የዓየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ሙቀት ግግር በረዶ እየቀለጠ መጠኑ ሲቀንስ መሬት ውስጥ የተዳፈነ ቅላጭ አለት እንቅስቃሴ ፈጥሮ እየተስፋፋ የእሳተገሞራ ፍንዳታን ሊያባባስ እንደሚችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::
የአውሮፓ ጂኦ ኬሚስትሪ ማህበር በመረጃ ምንጭነት ለንባብ እንዳበቃው ግግር በረዶ ከሥር የሚገኙ የእሳተ ገሞራ ቅላጭ እንቅስቃሴን ይገድባል:: ሆኖም የበረዶ ክምሩ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሲቀልጥ የተዳፈነው ተነቃቅቶ ፍንዳታው ሊጨምር እንደሚችል አረጋግጧል::
የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መጨመር ተመልሶ በዓየር ንብረት ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ማለትም የሙቀት መጨመርን አባባሽ መሆኑ ነው የተጠቆመው- በጥናቱ::
ተመራማሪዎች አንታርክቲክን በመሳሰሉ ግግር በረዶ ባለባቸው ቀጣናዎች በርካታ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ነው ያረጋገጡት:: የተዳፈኑት ንቁ ሆነው ሲፈነዱ በጥቅሉ በዓየር ንብረት ላይ እጅግ አሳሳቢ ጫና እንደሚያሳድሩም ነው ያሳሰቡት::
ተመራማሪዎቹ የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎች አሉ ተብለው በሚገመቱበት ቀጣናዎች ክትትል ጀምረዋል- ለአብነት በቺሊ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ ኒውዝላንድ እና ሩሲያ በመሳሰሉትም ላይ ትኩረት አድርገዋል::
የተጠቀሰውን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ስጋት በምርምር እና ውጤት ትንበያ ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ከአሜሪካ የዊስኮንስ ማዲሰን ተመራማሪዎች በቺሊ ስድስት ያንቀላፉ ወይም የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎችን በቅርበት መርምረዋል፤ ገምግመዋል:: በውጤቱም እሳተ ገሞራዎቹ ከላይኛው የመሬት ገጽ ከ10 እስከ 15 ኪሎ ሜትር ጥልቀት የቀለጠ ዓለት ታምቆ የተዳፈኑ መሆናቸውን አረጋግጠዋል::በቅድመ ልደት በበረዶ ዘመን ከበርካታ ሺህ ዓመታት በፊት ይህን መሰል ሁነት ሳይከሰት እንዳልቀረም ነው መላምታቸውን ያስቀመጡት::
በማጠቃለያነት አሁን ላይ ያለው የግግር በረዶ መቅለጥ የተዳፈኑ እሳተ ገሞራዎችን በየቀጣናው አንቅቶ የሚፈነዱ ከሆነ ተፅእኖዋቸው ተባብሶ አሁን ያለው የዓየር ንብረት ለውጥ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል ነው ያሳሰቡት – ተመራማሪዎቹ::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም