“እኔም የሚያዳምጡን አስተዋይ መሪዎች እንዲኖሩን አጥብቄ እመኛለሁ”

0
211

የዚህ እትም እንግዳችን  እድገቱ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 06 ወይም በተለምዶ እማ ማርያም ሰፈር ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ ደግሞ ቀበሌ 07 ኖሯል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ ዲፕሎማ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ደግሞ በቲያትሪካል አርት  በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል::

እንግዳችን ከ20 ዓመታት በፊት የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል በክልሉ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ሲቀጥር በውድድሩ በማለፍ ባህል ማዕከሉን ተቀላቅሏል:: በአሁነ ጊዜም በቲያትር ባለሙያነት  እያገለገለ ይገኛል::

እንግዳችን ከሠራቸው የሙሉ ሰዓት ቲያትሮች መካከል የመጨረሻው መንገደኛ፣ አራቱ የደም ጥሪዎች፣ መረብ ፣ውርስ፣ ርጉሙ  ሃዋርያ፣ የአሜሪካ ዲቪ፣  ትውፊታዊ የሆነው ጉማ ፣የአለቃ ገብረሃና ታሪክ የሆነው አራት ዐይና … እና በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ የማያስታውሳቸውን በርካታ የመድረክ የሙሉ ጊዜ ቲያትሮችን ሠርቷል::

ከተመልካች ጋር ቤተሰብ ያደርጋሉ በሚባሉት ፊልም እና ተከታታይ ድራማዎች እንደ ቲያትሩ በብዛት ባይሳተፍም እስካሁን አሜን፣ ገዳይ ሲያረፋፍድ ፣ ፍትህ አዳኝ፣ ሰው ለሰው ፣ ፍለጋ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዲኤስ ቲቪ እየታየ የሚገኘው የቄሳር ዲናሮች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱለት ሥራዎቹ ናቸው:: በዚህ ሳምንት የበኲር እንግዳችን ሁለ ገቡ የቲያትር  ባለሙያው ተዋናይ መላኩ ታደሰ ነው::ከተዋናይ መላኩ ታደሰ ጋር  ያደረግነውን ቆይታ በዚህ መልኩ አሰናድተነዋል፤ መልካም ንባብ!

ወደ ኪነ ጥበቡ  ዓለም እንዴት ገባህ?

የጥበብ ጅማሬዬ እና የመጀመሪያ መድረኬ ገና በአፍላ እድሜ ክልል እያለሁ በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት የሠራሁት ቲያትር ነበር፤  በቀጣይ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታዬ (ጣና ሃይቅ ትምህርት ቤት) በቲያትር ክበብ ውስጥ ቲያትሮችን ሠርቻለሁ። ንጋት የተባለውን የቲያትር ክበብ ከተቀላቀልኩ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ደግሞ  እኔ እና  ጓደኞቼ የራሳችንን አልፋ የቲያትር ክበብን አቋቁመናል:: በዚህም ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እያለሁ  ከ20 ዓመታት በፊት መሆኑ ነው … የሙሉዓለም ባህል ማዕከል በክልሉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ሲቀጥር ተወዳድሬ   የቲያትር ባለሙያ በመሆን ተቀጥሬያለሁ። አሁንም በዛው ማዕከል እያገለገልኩ እገኛለሁ::

የፈተነህ ገፀ ባህሪ የቱ ይሆን ?

አራት ዐይና ላይ ያሉት አለቃ ገብረሃናን በዋና ገፀ ባህሪነት ሥሠራ በገጸ ባህሪው ተፈትኛለሁ::  አለቃ ገብረሃና በልቦለድ የመጡ ገፀ ባህሪ (ካራክተር) ሳይሆኑ በእውኑ ዓለም የነበሩ ሰው ናቸው ፤ በጣም ብዙ ጥናቶች የተካሄዱባቸው ስለሆነ በጣምም የሚከብዱ ገፀ ባህሪ ነበሩ:: ሰው አለቃ ገብረሃናን እንደቀልደኛ ቢያያቸውም በጣም ከትውልዱ የቀደመ አስተሳሰብ ያላቸው ፣ ከ26 ዓመታቸው ጀምሮ በጎንደር የቤተ ክህነት ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ያገለገሉ፣በመሳፍንት ጊዜ የትንሹ ራስ አሊ አጫዋች የነበሩ፣ በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ደግሞ የፍትኃ ነገሥት ተርጓሚ የነበሩ እና በሁሉም ስብእናዎቻቸው ከፍ ያሉ ሰው ናቸው:: በቲያትሩ ከብዙ ተመልካቾች ጥሩ ግብረ መልስ ቢገኝም እንደተዋናይ ግን ገጸ ባህሪው ፈታኝ ነበር::

ለሙያህ አርዓያ ያደረከው ሰው ካለ?

ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም ከመግባቴ በፊት እግር ኳስ ተጫዋች ሁሉ የምሆን ይመስለኝ ነበር:: እውነት ለመናገር ለሙያዬ አርዓያ ያደረኩት ሰው አልነበረም ።ወደ ኪነ ጥበቡ ከገባሁ በ ኋላ ግን በወቅቱ ያሉትን ሰዎች ሁሉ አደንቅ ነበር ፤ በዘርፉ በተለየ የማደንቀው ሰው ባይኖርም ሥራ ላይ እያለሁ ግን ከሽመልስ አበራ እና አለማየሁ ታደሰ ጋር አብሬ ብሠራ ያልኳቸው ተዋናዮች ናቸው::

በትወናው ዓለም የማትረሳው ገጠመኝ?

የኛ የተዋናዮች ገጠመኞቻችን ብዙ ናቸው፤ በአንድ ወቅት ባሕር ዳር ቀበሌ 04 አዳራሽ የታቦር ገብረመድህንን “ተዋናዩ” የተባለ ቲያትር ለባለስልጣናት እናቀርብ ነበር፤ ገጸ ባህሪው ተዋናይ ነው እና ተወናዩ ለቲያትር ልምምድ ሲያደርግ ቤተ ዘመዱ አብዷል ብለው ወደ ፀበል መሄድ እንዳለበት  ያስባሉ:: መጨረሻ ላይ ገጸ ባህሪው አብዶ ብዙ የሚንኮሻኮሹ ነገሮችን፣ ቀንድ፣ ቆርቆሮ… ይዞ (ይዤ) ከመድረኩ ጀርባ ስገባ ከኋላ አንዱ ጠባቂ በጥይት ሊመታኝ ሲል ሌላኛው ጠባቂ ያዳነኝን አጋጣሚ ግን ፈጽሞ አልረሳውም::

ኪነ ጥበቡ በሃገራችን ያለበት ሁኔታ?

ጥበቡን ለማሳደግ ያለው ሰላም አሳሳቢ ነው፤ እንደ ክልል ምንም ዓይነት የኪነ ጥበብ እንቅስቃሴ የለም ፤እንደ ሃገር ግን አማራጮች  በዝተዋል። ዲኤስ ቲቪ፣ካናል ፕላስ… የተለያዩ የቴሌቪዥን አማራጮች ስላሉ ተከታታይ ደስ የሚሉ የእኛን የቄሳር ዲናሮች ጨምሮ ድራማዎች በዝተዋል::

በሀገራችን  የፊልሞች መብዛት በቲያትር እድገት ላይ ያሳደሩት ተፅእኖ አለ?

የለውም፤ ምክንያቱም ሁሉም የየራሳቸው ተመልካች ነው ያላቸው:: ሁሉም የየራሱ ወቅት አለው ፤ የሆነ ወቅት የመድረክ ቲያትር በጣም ይፈለጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፊልም… ፊልም… ይባላል:: ተመልካቻቸው ደግሞ የተለያየ ነው፤ አንዳንዱ ቲያትር ቤት ሄዶ ማየት ይፈልጋል፤ አንዳንዱ ደግሞ ፊልሞችን በቤቱ ያያል ፤ ነገር ግን ቲያትር እና ፊልሞችን በድርሰት ዐይን ስናያቸው  “ይችን ነገር ቲያትር አድርጌ ከምደክም ይልቅ ተከታታይ   ድራማ አድርጌ ትቀረፃለች፣ ጥሩ ክፍያም ያመጣል” ብሎ ማሰብ  ስላለ የመድረክ ሥራ እየተቀዛቀዘ ነው ማለት እችላለሁ፤ ከተመልካች አንጻር ግን ሁሉም የየራሳቸው ተመልካች ነው ያላቸው ::

አራት ዐይና ቲያትርን ይዘን ወደ አዲስ አበባ ስንሄድም የታዘብነው ብዙ የመድረክ ቲያትሮች የትርጉም ሥራ መሆናቸውን ነው፤ የቲያትር ጽሑፍ (ስክሪፕት) ጠፍቷል። ለምን? ከተባለ ደግሞ ምክንያት ሊሆን የሚችለው የተሻለ ክፍያ የሚከፍሉ  የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስላሉ ነው፤ ከፊልሞች የተሻለ ገቢ ስለሚገኝ ነው::

የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል የክልሉን ባሕል ከማሳደግ አንፃር ምን ሠራ?

የባህል ማዕከሉ ክልሉ ብዙ ችግር ውስጥ ቢሆንም እንኳን ሁልጊዜ ይሠራል፤ በብዙ ጥናት የታገዙ እንደ ጉማ፣ አራት ዐይና …. ቲያትሮች እንሰራልን፤ ተመልካቹን ግን ማምጣት አልቻልንም::

በፊት ላይ በደንብ ያልተሞከሩ ነገር ግን አሁን ቲያትሮችን ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ውጭ ሀገሮችም  ሄዶ ለማሳየት እየተሞከረ ነው:: ቲያትራችን ከባሕር ዳር የመጣ ነው ከተባለ ተመልካቹ የተሻለ ሥራ ሊሆን ይችላል ብሎ ይታደምልናል:: የዚህ ነገር ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ በፊት ተንቀሳቅሰን ያሳየናቸው ቲያትሮች በተመልካቾች ሥነ ልቦና ውስጥ ጥሩ ቦታ ስለተሰጣቸው ይመስለኛል፤ ለምናሳያቸው ቲያትሮች ጥሩ ግብረ መልሶች እየተሰጡንም ይገኛል::

የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል ተተኪን ከማፍራት አንጻርም አበረታች ሥራዎችን ሠርቷል:: ብዙ በጀት በጅቶ ስልጠናዎችን በውዝዋዜ፣ በዝግጅት፣ በትወና ፣በሙዚቃ መሣሪያ መጫወት ፣በሙዚቃ፣ በቲያትር እና በተውኔት አፃፃፍ ይሰጣል:: ሰልጣኞቹ ዝርዝራቸው ተይዞ ሥራ እና ማስታወቂያ ሲኖር ተጠርተው ይሠራሉ:: ይህ ማለት ደግሞ ልጆቹ ሰልጠነው አይጣሉም እንደማለት ነው:: በግልም ቢሆን ስልጠና እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ ሰዎች ሲኖሩ ባለሙያው ያለምንም ክፍያ  ያሰለጥናል::

በግል ለሚንቀሳቀሱም ባህል ማዕከሉ ከሰዓት በኋላ ያለምንም ክፍያ አዳራሽ እና ሌሎች ቁሶችን ፈቅዶላቸው ይጠቀማሉ፤ የባለሙያ እገዛ ቢፈልጉም ማዕከሉ ለማገዝ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል::

ከክልሉ ወጥተህ የመሥራት ዕድሉ አልገጠመህም?

በፊት የነበረኝ አቋም በፌዴራል እና በሌሎችም ቦታዎች ያሉ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ወደ እኛ ክልል ማምጣት ይቻላል የሚል ነበር፤ ምክንያቱም በኪነ ጥበብ ዘርፍ የክልሉ አቅም ያልተነካ ነው፤ ትውፊት አለ፣ የትወና እና የጽሑፍ ዝግጅት አቅም፣ የቀረፃ ባለሙያዎችም አሉ::  ለአብነት “ገዳይ ሲያረፋፍድ” የሚለው ፊልም  የስለሺ አምባው ሥራ ነው:: ስለሺ አምባው ደግሞ በባሕር ዳር የሚገኝ የፊልም ጽሑፎች ደራሲ ነው:: ስለዚህ የተለያዩ የፊልም ባለሙያዎች  እዚህ መጥተው አብረናቸው  እንሠራለን፤ ስለ ፊልሞቹ ሳቢነት እና ማራኪነት ደግሞ ውጤቱን የሚገመግመው  ተመልካቹ ነው::

የኔ የመጀመሪያው ሃሳብ እኔ ለፊልም ሥራዎች ብዬ ወደ ሌላ ሀገር ከምሰደድ ይልቅ ፊልሞቹ ራሳቸው ወደኛ ይመጣሉ የሚል ነበር፤ አሁን ግን በክልሉ በርከት ያሉ የጥበብ ሥራዎች ቢሠሩም   ተደራሽነት ይጎድላቸዋል:: ፌዴራል (አዲስ አበባ) ብንገባ ግን  በአንድ ሥራ አንወሰንም ፤አማራጭ ሥራዎችም ይበዙልናል::

የተገኘውን ሁሉ ሥራ መሥራት አልፈልግም፤ ግን ደግሞ የፊልም ጽሑፎችን ዐይቼ ጥሩ የሚባል ሥራ ካገኘሁኝ እሠራለሁ::  በዚህ ሙያ ውስጥ እዚሁ ባሕር ዳር ብቻ ከቀጠልን መሻሻል የምንችል አይመስለኝም:: ባለቤቴም እንደኔው የኪነ ጥበብ ባለሙያ በመሆኗ ተንቀሳቅሼ እንድሠራ ብትፈልግም ሁኔታዎች እኛ ባሰብነው መልኩ እየሄዱልን አይደለም፤ ያም ሆኖ ግን እኔም ተንቀሳቅሼ በመሥራት የተሻለ እድገት እንዲኖኝ እፈልጋለሁ::

ተመሳሳይ ሙያ እና ትዳርን እንዴት ትገልፀዋለህ?

በጣም ጥሩ (ምርጥ ነው)::  ሙያችን በሰዎች ዘንድ የሚታመን እና ደስ የሚል ሙያ ነው:: በዚህ ሙያ ውስጥ የራስህ የሆነ ሰው ማግኘት እና አብሮ መሥራት ደግሞ በጣም ጥሩ ነገር ነው::  በሙያዉ ውስጥ ያለች ሴት ስታገባ የፊልም ጽሑፍ (ስክሪፕት) አብሮ በማንበብ፣ በሥራ እያመሸሁ ብሆን እንኳን ሥራው ምን ላይ ነው? እንዴት ነው? የሚለውን እየጠየቀችኝ ልትረዳኝ ትችላለች:: ከሥራው ውጭ ያለች ሴት ግን ሥራውን ልትወደው ትችላለች እንጂ የሥራውን አሠራር  ላትረዳው እና የሚሠራበት  መንገዱም ላይመቻት ይችላል::

ለሥራው ሰፊ ጊዜ የመስጠት ሂደት  ስለሚኖር ይህንንም  ላትረዳ ትችላለች:: የኪነ ጥበብ ባለሙያ ስትሆን ዋናው ሃብትህ  ሰው የሚሰጥህ ክብር  ስለሆነ ይሄንን ለመገንዘብም በሙያው ውስጥ ማለፍን ወይም መኖርን ግድ ይላል:: በአጠቃላይ የኪነ ጥበብ ሰው ህይወትን ቀለል አድርጎ ነው የሚመራው፤ በዚህ ህይወት ውስጥ ያሉ ባለትዳሮች በትዳራቸውም ሆነ በሙያቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆናቸው የማይቀር ነው::

ለዛ አዋርድ እጩ እንዴት ሆንክ? ውጤቱስ?

በአዲስ አበባ ያሉ ጓደኞቼ “በቄሳር ዲናሮች” ተከታታይ ድራማ ለሽልማት መታጨቴን ሲነግሩኝ ደስ አለኝ ፤ ምክንያቱም ሽልማቶች ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ወጥተው በየክልሉ ያለውን የሥራ አቅም መመልከት እንደቻሉ ያሳያልና ነው:: ባለፈው ዓመት ባለቤቴ ተዋናይት መስከረም ነጋ ጉማ አዋርድ ላይ ታጭታ አሸንፋለች:: በዚህ ዓመት ደግሞ በሙሉዓለም የባሕል ማዕከል የምንሠራው እኔ ፣ መስከረም ነጋ (ባለቤቴ) እና ግዮን ዓለምሰገድ ከክልላችን ዕጩ ተወዳዳሪዎች መሆን ችለናል፤ በዚህ ሂደት ባንሸለምም እንኳ መታጨታችን በራሱ በክልላችንም ጥሩ የኪን ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለው ማየት ጀምረዋል ብለን እንድናስብ ያደርገናል::

እስካሁን ባለው ሂደትም ምርጥ አምስት ውስጥ መግባት ችለናል:: ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል::

ኪነ ጥበቡ ለሀገር ሰላም እና አንድነት  ምን ማበርከት አለበት?

የኪነ ጥበብ መሰረታዊ ነገሩ ችግር አለበት በተባለው ነገር ላይ ሁሉ የመፍትሄ አካል ይሆናል:: የኪነ ጥበብ ሥራን እንደ ካህኖች ሥራ መቁጠር ይቻላል::የካህናት ሥራ እና የኪነ ጥበብ ሥራዎች የሚያስቀድሙት በጎ ነገርን መስበክ ነው:: ችግርን አስታሞ እና ሚዛናዊ አድርጎ በመድረክ ላይ ማቅረብ ችግሩን አያድነውም፤ ይልቁንም ጥበብ ችግሮችን ማከም ሳይሆን ማሳየት ነው ያለባት :: ኪነ ጥበብ የሰላም እና የመግባባት መንገዶችን ጠቋሚ ናት፤ እንደ ሀገር በመግባባት መሥራት አለመቻሉ ደግሞ ኪነ ጥበቡን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር የሚጎዳው ነው፡

በመጨረሻ የምትለው ሃሳብ ካለ?

በኪነ ጥበብ የማይፈታ ነገር የለም፤ እንዳለመታደል ሆኖ  ግን  በሦስተኛው ዓለም ያለን ሰዎች አንደማመጥም፤ በውይይት ችግሮችን መፍታት ላይ ውስንነቶች ይታዩብናል::

አራት ዐይና ቲያትር ላይ በአንድ ገጸ ባህሪያቱ በሚያደርጉት ቃለ ምልልስ ላይ   ‘የሚያዳምጥ አስተዋይ መሪ እንዲኖረን ነው የዘወትር ፀሎታችን’ ይላል:: እኔም የሚያዳምጡን አስተዋይ መሪዎች እንዲኖሩን አጥብቄ እመኛለሁ::

ከታሪካችን የመጣንበት እና የተሠራንበት መንገድ ጦርነት ነው፤ ይሄ ደግሞ ይሰለቻል እና የሕዝብን ችግር መንግሥትም ማዳመጥ   አለበት እላለሁ::

ለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን!

እኔም በጋዜጣችሁ ለተሰጠኝ ዕድል ምስጋናዬ ከልብ ነው!

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here