በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ 591/2000 ላይ ማንኛውም ግለሰብ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ እንዲሁም ድርጅቶች ደግሞ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በላይ በእጃቸው ማስቀመጥ እንደማይችሉ አስፍሯል፡፡ አዋጁን ጥሶ የተገኘ አካልም በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተይዞ እስር እና የገንዘብ ቅጣት እንደሚከተለው መረጃው አመላክቷል፡፡
በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉደዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ስንታየሁ ቸኮል ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ገንዘብ ከቦታ ቦታ ማዘዋወር ማለት ነው፡፡ ዝውውሩ ደግሞ በሁለት ዐቢይ መንገዶች ይፈፀማል፡፡ እነዚህም አንድ ሰው በሕግ ከተወሰነው የገንዘብ መጠን በላይ እና በሀሰት የተዘጋጀ ገንዘብ ይዞ ሲዘዋወር ሲገኝ ነው፡፡
እንደ ዐቃቤ ሕጉ ማብራሪያ ሀሰተኛ ገንዘብ በሦስት መንገዶች ይገለጻል፡፡ እነዚህም ከብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ውጭ የታተመ ገንዘብ፣ ከሕጋዊ ገንዘብ ጋር ተመሳስሎ የተሠራ ገንዘብ እና በንግዱ ዓለም ውስጥ እንደ ገንዘብ የሚቆጠሩ ሰነዶችን በሀሰት ማዘጋጀት ናቸው፡፡
በሕግ ከተፈቀደው በላይ ገንዘብ ማዘዋወር የሚለውን የሕግ ባለሙያው ሲያብራሩ፤ “ገንዘቡ ሕጋዊ ነው፡፡ ነገር ግን ‘ከዚህ በላይ ገንዘብ መያዝ አይቻልም‘ ተብሎ ክልከላ ከተደረገበት በላይ ይዞ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ነው፡፡ ይህን እንቅስቃሴም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቁጥር 591/2000 ያወጣው መቋቋሚያ ሰነድ በአዋጅ ገድቦታል፡፡
የገንዘብ ዝውውርን የሚገድበው መመሪያ ለምን አስፈለገ? ተብሎ ዐቃቤ ሕጉ ለተነሳላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል፤ ገንዘብ ሲታተም ብዙ መዋዕለ ነዋይ ይፈሳል፡፡ እናም በመመሪያው ከተቀመጠው በላይ ገንዘብ በግለሰቦች እጅ ሲያዝ ደግሞ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ይህን ተከትሎም ከተፈቀደው ገንዘብ በላይ ይዞ የተገኘ ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡
ሌላው ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ የማተም ሥልጣኑን ተጠቅሞ ራሱ እንዲሁም ለሌሎች ድርጅቶች ዕውቅና ሰጥቶ ሊያሳትም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ዕውቅና የተሰጣቸው ድርጅቶች ከብሔራዊ ባንክ ዕውቀና እና ፈቃድ ውጭ አትመው ከተገኙ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጸሙ ተብለው እንደ ሚጠየቁም አቶ ስንታየሁ ቸኮል ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ተመሳሳሎ የተሠራ ሀሰተኛ ገንዘብ /ፎርጅድ/ ሕጋዊ አይደለም፡፡ ይህን ይዞ መገኘትም ሕገ ወጥ ድርጊት በመሆኑ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡
እንደ ገንዘብ የሚቆጠሩ ሰነዶችን /ሀዋላ፣ ቼክ …/ የመሳሰሉ በሀሰት አዘጋጅቶ ለመጠቀም ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብም ባንኩ ያወጣውን ክልከላ መተላለፍ በመሆኑ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ለአብነት በመቶ ሺህ ብር ውል ላይ የግዴታ ወረቀት፣ የዋስትና ወረቀት ወይም ቼክ ሆኖ እያለ መጠኑን ለመጨመር ወይም ለማሳነስ ሲባል በሀሰት ተዘጋጅቶ የቀረበ ሰነድ እንደ ሀሰተኛ የንዘብ ዝውውር እንደሚቆጠር ዐቃቤ ሕጉ አስገንዝበዋል፡፡
ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር የሚያመጣውን ተፅዕኖ ባለሙያው ሲያብራሩ ለሀገር ኢኮኖሚ መሰረት የሆነው ገንዘብ በሕገ ወጥ መንገድ ከተበራከተ ገበያው ላይ አለመረጋጋትን በማምጣት በሀገር እና በሕዝብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ኢኮኖሚን በመጉዳት ሀገር እንዳይረጋጋ ያደረጋል፡፡ ያልተረጋጋ ኢካኖሚ ያለው ሀገር ደግሞ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል፡፡ ይህን ተከትሎም የኑሮ ውድነት ይባባሳል፡፡
በሀገር ዕደገት እና በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ምስቅልቅል የሚፈጥረውን ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል፤ በድርጊቱ የሀገር ውስጥ ገንዘብ በማዘዋወር የተሳተፉ ግለሰቦችን ለጠቆመ ከተያዘው ገንዘብ 15 በመቶ፣ የውጭ ሀገር ገንዘብ ዝውውር ለሚጠቁሙ 15 በመቶ፣ ሕገ ወጥ ሐዋላን ለሚጠቁሙ 25 ሺህ ብር ወሮታ እንደሚከፍል በመግለጫ ማሳወቁን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡
ለሀገር ዕድገት ማነቆ፣ ለኢኮኖሚ ድቀት ዋና ምክንያት እና የዜጎችን ኑሮ የሚያመሰቃቅለው ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር የተጠያቂዎች ጉዳይ በሁለት መልኩ ይታያል፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት ወይም ብሔራዊ ባንክ ከፈቀደው በላይ ይዘው የተገኙ ሰዎች እና ሀሰተኛ ገንዘብን በተመለከተ ደግሞ የመጀመሪያ አዘጋጆች /የሚያትሙ/ ናቸው፡፡ ቀጥሎ ሀሰተኛ ገንዘብ ይዘው ሲያዘዋውሩ፣ ለግብይት ሲጠቀሙ የተገኙ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ሰነዶችን በተመለከተም ያዘጋጁ እና የተጠቀሙ ተጠያቂ ናቸው፡፡
የቅጣት ወሰኑም ከተፈቀደው በላይ ይዘው የተገኙ ሰዎች ገንዘቡ ከመወረሱ በተጨማሪ እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣሉ፡፡ ሀሰተኛ ገንዘብ ያዘጋጁ /ያተሙ/፣ ያዘዋወሩ፣ ይዘው የተገኙ ሰዎች ደግሞ ሰነዶችን ይወረሳሉ፡፡ ከአምስት እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራትም ይወሰንባቸዋል፡፡
ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለማስቆም ሁሉም አካላት እንደየ ድርሻቸው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም ኅብረተሰቡ ከሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መራቅ እና የሚገበያይበትን ብር ሀሰተኛ መሆኑን እና አለመሆኑን በጥንቃቄ ማየት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ እውነተኛ እና ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በተመለከተ የሚመለለከተው አካል ግንዛቤ መፍጠር ይገባዋል፡፡
ገንዘብ የሚያትሙ ድርጅቶችም ሀሰተኛ ገንዘብ ለሀገር ዕድገት፣ ለኢኮኖሚ ውድቀት፣ ለገበያ አለመረጋጋት እና ለኑሮ ውድነት መንስኤ መሆኑን በመረዳት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡
እንደ ዐቃቤ ሕጉ ገለፃ ሕግን መንግሥት ብቻውን ማስከበር አይችልም፤ ወንጀሉ ተፈጽሞ ሲገኝ ማኅበረሰቡ ለመንግሥት አካላት ጥቆማ መስጠት እና ምሥክር ሆኖ በመቅረብ የድርሻውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
የመንግሥት ተቋማት /በዋናነት ፖሊስ/ ምርመራ ሲያደርጉ ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ የተገኘውን ብቻ ሳይሆን እስከ አታሚው ድረስ በመውረድ ችግሩን ከምንጩ ለማጣራት ምርመራ ማድረግ አለባቸው፡፡ ዐቃቤ ሕግም አንዱ ሲቀጣ ሌላው እንዲማር ተገቢውን ክስ መስርቶ ክርክር በማድረግ የተያዘው ግለሰብ የማያዳግም ቅጣት እንዲያገኝ ማድግ እንደሚገባ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
ዳኞችም በተመሳሳይ ሁኔታ በአጥፊዎች ላይ ከአድሎ የፀዳ ውሳኔ በማሳለፍ፣ ብዙኃን መገናኛዎች ሕብረተሰቡ ስለ ሀሰተኛ ገንዘብ ግንዛቤ ሥስለሌለው የባንክ ባለሙያዎችን ጋብዞ ግንዛቤ በመፍጠር ችግሩን ለመቀነስ ይቻላል፡፡ ማህበረሰቡም የብር ኖቶችን ከተጠራጠረ ለፖሊስ፣ ግንዛቤ ላላቸው ሰዎች በማሳየት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
(ሙሉ ዓብይ)
በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም