እምዬ እና እቴጌ

0
30

ልጅ ምኒልክን በ11 ዓመታቸዉ ዐፄ ቴወድሮስ ወደ ሸዋ ለዘመቻ በመጡ ጊዜ ይዘዋቸው ወደ ጎንደር ሄደው ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስም እንደ ልጃቸው ይንከባከቧቸው እንደነበር ዐፄ ምኒልክ ተናግረዋል፡፡ በ1857 ዓ.ም ከወሎ እና ከሸዋ ባላባቶች ጋር ውስጥ ውስጡን ሲላላኩ ቆይተው ከመቅደላ አምልጠው ወደ ሸዋ ገቡ፡፡ 10 ዓመትም በግዞት ነበሩ፤

ደጃዝማች ምኒልክ መቅደላ ላይ ከባድ ዝናብ ጥሎ ባደረበት ሰኔ 24 ቀን 1857 ዓ.ም በቆቂት በር ከ20 ተከታዮቻቸው እና ከእናታቸው ከወይዘሮ እጅጋየሁ ጋር አምልጠው ወደአባታቸው ወዳጅ ወደ ወሎዋ ገዥ ወይዘሮ ወርቂት አመሩ። ሆኖም ወይዘሮ ወርቂት በቴዎድሮስ እጅ ወድቆ የነበረውን ልጃቸውን አመዴ አሊ ሊበንን ማስፈቻ ይሆነኛል በሚል ምኒልክን እና ተከታዮቻቸውን በእስር ይዘዋቸው ነበር።

ወይዘሮ ወርቂት ዐፄ ቴዎድሮስ ልጃቸውን ገደሉት የሚል ወሬ ሲሰሙ ቦሩ ሜዳ ላይ ምኒልክን ተቀብለው፣ “የሸዋ ሰው አውራህ መጥቷልና ደስ ይበልህ፤ ተቀበል” ብለው አዋጅ አስነግረው፤ አጃቢ አድርገው በመለከትና እምቢልታ አሳጅበው ከሸዋ ድንበር ድረስ ላኳቸው።

ልጅ ምኒልክ ከ10 ዓመት የግዞት ዘመን በኃላ ወደ ሸዋ ደብረ ብርሃን ተመልሰው በአባታቸው ዙፋን ተቀምጠው ንጉሥ ሚኒልክ እየተባሉ ሸዋን ብቻ ሲገዙ ቆዩ፡፡ በግዞት በነበሩ ጊዜም ሸዋን ይገዛ የነበረዉ አቶ በዛብህ አፍቅሬ የተባለ ሰው ነበርና ከተባባሪዎቻቸው ጋር ማርከው ዙፋኑን አስለቀቁና ለ12 ዓመታት ያህል እስከ 1870 ዓ.ም ተቀናቃኝ ሳይኖርባቸው ኃይላቸውን ሲያጠናክሩ ቆዩ፡፡ በዚህም ዐፄ ዮሐንስ ስጋት ገባቸውና ሸዋን ለማስገበር ወደ ደብረ ብርሃን መጡ፡፡ የፈሩት ሳይደርስ ቀረና ንጉሥ ምኒልክ ለዐፄ ዮሐንስ እገብራለሁ የሚል መልዕክታቸውን ከላኩ በኃላ ደብረ ሊባኖስ ሄደው በአካል ተገኝተው ከተስማሙ በኃላ ዐፄ ምኒሊክ ንጉሥነታቸው ሙሉ እውቅና ሊያገኝ ችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ንጉሥ ምኒልክ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰዎችን ወደ ሸዋ አምጥተው በክብር እያሳደጉ፣ እያስተማሩ፣ ግዛት እና ሹመት እየሰጡ፣ በጋብቻ እና በባሕል እንዲተሳሰር፤ አንዱ የአንዱን ጎሳና ሐይማኖት እንዲያከብር እና ተስማምቶ እንዲኖር አድርገዋል፡፡ ሰው ባሪያ አይባልም በማለት ከልክለዉ አስተምረዋል፡፡

ንጉሥ ምኒልክ ከቦሩ ሜዳ (ከዉጫሌ) ተነስተዉ ሐምሌ ዘጠኝ ቀን 1881 ዓ.ም እንጦጦ ገቡ፡፡ በደረሱ በ4ኛው ወር ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተቀብተው ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው በእንጦጦ ማሪያም ቤተክርስቲያን ነገሡ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ የተባሉትም የንግሥተ ሳባና የሰለሞን ልጅ ምኒልክ ቀድሞ ነግሦ ስለነበር ነዉ፡፡

ዐፄ ምኒልክ በሳል እና ሁሉን አካታች፣ ችግሮችን ደግሞ በስልት እና በጥበብ የሚፈቱ ነበሩ:: ከስሜታዊነት ይልቅ እርጋታ፣ በመጀመሪያ ኃይል ከመጠቀም ይልቅ ንግግር እና ስምምነትን የሚያስቀድሙ ነበሩ::  በምኒልክ ቤተ መንግሥት ወሳኝ የነበሩ ሰዎች ከተለያየ ብሔረሰብ የተገኙ እንደሆኑ ሁሉ በሀገር አንድነት ዘመቻውም የተሳተፈው ሰራዊትም ኅብረ ብሄራዊ እንደነበር በዕውቀቱ ስዩም ከአሜን ባሻገር በተሰኘው መጽሐፉ አስፍሯል::

በወላይታ ዘመቻ ንጉሥ ጦናን አቁስለው የማረኩት የራስ ሚካኤል ወታደሮች ናቸው:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳ የምኒልክን መሐሪነት እና ደግነት የሚያወሳ ሁነት እናንሳ:: የወላይታው ንጉሥ ጦና ለኢትዮጵያ ግዛት አንድነት ሲባል ለማዕከላዊ መንግሥት በሰላም እንዲገብሩ በምኒልክ ቢጠየቁ አልስማማም አሉ:: በዚህም የግዛት ማስከበር እርምጃ ተወሰደባቸው:: ከእልህ አስጨራሹ ጦርነት በኋላ ቆስለው የተማረኩትን ንጉሥ ጦናን የምኒልክ ወታደሮች በማይረባ ወሳንሳ ተሸክመው ለምኒልክ ሲያቀርቡ፣ ምኒልክም “ወንድሜን በማይረባ ወሳንሳ ታመጡታላችሁ!” ብለው መቆጣታቸው እና ከዙፋናቸው ወርደው መቀበላቸው በታሪክ ሰፍሯል:: ንጉሥ ጦናንም ራሳቸው አስታመው ካዳኗቸው በኋላ መልሰው የወላይታ ግዛት ገዥ እንዳደረጓቸው ይነገራል::

ዐፄ ምኒልክ ዘመናዊነትን ለሀገራቸው ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው፣ እንዲሁም በባቡር፣ ስልክ፣ ፖስታ፣ ኤሌክትሪክ፣ አውቶሞቢል፣ የውኃ ቧንቧ፣ ህክምና፣ ሆሰፒታል/ መድኃኒት ቤት፣ ባንክ፣ ገንዘብ ማተሚያ ቤት፣ ጋዜጣ፣ ሆቴል እና ፖሊስ አገልግሎት መኪና፣ ወፍጮ፣ ቀይ መስቀል፣ የሚኒስተሮች ሹመት፣ የሙዚቃ ሸክላ የመሳሰሉትን ሥራዎች ያስገቡ ነበሩ:: ዐፄ ምኒልክ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን በአስተዳደር፣ በበጎ ተግባር፣ በውጭ ግንኙነት እና በሌሎች መስኮች የተዋጣላቸው መሪ እንደነበሩ የተለያዩ ጸሐፊያን፣ የታሪክ ምሁራን እና የውጭ ሀገር ዜጎች ሳይቀር መስክረዋል::

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ዐፄ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች በመመርመር ማጠቃለያ ሀሳቡን ሲያስቀምጥ “ሁሉም ደብዳቤዎች የንጉሠ ነገሥቱን ትሁት ግለ- ባህርያት ያንጸባርቃሉ” ብሏል:: ሌላው ቀርቶ ይላል ጳውሎስ ኞኞ ምኒልክ የማይስማሙበት ነገር እንኳን ቢገጥማቸው አሉታዊ መልሳቸው ተቀባዩን ቅር እንዳያሰኝባቸው ተጨንቀውና ተጠበው ነበር ደብዳቤውን የሚጽፉት:: ዐፄ ምኒልክን እምዬ በሚል ሙገሳ ሕዝቡ የሚጠራቸው ያለ ምክንያት አልነበረም:: ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሤም የጳውሎስ ኞኞን ሀሳብ ይጋሩታል፤ ጸሐፌ ትእዛዙ ዐፄ ምኒልክ አስተዋይ እና ሩህሩህ እንደነበሩ ጽፈዋል::

አንጋፋው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ ዐፄ ምኒልክ እንደጻፉት፣ ምኒልክ የቆሰለውን ምርኮኛ ገድሎ በመጨረስ ፋንታ ቁስላቸውን ራሳቸው አክመው አጠገባቸው አስቀምጠው አብረዋቸው እንዲመገቡ በማድረግ ፍቅር ያሳዩአቸው ነበር:: ሀገራቸውን ለመውረር የመጡ ምርኮኞች ጣሊያኖችን እንኳን በርህራሄ እና በደግነት ነበር የያዟቸው:: ዐፄ ምኒልክ ከአባታቸው ከንጉሥ ኃይለ መለኮት ጋር ከኖሩበት 10 ዓመታት ይልቅ፤ ከዐፄ ቴዎድሮስ ጋር በኖሩበት 11 ዓመታት ውስጥ አያሌ ነገሮችን መማራቸውን ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ያስረዳሉ:: የውጭ ግንኙነት እና ሕዝብን የማሰልጠን የመሳሰሉ ጽንሰ ሃሳቦችን ከቴዎድሮስ ገና በልጅነታቸው የቀሰሟቸው ናቸው:: ይህም በኋላ ላይ በዓድዋ ጦርነት እንደጠቀማቸው ማየት ይቻላል::

ለዐፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች መረታት፣ ለተክለ ጊዮርጊስ በዮሐንስ መሸነፍ እንዲሁም ራሳቸው ምኒልክ ለዮሐንስ መገበር ዋናው ምክንያት የጦር መሳሪያ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል:: ጎራዴ እና ጦር ብቻቸውን ዘመኑን እንደማይዋጁ እና እንዳለፈባቸው ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉሥ ሳሉ ገብቷቸዋል:: በዚህም ዘመናዊ ጠመንጃ እና ጥይት ማምረት ከሚችሉ ሀገራት ጋር መወዳጀት መሣሪያዎቹ በብዛት እጃቸው እንዲገቡ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው:: ለዚህም ደግሞ የእነዚህን ሀገራት ዜጎች በቅርባቸው አድርገው መንከባከብ ከዚያም ለመንግሥቶቻቸው ስጦታ እየላኩ መወዳጀት አንዱ የዲፕሎማሲ አካሄዳቸው ነበር:: ከጠቡ በፊት ከጣሊያን፣ በኋላ ግን ከፈረንሳይ እና ሞስኮቭ (ሩሲያ) ጋር ወዳጅነት መስርተዋል:: በዚህም ወደ ንጉሠ ነገሥትነት ማዕረግ ለመምጣትም ሆነ ወራሪውን ጣሊያንን ድል አድርጎ ለመመለስ የረዳቸውን የጦር መሣሪያ ከእነዚህ ሀገራት ማግኘት ችለዋል::

ዐፄ ምኒልክ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለመፍጠር የሄዱበትን ርቀት እና ብስለት በመመልከት አንዳንዶች ከጀርመኑ ኦቶማን ቢስማርክ ጋር ያመሳስሏቸዋል:: ቢስማርክ የተበታተነች ጀርመንን ሰብስቦ አንድ ሀገር በማድረግ እንዳቆማት ሁሉ ዐፄ ምኒልክም አንድነቷ የጠነከረና ለቅኝ ግዛት ያልተበገረች ኢትዮጵያን በመፍጠር ቁልፍ ሰው ነበሩ::

ዐፄ ምኒሊክ የንጉሠ ነገሥትነቱን ማዕረግ ባገኙ በሦስተኛውም ቀን ወ/ሮ ጣይቱ ብጡል በጳጳሱ በአቡነ ማቴወስ እጅ የሚገባቸዉን ዘውድ ደፍተዉ እቴጌ ተባሉ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮም ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ እየተባሉ መጠራት ጀመሩ፡፡

እቴጌ ጣይቱ በአስተዳደር አንፃር የነበራቸው ችሎታና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በታሪክ አዋቂዎች ዘንድ ተደናቂነትን አትርፎላቸዋል። በየጊዜው ይነሱ በነበሩ የሀገር ጉዳዮች ላይ ይይዙት የነበረው አቋም፣ ይሰጡት የነበረው ውሳኔና ያስተላልፉ የነበረው ትዕዛዝ ተሰሚነትና ተቀባይነት እያገኘ እንደመሄዱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄድ ለነበረው ሥልጣናቸው ዓይነተኛ ምክንያት ነበር።

እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሳትፏቸው የገነነውና በሀገር አስተዳደርም ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመሩት፤ ኢትዮጵያ ሚያዝያ 25 ቀን 1981 ዓ.ም በውጫሌ ላይ ከኢጣሊያ ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በኢጣሊያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ ውንብድና መኖሩ ከታወቀ ወዲህ ነው።

እቴጌ ጣይቱም ይህ ውል ተግባራዊ ሊሆን አይገባውም፤ በማለት «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» የሚለውን አቋማቸው በታሪክ ቅርስነቱ ለትውልድ ትተውት ያለፉት አባባል ዘመን ተለውጦ ዘመን እየተተካ በሄደ ቁጥር የሚነገር ሆነ። ስለዚህ የእቴጌን ጀግንነት የቁርጠኛ ኢትዮጵያዊ ልጅ ለመሆናቸው ሌላ ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም።

ስለ እቴጌ ጣይቱ ሲወሳ በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው የከተማዋ የመጀመሪያው ሆቴል «ጣይቱ ሆቴል» አብሮ ይነሳል።

 

ሳምንቱ በታሪክ

አብዮተኞቹ

የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለስላሴ ንጉሣዊ አገዛዝን በ1960ቹ ክፉኛ የተገዳደሩት አብዮተኞቹ እነ ዋለልኝ መኮንን ያልተሳካውን የአውሮፕላን ጠለፋ ያካሄዱት ልክ በዚህ ሳምንት ህዳር 29 ቀን 1965 ዓ.ም ነበር።

በስልሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ስር ነቀል ለውጥን በማቀንቀንና መሬትን ለአራሹ በሚል እንቅስቃሴያቸው የአብዮቱ ጠባቂ (ዘ ጋርዲያን ኦፍ ዘ ሪቮሉሽን) ተብሎ በሚጠራው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በህቡዕ እና በግልፅ ጭምር እንቅስቃሴ ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ነበር። ትግሉን ከሚመሩት ወጣቶች መሃል ታዲያ ዋለልኝ መኮንን፣ ማርታ መብራህቱ፣ አማኑኤል ዮሃንስ፣ ጌታቸው ሐብቴ፣ ዮሃንስ በፍቃዱ፣ ተስፋዬ ቢርጋና እና ታደለች ኪዳነ ማርያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነን ቦይንግ ስሬት አውሮፕላን በአስመራ በኩል ወደ አቴንስ፣ ሮም ከዛም ወደ ፓሪስ በመብረር ላይ እንዳለ በመጥለፍ፤ ወደ አልጄሪያ በማቅናት ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መንገድ አውሮፕላን ጠልፈው ከወጡት እነ ብረሀነመስቀል ረዳን ከመሳሰሉ ጓዶቻቸው ጋር በኢህአፓ መስራች ጉባኤ ላይ ለመገኘት ነበር።

አውሮፕላኑ 94 መንገደኞችን ከዘጠኝ የበረራ አስተናጋጆች ጋር ጭኖ ከተነሳ ከ13 ደቂቃ በኋላ የደህንነት ፍተሻን አልፈው ሽጉጥና ቦንብ ይዘው የገቡት እነዚህ ሰባት ወጣቶች አውሮፕላኑ መጠለፉን አወጁ። ይሁንእንጂ ከአንድ አባላቸው በስተቀር በፀረ አውሮፕላን ጠላፊዎች ጭምር በተወሰደባቸው እርምጃ ስድስቱም ወዲያውኑ ህይወታቸው እንዳለፈ እና የተወሰኑ መንገደኞች መቁሰላቸውን “ደንዲ የግዞት አምባ” የተሰኘው የደራሲ ደርባቸው ሙሐመድ መጽሐፍ ይተርካል፡፡

የተሳካው ንቅለ ተከላ

እ.ኤ.አ. በ 1983 የቀዶ ጥገና ሐኪሞች በብሪታንያ የተደረገውን የመጀመሪያውን የልብ እና የሳንባ ንቅለ ተከላ  ጥገና በተሳካ ሁኔታ አጠናቀዋል። ለስዊድናዊው ጋዜጠኛ ላርስ ሉንግበርግ፣ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየችው እንግሊዛዊት ሴት የአካል ክፍሎችን በመውሰድ ንቅለ ተከላው ተፈጽሞለታል።

 

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here