“እምቢ!…”

0
210

የዘጠና ሦስት ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ነው። ከቀደምቱ ስኬታማ የንግድ  ሥራ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። ፎርብስ መጽሔት በአሁኑ ጊዜ የዚህን ባለጸጋ ጠቅላላ የሀብት መጠን 134 ቢሊዮን ዶላር ነው ይላል። ከዓለም ባለጸጋዎች መካከል በ6ኛ ደረጃ የሚገኘው ይህ ሰው ስመ ጥሩው ዋረን ብፌት ነው። ከዚህ ለደረሰበት ስኬት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም እንኳን ጠንክሮ በጥበብ መሥራት ዋናው ጉዳይ  ነው። እሱም ሲናገር “የስኬታማ ሰዎች ዋናው መለያቸው በአብዛኛው ሁሉንም ነገር እምቢ የሚሉ መሆናቸው ነው” ይላል።

የሀገራችን ዘፈን እንደሚለው ዛሬ እምቢ በል የሚለውን ጉዳይ አንስተን እናፍታታዋለን። በአኗኗራችን ብዙ እሽም  እምቢም የምንልባቸው ጉዳዮች አሉ። ዛሬ ግን እሽታውን ትተን እምቢታውን እንመረምራለን። በትሕትና እና አክብሮት እምቢ ማለት በሚል ርዕስ ቻርሊን ሪቻርድ  መጽሐፏ ላይ ባሰፈረችው ሐተታ፣ እምቢ ማለት በሰዎች ዘንድ የሚያስከብር፣ ሕይወትንም የሚለውጥ ነው። የራስን ዋጋ እና ክብርንም ከፍ ያደርጋል።ሁሉንም እሽ ማለት ያረክሳል፤ የሁሉም የሆነ ርካሽ ነው።

ከዚሁ በተመሳሳይ የጉድቱ ግሬት መጽሐፍ ደራሲ ጂም ኮሊንስ “ማድረግ የሚገቡንን ነገሮች ከመዘርዘር ይልቅ  ማድረግ የሌሉብንን ሐሳቦች ጽፎ ማስቀመጥ ጥሩ ነው” ይላል። ጂም ስኬታማ ሰዎች በኑሯቸው ተግባራዊ የሚያደርጓቸውን እምቢታዎች ይዘረዝራል። እነሱም ምንም እንኳን ጥሩ አጋጣሚዎች እጃቸው ላይ ቢቀርቡላቸው እስካልጠቀሟቸው ጊዜ ድረስ እሽ አይሉም፣ አይቀበሏቸውም። የማይደሰቱባቸውን ተግባራት አይመርጡም። የግላቸውን እሴት እና የሕይወት ዓላማ ያስቀድማሉ። ዋጋቸውን ከፍ አድርገው የሚተምኑላቸውን እንጂ ዝቅ የሚያደርጓቸውን ሰዎች እሺ አይሉም። አሉታዊ ሐሳብ በሞላቸው ሰዎች ዙሪያ የሉም። ጊዜ ውድ ነገር መሆኑን ያምናሉ፤ በጠባብ የግንኙነት ስብስብ ውስጥ አቅም የሚፈጥሩላቸውን እና ወደ መልካም ነገር በሚለውጧቸው ሰዎች ዙሪያ ይገኛሉ። ነገሩን ብዙዎች ባይቀበሉትም እንኳን ብዙ መሥራትን እምቢ የሚሉ ናቸው። ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ትተው በሥራ ሱስ የሚጠቁ አይደሉም። ራሳቸው ለራሳቸው ካልሆኑ ማንም እንደማይደርስላቸው ያውቃሉና ጠንቃቃዎችም ናቸው። ለራሳቸው ደኅንነት ቅድሚያ ይሰጣሉ። ለራሳቸው ክብር ስላላቸው ያገኙትን ሥራ ሁሉ አይሠሩም። በመጨረሻም ጂም ኮሊንስ የሚያስቀምጠው ስኬታማዎቹ እምቢ የሚሉት ጉዳይ “ምኞት እና ዓላማቸውን ለሌሎች ደስታ ሲሉ መስዋእት አያደርጉም” የሚለውን ነው።

እምቢ ማለት የራስን ግብ እና ሕይወት መዳረሻ ማወቅ፤ወደ መዳረሻው ለመድረስ እስካልጠቀመ ድረስ አለመቀበል ነው። ሲጓዙ የጎን፣የኋላ እና የፊት ጫጫታዎችን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ነው። በእኛ ሀገር ከዓላማችን ሊያናጥቡን የሚችሉ ነገሮች ብዙ ናቸው። ሲጠቃለል  “ይሉኝታ” ነው ስሙ። ሰው ምን ይለኛል እና እንደ ሰው መመሳሰል አኗኗራችንን የሚያዛቡት መጥፎ ልምምዶች ናቸው። አንዳንድ ሰዎች በሕይወታቸው ማን የት ድረስ፤ በምን መጠን ጣልቃ መግባት እና ማገዝ እንዳለበት አያውቁም። ቢያውቁም እንኳን “እንዴት ብዬ ልንገረው፣ እንደዚህ ብለው ይከፋዋል፣ ትቀየመኛለች፣ ተይ እረፊ ብላት ትታኝ ትሄዳለች፣ በቃ ብላቸው ትዳሬን ያፈርሱብኛል” በማለት ግላዊ ድንበራቸውን በይሉኝታ ያስደፍራሉ። የተደፈረ ድንበር፣ ጣልቃ የተገባበትን አኗኗር ደግሞ ለማስተካከል ሞክረው ሲያቅታቸው “ሰዎች መልካምነቴን አይተው ይበዘብዙኛል፣ የዓርባ ቀን ዕድሌ ነው” ብለው ያማርራሉ።

ሰዎች የትኛውንም  ያህል ቢያፈቅሩ እና ቢቀርቡን የግላዊነት ድንበር አላቸው። ለማንም ሳንናገረው ይዘነው የምንሞተው ሐቅ አለን። ለማንኛውም ሰው የምንናገረው ጉዳይ አለ። ቤተሰባችን ብቻ የሚያውቀው እውነት አለን። ከትዳር አጋራችን ጋር ብቻ የምናውቀው ታሪክ አለን። ሁሉም ለሁሉም አይደረግም፤ አይነገርምም። ሰዎች የግላዊነት ድንበራችንን ሲጥሱብን ምቾት ያሳጡናል። በይሉኝታ ያስጣስነውን ድንበር በለቅሶ ልናጣው እንችላለን።

ሄነሪ ክላውድ እና ጆን ታውንሴንድ ድንበሮች (ባውንደሪስ) በሚል ባዘጋጁት መጽሐፍ “ድንበር እኔ የሚያበቃበት፣ሌላ ሰው ደግሞ የሚጀምርበት መስመር ነው” በማለት ጽፈዋል። እኔ የሚለው መስመር ኀላፊነትን በመውሰድ ባለቤት የሚሆኑበት ነው። ነጻነትን የሚሰጥ መንቀሳቀሻ ቦታ ነው። የግል ቤታችሁ ውስጥ ስትሆኑ የሚሰማችሁ ስሜት  እኔ የሚለውን ድንበር ይመስላል። የእኔ ድንበር ሲያበቃ የሰው ቤት እንዳላችሁ ቁጠሩት እና ነጻነታችሁን መዝኑት። ሰው የራሱን ድንበር እና የመጫዎቻ ሜዳ  አውቆ መንቀሳቀሱ ሌሎችንም ለማክበር፤ራሱንም ለማስከበር ነጻነት ይሰጠዋል።

የሰው ልጆች ለሌሎችም ፍጥረታት ኀላፊነት ቢኖርባቸውም እንኳን ራሳቸውን እንዲያስቀድሙ ነፍሳቸው ትፈልጋለች። “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” ብንልም እንኳን የከፋ ነገር ሲመጣ እናት ጎሽም ነፍሷን ለማትረፍ ልጇን  ጥላው ትሮጣለች። ሁሉም የራሱን ሸክም እንዲሸከም ኀላፊነት ተሰጥቶታል። ለራሱ ያልተሸከመውን ኀላፊነት ለሌሎች እንዲሸከም አይጠበቅም።

ድንበር ሕሊናዊ፣ አካላዊ፣ሐሳባዊ እና መንፈሳዊ ተብሎ ሊታይ ይችላል። ባውንደሪስ መጽሐፍ “የራሳችን ሐሳብ ሊኖረን ያስፈልጋል” በማለት “ብዙዎች የራሳቸውን የማሰብ ሒደት አይቆጣጠሩትም፣ የሌሎችን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ  ወስደው፣ ከሰው መውሰዳቸውን እንኳን ሳይረዱት ይዘውት ይኖራሉ። የሰዎችን ሐሳብ እና መረዳት ሳይለውጡ ይወጣሉ። መመዘን፣ ማሰላሰል እና በምክንያት ማሰብ ተገቢ ነበር” ሲል አስፍሯል።

ቤተርአፕ ዶት ኮም እምቢ ማለት ለብዙዎች የጥፋተኝነት እና ክብር የመንሳት ምልክት መስሎ ይታያቸዋል ይላል። ሰዎች እንዳይቀየሙ፣አለቃን በመፍራት፣ ከሰዎች ላለመለየት ወይም በሌላ ምክንያት እምቢ ማለት የሚከብድህ ከሆነ  ሠላምህን፣ ጊዜ እና አቅምህንም ለመጠቀም ስትል እምቢ ማለትን ልመድ በማለት ያትታል። ውስን አቅም እና ጊዜ ያለው የሰው ልጅ ሁሉንም እሽ በማለት መከወን እንደማይችል ያስገነዝባል።

መንጋው የሚከተለውን አንድ መንገድ ትቶ በሌላ አቅጣጫ  መጓዝ ርግጥ ውግዘት ያስከትል ይሆናል። መንጋው የሚያደንቀውን ሰው መተቸት ርግጥ ነው የሚያስወቅስ ነው። አሸናፊዎች እና ስኬታማዎቹ  ግን ምስጢራቸው ይህ ነው። የማይመስላቸውን ነገር እምቢ፣የማይጠቅማቸውን ጉዳይ አይሆንም ይላሉ።

እምቢ ማለት ለምን እንፈራለን? ዘ ቫይስ ዶት ኮም መልስ አለው። የመጀመሪያው ጉዳይ ሁሉንም እሽ ፣ ይሁን፣ እንዳላችሁ የማለት ልማድ ነው። ሁለተኛው ከሰዎች መለየት የሚያስከትለውን ውግዘት ለመከላከል ሲሉ ሰዎች እሽታን ይመርጣሉ።

በ2010 ዓ.ም  የገጠመኝን የራሴን እውነት ላንሳላችሁ። የመንግሥት ለውጡን ተከትሎ አብዛኛው ሰው የእብደት ስሜት ውስጥ ሆኖ ነበር የሚታየኝ። አንዱን ዜና ሳንጨርስ ሌላ ሰበር ዜና ይመጣል። ብዙ የመረጃ ፍሰት የነበረበት፣በግርግር ያለፈ ዓመት ነበር 2010። ምን እየተካሄደ ነው ብሎ ለመገምገም እንኳን የሚለቀቁ የሚዲያ አጀንዳዎች ዕድል የሚሰጡ አልነበሩም። የለውጡን መንግሥት መደገፍ ፋሽን ነበር። እኔ በራሴ ምክንያት መሐል ላይ ቆምሁ። ብቃወም በወቅቱ ምን ልባል  እችል እንደነበር ስለማውቅ መሐል ላይ ቆሜ ነበር። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ተጠራ። ጓደኞቼ፣ የሥራ ባልደረቦቼ ቲሸርት፣ ኮፍያ እና ልባቸው የፈቀደውን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው  ወደ ሰልፉ ተመሙ። እንሂድ ሲሉኝ አልሄድም አልሁ። ብዙ ተከራከርን፤ ተነቋቆርን። “ከዚህ በላይ መንግሥት ምን ይምጣልህ? ሙሴ ራሱ እኮ ነው፤ ሲጀመር አንተ ጨለምተኛ ነህ” ብለው አውግዘውኝ ወደ ድጋፍ ሰልፋቸው ሄደዋል። ሰልፍም አልወጣሁም፤ እኔም እነሱም አሁንም  በሕይወት አለን። ለውጡን እያየን ነው።

ወደ ቤተር አፕ ድረ ገጽ ልመልሳችሁ። እምቢ ማለትን  መፍራት በልጅነት የሚነሳ ችግር ነው ይላል።ሕጻናት በልጅነታቸው  ጨዋ እና ሁሉንም እሽ የሚሉ እንዲሆኑ ተደርገው ያድጋሉ። በዚህም ይበልጥ ይበረታታሉ። አስተማሪው ወይም ወላጅ አድርግ የሚለውን የማያደርግ ሕጻን ልጅ ቅጣት ይጠብቀዋል። ወይም ይወቀሳል። በዚህ ሒደት ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ምርጫዎቻቸውን ለማስቀደም ይቸገራሉ። የሚፈልጉትን ሳይሆን በዙሪያቸው ያለ ሰው የሚፈልገውን በማድረግ እና በመሆን ያድጋሉ። አንዳንዶች እስከ ሽምግልና ዕድሜ ድረስ የራሳቸውን ፍላጎት ለመናገር የሚቸገሩ ሆነው ያልፋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኢምፖስተር ሲንድረም (ለነገሮች ብቁ አይደለሁም ብሎ ማሰብ) የራሳችንን ድንበር በሌላ እንዲደፈርብን ሊያደርግ ይችላል። “አይቡን ሲሉ አጓቱን፣ ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ” የሚሉ እና ሌሎች አቻ ሐሳቦቻችን ከሰዎች ላለመነጠል፣እምቢ ላለማለት ፣የእኛን ምኞት እና ዓላማ ብንናገር የሚደርስብንን መነጠል ለመሸሽ የምጠቀምባቸው ናቸው። መጀመሪያ ለምጣዱ ብለህ እንጀራ የምትበላበትን የክብር እቃ በአይጥ ታስረግጣለህ፤ ታስደፍራለህ። መጀመሪያ አይብ አገኛለሁ ብለህ እጓት ትጋታለህ። የአይብ ክብርህን በትንሽ አጓት ታስደፍራለህ። ቀጥሎ የሚመጣብህን ግን አትገምተውም፤አትጠብቅም።

የቤተር አፕ ሥራ አስኪያጇ እና የሕይወት ክህሎት አሰልጣኟ ኤልሳቤት ፔሪ መቼ እምቢ ማለት እንዳለብን ጽፋለች። በመጀመሪያም ምቾት ካልተሰማችሁ እምቢ ወይም አይሆንም በሉ  ትላለች። ለሰው ከራሱ የበለጠ ልክ እና ገደቡን የሚያውቅለት ማንም የለም። ምቾት የማይሰጠውን ነገር እንዲያደርግ ሲጠየቅ እምቢ ማለት ምርጫው ነው። በመቀጠልም ከተገደዳችሁ እና የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማችሁ የሚያደርጋችሁ ነገርን እንድትከውኑ ስትጋበዙ እምቢታን ምርጫ አድርጉ ትላለች። በሥራ ቦታዎች እምቢ ማለት ከባድ ቢሆንም ከክብራችሁ ስለማይበልጥ ምርጫችሁ አይሆንም የሚል ይሁን ትላለች። በሦስተኛ ደረጃ  የበዛ የሥራ ክንውን እንድትፈጽሙ ስትጋበዙ አይ በቃ ማለትን ልመዱ  የምትለው ይጠቀሳል። እንዲሁም ሰዎች ግላዊ ድንበራችሁን አልፈው ሲገቡባችሁ እምቢ ማለት ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት እና ሰዎችንም ለማስደሰት ብላችሁ ምንም ነገር እሽ አትበሉ፤ ነገሩን ከእናንተ ጥቅም አንጻር ተመልከቱት ትላለች።

የሕንዱ ኢንዲያን ታይምስ ድረ ገጽ እምቢ ማለት ያለውን ጠቀሜታ ሲያስረዳ “በኑሯችን ጤናማ  ግንኙነቶች እንዲኖሩን ያደርጋል፤ በሌሎች የሚወሰድብንን ብልጫ እና ብዝበዛ እንድንከላከል ያግዛል፤የግል ጤናችንንም ይጠብቅልናል” ብሏል። እምቢታ የግላችንን እሴት እና ማንነት እንድናሳውቅም ያደርጋል። ሰዎች  ሲያውቁን ድንበራችንን ያከብራሉ። “እሱ’ኮ እንደዚህ አይወድም፤ እሷ’ኮ እንትን አይመቻትም” በሚሉ መገለጫዎች የሚታወቁ አሉ።በተቃራኒው “እሱ ችግር የለበትም፤ እሷ ምንም አትልም” በሚል የሚታወቁ ሰዎች አሉ። የመጀመሪያዎቹ ድንበራቸውን የሚያስከብሩት ናቸው። ሁለተኛዎቹ ደግሞ ሰዎች የሚበዘብዟቸው ናቸው።

“ትግደረደሪያለሽ እያሉ ሰዎቹ ያሙሻል፣

ምን ይሉኝ መሆኑን ማን ይረዳልሻል”

በሚለው የፋሲል ደመወዝ ሙዚቃ ውስጥ ይሉኝታ ትልቅ ሀብት ሆኖ እናያለን። ጎረቤታችንን ስንታየሁን ያስታውሰኛል። “ታድላ ቤት አራት ስኒ ቡና ጠጣሁ፤ አሁን ጨጓራየን አነደደኝ” ትላለች። ባለቤቷ አንለይ ደግሞ “ካልተስማማሽ ለምን መጠጣቱን አትተይም” ብሎ ቆጣ ይላል። እሷም “ታድላ እኮ አብሯት ቡና ሚጠጣ የለም፤ እና አፍልታ ቡናዋ ሳይጠጣ ይቅር?” ትላልች። ጉዳዩ የታድላ ቡና ከሚበላሽ እኔ ልበላሽ ነው። የታድላ ቡና ተርፎ ከሚደፋ የእኔ ጨጓራ ይንደድ ነው። በሕይወታችን እንዲህ ዓይነት ብዙ ነገሮች አሉን። ለሰው ደስታ ብለን ራሳችንን አሳልፈን እንሰጣለን። እምቢ ማለትን ከራስ ወዳድነት ጋር የሚያያይዙት ብዙ ናቸው። ራስን ካልወደዱ ማንን ይወዳሉ? ከሚደፋው ቡና ይልቅ ጤናዋን ማስቀደም አልነበረባትም? ቡናው በሰው ልክ እንዲፈላ ማድረግ አይቻልም ነበር?

በመጨረሻም ቬሪ ዌል ማይንድ ዶት ኮም እምቢ ወይም አይሆንም ስንል በትህትና እና ፍቅር  እንዲሆን ይመክራል። በግልጽ እና በቀጥታ አድርጉ የተባላችሁት ጉዳይ እንደማይስማማችሁ አሳውቁ ነው ነገሩ። አራት ስኒ ቡና ጠጪ ስትባል “ይቅርታ ታድላዬ ሁለት ስኒ ይበቃኛል፤ ሲበዛ ጨጓራዬን አይስማማኝም” እንደ ማለት ነው።

ቸር ሰንብቱ!

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here