ኤግዚቢት የእንግሊዝኛ ቃል ሲሆን በተለምዶ በሕግ አካል በጥርጣሬ ተይዞ ለሚገኝ ቁስ ወይም ንብረት ለመግለጽ እንጠቀምበታለን። በዛሬው መጣጥፋችን ታዲያ ኤግዚቢትን በተመለከተ ከሙያው ባለቤት ጋር ቆይታ አድርገናል።
ሙሉጌታ አሻግሬ ይባላሉ። በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የምጣኔ ሀብት ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። ዳይሬክተሩ የኤግዚቢትን ምንነት ብያኔ በመስጠት ነበር የሐሳብ ልውውጣችንን የጀመሩልን። እንደ አቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ ኤክዚቢት ፍርድ ቤት ወይም መርማሪ ፊት ቀርቦ በማስረጃነት ሊያገለግል የሚችል ሰነድ ወይም ግዙፋዊ ነገር ነው የሚል ትርጉም አለው። ይህም ሊታይ እና ሊቀርብ የሚችል ሲሆን ተንቀሳቃሽ የሆነ ዕቃ መሆን አለበት የሚለው ደግሞ አንደኛው መገለጫው ነው።
ከማብራሪያው እንደምንገነዘበው ኤግዚቢት ከማይንቀሳቀስ ንብረት የተለየ ወይም እራሱ ተንቀሳቃሽ የሆነ ነገር መሆን አለበት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ነው።
ሌላኛው መገለጫው ደግሞ በማስረጃነት ያገለግላል የሚለው ነው። ይህ ሲባል የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ሊያስረዳ የሚችል (ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ) በማስረጃነት ሊያገለግል የሚችል መሆን አለበት ማለት ነው።
ግዙፋዊ ነገር መሆን አለበት የሚለው ደግሞ ሦስተኛ መገለጫው ነው። ይህም ሲባል ደግሞ በዓይን ሊታይ እና ሊዳሰስ የሚችል መሆን አለበት፤ እንዲሁም በሌሎች አጋዥ መሣሪያዎች ግዙፋዊ ነገርነቱን ሊረጋገጥ የሚችል መሆን አለበት ማለትም ነው።
አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ ከላይ ያነሷቸውን ነጥቦች መሠረት በማድረግ ኤግዚቢት በዋናነት ሦስት ዋና ነገሮችን የያዘ፣ ሊንቀሳቀስ የሚችል ተንቀሳቃሽ የሆነ፣ በማስረጃነት ሊያገለግል የሚችል እና በስሜት ሕዋሳት እና በአጋዥ መሣሪያዎች ሊታይ እና ሊዳሰስ የሚችል ነው ሲሉ ነው የኤግዚቢትን ምንነት ያብራሩት።
አቶ ሙሉጌታ ኤግዚቢት ከሌሎች ማስረጃዎች የሚለይባቸውን መገለጫዎች እንደሚከተለው ያብራሩታል። ኤግዚቢት መርማሪው ወይም ፍርድ ሊሰጥ የሚችለው አካል ከሌሎች ማስረጃዎች የተሻለ በአይኑ የሚያየው፣ የሚዳሰሰው፣ በእውነትም ወንጀል ተፈጽሞበታል የተባለው ነገር ተረጋግጧል ብሎ ሊያሳይ የሚችል ነው። ይህም ወንጀሉ ስለመፈጸሙ የበለጠ ታማኝ እና ተመራጭ ያደርገዋል። ይህም ለዳኛውም ሆነ ለሚመለከተው አካል አሳማኝ ማስረጃዎች ስለሆኑ ከሌሎች ማስረጃዎች ተመራጭ ያደርጋቸዋል።
ይህም ሲባል ኤግዚቪት በወንጀል ምርመራ ወይም ክስ ሂደት አንድን ፍሬ ነገር ለማረጋገጥ ማስረጃ ተደርጎ የሚቀርብ ተጨባጭነት ያለው ንብረት ወይም ቁስ ነው፡፤ አንድ ቁስ ኤግዚቪት ሊባል የሚችለው ተፈጸመ ከተባለው የወንጀል ድርጊት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አሳማኝ ግንኙነት ያለው ሲሆን ነው፡፡
ኤግዚቪት በብዙዎች ዘንድ በፖሊስ ብቻ እንደሚቀመጥ እሳቤ አለ። ነገር ግን የሚቀመጠው እንደሁኔታው መሆኑን ነው አቶ ሙሉጌታ የገለጹልን፡፡
የኤግዚቢትን አያያዝ እና በማን ይያዛል? የሚለውንም እንደሚከተለው ነው ያብራሩልን። ኤግዚቢት ከተያዘ በኋላ ወንጀል ከተፈጸመበት አካባቢ ወይም ወንጀሉ ተፈጽሟል ተብሎ ሲታሰብ ኤግዚቢቶችን ሊይዝ፣ ሊያስቀምጥ እና ሊጠቀም የሚችል አካል መኖር አለበት። የኤግዚቢት ሂደቱም አንደኛው መያዝ ነው። ሁለተኛው መጠቀም፣ ሦስተኛው ማስወገድ፣ አራተኛው መወረስ ሊሆን ይችላል።
ኤግዚቢት ተሽከርካሪ፣ ቴሌቪዥን፣ ቴፕ፣ ሬድዮ፣ የጦር መሣሪያዎች፣ ምግብና መድኃኒት፣ እንዲሁም ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ። የሚይዛቸውም እንደ አይነታቸው ሊለያይ ይችላል። ለአብነትም ከምግብና መድኃኒት ጋር ተያይዞ ያሉትን ነገሮች ጤና እና ጤና ተቆጣጣሪ አካላት ሊይዙት ይችላሉ። ከዚያ በኋላ መወገድ ያለበት ይወገዳል፣አስተዳደራዊ ርምጃም ይወሰዳል። ጊዜው ያላለፈ ከሆነ ደግሞ ልንጠቀመው እንችላለን።
ከቁም እንስሳት ጋር ተያይዞ በተለይ ሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ዝውውር ሲኖር የቁም እንስሳት ተቆጣጣሪ አካላት አሉ። ከንግድ ቢሮ ጀምሮ የቁም እንስሳትን የሚከታተሉ አካላት ሲይዟቸው፤ መያዝ ካለባቸው ወጪያቸውን በሚሸፈንበት ወይም እንስሳት ሊቆዩ በሚችሉበት አግባብ እንዲቆዩ ይደረጋል፤ ከዛ ውጪ ደግሞ ተሽጠው በሞዴል 85 ሊቀመጡ የሚችሉበት የሕግ አግባብ አለ።
ከጦር መሣሪያ እና ከሌሎች ነገሮች ጋር በተለይ ከጉምሩክ ጋር ተያይዞ ያሉ ነገሮች ደግሞ የጉምሩክ አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት የጉምሩክ ኮሚሽን በአስተዳደራዊ ውሳኔ የሚወርስበት ወይም መጋዘን የሚያስቀምጥበት ሁኔታ አለ።
ሌላው ደግሞ ፖሊስ ኮሚሽን ነው። በዋናነት በተለይ ወንጀል እየተፈጸመባቸውን ኤግዚቢቶችን ፖሊስ ይይዛል። ፖሊስ ሲይዝ ሊያዙ የሚችሉ ኤግዚቢቶች ናቸው ወይ ብሎ መጀመሪያ ይለያል። ምክንያቱም አንዳንዶቹ በቆዩ ቁጥር የመጠቀምያ ጊዜ ሊያልፍባቸው የሚችሉ፣ በጤንነት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ፣ ወይም ሊፈነዱ የሚችሉ፣ የጤና ላይ ችግር የሚፈጥሩ ከሆኑ መወገድ ካለበት የሚመለከተውን የግብረ-ኃይል አደረጃጀት ይዞ በዛ ማስወገድ አለበት። መቆየት የሚችል ከሆነ ያቆያል፤ መሸጥ ካለባቸውም በጨረታ ተሽጠው ገንዘቡ በሞዴል 85 እንዲቀመጥ ይደረጋል።
ፍርድ ቤት ደግሞ ሌላው ተቋም ሲሆን የተያዘ ኤግዚቢት ላይ ክስ እንደተመሰረተ በኤግዚቢቱ ላይ ፍርድ ቤት መወገድ ወይም መቀመጥ አለበት የሚለውን ትዕዛዝ ይሰጣል። ከክርክር በኋላ ደግሞ ኤግዚቢቱ ሊወገድ ወይም ሊሸጥ ይገባል፣ አልያም ለግል ተበዳይ ሊመለስ ይገባል የሚሉትን ለይቶ ውሳኔ ይሰጣል።
በሌላ በኩል ፖሊስ ጣቢያ ላይ የሚያዙ ኤግዚቢቶች ጉዳዩ ተጣርቶ በዋስ ከተለቀቀ ወይም ነጻ ከተሰናበተ በኋላ ንብረቱንም የማይጠይቅ እና የግለሰቦች ንብረት አላስፈላጊ ብልሽት ሲጋለጡ ይስተዋላል። ይህን መነሻ በማድረግ ንብረቱን የማስመለስ መብትን በተመለከተ ጥያቄ አንስተንላቸዋል። አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ እንዳስገነዘቡት በተለይ ወንጀል ከተፈጸመበት ቦታ ላይ የሚያዙ ኤግዚቢቶች ላይ ተከሳሹም የሚጠፋበት፣ ባለቤትም የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን በተመለከተም እስከ አምስት ዓመት ይጠበቅና ከአምስት ዓመት በኋላ ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ የወንጀል ሕጉ አስቀምጧል።
በተመሳሳይ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎች (ስኳር፣ ዘይት፣ ዱቄት እና ሌሎች ነገሮች) በወቅታዊ ዋጋ ተሽጠው ገንዘቡ በሞዴል 85 እንዲቀመጥ ነው የሚደረገው። ፖሊስ ጣቢያ ላይ ሊቀመጡ የሚገባቸው ግን ወንጀል የተፈጸመባቸው፣ ስለታማ ነገሮች ወይም ስለታም ያልሆኑ በሰው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ጉዳዮች መሆን አለባቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤግዚቢትን በተመለከተ የውሳኔ መዘግየት ይስተዋላል። ኤግዚቢት በራሱ ደግሞ ማስረጃ ነው። ለምን? ስንል ለአቶ ሙሉጌታ አሻግሬ ሙያዊ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል።
ኤግዚቢቶች ብቻቸውን ገላጭ ማስረጃዎች አይሆኑም የሚሉት አቶ ሙሉጌታ ኤግዚቢቱን ሊያስረዳ የሚችል ሌላ ማስረጃ ያስፈልጋል ይላሉ። በኤግዚቢቱ እና ኤግዚቢቱን መሰረት አድርገው የሚሰጡ የሙያ ማስረጃዎች በቂ ከሆኑ በዛ ውሳኔ መሰጠት ይቻላል። ነገር ግን ከኤግዚቢት ማስረጃው በተጨማሪ የሰው ማስረጃዎች፣ ምስክሮች ማስረዳት ካለባቸው ው ምስክሮችን መጠበቅ የሚያስገድድበት ሁኔታ አለ። ነገር ግን በኤግዚቢቱ እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን መሰረት ብቻ ውሳኔ መሰጠት የሚያስችል ከሆነ ምስክሮች ሳይሰሙም ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል ነው ያስገነዘቡት።
ኤግዚቢትን በተመለከተ የሕግ ክፍተት መኖሩን አቶ ሙሉጌታ ያነሳሉ። ፖሊስ ጣቢያ ላይ ያለው የኤግዚቢት አስተዳደርም ክፍተት ያለበት ነው። ይህም ኤግዚቢቶች እንደተያዙ ማንነታቸው ሳይለወጥ፣ ሙሉ ሆነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ኤግዚቢቶች ከገቡ በኋላ ባህሪያቸው ተለውጠው፣ ተቀድተው፣ ቁጥራቸው እና መጠናቸው ቀንሶ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ኤግዚቢት በተመለከተ ደረሰኝ ሊሰጥ ይገባል። ፖሊስም እንደዚህ አይነት ኤግዚቢት ይዣለሁ የሚል ማስረጃ መስጠት ይጠበቅበታል።
ነገር ግን በብዛት ይህ ሲሆን አይስተዋልም። በዚህም ምክንያት የመጨረሻ ውሳኜ ከተገኘ በኋላ ተጠርጣሪው ነጻ እንኳን ቢወጣ ንብረቱን ላያገኝ ይችላል።
ይህን ችግር ለመፍታት ታዲያ “በትኩረት እየተሠራ ይገኛል” ነው ያሉት። ለዚህ ማሳያም ፍትሕ ቢሮ እያዘጋጀው የሚገኘውን (በቅርብ የሚተገበር) አሠራር እንዳለ ነው አቶ ሙሉጌታ ያነሱት።
የሕግ አንቀጽ
ፍርድ ቤት ኤግዚቢት በማስረጃነት ተጠቅሶ ከቀረበለት ኤግዚቢቱ ለወንጀል ተግባር ሊያገለግል የሚችል ወይም ያገለገለ ወይም የወንጀል ተግባር ፍሬ ከሆነ እና የሕዝብን ሰላም፣ ጤና እና መልካም ጠባይን የሚጎዳ ሲሆን እንዲወረስ የመወሰን ስልጣን አለው፡፡
በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 100(1) መሠረት ወንጀል ለመፈፀም ማነሳሻ፣ ለተፈፀመ ወንጀል ዋጋ የተሰጠ ወይም ሊሰጥ የታቀደ ጥቅም ሁሉ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡
በወንጀል ሕግ አንቀፅ 98(2) ላይ እንደተመለከተው ደግሞ ተከሳሹ ጥፋተኛ ከተባለ ወንጀለኛው በወንጀል ተግባሩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያገኘውን ንብረት ሁሉ እንዲወረስ ሊወሰን ይችላል፡፡
(ጌታቸው ስንታየሁ)
በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


