ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው:: ሀገሪቱ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እንድትሠራ ያደረጋት ከአጠቃላይ የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ገቢ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ መመንጨቱ፣ ከ80 በመቶ በላይ የኤክስፖርት ገቢ የሚገኝበት መሆኑ እና 85 በመቶ የሥራ ዕድልን መሸፈኑ እንደሆነ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያሳያል::
ሀገሪቱ ያላት ሰፊ የእርሻ መሬት እና ምቹ የአየር ሁኔታ አስተማማኝ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን እንዳስቻላትም መረጃው ይጠቁማል:: ይህንን አስተማማኝነት አስቀጥሎ ለመጓዝም በተለያዩ ክልሎች የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትርያል ፓርክ እየተገነባ ይገኛል። ከቢሮ ክራሲ እና ከኅይል አቅርቦት ጋር የተገናኙ ችግሮች የኢንቨስትመንት ዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ ሲነሳ መቆየቱም የአደባባይ ሀቅ ነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስተዋሉ ያሉ የሰላም መደፍረሶች ደግሞ ኢንቨስትመንቱን ውጤታማ አድርጎ ለመጓዝ የሚደረገውን ጥረት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዳያደርገው ተሰግቷል:: አሁናዊ ምልክቶች የሚያረጋግጡትም ይህንኑ ነው::
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨትመንት መዳከሙን ነገሩ ብሎ ቪኦኤ በፈረንጆቹ ግንቦት 17 ቀን 2023 ዘግቧል:: ለኢንቨስትመንቱ ድክመት እና ውጤት ማነስ በሀገሪቱ ያጋጠመው አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና የሠራተኛ እጥረት ዋና ምክንያት ሆኖ ተመላክቷል።
የዘመኑ ትልቁ ደም አፋሳሽ ጦርነት ኢንቨስትመንት ተቋማትን ለከፍተኛ ጉዳት ዳርጓል:: ይህም የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ከመገደብ ጀምሮ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው መጠን አምርተው የውጭ ምንዛሪ እንዳያስገኙ፣ ገበያ እንዳያረጋጉ፣ በሙሉ አቅማቸው የሥራ ዕድል እንዳይፈጥሩ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው:: ይህ ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ የተቀዛቀዘውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት ጉዳት የደረሰባቸውን በመልሶ ግንባታ ወደ ቀደመ ሥራቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎች ተሠርተዋል:: በዚህም የተሻለ የኢንቨስትመንት ፍሰት ታይቷል::
ጦርነቱ መልኩን ቀይሮ እንደ አዲስ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መከሰቱ ግን ሌላ ተግዳሮት ሆኖ ብቅ ብሏል:: በተለይ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተከሰተው በትጥቅ የታገዘ ግጭት ክልሉን ለከፋ ጉዳት ዳርጎታል:: የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በክልሉ የተከሰተው ግጭት 15 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ጉዳት እንዳደረሰ መግለጹ ለዚህ አብነት ነው::
ግጭቱ በተለይ የኢንቨስትመንት ዘርፉ በሚፈለገው መጠን እንዳይጓዝ አድርጓል:: የሰላም እጦቱ በ605 ሄክታር መሬት ላይ ተሰማርተው የነበሩ 20 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለጉዳት እንዲዳረጉ ማድረጉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት በጽሑፍ የላከልን መረጃ ይጠቁማል:: በእነዚህ ፕሮጀክቶች የደረሰው አጠቃላይ የጉዳት መጠንም 1ቢሊዮን 516 ሚሊዮን 825 ሺህ 340 ብር ነው::
በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት ፕሮጀክቶቹ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሲያበረክቷቸው የነበሩ የመንገድ፣ የመብራት እና የቁሳቁስ ድጋፎች እንዲቋረጡ ማድረጉን ቢሮዉ ጠቁሟል::
የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መገደቡ አምራች አንዱስትሪዎች ጥሬ ግብዓት በሚፈለገው መጠን እንዳያገኙ አድርጓቸው ቆይቷል:: ለዚህ አንድ አብነት እናንሳ፤ በ2015 ዓ.ም ግማሽ ዓመት 102 ሺህ 823 ነጥብ 68 ቶን የሀገር ውስጥ ግብዓት ሲቀርብላቸው በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት መቅረብ ከነበረበት 27 ሺህ 568 ቶን ግብዓት ውስጥ የቀረበላቸው 5ሺህ 91 ነጥብ 29 ቶን ብቻ መሆኑን ቢሮው አስታውቋል::
የሰላም መናጋቱ እንደ አዲስ እየተፈጠሩ ያሉ የሥራ ዕድሎችን ከመገደብ ባሻገር ነባሮችም እንዲፈናቀሉ እያደረገ መሆኑንም ነው ቢሮዉ ያስታወቀው፤ ፕሮጀክቶች ላይ በደረሰው ጉዳትም 2ሺህ 239 ሠራተኞች ከሥራ ውጪ መሆናቸውን በአስረጂነት በመጠቆም ነው::
ግጭቱ ወደ ክልሉ የሚመጡ የውጪ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲቀንስ ስለማድረጉም ቢሮው ያደረሰን መረጃ ይጠቁማል:: ለአብነት በ2015 ዓ.ም 483 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 4 ሺህ 724 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል:: በ2016 ዓ.ም ስምንት ወራት 251 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 2 ሺህ 520 ባለሐብቶች ፈቃድ መሰጠቱን ቢሮዉ አስታውቋል::
በክልሉ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የሰሜን ሸዋ ዞን ነው:: የሰሜን ሸዋ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ደምሰው መንበሩ ለበኩር በስልክ እንዳስታወቁት ዞኑ ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል:: ይህም እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::
በዞኑ 130 ቢሊዮን 27 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 315 የአምራች ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ:: 1ሺህ 172 ሄክታር መሬት መተላለፉን ያስታወቁት ኃላፊዉ፣ ፕሮጀክቶቹ ወደተሟላ የማምረት ሥራ ሲገቡ 303 ሺህ 129 ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደርጋሉ:: በአሁኑ ወቅትም ለ25 ሺህ 703 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል::
በአገልግሎት ዘርፉም 797 ፕሮጀክቶች ይገኛሉ:: 38 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ነዋይ ማፍሰሳቸውን ገልጸዋል:: እነዚህ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ስምንት ሺህ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ኃላፊዉ፣ ወደ ሙሉ ሥራ ሲሸጋገሩ ለ43 ሺህ 900 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ::
በግብርናው ዘርፍም 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተመዘገበባቸው 263 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን ኃላፊዉ አስታውቀዋል:: ከ51 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያላቸው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የፈጠሩት ከ5 ሺህ 932 የበለጠ አለመሆኑንም ጠቁመዋል::
በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ በአሁኑ ወቅት 812 ፕሮጀክቶች በቅድመ ግንባታ፣ በግንባታ እና ግንባታ አጠናቀው በሥራ ላይ እንደሚገኙ አቶ ደምሰው አረጋግጠዋል::
የሰሜኑ ጦርነት እና አሁንም በክልሉ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ ጫና መፍጠሩን ኃላፊዉ ገልጸዋል:: የሰሜኑ ጦርነት በተለይ በኢፋት ቀጠና በሚገኙ የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱን እና ፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል:: በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው የሰላም መታጣት በ2016 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ኃላፊዉ አስታውቀዋል:: ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር የተሻለ የኢንቨስትመንት ፍሰት መኖሩ እና በዚህ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት 142 ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ መስጠት መቻሉን ጠቁመዋል::
የደሴ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ በከተማዋ ካሉ ባለሐብቶች እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል:: የመምሪያው ኃላፊ አቶ አለባቸው ሰኢድ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ 45 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 160 ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል:: እነዚህ ባለሐብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ ከ40 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል::
በዓመቱ የተሰጠው ፈቃድ ከዕቅድ በላይ መሆኑን ኃላፊዉ ጠቁመዋል:: ከተማዋ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነባት መሆኗ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥራው እየተሻሻለ መምጣቱ፣ በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የደሴ ከተማ የኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል እንድትሆን ያስቻሉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል::
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ የኢንቨስትመንት ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እና በማዳን እንዲሁም ገበያን በማረጋጋት ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል:: ለአብነት ባለፈው በጀት ዓመት በተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ63 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውሰዋል::
ክልሉ በአሁኑ ወቅት በጸጥታ ችግር ውስጥም ሆኖ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማምረት 33 ሺህ 403 ቶን ምርት ማምረት መቻሉን ገልጸዋል:: ይህም 195 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያዳነ መሆኑን ጠቁመዋል::
30 አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ዘጠኝ የአበባ ልማት ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ 78 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉንም ጠቁመዋል:: ክልሉ አሁንም ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ በዘርፉ ከ18 ሺህ 840 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል::
ሀገራት ከሥራ ዕድል ፈጠራ እስከ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መገኘት ምሰሶ የሆነውን ኢንቨስትመንት ማነቃቃት ቀዳሚ ጉዳያቸው ሊሆን ይገባል:: ታዲያ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሐብቶችን መሳብ ደግሞ ቀዳሚው ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ ሊንክ ዲን ድረ ገጽ (linkedin.com) አስነብቧል::
የተረጋጋ እና ሊገመት የሚችል የንግድ አካባቢን መፍጠር ለጠንካራ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መሠረት መሆኑን ጽሑፉ ጠቁሟል:: ሀገራት በባለሃብቶች ላይ እምነት ለመፍጠር የፖለቲካ መረጋጋት እውን ሊያደርጉ ይገባል:: ጠንካራ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመፍጠር ደግሞ ከሌሎች ሀገራት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ጋር ያለን ግንኙነት (ሽርክና) ማጠናከር ይገባል:: ለዚህ ደግሞ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል:: ልዩነቶችን በጠብ መንጃ ለመፍታት ከመሞከር ቁጭ ብሎ መነጋገር ማስቀደም ተገቢ ነው:: ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኅይላት ለውይይት አወንታዊ ምላሽ ሊያሳዩ ይገባል::
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም