“እናንብብ!” የባሕር ዳሩ ክበብ ጥሪ

0
124

“ሰውን ሰው ያሰኘው ስራ ነው” ይላል የኮሚኒዝም ሥርዓት አቀንቃኙ ቭላድሚር ሌኒን:: ሥራ በእውቀት እና ጥበብ ሲደገፍ ደግሞ እድገት፣ ብልፅግና እና ስልጣኔን ያጐናፅፋል፤ የሰው ልጆችን ህይወትም ምቹ እና ጣፋጭ ያደርጋል:: ለመሆኑ ዕውቀት እና ጥበብ ከወዴት ይቀዳል? ከትምህርት እና ከንባብ አይደለምን?! ምዕራባውያኑ ከት/ቤት፣ ቤተመፃህፍት እና ከቤታቸው አልፈው በየመዝናኛው እና በጉዞ ላይ እያሉ ጭምር መፃህፍትን የማንበብ ባህል የገነቡበት ምስጢርም ይኸው ነው፤ እውቀት እና ጥበብን ፍለጋ::

ከዚህ አኳያ በእኛ ሀገር ያለው የንባብ ባህል ግን ደካማ እንደሆነ ለመጥቀስ ማስረጃ ካላቀረብክ የሚያስብል እንዳልሆነ ይሰማናል:: ለዚህም ነው “ትውልዱ ካለማንበብ እንዳይመክን ንባብን ባህሉ እንዲያደርግ መስራት አለብን” በሚል አቋም ቁርጠኛ የሆኑ በባሕር ዳር ከተማ የሚኖሩ ጥቂት ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎች /ፀሀፍት እና የኪነ ጥበብ ሰዎች “እናንብብ” የተሰኘ የንባብ ክበብ ያቋቋሙት::

ክበቡ ተቋቁሞ እውቅና በተሰጠው በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥም የመጀመሪያውን የሥነፅሁፍ ምሽት ሰሞኑን አካሂዷል- በሙሉአለም  የባህል ማእከል::

የክበቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው ታዳሚያን የተገኙበት ይኸው ዝግጅት ዳረጐት የኪነጥበብ ማህበር ባቀረባቸው ልዩ ልዩ ኪነጥበባዊ ክዋኔዎች ታጅቦ እና ደምቆ ነው የተካሄደው::

በዕለቱ የእናንንብ ክበብ ሰብሳቢ ደራሲ ጥላሁን ፋንታ “ሰውን  ወደ ምሉዕነት ከፍታ የሚያደርሱት ንባብ እና መጻሕፍት መሆናቸውን ጠቅሶ የራሷ ፊደል ያላት አገር ዜጐች ሆነን ሳለ የንባብ ባሕላችን ዝቅተኛ መሆን ያስቆጨን ጥቂት ጋዜጠኞች እና ፀሀፍት የንባብ ክበብ አቋቁመናል፤ እናም “ኑ”ና እናንብብ! ሲል ጥሪውን አቅርቧል:: ይህንኑ አላማ በዘላቂነት ከግብ ለማድረስም ቤተመፃሕፍትን እስከ ማስፋፋት ድረስ እንደሚሰሩ ተናግሯል::

ለመሆኑ ከንባብ ምን ይገኛል? የእናንብብ ክበብን ጥሪ ለመቀበል በቅድሚያ የንባብን ፋይዳ ማጤን ግድ ይላልና እነሆ፡-

ማርክሃም የተሰኘ የህዝብ ቤተመፃሕፍት በድረገፁ እንዳሰፈረው ንባብ በየትኛውም ዕድሜ ለሚገኙ ሰዎች 10 ያህል ጥቅሞችን ያበረክታል::

የመጀመሪያው የንባብ ጥቅም አእምሮን ንቁ እና ስልጡን ማድረጉ ነው:: አንጐል ጤናማ እና ጠንካራ ሆኖ እንዲቆም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያስፈልገዋል:: የአእምሮ ማነቃቂያ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት እንደ እንቆቅልሽ እና ቼዝ እንደመጫዎት ሁሉ በንባብ እውቀትም አእምሮን ለማነቃቃት ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል::

የመርሳት በሽታ /አልዛይመር/ እንዳይባባስ በመከላከል ወይም በማዘግየት የማስታወስ ችሎታንም ያሻሽላል – ንባብ::

ሁለተኛው የንባብ ጥቅም ጭንቀትን መቀነሱ ነው:: ዕለት ከዕለት ሊያጋጥሙን ከሚችሉ በርካታ ችግሮች እንድንርቅ የማድረግ ሀይል አለው:: በተለይ ማራኪ ፅሁፎችን ሲያነቡ ውጥረቶች ተወግደው ዘና እንዲሉ ያደርጋል፤ ያኔ የልብ ምት እና የደም ግፊትም ይቀንሳል፤ ጭንቀትዎንም ይረሳሉ ይለናል::

ዕውቀትን ማስገኘት ደግሞ 3ኛው የንባብ ትሩፋት ነው:: የምናነበው ነገር ሁሉ አእምሮአችንን በአዲስ መረጃ ይሞላል:: በቂ መረጃ እና ዕውቀት ያለው ሰው ደግሞ የትኛውንም ፈተና የመቋቋም ብቃት ይኖረዋል:: “ማንም ሰው ሊወስድብዎ የማይችል የእርስዎ እውነተኛ ሀብት እውቀትዎ ነው” የሚለውን ብሂል ልብ ይበሉና ያንኑ ዕውቀት ለመገብየት ንባብን ምርጫዎ ያድርጉ!

አራተኛው የንባብ ጥቅም የቃላት ዕውቀትን፣ የመግባባት ችሎታን እና የአፃፃፍ ስልቶችን ማስተማሩ ነው:: በአነበብን ቁጥር አዳዲስ ቃላትን እንማራለን:: በዚህም አንደበት ርቱዕ እንሆናለን፤ በራስ መተማመንን እናዳብራለን፤ የመግባባት ችሎታችንም ያድጋል:: የተለያዩ የአፃፃፍ ስለቶችን በመረዳት የፅሑፍ ክህሎታችን ይሻሻላል::

በእናንብ ክበብ የሥነ ፅሁፍ ምሽት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባ/ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር አንተነህ አወቀም በዚህ ጉዳይ ላይ ተሞክሯቸውን ጠቅሰው እንዲህ ነበር ያሉት፡- “አንዳንድ ጀማሪ ፀሐፍት ፅሑፎቻቸውን እንዳይላቸው ሲሰጡኝ ካስተዋልኳቸው ችግሮች አንዱ የአፃፃፍ ቴክኒክ /ስልት/ጉድለት ነው፤ ይሄ ደግሞ ካለማንበብ የሚመጣ ነው” በማለት ከንባብ አዳዲስ የአፃፃፍ ስልቶችን መማር እንደሚቻል አስገንዝበዋል::

ክራዉሽ አካዳሚ ዶት ዩኬ እንደሚለው ደግሞ መፃሕፍትን ማንበብ አዲስ ቋንቋ ለመማርም ይጠቅማል! ምክንያቱን ሲያስረዳም የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆኑ ተናጋሪዎች በአውድ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ቃላትን ስለሚያውቁ የራሳቸውን የንግግር እና የፅሑፍ ቅልጥፍና ያሻሽልላቸዋል ይላል::

ተቋማቱ ያስቀመጡት አምስተኛው የንባብ ጥቅም ርህራሄ ነው፤ ርህራሄ የሌላውን ስሜት የመረዳት እና የመጋራት ችሎታ ተብሎም ይጠራል::

ንባብ ያልተከፋፈለ ትኩረትዎን ከሚጠይቁ ጥቂት ተግባራት አንዱ በመሆኑ በትኩረት ባነበቡ ቁጥር ሀሳብን አሰባስቦ የመመሰጥ ችሎታዎን ያሻሽላል:: ይህ ደግሞ ስድስተኛው የንባብ ፋይዳ ነው:: ንባብ የመልካም ገፀባህሪያትን ባህሪ እንድንወርስ፣ በችግሮች ተስፋ እንዳንቆርጥ እና ለአዎንታዊ ተግባራት እንድንነሳሳ የማድረግ ጥቅሙም በሰባተኛነት ተጠቅሷል::

በቤተመፃህፍት እየተገኙ የሚፈልጓቸውን አይነት መፃሕፍት በነፃ እያነበቡ የሚማሩበት ነፃ መዝናኛ መሆኑ፣ ከልጆች ፊት በማንበብ መልካም ምሳሌነትንና አርዓያነትን የሚያስተላልፉበት መሆኑ እና ‘‘ለሽ” ለሚሉበት ሰላማዊ እንቅልፍ የሚመራ መሆኑም ቀሪዎቹ የንባብ ትሩፋቶች ተብለዋል::

ይህን ያህል ጥቅም የሚያስገኘው ንባብ በእኛ ዘንድ ችላ መባሉ ነው እንግዲህ ለባሕርዳሩ የእናንብብ ክበብ መመስረት ዋነኛው መነሻ:: እናም የክበቡ አባላትና ታዳሚዎቻቸው “የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍለን አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ተግተን እንሠራለን!” ሲሉ በጋራ ቃል ገብተው ነው የተለያዩት:: ህልማቸው እውን ይሆን ዘንድ ግን ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፤ በእለቱ ያነጋገርናቸው የማህበሩ አባላት ፍላጐትም ይኼው ነው:: ትውልድን በእውቀት ለማነፅ የዩኒቪርሲቲዎችን፣ የመገናኛ ብዙሃንን፣ የመንግሥታዊ እና የግል ተቋማትን እገዛ ጭምር ይጠይቃልና “ትኩረት ለንባብ” እንላለን::

 

(ጌታቸው ፈንቴ)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here