እመ ብዙኀን

0
12

አዲስ አበባ ከተማ በእቴጌ ጣይቱ በ1879 ዓ.ም የአሁን መጠሪያዋን እንዳገኘች የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት። የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንዲሁም የብዙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፎችና ሌሎችም የዓለም የዲፕሎማቲክ ልዑካን መሰብሰቢያ ከተማ ሆናለች።

በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ፣ ስነ ጽሑፍ፣ መዝናኛ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ  እና ሌሎች ዘርፎች ውስጥ ጉልህ አሻራ ያስቀመጡ አንጋፋ ሰዎችን ተቀብላ ለወግ ማእረግ ያበቃች ከተማ ናት።  አዲስ አበባ እንደ ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ናት። ኢትዮጵያን የሚመስል መልክ አላት። ብዙዎች ባዶ እጃቸውን ገብተው ሀብት ፈጥረዋል። ልጆች ወልደው አሳድገዋል።

ደግሞም ልጆቼ ብላ ተቀብላ እንዳሳደገቻቸው በተሰማሩበት የስራ መስክ ፍሬያማ ሆነው ውለታ የከፈሏት ድንቅ ልጆችም አሏት። ስሟን፣ መልኳን፣ ታሪኳን፣ ዘመኗን፣ ኪነ ጥበቧን እና ሁለንተናዋን የቀየሩላት ልጆች አሉ።

ትውልድ እየተቀባበለ ዛሬ ላይ ያደረሳት፣ ከደሳሳ ሳር ጎጆ ወደ አስደናቂ ሕንጻዎች እና ጎዳናዎች የለወጣት፣ በየዘመኑ ውብ የምትሆን ማራኪ ከተማ ሆናለች:: ልጆቿ እየበዙ፣ ሰውነት እየጨመረ ነው። የትናንቱን መልኳን እየለወጠች እንደ ጊዜው ዘመናይነትን እየተቀበለች ከቴክኖሎጂ ጋር እየተጓዘች ነው።

ጸጋዬ ገብረ መድህንን የመሰለ ደራሲ፣ አፈወርቅ ተክሌን የመሰለ ሰዓሊ፣ ስብሐት ገብረእግዜአብሔርን የመሰለ ጸሐፊ፣ ጥላሁን ገሰሰን የመሰለ ዘፋኝ፣ ብዙነሽ በቀለን የመሰለች አቀንቃኝ… መዘርዘር ራሱ ያደክማል። አዲስ አበባ ሁሉን ተቀብላ በፍቅር ያቀፈች፣ ያሳደገች፣ በክብር የቀበረች መዲና ናት።

በዬ ዘርፉ ስማቸውን ብንጠቅስ አዲስ አበባ በእናትነት ተቀብላ ሕይወቱን ያልቀየረችው ማን አለ?

ይህን ውለታ ለማስታወስ ሲሉ ብዙዎች ድምጻዊያን አንጎራጉረውላታል። በአለማየሁ እሸቴ፣ ዙሪያሽ አብዩ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ሀይማኖት ግርማ፣ ታምራት ደስታ፣ ሒሩት በቀለ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ጆኒ ራጋ፣ ጌታቸው ካሳ፣ መስፍን እርስቱ፣ ግሩም ታምራት፣ ፍቅር አዲስ ነቅዓጥበብ፣ ብርሀኑ ተዘራ፣ አብዱ ኪያር፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አለም ከበደ፣ እየሩሳሌም አስፋው፣ ፍጹም ቲ እና በሌሎችም ተዚሞላታል።

ጥቂት ዘፈኖችን በጥቂት ዕይታ እንመለከታለን።

የማህሙድ አህመድ የ1986 አልበም ውስጥ የተካተተው አዲስ አበባን የሚያነሳሳው ዘፈን ከምስረታዋ ጀምሮ ታሪኳን እና አቃፊነቷን የሚገልጽ ነው።

ለንጋት ጮራይቱ

የታየሽ ለጣይቱ

አዲስ አበባይቱ

እቴጌ ጣይቱ አዲስ አበባን ስም በመስጠት እና ከእንጦጦ ወደ ግርጌ በመውረድ የመረጡ ንግሥት ናቸው። አዲስ አበባን ብዙ ሰዎች በብዙ ቅርጽ ሊገልጿት ሞክረዋል። ጎድጓዳ ሳህን ዓይነት ቅርጽ አላት። ማእከሏ ስርጉድ ነው። ዙሪያዋን ደን እና ዛፍ ከተራራ ጋር ያጀባት ናት። በርግጥ አሁን አዲስ አበባ እነዚያን የከበቧትን ተራራዎች አልፋ እየሰፋች ነው። ማህሙድ በዘፈኑ

“ክው ባለው በጋ ተለይተሽ ያበብሽ

በነደደው ፀሐይ ጤዛ የከበበሽ”

የሚላትም ይህንን በደን ዙሪያዋን የመከለል ድንቅ ውበት ነው። አሁን ላይ እንዳለባት የሕዝብ ብዛት እና ግርግር ዙሪያውን እነዚያ የጽድ እና ባህር ዛፍ ደኖች ባይኖሩ ኖሮ ምናልባትም አዲስ አበባ በጣም ሞቃት ከተማ፣ ትንፋሽ የሚያጥራት ገደል ልትሆን ትችል ነበር። ግን አዱ ገነት ተብላ በገነት አምሳል የምትጠራ ውብ ያድረጓት ልጆችን ወልዳለች::

የአዲስ አበባ ባህሪ ማቀፍ ነው። እንኳንስ ከኢትዮጵያ ይቅርና የዓለም ሕዝቦችንም ተቀብላ የምታኖር ዓይነ ሰፊ፣ ረድኤት ያላት እናትን ነው የምትመስለው። ከየት ነህ፣ ወዴት ነህ፣ የማን ነህ፣ ለምን መጣህ? የሚል ተፈጥሮ የላትም። የሁሉም መኖሪያ ናት።

የሸዋው የወሎው የሚገናኝባት

ከትግራይ ተሳፍረው መተው የሚያርፉባት

ከጎንደር ከጎጃም ጎራ የሚሉባት

ከአርሲ ከአርባ ምንጭ ሁሌ ሚመጡባት

ከበስተሰሜን ጭነው ቢመጡ

ከበስተምስራቅ ጭነው ቢመጡ

ከየዳርቻው ጭነው ቢመጡ

ማነው ባንቺስ ላይ ጸጉረ ልውጡ? ብሏል ማህሙድ:: ዛሬ ላይም ይሁን የማህሙድ የሙዚቃ የወጣበት ዘመን አዲስ አበባ የሁሉም የሰው ልጅ መሰብሰቢያ፣ የኢትዮጵያዊያን አብሮነት ደሴት ናት። መኖር የሚፈልግ ሁሉ የሚገባባት፣ ሰርቶ፣ ሀብት አፍርቶ የሚኖርባት የእድል እና ሕይወት ከተማ ናት። የሁሉ ማረፊያ፣ የሁሉ መዳረሻ፣ የአፍሪካ ሕብረት መናገሻዋ አዲስ አበባ የፍቅር እንጂ የጸብ ምልክት አትሆንም።

የደቡብ ልጆች የታችኞቹ

የምእራብ ልጆች የዳርኞቹ

የሐበሻ ዘሮች ወገንተኞቹ

በአንቺ አይጣሉም ወሰንተኞቹ በሚል ማህሙድ ፍቅር ምርጫ ሳይሆን የሕልውና መሰረት በመሆኑ ነው::

ታምራት ደስታም ከዚሁ ሐሳብ ጋር የሚቀራረብ ዘፈን አለው። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ስሙ የሚጠቀስ አሻራ እንዲያስቀምጥ ከደቡብ ክልል ጥቁር ውኃ ተቀብላ ያሳደገችውን እና ያኖረችውን አዲስ አበባን ለማወደስ የዘፈነው ይመስላል።

ሳትነፍጊ ያለሽን ሰጥተሽ

ለአዳም ዘር ፍቅርን ያስተማርሽ

ከዚህም ከዚያም ሁሉም መጥቶ

አንቺን አምኖ ተጠግቶ

ሁሌም ሲኖር ቢያወድስሽ

አንቺ እማማ እንዳይገርምሽ

በሚል ታምራት አዲስ አበባ በባዶ እጁ ተፈጥሮ የለገሰችውን አቅም ይዞ ወደ ጓዳዋ የሚመጣን ሰው ሁሉ በመቀበል የምታሳድግ ደግ እናት መሆኗን አዚሟል። አዲስ አበባ የማትሰስት፣ የተረፋት፣ ቀና እናት ሆና እንመለከታታለን።

ፍቅር አዲስ ነቃ ጥበብ ዙማ በሚለው ዘፈን አዲስ አበባን አውስታለች። ፍቅር አዲስ ነቅዓጥበብ ከጎንደር ቆላድባ በ1983 ነበር አዲስ አበባ የገባችው። ጎንደር ከተማ ትዘፍን ነበር። ምናልባት ወደ አዲስ አበባ ባትሄድ ኖሮ ዛሬ ስሟ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ላይሰማ ይችል ነበር። በግል ዘጠኝ የሙዚቃ አልበሞችን፣ ከሌሎች ድምጻዊያን ጋር አራት አልበሞችን ሰርታለች። ይህን እድል የሰጠቻት አዲስ አበባ ናት። እሷም ይህን በአንደበቷ ተናግራ ስላልጠገበች በሙዚቃ ልትነግረን ፈለገች።

ከዘር ከሀይማኖት ከቋንቋ ከነገድ

ሸገር ላይ ይተማል በአራት መንታ መንገድ

አቤት አፈጣጠን አዲስ ሰው ለማልመድ

በአራቱም ማእዘን አውጥቶ እያገባ

ስንቱን አዋደደው ወይ አዲስ አበባ

የምትለው የአዲስ አበባን አቃፊነት፣ ተቀባይነት እና ቸርነት ለመግለጽ ነው። ፍቅር አዲስ ስለ አዲስ አበባ “ብቻዬን መጥቼ፣ ባል ያገባሁበት፣ ልጅ የወለድሁበት እና ዝነኛ የሆንሁበት ከተማ ነው” ስትል ተናግራለች። መዚቃዋም የሚናገረው ይህንኑ ሐቅ ነው።  የአዲስ አበባ ልጅ ቃሉን የሚያከብር፣ ለስልጣኔ የቀረበ፣ ሰው ቶሎ የሚያለምድ ስለመሆኑ ነው የምታዜመው።

በፍጹም ቲ እና ብርሀኑ ተዘራ ዘፈኖች ውስጥ አዲስ አበባ የቁንጅና እና ውበት ምልክት ሆና ቀርባለች። ውበት ስልጣኔን እና አኗኗርን ይከተላል። ዘመናዊነት ውስጥ ያድጋል። የሰለጠነ ሕዝብ፣ ራሱን የሚጠብቅ ሕዝብ የውበት አክሊል የለበሰ መሆኑ ርግጥ ነውና አዲስ አበባ የውበት ምልክትም ናት።

አስናቀች ወርቁ አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነች ሰሞን የዘፈነችው  ዜማ አለ። ተዋበች፣ አሸበረቀች፣ የአፍሪካ ሕብረት መሰረት ሆነች እያለች አዚማላታለች። መናፈሻዋ እና መንገዶችን የውበት ምሳሌ አድርጋ ዘፍናለች። ዛሬም አዲስ አበባ በውበት ላይ ውበትን እየደረበች፤ እያማረባት ቀጥላለች።

ድምጻዊ መስፍን ርስቱ አዲስ አበባዬ በሚለው ዘፈኑ “ዘር አንጠያየቅም”  ይላል። ትንሿ የኢትዮጵያዊያን ማሳያ አዲስ አበባ ከተማ ስለመሆኗ ጠቅሶ፤ የአንድነት ምስጢሩ ፍቅር እና አንድነት ነው ብሏል። ሰፈር እንጂ ዘር መጠያየቅ የአንድነት ጸር በመሆኑ ከፍቅር በቀር ምርጫ የሌለ መሆኑን አዚሟል።

ድምጻዊ ግሩም ታምራት እንዲሁ ስለ አዲስ አበባ ካዜሙት መካከል የሚጠቀስ ነው። አዲስ አበባ የመናገሻ ከተማነቷን ታሪክ ያስታውሳል። ደግም ይሁን ክፉ መሪ የተፈራረቀባት ብትሆንም እንኳን ሕዝቧ ግን በአንድነቱ መቀጠሉን ይገልጻል:: የዓለም ታሪክ እንደሚነግረን መሪዎች አልፈዋል:: ስልጣኔዎች ከስመዋል:: እንደገናም በሌላ ዘመን ተነስተዋል:: ጅረቱ ሕዝብ ግን ጉዞው አይገታም:: በትውልድ ቅብብሎሽ ይቀጥላል::

እናት ዓለም ሸገር ውብ አዱ ገነት

ሁሉም እንደ ፍቅሩ ሚላት የኔ ናት

የአንተም እኔም የእሷም  ነች የሁሉ እናት

የአዲስ አበባ ውበት እና ስልጣኔ በጸሎት አልመጣም። ሁሉም ነዋሪ የእጁ አሻራ አለበት። ሁሉም ነዋሪ እና ተወላጅ ዋጋ ከፍሎላታል። በዚህም ደስታም ይሁን ኀዘን የጋራ እዳ እና በረከት ነው:: እንዲያው የአዲስ አበባ መታወክ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ዳፋ የሚፈጥር ነው:: ለዚህ ነው ድምጻውያን የሁላችን እናት አማረባት እሰይ የሚሉት:: ለተከፉት መጠጊያ  የሰላም ደሴት ናት:: መጽናኛ ናት:: እንጀራ ናት:: ክፉ ቀንን ማሳለፊያ ናት:: የዳሩን እሳት ማጥፊያ ውኃ ናት:: የሁሉ እናት ናትና የሁሉም ልጆቿ ሰላም ያሳስባታል:: ሰላም ይስጠን::፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here