እንቅልፍ ለደም ግፊት

0
175

በቀን ከሰባት ሰዓታት በታች ወይም ያነሰ በእንቅልፍ  የሚያሳልፉ ሴቶች በጊዜ ሂደት ለከፋ የደም ግፊት ህመም የሚጋለጡ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል::

በአሜሪካ የካርዲዮሎጂ ኮሌጅ በዓመታዊ የሳይንስ ምርምር ጥናቱ  ከሰባት ሰዓታት በታች በእንቅልፍ የሚያሳልፉ ሴቶች በጊዜ ሂደት ለከፋ የደም ግፊት እንደሚጋለጡ በግኝትነት ቀርቧል::

ከ2000 እስከ 2023 እ.አ.አ በተደረጉ ጥናቶች እና ምርምሮች ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የናሙና ተሣታፊዎች ተካተዋል:: በአምስት ዓመታት የከፋ የደም ግፊት ህመም ባልነበረባቸው ላይ በተደረገ ክትትል በባለሙያዎች ከሚመከረው የእንቅልፍ ጊዜ ያነሰ የተመዘገበባቸው የከፋ የደም ግፊት ተስተውሎባቸዋል::

በጥናቱ በቀን ከሰባት  ሰዓታት ያነሰ የእንቅልፍ ጊዜ የሚያሳልፉ በጊዜ ሂደት ለከፋ የደም ግፊት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው የጥናት እና ምርምሩ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር ካቬ ሆሴይኒ ያረጋገጡት::

ለእንቅልፍ ጊዜ ማነስ ወይም መዛባት የእኗኗር ልምዶች፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ ከመጠን በላይ መብላት፣ አልኮል መጠጣት፣ መድሀኒቶችን መጠቀም፣ ጭንቀት እና ድብርት መንስኤ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ባለሙያዎቹ የጠቆሙት::

በምርምሩ የተሳተፉ ከ35 እስከ 60 ዓመት እድሜ ያላቸው ሲሆኑ የእድሜ ልዩነታቸው ብዙ ተጽእኖ አለማሳደሩ ነው የተነገረው። ነገር ግን ፆታን በተመለከተ ለከፋ የደም ግፊት የተጋለጡት 61 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን አረጋግጠዋል::

ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር ሴቶቹ ሰባት በመቶ ለከፋ የደም ግፊት የመጋለጥ እድላቸው ያደገ ሆኖ ተመዝግቧል:: ይህ ማለት የወንዶች 54 በመቶ መሆኑን ነው የድረ ገፁ ጽሑፍ ማደማደሚያ ያደረገው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here