ለጤናማ ሰው ከሚመከረው የእንቅልፍ ጊዜ ያነሰም ሆነ የበዛ ምጣኔ የሚያሳልፉ ጐልማሶች ለአይነት ሁለት የስኳር በሽታ ተጋላጭነታቸውን እንደሚያመላክት ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
ዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን ያገኙትን ውጤት የቫንደር ቤልት ዩኒቨርሲቲ በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው ጤናማ ያልሆነ፣ በባለሙያ ከሚመከረው ያነሰም ሆነ የተራዘመ እንቅልፍ ማዘውተር ከስኳር በሽታ ተጋላጭነት ጋር ይገናኛል::
ባለሙያዎቹ ለአንድ ጤናማ ሰው ከሚመከረው በቀን ከሰባት ሰዓት ያነሰም ሆነ ከዘጠኝ ሰዓት የበለጠ የእንቅልፍ ጊዜ ማዘውተር ከስኳር በሽታ ተጋላጭነት ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል:: ይህ ማለት ኢንሱሊን ሲበዛ በሚደርሰው መነቃቃት የእንቅልፍ ጊዜ ሲያንስ በመድከም ረዘም ላለ ሰዓት መተኛትን ያስከትላል ሲሉ ነው ያብራሩት::
ሰላሳ ስድስት ሺህ ለሚሆኑ ተሳታፊዎች የተዘጋጀውን መጠይቅ ያስሞሉት ተመራማሪዎቹ ቀደም ብሎ ከተደረጉት በተሻለ በእድሜ፣ በሥራ መስክ፣ በመኖሪያ አካባቢ ስብጥር እዲኖራቸውም አስችለዋል:: መጠይቅ የሞሉት ተሣታፊዎችም በማህበረሰብ ጤና ማእከሎች የተመረጡ መሆናቸውን በጠንካራ ጐንነት ገልፀውታል- ተመራማሪዎቹ::
በመጠይቁ የተሰጡ ምላሾችን የተነተኑት ባለሙያዎቹ በባለሙያ ከሚመከረው በቀን ከሰባት ሰዓት ያነሰ በእንቅልፍ የሚያሳልፉ ለዓይነት ሁለት የስኳር ህመም ሊጋለጡ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል::
የአጠረ ጊዜ በእንቅልፍ የሚያሳልፉ ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ እና የአካል እንቅስቃሴ ባለማድረግ የሚመጣ ሊሆን ይችላል ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ:: ሚመከረው የተራዘመ የእንቅልፍ ጊዜ የሚያሳልፉ የስኳር ህመም በሚያደርሰው ድካም መንስሄ ሊሆን እንደሚችልም ነው የጠቆሙት:: በመሆኑም የተራዘመ የእንቅልፍ ጊዜ በተከታታይ መስተዋል የስኳር ህመም ተጠቂነትን መተንበያ ተደርጐ ሊወስድ እንደሚችል አስገንዝበዋል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም