ኢንሱሊንን በጠብታ

0
135

የስኳር በሽታ ታማሚዎች በሽታውን በቀላሉ እንዲቆጣጠሩ እና ጤናቸውን እንዲጠብቁ  በመርፌ የሚሰጥ ኢንሱሊንን በአፍ በሚወሰድ ጠብታ መተካት መቻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ  አስነብቧል::

የስኳር በሽታ ህሙማን ቁጥራቸው መጨመሩን የጠቆሙት የብሪቲሽ ኮሎምቢያ የሳይንስ ተመራማሪዎች በምላስ ስር የሚሰጥ ጠብታዎችን ለህሙማን የስኳር መጠን መቆጣጠሪያነት ማግኝታቸውን አስታውቀዋል::

የሊላብ ተመራማሪዎች የሰሩት የኢንሱሊን ጠብታ ምላስ ስር ሲቀመጥ በተቀላጠፈ መልኩ ወደ ሰውነት ሟሙቶ የሚገባ ነው:: ይህም በመርፌ የሚወሰድ ኢንሱሊንን እንደሚተካ ነው ያብራሩት::

የተመራማሪዎቹ መሪ ዶ/ር ሊ እንደተናገሩት በምላስ ስር የሚሰጠው ጠብታ ከዓሳ ተረፈ ምርት ጋር ተጣምሮ በመሰራቱ ፈጥኖ ወደ ህዋሳት መዝለቅ ይችላል:: በእንክብል መልክ የሚዋጥ ተዘጋጅቶ ሲሞክር በሆድ ውስጥ ባክኖ እንደሚቀርም ነው የደረሱበት::

በመሆኑም የኢንሱሊን ጠብታው በራሱ ፈጥኖ ሟምቶ ወደ ህዋስ ስለማይገባ ለየት ባለ ወደ ህዋስ የሚዘልቅ ኢንሱሊን በጠብታ መልክ ተቀላቅሎ መሠራቱን አስረድተዋል- መሪ ተመራማሪው::

ቀደም ብሎ በተደረገ ሙከራ ያለ “ፔፕቲድ” በጠብታ የሚሰጠው ኢንሱሊን ፈጥኖ ወደ ህዋስ ሳይገባ በአፍ ጥጋት ወይም በምላስና በትናጋ ግድግዳ ተጣብቆ ይቀር ነበር:: ይህንን ችግር የተረዱት ተመራማሪዎች መፍትሄ አፈላልገው ማግኘታቸውን ከጥናት ቡድን አባላት ዶ/ር ጂያሚን ዉ አስታውቀዋል::

ያልተመጠነ ግሉኮስ አደገኛ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪዎቹ የስኳር ህሙማን የግሉኮስ መጠንን መከታተል፣ አንሶ ሲገኝም ኢንሱሊንን መውሰድ ግድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጤናማ ሰዎች ኢንሱሊንን ከሚመገቡት ምግብ በጣፊያ አማካይነት እንደሚያገኙት የጠቆሙት ተመሪማሪዎቹ የስኳር በሽታ ህሙማን ግን ተጨማሪ ማመጣጠኛ ከውጪ በመርፌ ወይም በጠብታ ማግኘት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት::

በመርፌ የሚሰጠው ኢንሱሊን ፈጥኖ ወደህዋስ የሚደርስ ቢሆንም በየቀኑ ለመርፌ ተጨማሪ ወጪ መጠየቁ እና ለረዥም ጊዜ መርፌ  መጠቀም የኩላሊት እና ነርቭ ችግር ሊያሰከትል መቻሉ የጐንዮሽ ጉዳቶች መሆናቸውን ነው በማደማደሚያነት ያሰመሩበት- ተመራማሪዎቹ::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here