እኔን ያየህ…

0
113

በጉንጮቹ፣ በዓይኖቹ እና በራስ ቅሉ ላይ የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው ምስሎችን በጉልህ የተነቀሰው የ24 ዓመት ወጣት ላለፉት ስድስት ዓመታት ስራ ለማግኘት ያደረገውን ጥረትም ሆነ መደበኛ ህይወቱን ለመምራት አስቸጋሪ እንዳደረገበት ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል::

በቻይና መገናኛ ብዙሃን “አቶ ኤ” በሚል ስሙ ሳይገለፅ ሞርኒንግ ስታር ኒውስ የተሰኘ መገናኛ ብዙሃን የቀረበው ወጣት ባልተለመደ የፊት ገፅታው ተመልካቾችን አስደንግጧል:: ወጣቱ ግን በጉርምስና እድሜው መጀመሪያ ዓመታት አመጸኛ እንደነበር እና ካጋጠመው የመንፈስ ጭንቀት ለመሸሸግ ገፅታው እንዳይለይ መነቀሱን ነው የተናገረው::

ወጣቱ እንደተናገረው ከጥቂት ዓመታት በፊት በአፍንጫና ጉንጮቹ ላይ የራስ ቅል ምስል በተላጨው የራስ ቅል ቆዳው ላይ የአንጐል እጥፋትን የሚያሳዩ ምስሎችን ተነቅሷል:: በወቅቱ ራሱ ደስተኛ ቢሆንም እያደረ ከተመልካች በሚደርስበት ነቀፌታ መደበኛ ህይወቱን ለመምራት መቸገሩን ጠቁሟል::

ያለፉት ስድስት ዓመታት ለሱም ሆነ ለቤተሰቡ እጅግ ፈታኝ እንደነበሩ የጠቀሰው ወጣቱ በተለያዩ ቦታዎች ስራ ለማግኘት ባደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት፣ በቀጥታ የሚዲያ ስርጭቶች ስድብ አዘል ውርጅብኝ እንደደረሰበት አልሸሸገም:: ከተመልካች በሚደርስበት የጥላቻ አመለካከት የተነሳም የፊቱን ምስል በስልኩ የፊት ገጽ ላይ ለማዋል ማፈሩን መሸማቀቁን በምሬት አስረድቷል::

ንቅሳት አስወጋጁ ባለሙያ በተለይ  በወጣቱ ዓይን እና አፍንጫው ላይ ያለውን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ መሆኑን በመግልጽ አመላክቷል:: በፊቱ ላይ ከፍተኛ ጨረር መልቀቅ በዓይኑ እና እንደ ልብ ባሉ አካላቱ ላይ ችግር ሊየስከትል እንደሚችል ነው አፅንኦት ሰጥቶ ያስጠነቀቀው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here