የህዳር 2ቀን 2017 ዓ.ም
እቴጌ ምንትዋብ በዙፋን ስሟ ብርሃን ሞገስ በ1698 ዓ.ም ከአባቷ ደጃዝማች መንበር እና ከእናቷ ልዕልት እንኮይ በቋራ፣ ጎንደር ተወለዱ። እናታቸው ልዕልት እንኮይ ከዐፄ ሚናስ ዘር እንደሚወለዱ ይጠቀሳል። ምንትዋብ በ18ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያ ላይ ብዙ አሻራ ትተው ያለፉ ንቁ፣ ሃይለኛና ተራማጅ መሪ ነበሩ። ከባለቤታቸው ከዐፄ በካፋ ዘመን ጀምሮ እስከ ልጃቸው ዳግማዊ ዐፄ ኢያሱ እና የልጅ ልጃቸው ዐፄ እዮአስ ዘመን ድረስ ለ40 ዓመታት በሀገሪቱ እኩል መሪ ነበሩ። እቴጌ ምንትዋብ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የህንጻዎች ግንባታ እና የቤተክርስቲያን ድርሰት እንዲሁም ስነ ጥበብ እድገት ታይቷል። በፋሲል ግቢ የመጨረሻውን ግንብ ያስገነቡትም ምንትዋብ ነበሩ።
እቴጌ ምንትዋብ ከዐፄ በካፋ ጋር የተገናኙት በተለየ አጋጣሚ ነበር። የዐፄ እያሱ ልጅ በካፋ በልጅነታቸው በጠባይ እና በአስተዋይነታቸው የሚወደዱ ነበሩ። በዚህ የተነሳም አባታቸው ዐፄ እያሱ ካጠገባቸው ሳይለዩ በሄዱበት ሁሉ ይዘዋቸው ይጓዙ ነበር፤ ወደፊት የመንገሥ አቅም እንዳላቸውም ብዙዎች ያወሩላቸው ጀመር። አባታቸው ከእናሪያ ሲመለሱ ብላቴናውን በካፋ ወደ ጎንደር አምጥተው የቤተመንግሥት ስርዓት እያስተማሯቸው ሳለ የአባታቸው ልጅ ራስ ተክለሃይማኖት በመርዝ ሊያስገድላቸው እንደተማከረ ሰምተው ከአባታቸው ጋር ሳይሰናበቱ ወደ ማህበረ ስላሴ እንደተሰደዱ መሪ ራስ አማን በላይ ‘የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ’ በተሰኘ መፅሀፋቸው ላይ ያስረዳሉ።
መሪ ራስ አማን አክለው እንደፃፉት በማህበረ ሥላሴ ገዳም ሳሉም አባታቸው እያስፈለጓቸው እንደሆነ ሰሙ እና በሱዳን አድርገው ወደ ግብፅ መሄድ ሲጅምሩ ወባ ታመው ወደቁ። በዚህ ጊዜ የቋራው ባላባት ቀኛዝማች እሸቴ ጌታ ልጅ በካፋን ታመው ሲያገኟቸው ወስደው በቤታቸው አስተኟቸው። ከዚያም ከመልካቸው ማማር የተነሳ ልጃቸውን አጋብቶ ለማስቀመጥ ስለፈለጉ፤ ከልጆቻቸው ታላቂቱን እና ቆንጆዋን ምንትዋብን እንድታስታምማቸው እና እንድታገለግላቸው አደረጉ። “ወጣቷ ምንትዋብ ከመጠን በላይ ቆንጆ እና ተግባቢ” የነበሩ ሲሆን ታማሚውን ንጉሥ በካፋን ተንክባክበው በደንብ እስኪሻላቸው አስታመሟቸው። ከዚያ በኋላም ሁለቱ በፍቅር ቀጠሉ። በካፋ ዙፋን እንደወጡ በ1716 ዓ.ም ድል ባለ ሰርግ ተጋብተው በካፋ ራሳቸው ለምንትዋብ የንግሥትነት ዘውድ ጫኑላቸው። ሲመተ በዓላቸውም በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ እንዲውል አድርገው ነበር። እቴጌ ምንትዋብ በ1717 ዓ.ም ዳግማዊ ዐፄ ኢያሱን ወለዱ።
የእንደራሴነት ዘመኗ
ተክለ ፃድቅ መኩሪያ እንደፃፉት እቴጌ ምንትዋብ እንደ እቴጌ እሌኒ እና እንደ እቴጌ ጣይቱ በቤተመንግሥት እና በሕዝቡ ዘንድ የተከበሩ እና የተፈሩ ነበሩ። በባለቤታቸው በዐፄ በካፋ ዘመን፣ በልጃቸው በዳግማዊ እያሱ ዘመን እና በልጅ ልጃቸው እዮአስ ዘመን ከዚያም እስከ ተፍፃሜተ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ ዘመን ድረስ በሙሉ ስልጣን ያዝዙ ነበር። ከፍተኛ ውሳኔዎችን ያሳልፉ ነበር። ሿሚም ሻሪም እየሆኑ እንደ ሀገር መሪ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወቱ ነበር። በተለይ ከዐፄ በካፋ መሞት በኋላ የእቴጌ ምንትዋብ ስልጣን እና ሚና ከፍ ያለ ነበር።
አባ ጋስፓረኒ፣ “የጥንት ታሪክ” በሚል መፅሐፋቸው እንደፃፉት ዐፄ በካፋ በ1722 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ ልጃቸው ዳግማዊ እያሱ መንግሥታቸውን ወረሱ። ዐፄ ብርሃን ስገድ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ። ምንትዋብም እጅግ አዋቂ እና ብልህ ሴት ስለነበሩ በሴትነታቸው፣ በልጃቸውም ሕፃን መሆን ምክንያት በልጇ መንግሥት ስንፍና እንዳይገባበት ከቋራ ወንድሞቻቸውን አምጥተው የቤተመንግሥት ስልጣን ሰጡ። ከወንድሞቿ መምጣት በኋላ እርሷና ዘመዶቿ ሆነው የሰባት ዓመት ልጇን ኢያሱን ለማንገሥ ቻሉ። ከሁለት ወር በኋላ ታህሳስ 15 ቀን 1722 ዓ.ም ልጇ እያሱ ህፃን ስለነበር እናቱ ምንትዋብ ዘውድ በመጫን በንግሥትነት ሥልጣን እንደራሴነታቸውን አሳወጁ።
እቴጌይቱ ልጃቸው ለአቅመ አዳም እስኪደርስ ድረስ በዐፄ እያሱ ስም መንግሥቱን በሙሉ ስልጣን ሀገር ይመሩ ጀመር። ስልጣኑን የተቆጣጠሩት ዘመዶቻቸው ቋረኞቹ የብላቴናውን እያሱን እየደገፉ እና እየረዱ ለእቴጌይቱም ምክር እየሰጡ ሕፃኑ እስኪያድግ ድረስ መንግሥቱን ፀጥ አድርገው ይዘውለት ቆዩ። የመንግሥት ዋና ዋና የስልጣን ቦታዎችን የያዙት የእቴጌይቱ ዘመዶች በመሆኑ ማንም ሳይደፍራቸው በልጃቸው ዙፋን ላይ ለዓመታት ገዝተዋል።
ከየጁ ባላባቶች ጋር መተሳሰር
በዘመኑ ስልጣንን ለማቆየት በጋብቻ የመተሳሰር ልማድ የተለመደ ስለነበር እቴጌይቱ በመንግሥታቸው የቋረኞች የበላይነት ተቃውሞ እያስነሳባቸው ስለነበር ስልጣናቸው እንዳይናጋ በማሰብ፤ የጁዎችን ለመያዝ ሲሉ ልጃቸውን ዐፄ ኢያሱን ለየጁ ባላባት ልጅ ለሆነችው ወለተ ቤርሳቤህ ዳሩት። ጋብቻው የታሰበውን ግብ ስላልመታ ተቃውሞ አገኘው። በመካከሉ ልክ እንደ ምንትዋብ ሁሉ ወለተ ቤርሳቤህም ቀስ በቀስ የየጁ ዘመዶቿን በቤተመንግሥት ትሰገስግ ነበር። በዚህ ሁኔታ በየጁዎች እና በቋራዎች መካከል ውስጥ ውስጡን ፉክክር ተጀመረ። በዚህ መካከል ዳግማዊ ዐፄ እያሱ እድሜው ስለደረሰ ስልጣኑን ከእናቱ በመረከብ ራሱን ችሎ ማስተዳደር ከጀመረ ጥቂት ዓመታት በኋላ በ1747 ዓ.ም ሞተ። ይሁን እንጂ ከወለተ ቤርሳቤህም የወለደው ልጁ እዮአስ በአባቱ ዙፋን ነገሠ። አሁንም የልጅ ልጃቸው እዮአስ ሕፃን ስለነበር እቴጌ ምንትዋብ እንደገና እንደራሴነታቸውን አፅንተው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብቅ አሉ። ።
በርግጥ የእቴጌነት ስልጣን የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር ጠቁሞ ማለፍ ይገባል። ልጅ እዮአስ እንደነገሠ እናቱ ወለተ ቤርሳቤህ ልክ ምንትዋብ የእያሱ ሞግዚት እቴጌ እንደነበረች ሁሉ እርሷ በተራዋ ለእዮአስ እንደራሴነት(እቴጌነት) ይገባኛል በማለቷ በሁለቱ መካከል ጥል ተነሳ። በዚህ ወቅት ዐፄ እዮአስ አያቱን ምንትዋብን ከመደገፍ ይልቅ የእናቱ ውቢት እና የየጁዎች ወገን ሆነ። ውዝግቡ በ1759 ዓ.ም ወደ የርስ በርስ ጦርነት አመራ። በዚህ ጦርነት የየጁም ሆነ የቋራ ክፍሎች ሃይላቸው ስለተዳከመ ከትግሬ ገዢ ራስ ሥዑል ሚካኤል እገዛ ፈለጉ። ሥዑል ሚካኤል መጀመሪያ የንጉሡ እና የየጁዎች ደጋፊ ቢሆንም በምንትዋብ የዲፖሎማሲ ስራ ኋላ የርሷ አጋር በመሆን አቋሙን ቀየረ። በመጨረሻም 1769 ዓ.ም ሥዑል ሚካኤል፤ ዐፄ እዮአስ የጁዎችን በጦርነት ደግፏል በሚል ክስ እንዲገደል አደረገ። የንጉሡ መገደል በሀገሪቱ ሲሰራበት የነበረውን ትውፊት የቀየረ እንግዳ ስራ ነበር። እንግዲህ እስከ ብዙ ዘመን ድረስ የነበረውን የንጉሥ ክብር የነካ ስለነበር የሚፈራ አንድ ሃይል በመታጣቱ ሀገሪቱ ወደ ዘመነ መሳፍንት ጦርነት ገባች።
የእቴጌዋ ትሩፋቶች
በልጃቸው ዳግማዊ እያሱ እና በልጅ ልጃቸው እዩአስ የአስተዳደር ዘመናት ለ40 ዓመት ያህል ሙሉ የመሪነትን ሥልጣን ይዘው ኢትዮጵያን መምራት ችለዋል። ከዚህም በላይ እቴጌ ምንትዋብ በርካታ ስራዎችን ማከናወን ችለዋል። ከእነዚህም መካከል በርካታ ዘመናዊ ሕንፃዎችን አሰርተዋል። በፋሲል ግቢ ውስጥ የመጨረሻውን ግንብ ያስገነቡ እርሳቸው ነበሩ። ለዚህም አንዱ ማሳያ እቴጌ ምንትዋብ በጎንደር ከተማ ውስጥ በደብረ ፀሐይ ወይም ቁስቋም ያሰሯቸው ህንጻዎች ናቸው።
የስኮትላንድ ተጓዥ ጄምስ ብሩስ በቁስቋም ስለተሰሩት ህንጻወች ሲጽፍ ባለ ሦስት ፎቅ የሆነ ቤተመንግሥት፣ ክብ የሆነ ቤተክርስቲያን እና ብዙ የተለያዩ የሰራተኞችና ዘበኞች ቤቶች እንዲሁም ግብዣ ቤት በአንድ ማይል ዙርያ በታጠረ ግቢ ይኖር እንደነበር አስፍሯል። እነዚህን ቤተመንግሥቶችና ቤተክርስቲያኖች ከ1723 ዓ.ም ጀምሮ በማሰራት በ1732 ዓ.ም ነበር ያስመረቋቸው። በግቢው ውስጥ የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ደብረ ፀሐይ ማርያም ይባላል። በጄምስ ብሩስ ግምት ኢትዮጵያ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሃብታም የነበረና ብዙ ምርጥ ምስላትንና በወርቅና በብር የተሰሩ የቤተክርስቲያን መገልገያ ዕቃዎች የተመላ ነበር። የተገነባውም በአናጢዎች መሪ በጅሮንድ ኢሳያስ እና አዛዥ ማሞ፣ አዛዥ ህርያቆሳና አዛዥ ናቡተ መሪነት ነበር። ቤተክርስቲያኑ በቀይ ሃር አሸብርቆ በዙሪያው 380 መስታዎቶች ተተክለውለት ብርቅርቅታው ጎንደር ከተማ ድረስ ይታይ ነበር። ነገር ግን ቤተክርስቲያኑ እና ሌሎች በግቢው የነበሩ ህንጻዎች በሱዳን ወራሪ መሃዲስቶች በ1880 ተቃጠሉ። አሁን በጊቢው የሚገኘው ቤተክርስቲያን በዚህ ፍርስራሽ ላይ የተሰራ ነው።
ምንትዋብ እጅግ መንፈሳዊ ነበሩ። ለዚህ ሲሉም ብዙ መንፈሳዊ ስራዎችን በገንዘብ ይደጉሙ ነበር። ብዙ መጻህፍት በዚህ ዘመን ተጽፈዋል፤ ከአረብኛም ተተርጉመው ወደ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተሰራጩት ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም። እቴጌይቱ ለስነጥበብ ከነበራቸው ትኩረትና ከሚያደርጉት ድጎማ የተነሳ በዚሁ ዘመን በድንገት የተፈጠረ ልዩ አይነት የሥነ-ስዕል ስራ ተጀመሮ ነበር። ይህ እንግዲህ በውጭ ሃገር አጥኝዎች ዘንድ ሁለተኛው የጎንደር የስነ-ስዕል ስልት የሚባለው ነው። በአዲሱ ስልት ሥነ ስዕል የቀጥተኛ መስመሮች ጥንቅር መሆኑ ቀርቶ በጎባጣ መስመሮች ጥንቅር የሚሰራ እና በህብረ ቀለማት የደመቀ ሆነ። እውነተኛ ሰዎች የሚመስሉ ምስሎችም መታየት ጀመሩ። በዚህ ሁኔታ በጣና ሃይቅ እቴጌይቱ ባስገነቧቸው ናርጋ ሥላሴ ቤተክርስቲያን እና በቁስቋሙ ደብረፀሐይ ማርያም ግድግዳዎች ላይ አይን የሚስቡ ምስሎች ተሰርተው ነበር። ሆኖም ብዙዎቹ በመሃዲስት ሱዳኖች ሲወድሙ ንግሥቲቱ በራሳቸው ክትትል ያስደረሱት “መጽሐፈ ራዕይ” የተሰኘው በምስል ያሸበረቀ መጽሓፍ አሁን እንግሊዝ አገር ስለሚገኝ የአዲሱ የሥነ ሥዕል ስርዓት ቅርስ ከጥፋት ድኖ አሁን ቅርሱን መዝግቦ እንደሚገኝ ተክለ ፃዲቅ ፅፈዋል።
ምንትዋብ ምንም እንኳ የየጁዎች ዋና ተቃዋሚ የነበሩ ቢሆንም፤ የልጅ ልጃቸውን መገደል እና የሥዑል ሚካኤልን መግነን በመጥላት 1762 ዓ.ም ላይ ወደ ጎጃም ሸሽተው ከሄዱ በኋላ በ1763 ዓ.ም ተመልሰው ጎንደር ቁስቋም ውስጥ ባሰሩት ቤተ መንግሥት ኑሮ ጀመሩ። ታላቋ ንግሥት ምንትዋብ ግንቦት 26 ቀን 1765 ዓ.ም አርፈዋል፤ አበቃን።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም