“ልጆቼ ሌሎች ሕፃናት ዳቦ ሲበሉ ዐይተው ‘ዳቦ ግዥልን?’ ሲሉኝ የምገዛበት አስር ብር እንኳን ስላልነበረኝ ባልወለድኩ በማለት ከፀፀት ሳልወጣ ወላጅ እናቴ ደግሞ ገንዘብ የሌለኝ መሆኑን ባለመገንዘብ ‘ሥጋ ግዥልኝ?‘ ትለኛለች፡፡ ለጠየቁኝ ሁሉ መፍትሔ ሳጣ የማውቃቸውን ሰዎች ‘ስጋ ጋብዙኝ!‘ ብዬ ለምኜ ሲጋብዙኝ ‘ከቤቴ ወስጄ ልብላው!‘ በማለት እናቴን ያበላሁበትን አጋጣሚ መቼም አልረሳውም!” በማለት እንባ እየተናነቃት ያሳለፈቻቸውን ጊዜያት እና አሁን የደረሰችበትን ታሪኳን ያጋራችን የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ እናኑ ደምሴ ናት፡፡
ባለታሪካችን በባሕር ዳር ከተማ በተለምዶ ኪዳነምሕረት በሚባለው ገበያ በመንግሥት የተሰጣትን የመሥሪያ ቦታ/ ሼድ/ ለሁለት ከፍላ አንዱን የጫማ እና ልብስ መሥፊያ ሌላኛውን ደግሞ ምግብ እና ሻይ መሸጫ በማድረግ እየተመላለሰች ሥትሠራ ነው ያገኘናት፡፡ እንደ ወቅቱ ገበያው የሚፈልገውን ያላትን ሙያ ሁሉ ተጠቅማ ኑሮዋን ለመለወጥ እና ልጆቿን ለማስተማር ከወዲያ ወዲህ ትሯሯጣለች፡፡
ፒጃማ እና ሌሎች የሥራ ልብሶች ትሰፋለች፤ የስፌቱ ሥራ ሲቀዘቅዝ ደግሞ በእጇ በክር ጫማ በመሥራት ትሸጣለች፡፡
ትውልድ እና እድገቷ ደቡብ ጎንደር የሆነችው ወይዘሮ እናኑ ደሴ እድሜዋ ደርሶ ትዳር ስትመሠርት አካባቢዋን ለቃ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዳንሻ ከተማ መኖሪያዋን አደረገች፡፡ ለሦስት ዓመታት ዳንሻ አካባቢ ቆይታ የተሻለ ኑኖ ለመኖር ከባለቤቷ ጋር ወደ አዲስ አበባ አቀኑ፡፡
በተከታታይ ሁለት ልጆችን በመውለዷ ባለቤቷ ሥራ እንድትሠራ አልፈለገም ነበር፡፡ ወይዘሮ እናኑ ግን ልጆቿ ሕጻን ቢሆኑም የተለያየ ሙያ ለመማር እና ለመሥራት ባላት ፍላጎት ሕፃናት ማዋያ እያዋለች፤ አንዳንዴም ትንሿን እያዘለች ረጅም መንገድ በመጓዝ የፀጉር ሥራ እና የምግብ ዝግጅት ሙያ ሰልጥናለች፡፡
ይሁንና ከባለቤቷ አልፎ ሌሎች ሰዎች “ምን ጎደለብሽ! ለምን ትሠሪያለሽ?” ቢሏትም እሷ ግን በመሥራት ላይ ያላት አቋም ጠንካራ በመሆኑ የሰዎችን ተግሳጽ ባለመቀበል ከሥራ ቦዝና እንደማታውቅ ታስታውሳለች፡፡
ወ/ሮ እናኑ ከትዳር አጋሯ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት አይሎ በፍች ተጠናቀቀ፡፡ “ከድጡ ወደ ማጡ” እንደሚባለው ሱሉልታ አካባቢ የነበረው ቤታቸው በሕገ ወጥነት ሲፈርስ የነሡ ቤትም አብሮ ፈረሰ፡፡ ባለታሪካችን እቃዋን ይዛ እናቷ ወዳለችበት ወደ ትውልድ ቦታዋ የገጠር አካባቢ ተመልሳ እንድትገባ ሁኔታው አስገደዳት፡፡
በወቅቱ የወይዘሮ እናኑ ሃሳብ እናቷ ልጆችዋን ብትይዝላት እሷ ትልቅ ሆቴል ውስጥ ወጥ ቤት አልያም በሰለጠነችበት ፀጉር ቤት ሠርታ ለመለመወጥ ነበር፡፡ ቢሆንም ወደ አካባቢዋ ስትመለስ የገጠማት ሁኔታ ግን የእናቷ ጤንነት ታውኮ አልጋ ላይ ወድቃ ነበር ያገኘቻት፡፡
በወቅቱ የመጀመሪያ ልጇ ትምህርት ጀምራ ነበር፡፡ በተፈጠረው ችግር ግን ትምህርቷን አቋርጣ ለመቀመጥ ተገደደች፡፡ ከዛ በላይ ደግሞ ልጆቿ “ዳቦ ግዥልን?” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ መመለስ የምትችልበት አቅም በማጣቷ እንዲሁም ወላጅ እናቷም የጤናዋ ሁኔታ አሳሳቢ ስለነበር ችግሯን ብትነግራትም ህመሟን ያባብሳል በሚል ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደገባች ታስታውሳለች፡፡
ወይዘሮ እናኑ አዲስ አበባን ስትለቅ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ በሄደችበት አካባቢ ለሥራ ትብብር እንዲያደርግላት ድጋፍ ጠይቃ ጽፎላት ነበር፡፡ ገጠር ተቀምጣ እጇ ላይ አንድም ብር ከማጣት ደረጃ ስትደርስ የትብብር ደብዳቤዋን በመያዝ ወደ ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመምጣት ለቢሮ ኃላፊዋ ያለባትን ችግሮች ሁሉ ዘርዝራ መፍትሔ እንዲሰጣት ተማጸነች፡፡
“ችግሬን የማካፍለው ሰው ስለሌለ እና በጭንቀት ሕመም ውስጥ ስለነበርሁ እያለቀስሁ ያለፍኩበትን እና ያለብኝን ችግር በማካፈሌ በራሱ ትልቅ ረፍት ተሰማኝ” በማለት የምትገልፀው ወይዘሮ እናኑ፤ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከቢሮው ተደውሎ ወደ ሥራ ለማስገባት ሥልጠና እንድትወስድ ተጠራች፡፡
ወይዘሮ እናኑ ያንጊዜ ስታስታውስ “በወቅቱ ሥልጠናውን ወሰድሁ፤ ለመሥራት ግን የማርፍበት ቤት እንኳን ስለሌለኝ በቢሮው ‘ሥራ ለመጀመር ድጋፍ ይደረግላችኋል‘ ስለተባልን ወደ እናቴ ተመለስሁ’ በማለት ነበር፡፡
ከወራት በኋላ ወይዘሮ እናኑን ቢሮው የገባውን ቃል ለመተግበር ጥሪ አደረገላት፡፡ ወይዘሮ እናኑ የልብስ ጥልፍ ማሽን ፣ መተኮሻ፣ ለሥራው መጀመር የሚጠቅም የስፌት ክር እንዲሁም ጨርቅ በቢሮው ተገዝቶ ተሰጣት፡፡
በቢሮው የተደረገው ድጋፍ ዕቃውን ጨምሮ 100 ሺህ ብር የሚጠጋ እንደነበር ወይዘሮ እናኑ ያስታውሳሉ፡፡ ባገኘችው ድጋፍም ከነቁሳቁሱ ጥበብ ለመሥራት ሸማ ተራ አካባቢ ተከራይታ ሥራውን ጀመረች፡፡ በወቅቱ ግን ሥራው ጥሩ ገበያ ስላልነበረው ትሠራበት የነበረውን የኪራይ ቤት ለቀቀች፡፡
ከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነት ያላት ወይዘሮ እናኑ ሥራዋ ገበያ አጣ ብላ አልተቀመጠችም፤ ድጋሚ ወደ ሴቶች ሕፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በማቅናት መሥሪያ ቦታ ጠየቀች፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ያለችበት የኪዳነምህረት ገበያ ሼድ ተሰጣት፡፡ የጥልፉን ማሽን በመሸጥ የልብስ ስፌት ማሽን በመግዛት ወደ ልብስ ስፌት ፣ዲዛይን፣ ጫማ ሥራ ገባች፡፡
ወይዘሮ እናኑ ከአዲስ አበባ 2015 ዓ.ም መጨረሻ ወደ ባሕር ዳር አቀናች፤ 2016 ዓ.ም ሰኔ አካባቢ የመሥሪያ ቁሳቁስ እና ብር ከሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ቢሮ ባገኘችው ዳጋፍ አላሠራ ያላትን ዘርፍ ብሩ ሳይጠፋ ቶሎ በመቀያየር እና አዋጭ የሆነውን ሁሉ በመሞከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሽን እና ጥሬቃውን ጨምሮ ዛሬ ካፒታሏ 225 ሺህ ብር ደርሷል፡፡
“ብዙ ሙያ ስላለኝ ከሰው በጥገኝነት እንዳልወድቅ እና ልጆቼን የተሻለ ለማኖር ባደረኩት ጥረት በጥቂት ጊዜ ውጤታማ ለመሆን አበቃኝ፡፡ ለልጆቼ ዳቦ ለመግዛት እንኳን አስር ብር እጄ ላይ በማጣቴ እረፍት የለኝም ነበር፡፡ ራሴን በማሳመን ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መሥራቴ ለለውጥ አብቅቶኛል” በማለት ወይዘሮ እናኑ ያለፈችባቸውን ፈታኝ ጊዜያት እና የደረሰችበትን ስኬት ታስታውሳለች፡፡
የክር ጫማ የጀመረችው ሌሎች ሰዎች ሲሠሩ ዓይታ ለመሥራት አንድ ሰዓት ብቻ ቁጭ ብላ በተመለከተችው መሆኑን የምትናገረው ወይዘሮ እናኑ፤ የጫማም ሆነ የልብሥ ሥራው ሳይኖር ዳቦ፣ፒዛ… ቶሎ የሚደርሱ …የተለያዩ ምግቦችን በመሥራት በትንሽ ዋጋ ለተጠቃሚው ከሻይ እና ቡና ጋር በመሸጥ ኑሮዋን ለማሸነፍ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ በመቀጠል አሁን ካለችበት በላይ ሀብት ማፍራት እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም