“እኔ ማስተማር በጀመርኩበት ጊዜ መምህራን መኪና ሁሉ ነበራቸው”

0
304

በመምህርነት ሙያ ከ33 ዓመታት በላይ አገልግለዋል:: አስመራን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አስተምረዋል:: ከዲፕሎማ ጀምረው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል:: ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ70 ዓመታቸው ነው የያዙት:: ከዓመታት የመምህርነት አገልግሎታቸው በኋላ ጡረታ ወጥተዋል:: በአሁኑ ጊዜ የሰሌክት የርቀት ትምህርት የአማራ ክልል አስተባባሪ ናቸው:: በግል ሕይወታቸው ላይ ያጠነጠነ እና የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ ግጥሞች ጎን ለጎን የያዘ መጽሐፍ ሊያሳትሙ ነው:: ባለትዳር እና የስምንት ልጆች አባት የሆኑት መምህር አወቀ በላይ እንግዳችን ናቸው::

 

የመምህርነት ሙያን እንዴት መረጡ?

የተወለድኩት በቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር ደብረ ማርቆስ አውራጃ በደጀን ከተማ ነው:: በሰባት ዓመቴ አንደኛ ክፍል ገባሁ:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴንም በደጀን ከተማ ነው ያጠናቀቅኩት:: በወቅቱ ብቸኛው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረው ደብረ ማርቆስ በመሆኑ ወደ እዛው አቀናሁ:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም እዛው ጨረስኩ:: በወቅቱ ለኮሌጅ የሚያበቃ ውጤት ስለነበረኝ  ጅማ የእርሻ ኮሌጅ ተወዳድሬ አለፍኩ:: ከሁለት ዓመትታት ትምህርት በኋላ ዲፕሎማየን ያዝኩ::

በልጅነታችን ስንማር ራሳቸውን ጠብቀው፣ ሱፍ ከእነ ከራባቱ ለብሰው የምናያቸው መምህራንን ነበር:: አርአያዎቻችን የሚያስተምሩን መምህራን ነበሩ:: አብዛኛው ተማሪ ነገ ከነገ ወዲያ መምህር የመሆን ፍላጎት ነበረው:: እኔም በዚህ ምክንያት ልዩ ፍቅር ነበረኝ፤ ለዚያም ነው ሌሎች ከእርሻ ሳይንስ ጋር የተዛመዱ ሙያዎችን ትቼ ወደ መምህርነቱ የገባሁት::

 

በመምህርነት የት ነው የተመደቡት? የመጀመሪያ ገጠመኝስ አለዎት?

ለመጀመሪያ ጊዜ መምህር ሆኜ የተመደብኩት በኤርትራ ክፍለ ሀገር  ነው:: የተመደብኩበትን ደብዳቤ እና አንዳንድ መረጃዎችን ይዤ ወደ ትምህርት ቤቱ ሄድኩ:: ትምህርት ቤቱ ደቀ መሀሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይባላል:: በወቅቱ የ20 ዓመት ወጣት ነበርኩ እና እኔ ራሴ ተማሪ ነበር የምመስለው:: በዚህም ምክንያት ከርዕሰ መምህሩ ዘንድ ስቀርብ ሳቀና በትግርኛ አናገረኝ:: እኔ ደግሞ ትግርኛ አልችልም፤ ስላልተግባባን በተማሪ ደንብ ነበር ዝቅ ባለ ክብር ያስተናገደኝ:: አሁን ሲገባኝ በትግርኛ ምን ፈለክ ነበር ያለኝ:: እኔ አልተረዳሁትም:: ወዲያው የተመደብኩበትን ደብዳቤ አውጥቼ ሰጠሁት፤ አየው እና በጣም ይቅርታ ጠየቀኝ:: አንቱ ብሎ እንድቀመጥ ጋበዘኝ:: ይህን አልረሳውም::

በመጀመሪያው ቀን ከተማውን ዞር ዞር በል እና ተመልክተህ ነገ ና አለኝ::  በሚቀጥለው ቀን ፕሮግራሜን ይዤ ክፍል ወስጥ ገባሁ:: አብዛኞቹ አማርኛ አይችሉም ነበር:: ስለሆነም በእንግሊዝኛ ማስተማር ጀመርኩ:: ተማሪዎቹ በደንብ ይሰሙኝ ነበር::

 

በንጉሡ እና በደርግ የነበረው ስርዓተ ትምህርት ምን ይመስል ነበር?

የንጉሡ ስርዓተ ትምህርት የተቀዳ የነበረው ከእንግሊዝ እና ከአሜሪካ ነው:: በዋናነት ደግሞ የእንግሊዝ ነበር:: ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ሁሉም ትምህርት በእንግሊዝኛ ነበር የሚሰጠው::  ከትምህርቱ ውጪ እንድናነብ ይሰጠን የነበረው የእንግሊዝኛ ጽሑፎችን እና የእንግሊዝ ታሪኮችን ነበር:: የራሳችንን ሀገር ታሪክ መማር የጀመርነው ሁለተኛ ደረጃ ከገባን በኋላ ነው:: የእነ ዐፄ ቴዎድሮስን፣ ዐፄ ዮሐንስን፣ ዐፄ ምኒልክን እና ሌሎችን ታሪክ መማር የጀመርነው እያደግን ስንመጣ ነበር:: ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣን ሊነሱ ትንሽ ሲቀራቸው ነበር ወደ መምህርነቱ የገባሁት:: የደርግን ሥርዓተ ትምህርት የማውቀው በመምህርነት ነው:: በፊት ከነበረው የተሻለ ቢሆንም ችግሮች ግን አልነበሩትም ማለት አይቻልም

 

ባለፈው ዘመን የነበረው የተማሪ እና የመምህር ግንኙነት እንዲሁም የማኅበረሰቡ አክብሮት ምን ይመስል ነበር?

ቀደም ባለው ጊዜ የተማሪው እና የመምህሩ ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሠረተ ነበር:: መምህር በከፍተኛ ደረጃ የተከበረ ነው:: መምህር አንተ አይባልም፤ አንቱ እየተባለ ነበር የሚጠራው:: ይህ ደግሞ በተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በወላጆች እና በማኅበረሰቡም ያለ ነው:: በመንገድ ላይ አሊያም የሆነ ቦታ ስንገባ ሽማግሌዎች ሳይቀር ከመቀመጫቸው ተነስተው ነበር አክብሮታቸውን እና ፍቅራቸውን የሚገልጹልን:: ሱቅ ላይ እንኳ “መምህር የፈለጉትን ይውሰዱ፤ ቀስ ብለው ይከፍላሉ” ነበር የምንባለው::

 

የመምህሩ የኑሮ ሁኔታስ ምን ይመስል ነበር?

እኔ ማስተማር በጀመርኩበት ጊዜ መምህራን መኪና ሁሉ ነበራቸው:: የእኛ ጓደኛ በ850 ብር የገዛት ቶፖሊኖ የምትባል መኪና ነበረችው::  መምህር በቲቲአይ 250 በዲፕሎማ ደግሞ 350 ነበር ደሞዙ:: 306 ብር እጃችን ላይ ገብቶ አያልቅም ነበር፤ የፈለግነውን አድርገንበት በረከት ነበረው:: መምህር 350 ብር ሆኖ ደሞዙ የአውራጃ አስተዳዳሪው 180 ብር ነበር ደሞዙ:: ለመምህራን መንግሥት ሳይቀር ክብር ነበረው::

 

ከኤርትራ በኋላ የት የት አስተማሩ?

የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ደቀ መሀሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዘጋ:: ይህም የሆነው በሻዕቢያ እንቅስቃሴ ምክንያት ትምህርት ከነጻነት በኋላ በሚል  ተማሪዎቹ በአመጽ መማር ስላቆሙ ነው:: በዚህ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ተጠርተን ከመንግሥት ጋር ከተወያየን በኋላ ኤርትራ ውስጥ የነበርነው የሁለተኛ ደረጃ መምህራን በሌሎች ክፍለ ሀገራት ተመደብን:: እኔ በአጋጣሚ ዳንግላ ከተማ ተመደብኩ::

በዳንግላ ከተማ የሠራሁባቸው ጊዜያት በሕይወቴ የሚያስደስቱኝ እና ትልቅ ነገር አደረኩ ብየ የምኮራባቸው  ናቸው:: በወቅቱ የእርሻ ትምህርት ስነ ዘዴው በባለሙያ የተሠራ ስላልነበረ ውጤታማ አልሆነም:: ስለሆነም በኮሌጅ የተማርኩትን ተጠቅሜ አዲስ የትምህርት ስነ ዘዴ አዘጋጀሁ:: ስነ ዘዴው ከዘጠነኝ እስከ 12ኛ ክፍልን የሚሸፍን ነው:: እኔም ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሬ የያዝኳቸውን  ሁለት ክፍሎች እስከ 12ኛ አድርሻለሁ:: አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲ ነው የገቡት:: በዳንግላ ስድስት ዓመት አገልግዬ ወደ ባሕር ዳር ተዘዋወርኩ::

በባሕርዳር ከተማ ጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጡረታ እስከወጣሁበት 2000 ዓ.ም ድረስ እርሻ እና ሲቪክስ ( ሥነ ዜጋ እና ሥነ መግባር) ትምህርቶችን አስተምሬያለሁ:: የእርሻ ትምህርትን እስከ 1996 አስተምሬያለሁ:: እርሻ መሰጠት ሲቆም ሥነ ዜጋ እና ስነ ምግባር ትምህርት ተጀመረ፤ እኔም እንግሊዝኛ ቋንቋ  ችሎታ ስለነበረኝ  ያዝኩት::

 

የእርሻ ትምህርት በውስጡ ምን አንኳር ይዘቶች ነበሩት? ጠቀሜታውስ?

የእርሻ ትምርት በሁለት ዋና ክፍሎች ይከፈላል:: እነሱም እንስሳት እና እጽዋት ናቸው:: በእጽዋት ውስጥ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም አዝርዕት አሉ:: የእንስሳት ዘርፍ ደግሞ የወተት ላሞች፣ የሚደልቡ በሬዎች፣ የሚረቡ ዶሮዎች እና ንብ ማነብ አለ:: በእነዚህ ጉዳዮች ተማሪዎች በቂ እውቀት አግኝተው በትምህርት ቤታቸው እና በቤታቸው የከተማ ግብርናን እንዲጀምሩ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ፣ ከሽያጪ ገቢ እንዲያመነጩ ያለመ ነበር::

ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በቡድን ሆነው መሬት ይሰጣቸዋል፤ ያንን መደብ በመሥራት እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ያለማሉ፡ ሠርተው ያሳያሉ፤ ከሽያጭ ከሚገኝ ገቢ የተወሰነ ትምህርት ቤቱን ይደጉማሉ::

 

የእርሻ ትምህረት ተቋርጦ ነበር፤ ለምን እንደሆነ ያውቃሉ?

በኢሕአዴግ ዘመን ነው የቆመው፤ ይህ መሆኑ ደግሞ እንቆቅልሽ የሆነ እና እርስ በራሱ የሚጋጭ ነገር ያለበት ነው:: የኢሕአዴግ መንግሥት ፖሊሲ ኢትዮጵያ በግብርና መር ኢንደስትሪ ትመራለች ይላል:: ነገር ግን የእርሻ ትምህርትን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዳይሰጥ አገደ:: ይህ የተምታታ ነገር ነው፤ ለምን እንዲቀር እንደተደረገ እና ማን እንዳዘዘው አላውቅም::

 

የክፍል አያያዝ እና የመርጃ መሣሪያ አጠቃቀምዎ ምን ይመስል ነበር?

እንደ አርአያ የወሰድኩት አንድ ሕንድ መምህር ነበረን፤ በጣም ጎበዝ ነው፤ ተማሪው ይወደዋል፤ ያከብረዋል:: ክፍል ውስጥ ሲገባ ሁሉም ተማሪ ይነሳል:: ዞር ዞር ብሎ ያይና ሁሉም ተማሪ መነሳቱን ካረጋገጠ በኋላ ነው ማስተማር የሚጀምረው፤ የሱን አካሄድ ተከትዬ ነበር እኔ ሥርዓት የማስይዘው:: ተማሪዎች ክፍል ውስጥ እንዲረብሹ እድል አልሰጥም፤ ድምጽ ክፍል ውስጥ ከሰማሁ ድምጽ ወደ አለበት ጸጥ ብየ አያለሁ፤ የሚያወራ የነበረው ተማሪ ደንግጦ ዝም ይላል:: በሚረብሹ ተማሪዎች ላይ ጫና አሳድራለሁ፤ ሁሉንም ጊዜ እንዲሳተፉ ለማድረግ እሞክራለሁ::

የመርጃ መሣሪያ የሚያስፈልግበት ቦታ አለ፤ የማያስፈልግበት ይኖራል፤ በቃል ከማስተማር ይልቅ የመርጃ መሣሪያ የሚያስፈልጋቸው ክፍሎች ሲገኙ የራሴን አጋዥ ነገሮች አዘጋጃለሁ:: የትም ቦታ በነበርኩበት ሁሉ የመርጃ መሣሪያ አዘጋጃለሁ፤ ይህን ማድረግ የመምህሩን ጉልበት ይቀንሳል፤ ተማሪዎችም በደንብ ትምህርቱ እንዲሰርጻቸው ያግዛቸዋል::

 

አሁን ላይ ብዙ ተማሪዎች የሥርዓት እና የትምህርት አቀባበል ችግር እንዳለባቸው ይነገራል፤ ይህ ለምን ሆነ?

ይህ በሂደት የመጣ ነው:: ሙሉ ለሙሉ የጠፋው ግን በኢሕአዴግ ጊዜ ነው:: የሆነ ጊዜ ላይ ተማሪው መምህሩን ይገምግመው የሚል ነገር መጣ:: በዚህ ጊዜ ተማሪው ለካ መምህሩ በእኔ ቁጥጥር ሥር ነው ብሎ ማሰብ ጀመረ:: ገና በእድሜ ትንሽ ስለሆኑ ብስለትም ስለሚያንሳቸው መምህሩን መናቅ ጀመሩ:: ስለዚህ ክፍል ጥሎ መሄድ፣ ሳያስፈቅዱ መግባት፣ መቅረት፣ የተሰጣቸውን ሥራ አለመሥራት፣ አለማጥናት በአጠቃላይ ትምህርቱን መናቅ ተጀመረ::

ሌላው ደግሞ ብቁ ሳይሆኑ ወደ ሚቀጥለው ክፍል መዘዋወር ነው:: መድገም የለም በሚል ሁሉም ተማሪ ወደ ሚቀጥለው ክፍል ይዘዋወራል:: ይህን ፖሊሲ በዋናነት እንዲሰርጽ ያደረጉት ሰዎች የወጡበት ጎረቤት ክልል ግን ልጆች ብቁ ሳይሆኑ ወደሚቀጥለው ክፍል አይዘዋወሩም:: ለመምህራንም ልዩ ክብር አላቸው:: አንድ ጊዜ አስረኛ ክፍል እያስተማርኩ፤ የተወሰኑ ተማሪዎች አርፍደው መጡ፤ ግቡ አልኳቸው:: ሌሎች ገብተው ሲቀመጡ አንደኛው ልጅ ተንበረከከ:: ግባ ተብለሃል እኮ ስለው “አጥፍቻለሁ መምህር፤ ለጥፋቴ ነው የተንበረከኩ” ብሎ በክብር መለሰልኝ:: የኛዎቹ ተማሪዎች የእሱ አይነት ክብር የላቸውም፤ ከየት እንደመጣ ገባኝ እና ከዚህ ክልል ነው የመጣኸው አልኩት “አዎ!” አለኝ፤ ተነስቶ እንዲቀመጥ አደረኩት:: የራሳቸውን ልጆች ለመምህር  ክብር፣ ለትምህርት ፍቅር እያስተማሩ የእኛ ልጆች እንዳያከብሩ፣ ሳይበቁ እንዲዘዋወሩ ለትምህርት ፍቅር እንዳይኖራቸው ሲያደርጉን ኖረዋል:: ብዚ ጫናዎች እና ሴራዎች ተሰርተውብናል::

አሁን ላይ መምህራን በኑሮ ሁኔታቸው ሲያማርሩ ይሰማል፤ ማኅበረሰቡ ለመምህርነት ያለው አመለካከትም ቀንሷል፤ ይህ ከመቼ ጀምሮ የመጣ ነው ይላሉ?

የመምህሩ ኑሮ መክበድ የጀመረው ደርግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ነው፤ የኑሮ ውድነቱ ከፍ እያለ መጣ፤የቤት ኪራይ፣ አስቤዛ እና ሌሎች ወጪዎች ጨመሩ:: በኢሕዴግ ጊዜ ጭራሹን ተባብሶ ችግር ላይ መምህሩ ወድቋል::

 

ስለ ልጆች አስተዳደግ ምን ይላሉ? ለወጣቱስ ምን ይመክራሉ?

ልጆቼ እደማንኛውም የመምህር ልጅ የተጋነነ ነገር ሳይደረግላቸው ነው ያደጉት:: ጥብቅ ቁጥጥርም ሆነ ለቀቅ ያለ አስተዳደግ አልነበራቸውም፤ ሁሉም በልኩ ነው:: ሴት ልጆቼን ከማመን ጋር ነው ያየሁሽ ብየ አልቆጣም:: ሴትን ልጅ በጣም አጥብቀህ ከያዝክ ለመበላሸት መንገድ አታጣም:: ነጻነት ሲኖር ግን ጉዳት እና ጥቅሙን በነጻነት ታውቀዋለች፤ በሥርዓት ታድጋለች::

ለልጆቼ ከ1977 ጀምሮ ግጥም እጽፍላቸዋለሁ:: በግጥም አወድሳቸዋለሁ፤ እመክራቸዋለሁ:: በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ ነው ያለው:: አሁን በሦስት ጥራዝ ተደርጎ በመጽሐፍ ይወጣል:: አንድ ጊዜ ባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የክብር እንግዳ አድረገው ጠሩኝ፤ የጠሩኝ ልጄ አብሯቸው ስለሚሠራ ነው:: በዚያ መድረክ ለፈረንጆቹ ግጥም አነበብኩላቸው:: ግጥሟ የተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ብቸኛ ዘፈን ላይ ያለች ስንኝ ናት:: ስንኟ “ግቢና ተጫዎች ራቁቴን ነኚ፣ ካንቺ ምሸሽገው ምን አካል አለኝ” የምትለዋን በእግሊዝኛ ተርጉሜ ለውጪ ሀገር እንግዶች አነብኩላቸው:: ተገረሙ፤ ተደሰቱ::

ለወጣቶች የምመክረው ዕውቀት እጃችሁ ላይ ነው:: እናንተ የማወቅ የመመራመር ፍላጎት ይኑራችሁ:: ብዙ እድል አላችሁ:: ቴክኖሎጂው ማደጉ ነገሮችን አቅልሎላችኋል:: በአልባሌ ነገር ጊዜያችሁን አታጥፉ:: ቅንጥብጣቢ ነገር ሳይሆን የጠለቀ እውቀት ያስፈልጋል:: በእርግጥ ለወጣቱ መለወጥ የመንግሥት፣ የምሁራን፣ የመምህራን እንዲሁም የማኅረሰቡ ድጋፍ እና ቅንጅት ያስፈልጋል::

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ!።

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የመጋቢት 15  ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here