ኢንስቲትዩቱ ዘጠኝ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን መልቀቁን አስታወቀ

0
77

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምርታማነትን እና ጥራትን የሚያሳድጉ፣ ድርቅን፣ ተባይን፣ በሽታን እና አረምን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች መልቀቁን አስታውቋል። አንድ የጤፍ፣ ሦስት የማሽላ፣ ሁለት የእንቁ ዳጉሳ፣ ሁለት የአተር እና አንድ የምስር ዝርያዎች መልቀቁን ነው ምርምር ኢንስቲትዩቱ የገለፀው።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ምርምር ሲደረግባቸው የቆዩ በሀገር አቀፍ ዘር አጽዳቂ ኮሚቴ የምርምር ደረጃዎችን ያለፉ ዘጠኝ የሰብል ዝርያዎች መለቀቃቸውን ነው የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ.ር) ለበኵር የተናገሩት። ስሪንቃ የግብርና ምርምር ሰባት እንዲሁም ሰቆጣ የዝናብ አጠር የምርምር ማዕከል ሁለት የሰብል ዝርያዎችን እንደለቀቁ ነው የጠቀሱት። እነዚህን ዘጠኝ ዝርያዎች በቀጣይ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የማላማድ እና የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት እንደሚከናወን አስረድተዋል። ዝርያዎቹ ከአማራ ክልል አልፎ ለሀገር የሚጠቅሙ እንደሆኑም አመላክተዋል።

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በበጀት ዓመቱ ለመሥራት ካቀደው 584 የምርምር ሥራዎች ውስጥ 83 በመቶ ማከናወኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የምርምር ሥራዎቹ ሰብል፣ እንስሳት፣ የዘር ብዜት፣ አፈር እና ውኃ አያያዝ፣ ደን እና የተለያዩ ምርምሮችን ያካተቱ ናቸው። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ የምርምር ሥራዎችን እና አዳዲስ ተክኖሎጂዎችን የማፍለቅ፣ የማባዛት እና የማስተዋወቅ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ምርምሮችን ያካሂዳል፣ የሚያወጣቸውን መስራች ዘሮችን ያሰራጫል፤ የአቅም ግንባታ ሥራም ያከናውናል።

ፈጥነው የሚደርሱ፣ የተሻለ ምርት የሚሰጡ እንዲሁም አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እየተሰራጩ መሆኑን ገልፀዋል። በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በተለይም በአንዳሳ እና በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ሥራዎችን ለማከናወን አስቸጋሪ እንደነበር አንስተዋል።

በምርምር ኢንስቲትዩቱ ከተለቀቁት ዝርያዎች መካከል ሦስት የማሽላ ዝርያዎች ይገኙበታል። “ስሪንቃ አንድ” የተባለው የማሽላ ዝርያ በሄክታር 52 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ሲሆን ከበፊቱ ማወዳደሪያ ዝርያ 30 በመቶ የምርት ብልጫ አለው።  “ወለዲ” የተባለው የማሽላ ዝርያ ደግሞ በሄክታር 47 ኩንታል የሚሰጥ ሲሆን ከበፊቱ የማወዳደሪያ ዝርያ  29 በመቶ ብልጫ አለው።  “ዳግም” የተባለው የማሽላ ዝርያ ሌላዉ ሲሆን በሄክታር 44 ኩንታል እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ሌላው “እንቁ ዳጉሳ” በንጥረ ነገር ይዘቱ የተሻለ፣ ድርቅን መቋቋም የሚችል እና ፈጥኖ በመድረስ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ዓይነተኛ ሰብል ነው። ምርታማነታቸው አንደኛው የተሻሻለው ዝርያ በሄክታር 17 ነጥብ ሁለት ኩንታል፤ ሁለተኛው የተሻሻለው ዝርያ ደግሞ 20 ነጥብ ስምንት ኩንታል እንደሚሰጡ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

ሌላኛው በምርምር የተለቀቀው የተሻለ ምርት መስጠት የሚችል “ዛቲ” የተባለ የጤፍ ዝርያ ነው፡፡ በሄክታር 25 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እና ከተሻሻለው ማወዳደሪያ ዝርያ ደግሞ 20 በመቶ የምርት ብልጫ አለው ተብሏል። በስሪንቃ፣ ጃሪ፣ ጨፋ፣ ዓለም ከተማ እና ሰቆጣ አካባቢዎች መመረት የሚችል መሆኑም ተረጋግጧል፡፡

ቀድሞ የሚደርስ እና ድርቅን የሚቋቋም፣ የተሻለ ምርት መስጠት የሚችሉ “ሰርክ” እና “ለኪ” የተባሉ የአተር ዝርያዎችም ተለቀዋል፡፡ በሄክታር  ከ28 እስከ 32 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው። ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ በ27 በመቶ የምርት ብልጫ አለው። በወረኢሉ፣ ጃማ፣ መቄት፣ አዴት እና ተመሳሳይ ቦታዎች መመረት የሚችል መሆኑም ተረጋግጧል።  “የምስራች” የተባለው የምስር ዝርያ ደግሞ በምርምር የተለቀቀ ሲሆን በሄክታር 19 ኩንታል ምርት የሚሰጥ እና ከአካባቢው ማወዳደሪያ ዝርያ 57 በመቶ የምርት ጭማሪ እንዳለው አመላክተዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here