢትዮጵያውያን ፈርኦኖች ግብፅን ሊያጠፏት አሰፍስፈው ከነበሩ አደገኛ ወራሪ ጠላቶች ታድገው፣ ባህልና ወግ፣ እምነቷን ሳታጣ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ያደረጉ፣ በርካታ ፒራሚዶችን የገነቡ፣ ግብፅን እና ኑብያን (ኢትዮጵያን) ሁለት ለታላላቅ ሀገር እና ሕዝብ አስማምተው በአንድ ማስተዳደር የቻሉ አፍሪካ የምትኮራባቸው እነዚህ አባቶቻችን የማንነት ከፍታችንን ክብራችንም ናቸው። ድሯቸውን ጠንቅቆ የሚያውቀው የታሪክ ሰው ኤድዋርድ ጉቦን እነዚህን ጀግኖች፣ “ለአንድሺ ዓመታት ያህል ተረስተው አንቀላፍተዋል” ሲል ተፅፏል፣ ታዲያ እኛ ታሪካቸውን ወራሽ ለመሆን የነቃን፣ ፈለጋቸውን ተከትለን አዲስ ታሪክ የምንሰራ የኩሩ አባቶቻችን ልጆች ኩሩ ትውልድ መሆናችንን ታሪክ እንዲህ አስታወሰን። አበቃን።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም