ኢቶሻ ብሔራዊ ፓርክ

0
143

ኢቶሻ ብሔራዊ ፓርክ በናሚቢያ ሰሜናዊ ግዛት ነው የሚገኘው:: አጠቃላይ የፓርኩ ስፋት 22,270 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ተለክቷል:: ወደ ፓርኩ ለማምራት 420 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የናሚቢያ ዋና ከተማ ዊንድሆክን መነሻ ማድረግ ተመራጭ ነው:: ኢቶሻ  “ትልቅ ወይም ሰፊ ነጭ ቦታ” እንደማለት ነው::

በአፍሪካ የሚገኘው ሰፊ ረግረግ ስፍራ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ልምላሜን አጐናፅፎ በርካታ ቁጥር ያላቸው “ፍላሚንጐ” የተሰኙ አእዋፍን ይስባል፤ ያስተናግዳል::

ፓርኩን ልዩ የሚያደርገው በሁሉም ለጐብኚዎች አመቺ የሆኑ መስፈሪያ ቦታዎች፤ በጐርፍ የሚሞሉ የውኃ ጉድጓዶች አሏቸው:: በውኃ ጉድጓዶቹ አቅራቢያም ምስልን በካሜራ መቅረፅ የሚያስችሉ መሸሸጊያዎች ተዘጋጅተዋል:: በአብዛኛዎቹ የጐብኚዎች ማረፊያ (ሎጂዎች) ከፊት ለፊታቸው ምስል ማንሻ እና መመልከቻ በረንዳ አላቸው::

ፓርኩ 114 አጥቢ የዱር እንስሳት፣ 340 የአእዋፍ ዝርያዎች፣ 110 ተሳቢ እና 16 የውኃ ውስጥ እንስሳት ይገኛሉ:: 134 የእፅዋት ዝርያዎች መገኛነቱ ተለይቷል – በባለሙያዎች ቆጠራ:: የፓርኩ መልክዓምድራዊ ገፅታ በደረቅ ሳር፣ ቁጥቋጦ እና የግራፍ ደን የተሸፈነ ነው:: ከተዘረዘሩት ሰፊውን ክልል ማለትም አንድ ሶስተኛውን  ረግረጋማው ቀጣና ነው የሚሸፍነው::

በፓርኩ  ከሚገኙ የዱር እንስሳት ዝሆን፣ አውራሪስ፣ ሳላ፣ የሜዳ አህያ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ አቦሸማኔ፣ ጅብ፣ ቀጭኔ፣ የሜዳ ፍየል፣ ቀበሮ፣ ጥንቸል ፍልፈል፣ ሽኮኮ እንደሚገኙ ተረጋግጧል::

ቀጣናው የውኃ እጥረት ያለበት መሆኑን ተከትሎ ጎሽ፣ አዞ፣ ጉማሬ እንደማይገኙም ነው ለንባብ የበቃው::

በባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ኢቶሻን ለመጐብኘት የበጋ ወቅት ተመራጭ  ነው። ለዚህ ደግሞ የተቀመጠው አሳማኝ ምክንያት የዱር አራዊቱ በውኃ ጉድጓዶች ዙሪያ ሲሰባሰቡ ለእይታ ስለሚመች ነው::

ለዘገባችን ኢቶሻ ናሽናል ፓርክ፣ አፍሪካን በጀት ሳፈሪ፣ የሎው ዚብራ ሳፈሪ ድረ ገፆችን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ጥቅምት 11  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here