የወር አበባ መቆምን የሚያበስረው የሕይወት ደረጃ ማረጥ /እርጣት/ በእንግሊዘኛው ደግሞ menopause ተብሎ ይጠራል። ማረጥ የሴቶች የወር አበባ ዑደት ማብቃቱን የሚያመለክት ተፈጥሯዊ /ባዮሎጂያዊ/ ሂደት ነው::
በባሕር ዳር ከተማ በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል የማህፀን እና ፅንስ ሐኪም ዶ/ር ለዓለም መሠረት እንደሚገልፁት ማረጥ የሴቶች የወር አበባ የሚቆምበት ወቅት ሲሆን ይህም በአብዛኛው በአማካይ 51 ዓመት አካባቢ ይከሰታል። እርጣት በተፈጥሮ ሊመጣ የሚችል፣ እዛ ዕድሜ ላይ ለመድረስ የታደሉት ሊያገኙት የሚችሉት እንዲሁም ይህ ወቅት ሴቶች ልጆች የሚያፈሩበት ጊዜ የሚያከትምበትና አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መጀመሩን የሚያሳይ ነው።
የወር አበባ መቆራረጥ በአማካይ በ46 ዓመት የሚጀምር ሲሆን ይህም ቅድመ ማረጥ ይባላል። የማረጥ የእድሜ መነሻው ከ45 እስከ 55 እንደሆነ ዶ/ር ለዓለም አብራርተዋል::
ማረጥ በተለይም የወር አበባ ዑደትን የሚቆጣጠረው ኤስትሮጅንን ጨምሮ የሆርሞን መጠን የሚቀየርበት የዕድሜ ክልል ነው። ሴቶች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ እንቁልጢ (ኦቫሪ) ጥቂት እንቁላሎችን ያመርታል። ኤስትሮጅን የተሰኘው ሆርሞን መጠን ደጎሞ ይለዋወጣል:: ቀስ በቀስም ይቀንሳል፤ ይህ ደግሞ ወደ ማረጥ ምልክቶች ያመራል። ይህ ወሳኝ ሆርሞን መጠኑ ዝቅተኛ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ብዙ ዓመታትን ሊወስድ የሚችል ሲሆን በዚህም መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ይቆያል ፤ በሰውነት ላይም ለውጦችን ያመጣል።
እንቁልጢዎች (ኦቫሪ) ሙሉ በሙሉ እንቁላል ማምረት ሲያቆሙ እርግዝና የማይቻል በመሆኑ ማረጥ መከሰቱ ይረጋገጣል:: በዚህም ወቅት የወር አበባቸው መምጫ መለዋወጥ ወይም ከባድ መሆን ያጋጥማል:: በተጨማሪም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ስሜት ይቀያየራል ወይም አካላዊ ችግሮች ያጋጥማሉ። የወር አበባ ለአስራ ሁለት ወራት ወይም ለአንድ ዓመት ያህል ካልመጣ ማረጥ ተከስቷል ማለት ነው።
ማረጥ አልፎ አልፎ ከአማካይ እድሜ ወይም ከ40 ዓመት በታች ከተከሰተ ግን ቅድመ ማረጥ (premature ovarian faller) ይባላል:: ይህ ችግር ደግሞ ከ100 ሴቶች አንዷ ላይ ቀድሞ የመከሰት ዕድል አለው:: በአንዳንዶች ላይ በተፈጥሮ ወይም ለሌላ በሽታ ካደረጉት ህክምና ጋር ተያይዞ ቀደም ብሎ ሊከሰት ይችላል።
እንደ ዘርፉ ባለሙያ ማብራሪያ በሆርሞኖች ማነስ እንቁላል የሚያመርተው እንቁልጢ (ovary) ላይ እጢ ሲፈጠር ፤ ሁለቱም ኦቫሪዎች በማህፀን ቀዶ ጥገና ወይም በሌላ ቀዶ ጥገና ከተወገዱ እድሜ ምንም ይሁን ምን ማረጥ ወዲያውኑ ይጀምራል:: ለካንሰር ህክምና የሚሰጡ ኪሞቴራፒ እና የዳሌ ጨረር ህክምና ኦቫሪን በመጉዳት የወር አበባ ከተጠበቀው ጊዜ ቀድሞ ማረጥን ያስከትላል::
እርጣት ሲከሰት ከ80 ከመቶ በላይ ሴቶች ደረታቸው አካባቢ ከፍተኛ ላበት መከሰት፣ ሙቀት መሠማት፣ የእንቅልፍ እጦት፣ የጠባይ መቀያየር ፣ የመገጣጠሚያ አካባቢ ህመም፤ ኢስትሮጂን መመረት ሰለሚቆም እና በሰውነት ስለማይኖር የካልሺየም እጥረት፣ የአጥንት መሳሳት፣ በብልት መድረቅ በግንኙነት ወቅት ህመም መሰማት እና ምቾት ማጣት ፣ መደበኛ ያልሆነ የወር አበባ ማቆም፣ የሌሊት ላበት ፣ ብስጭት ወይም ጭንቀት፣ የወሲብ ስሜት መቀነስ ፣ በሆድ አካባቢ ክብደት መጨመር፣ ቀጭን ፀጉር እና ደረቅ ቆዳ መከሰት፣ የማስታወስ ችሎታ ማጣት ወይም ትኩረትን መሰብሰብ ማጣት፣ የመገጣጠሚያ አካባቢ ህመም እና ድካም ይከሰታሉ::
ታዲያ በዚህ ወቅት ባል እና ሚስት መናበብ ፣ መነጋገር እና መረዳዳት አለባቸው፤ በተለይ ባል የባለቤቱን ህመም በደንብ መረዳት ይገባዋል:: በግንኙነት ጊዜ በሚከሰት ህመም ሴቷ ደስተኛ ካልሆነች ትዳር ላይ ችግር እንዳይፈጠር በግልፅ በመነጋገር የኢስትሮጂን ቅባቶችን /ክሬም/ መጠቀም እና ማለስለስ ያስፈልጋል:: ወንዶችም የትዳር አጋራቸውን ችግር መረዳት ይገባቸዋል::
የእርጣት ምልክቶች እና ህመሞች እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ የሚሉት ዶ/ር ለዓለም፤ በዚህም ሆርሞኖቹ የተለያዩ በመሆናቸው በራሳቸው እስኪስተካከሉ ጊዜ ይወስዳሉ:: ለምሳሌ የሰውነት ሙቀት መጨመር ከስድስት ወር እስከ ዓመት ድረስ ሊቆይ ይችላል:: የብልት መድረቅ ፣ የሽንት መሽኛ ቱቦ አካባቢ መሳሳት፣ ልብ አካባቢ የሚፈጠር ችግር እንዲሁም የጡት መሟሟት በተሰጣት እድሜ ልክ አብሮ የሚቀጥል ችግር ይሆናል:: በመሆኑም እርጣት ሆርሞን የሚመረትበት ጊዜ ሲያልቅ የሚከሰት እድሜ ያመጣው ክስተት እንደሆነ ማወቅ እንደሚገባ ተጠቁሟል:: ለዚህም ሴቶች ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው በመጠበቅ ፤ ማስታገሻ መውሰድ፣ የህሊና ዝግጅት ማድረግ፤ የእንቅልፍ ችግርን ፣ የካልሺየም እጥረትን ፣የአጥንት መሳሳትን እየተከታተሉ መታከም ያስፈልጋል::
ማረጥ በሽታ ሳይሆን መደበኛ የሕይወት ደረጃ ነው:: ምንም እንኳን ከእሱ ጋር የሚመጡ አካላዊ እና ስሜታዊ ለውጦች በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ቢችሉም ሴቶች በተገቢው እንክብካቤ፣ ህክምና እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን በማድረግ ምልክቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መቆጣጠር እና ማረጥ ከጀመሩ በኋላ ጤናን መጠበቅ እንደሚችሉ ዶ/ር ለዓለም መሠረት አስገንዝበዋል::
ጤና አዳም
በማረጥ ጊዜ ሴቶች ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
የሁሉም ሴት የሆርሞን ለውጥ የተለያየ ነው። ይህ ደግሞ እንደ ማኅበራዊና ባህላዊ ሁነት፣ የሰውነት አወቃቀር እና አኗኗር የሚወሰን ነው።
ስለዚህ በእርጣት ወቅትም የሚታየው ለውጥ የሚጀርምርበት ጊዜና ለውጡ እንደየ ሴቷ አኗኗር ይለያያል። አማካዩ የማረጥ ዕድሜ 51 ሲሆን፣ ከ40 እስከ 60 ዕድሜ ውስጥ ባለው ጊዜ ሊሆንም ይችላል። ስለዚህ ለውጡ ሲከሰት
- ምቾትን መጠበቅ ፣ እንቅስቃሴ በማድረግ ክብደትን መቆጣጠር ፣ ቆዳን መንከባከብ፤
- እንደ ማግኒዚያም፣ ካልሽየም እና ቪይታሚን ዲ የሚይዙ ምግቦችን ማዘውተር ፣ እንቅልፍን በአግባቡ
መተኛት ፣ የአልኮል መጠን መቀነስ ፡፡
- ቅጠላማ አትክልቶች፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ ጥራጥሬዎች፣ ለውዝ፣ ኦሜጋ-3 የበለጸጉ ምግቦች እና ሙሉ
የእህሎች ዘሮችን መመገብ፡፡
- ቅመም የበዛባቸው ካፌይን፣ አልኮል እና የተቀነባበሩ ምግቦችን ፣ ትኩሳት እና የእንቅልፍ ችግሮችን
ሊያባብሱ ስለሚችሉ ማሶገድ፡፡
- የአጥንት እና የልብ ጤናን ለመደገፍ በካልሲየም፣ ቫይታሚን ዲ፣ ፕሮቲን ያላቸው /የበለፀገ/ የተመጣጠኑ
ምግቦችን ይመገቡ።
- እንደ መራመድ (ወክ) ፣ ስፓርት ወይም የጥንካሬ የሚሠጥ ስልጠናን መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ስሜትን ለማሻሻል እና የአጥንትን መሳሳት ለመቀነስ ይረዳሉ።
- በደንብ ማሰላሰል፣ በጥልቅ መተንፈስ ደግሞ ጭንቀትን እና ትኩሳት /የሰውነት ብልጭታዎችን/
ለመቆጣጠር እንደ ማስታገሻ ቴክኒኮችን መለማመድ።
ምንጭ- ሚድኮቨር ሆስፒታል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም