“ኢትዮጵያ ያላት የውኃ ሀብት ፈተና ውስጥ ሲከታት ቆይቷል”

0
108

ሀገራቸውን በውትድርናው ዓለም ከ1957 እስከ 1983 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡ የኮሎኔልነት ማዕረግም አግኝተዋል፡፡ በውጪ ሀገር የመጀመሪያውን የስለላ ተልዕኮ ተቀብለውም በሚገባ ከውነዋል፡፡ ሀገራቸው አንድነቷ ተጠብቆ ግዛቷ ተከብሮ እንድትቆይ ዋጋ ከከፈሉ የቁርጥ  ቀን ልጆች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በማኅበረሰብ ግልጋሎት እና በአካባቢ ጥበቃም ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋልለ – “የጽናት ትሩፋት” የሚል በሕይዎት ታሪካቸው ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ ጽፈዋል፤ሌትናል ኮሎኔል አለሙ መብራት፡፡ ከሌትናል ኮሎኔል አለሙ መብራት ጋር የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ አድርገናል፡፡

መልካም ንባብ!

 

የት ተወለዱ? አስተዳደግዎስ ምን ይመስላል?

የተወለድኩት በ1942 ዓ.ም  በአሁኑ አጠራር በደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ  ደብር አባጃሌ ቀበሌ  ነው፡፡ የኢትዮጵያ አብዛኛው ማኅበረሰብ እድገቱ በገጠር እንደሆነው ሁሉ እኔም ከብት አግጄ፣ ጥጃ ጠብቄ፣ አርሜ፣ ጎልጉዬ እና አርሼ  ነው ያደኩት፡፡ አባቴ አርበኛም ገበሬም ነበሩ፡፡ ሀገር ጠላት በገጠማት ጊዜ ወታደር፣ በሰላም ጊዜ ደግሞ ገበሬ ነበሩ፡፡ ሰባት ወንድሞችም ነበሩኝ፤ እነሱም አርበኞች ነበሩ፡፡

 

አባቴ ብዙ የእርሻ መሬት ነበራቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ በመሬት ይገባኛል የፍርድ ቤት ክርክር ይኖራቸው ነበር፡፡  እናም እሳቸው ማንበብ እና መጻፍ ስለማይችሉ በዚያ ክርክር  ማመልከቻ የሚጽፍላቸው እና ባንዳንድ ነገር  የሚያግዛቸው የተማረ ሰው ይፈልጉ ነበር፤ ፊደል አለመቁጠራቸውም ይቆጫቸው ነበር፡፡

በዚህ የተነሳ በአካባቢያችን በሚገኝ የአብነት ትምህርት ቤት ፊደል እንድቆጥር አስገቡኝ፡፡ በስድስት ቀናት ውስጥ ፊደሎቹን መለየት ቻልኩ፡፡ ነገር ግን ከቤተሰብ ሥራ ታዝዤ የተወሰነ ቀን ስለቀረሁ የኔታ በብርቱ ቀጡኝ፡፡ ከዛች እንደ መራራ ከቆጠርኳት ቅጣት በኋላ ወደ አብነት ትምህርት ቤት መመለስ አልደፈርኩም፡፡

 

ቆይቶ የአባቴ ወዳጅ በነበረ እና እብናት ከተማ ውስጥ ይኖር በነበረ መንግሥቴ በተባለ ፖሊስ አማካኝነት ከዘመናዊ ትምህርት ጋር ተዋወኩ፡፡ ከፖሊሱ ቤት በሥራ እያገለገልኩ ትምህርቴን እማር ነበር፡፡ እስከ ሦስተኛ ክፍል ድረስ በዚህ መንገድ ተማርኩ፡፡ ከአራተኛ ክፍል በኋላ ከመንደራችን ወደ እብናት የእግር ጉዞ እያደረኩ መማር ቀጠልኩ፡፡ አብረውኝ ከሚጓዙ ልጆች ጋር ለሁለት ሰዓት ያክል በእግር ተጉዘን ነበር ትምህርት ቤት የምንደርሰው፤ ሆኖም የትምህርት ፍቅሩ ስለነበረን መንገዱን ከመጤፍ አንቆጥረውም ነበር፡፡

 

ከትምህርት ቤት መልስ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብቶችን ለግጦሽ ከተሰማሩበት ወደ በረታቸው መመለስ፣ ወደ ዱር ወርዶ እንጨት ለቅሞ ማምጣት፣ ማረም እና መጎልጎል በመሳሰሉ የግብርና ሥራዎች እንሰማራለን፣ ቤት ውስጥ እንላላካለን፤ ረፍት የሚባል ነገር አይታሰብም ነበር፡፡ ሥራ ልጅን ያሳድጋል፤ አካልን ያጠነክራል የሚል እምነት ነበር፡፡ ከሥራ ጋር የተዋወኩት በዚህ መልኩ በጠዋቱ ነው፡፡

በልጅነት የገጠር ልጅን የሚገጥሙ ችግሮችን ሁሉ ተቋቁሜ ትምህርቴን ቀጠልኩ፡፡ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል በአዲስ ዘመን ከተማ ተምሬያለሁ፡፡ በወቅቱ በአለባበሳቸው እና በምግባራቸው እንዲሁም በእውቀታቸው እንደ አርአያ የማያቸውን መምህሮቼን አግኝቻለሁ፤ አሁንም ድረስ አይረሱኝም፡፡ ቀጥሎም ከትምህርቴ እንድስተጓጎል እንዲሁም ቤተሰቤ ፈተና ውስጥ እንዲገባ ያደረገ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡

 

አጋጣሚው ምንድን ነው?

ከስምንተኛ ክፍል ወደ ዘጠነኛ ክፍል አልፌ ወደ ጎንደር  ከተማ በመሄድ ፋሲለደስ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ትንሽ እንደተማርኩ በደም ምለሳ ጣጣ ቤተሰቤም እኔም ፈተና ውስጥ ገባን፡፡ ታናሽ እህቴ ተናኜ መብራት አግብታ አባቴ ምላሹን ድል አድርጎ ደግሶ ዘመድ ተሰብስቦ እየበላ እየጠጣ አለፈ፡፡ ከሦስተኛው ቀን በኋላ ዳሱ ፈርሶ ሙሽሮች ወደ ቤት ገቡ፡፡ አባቴ ላይ ታች ሲል ስለዋለ አረፍ ለማለት አልጋው ላይ ጋደም ባለበት የተኩስ እሩምታ ተሰማ፡፡ ጥይቱ አባቴን አልፎ ሙሽራውን እና የሙሽራውን ወንድም መታቸው፡፡ ነገሮች ከደስታ ወደ ሀዘን በቅጽበት ተቀየሩ፡፡ አባቴ ሲከታተሉት የነበሩት እና ደም የተቃቡት ሰዎች እንደተበቀሉት አልተጠራጠረም፡፡

 

አገቡሾቻችን የአባቴ መሳሪያ ባርቆ ሙሽራውን እና ወንድሙን እንደገደለ አድርገው ተረዱት፤ ይህም ሌላ ጥላቻን እና ችግርን ይዞ መጣ፡፡ አባቴ ወደ ጫካ ሸፈተ፤ እናቴ እና ሌሎች በሰርግ ዝግጅት ላይ የነበሩ የቤተሰቤ አባላት ታሰሩ፡፡ ከታላቅ እህቴ ባል ጋር በመሆን የታሰሩትን ቤተሰቦቼን ለማስፈታት ብዙ ጥሬ ተሳካልኝ፡፡ ትምህርቴነ ለመቀጠል ግን ክስተቱ አላስቻለኝም፤ ለእኔም ለቤተሰቤም የህልውና ስጋት ነበረብን፡፡ በዚህ መሀል ሀገሬን ለማገልገል ወደ ውትድርናው ለመግባት ወሰንኩ፡፡

 

ወደ ውትድርናው የገቡበትን ሁኔታ ይንገሩን?

በአንድ ጉዳይ ጎንደር ከተማ አራዳ  ከሚባለው ገበያ ቆይቼ ወደምኖርበት ሰፈር በእግሬ እየተጓዝኩ ፒያሳ ከሚባለው የከተማዋ አደባባይ አንድ ትኩረቴን የሳበው ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ማስታወቂያው በእስራኤሎች በሰለጠኑ አሰልጣኞች ወታደራዊ ስልጠና ለመስጠት የወጣ ነው፡፡ በበነጋታው ተመዘገብኩ፤ በቀናት ውስጥ ከ500 በላይ ተመዝጋቢዎች ለፈተና ቀርበን 65 ዕጩዎች ብቻ አለፍን፤ እኔ አንደኛ ሆኜ ነበር ያለፍኩት፤ ሀኖም ያልጠበኩት ፈተና ገጠመኝ፡፡

 

የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ ዋና አዛኝ ብርጋዴር ጄነራል ስዩም ገሠሠ ሰልጣኝ ወታደሮችን ለመጎብኘት ድንገት መጡ፡፡ ከዚያም የእጩ ወታደሮቹን ሁኔታ መፈተሽ ጀመሩ፡፡ ከእኔ ላይ ሲደርሱ አስተዋሉኝ፤ ቆፍጠን ብለው የማሰልጠኛውን አዛዥ ሻምበል አያሌው ፍታለውን ጠርተው “ይሄ ታዳጊ ወጣት ቺኮዝ ጠመንጃ ታጥቆ ጠላትን ሊመታ ነው ወይስ ከረሜላ ሊበላ?!” በማለት ኮስተር ብለው ጠየቋቸው፡፡ ወዲያው “ቶሎ ይውጣ!” ብለው አዘዙ፡፡ ሻምበል አያሌው እንዲያስወጣኝ የታዘዘውን ወታደር እንዳያስወጣኝ በጥቅሻ ጠቆሙት፡፡ እኔም ጀነራሉ እስኪሄዱ ድረስ ገለል ብዬ ቆየሁ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ስልጠናውን ጀመርኩ፡፡

 

ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ሊመርቁን የመጡት ብርጋዴር ጀነራል ስዩም ገሠሠ ነበሩ፡፡ አንደኛ ተሸላሚ ሆኜ ከፊታቸው ስቀርብ ቢደነቁም ትዕዛዛቸው ባለመከበሩ ቅር መሰኘታቸው አልቀረም፡፡ ምንተፍረታቸውን “አያሌው ይሄን አላባረርከውም እንዴ?” ብለው ጠይቀዋል፡፡

ስልጠናውን ካጠናቀቅነው ውስጥ 15 ወታደሮች ተመርጠን የሬዲዮ መገናኛ ወይም ሞርስ ስልጠና ለሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ተከታትለናል፡፡ እዚያም የደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው ያጠናቀቅኩት፡፡ ወታደር በሕይዎት ዘመኑ አሸናፊ የሚያደርገውን ትምህርት ይማራል፤ ሲበላም ሆነ ሲጠጣ ከጸጉሩ እስከ ጥፍሩ ሥርዓት አለው፡፡ ውትድርና በማንኛውም ጉዳይ አሸናፊ ለመሆን በአካል እና በአዕምሮ ሰው የሚቀረጽበት ሙያ በመሆኑ በሕይዎቴ ብዙ አትርፌበታለሁ፡፡

ስልጠናውን እንደጨረስኩ ሁመራ ከተማ ነበር የተመደብኩት፤ ትንሽ እንደቆየሁ በተማርኩት ትምህርት መሠረት በጎረቤት ሀገር የነበረውን ሁኔታ ለመከታተል እና ለመንግሥት መረጃ ለመስጠት ተላኩ፡፡ ተልዕኮውን በብቃት ፈጸምኩ እና ወደ ሀገሬ ተመለስኩ፡፡ ወዲያው የፖሊስ ሠራዊት አዛዥ ጠረፍ ሊጎበኙ ሲመጡ የካምፓችን አዛዥ የሆኑት ሻምበል በሀገራችን ታሪክ ተሠርቶ የማይታወቅ ግዳጅ መፈጸሜን በመንገር ቢቻል ሹመት እንዲሰጠኝ አሊያ ከራሳቸው ማዕረግ ተቀንሶ እንዲሰጠኝ ጠየቁልኝ፡፡

 

አዘዛዡ ምን እንደምፈልግ ጠየቁኝ፤ ያቋረጥኩትን ትምህርቴን መቀጠል እንደምፈልግ ነገርኳቸው፡፡ ሁለት ዓመት  በጎንደር ከተማ የማታ ከተማርኩ በኋላ አብዮቱ ፈነዳ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የፖለቲካ ትምህርት ተምሬ ወደ ፖለቲካው ገባሁ፡፡

 

ከጥቂት ዓመታት በኋላ የዚያድ ባሬ ጦር ኢትዮጵያን ሲወር በታጠቅ ጦር ሰፈር ሠራዊት አሰልጥነው ከሚያበቁ መኮንኖች መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ ሶማሊያ 26 ክፍለ ጦር ሲኖራት ኢትዮጵያ አራት ክፍለ ጦር ብቻ ነው የነበራት፡፡ ሌላው ፈተና የነበረው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ አማጺ ቡድኖች እስከ አፍንጫቸው ታጥቀው ሰፊ ግዛቶችን በተለይ የኤርትራን ክፍል የያዙበት ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ 300 ሺህ ሠራዊት አሰልጥነን ለድል በቃን፡፡

ከድል በኋላ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ማለትም ኤርትራ ተዘዋወርኩ፡፡ ኤርትራ ውስጥ ከፍተኛ ኋላፊነት ነበረኝ፡፡ ሥራየን እየሠራሁ የማታ ትምህረቴን ቀጠልኩ፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍልን እንደጨረስኩ ለተጨማሪ የፖለቲካ ትምህርት ወደ ሶቪየት ሕብረት ተላኩ፡፡ በወቅቱ ወደ ዉጪ የሚላኩት ማስተርስ እና ዶክትሬት ዲግሪ የነበራቸው ናቸው፡፡ ተመልሼ በተለያዩ ኃላፊነቶች ለ11 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡

 

የኤርትራ አማጺ ቡድኖች ሲደራጁ እና እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በተለይ የንጉሡ መንግሥት እውቅና ነበረው? ምንስ አደረገ?

ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ለማራቅ እና ዓባይን እንዲሁም ሌሎችን ጸጋዎቿን እንዳትጠቀም ተጽዕኖዎች እና ትንኮሳዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ያላት የውኃ ሀብት ፈተና ውስት ሲከታት ቆይቷል፡፡ በተለይ በነዳጅ ላይ የተመሠረተው ኢኮኖሚያቸው ዘላቂ እንደማይሆን የተገነዘቡ  ሀገራት ከቅኝ ገዢዎች ጋር በመሆን ሴራ ሲያጠነጥኑ ኖረዋል፡፡

 

ጣሊያን ከዓድዋ ጦርነት በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ኤርትራን ይዛ ቆይታለች፡፡ በተለያዩ ጥረቶች ኤርትራ ከጣሊያን ነጻ ከወጣች በኋላ እንግሊዝ ለ10 ዓመታት በሞግዚትነት አስተዳድራለች፡፡ በኢትዮጵያዊያን የዲፕሎማሲ ጥረት እንግሊዝ ለቃ ከወጣች በኋላ ለነጻነት የታገሉ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ብለው ደማቸውን ያፈሰሱ አርበኞች በንጉሡ ተገፉ፡፡ ይባሱኑ “ኤርትራ አረባዊት ናት” እንዲሁም “እንግሊዝ ትግዛን” ብለው የታገሉ ወደ ስልጣን መጡ፡፡ በግብጽ የተቋቋመው “ራቢጣ አል እስላሚያ” የተሰኘው ቡድን የትጥቅ ትግል ጀመረ፡፡ ይሄን ቡድን ለማክሰም ሻዕቢያ በመንግሥት አማካኝነት ተመሠረተ፡፡ ነገር ግን በውጪ ኀይሎች ተጠልፎ ከቁጥጥር ውጪ ወጣ፡፡ ከዚያም ወያኔ ተፈለፈለ፡፡

ይቀጥላል

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here