የ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ለተከታታይ 15 ቀናት ተደርጎ ተጠናቋል። ፓሪስ ለሦስተኛ ጊዜ ባዘጋጀችው የኦሎምፒክ መድረክ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ በሴይን ወንዝ ነበር የተደረገው። ይህም አንድ ክፍለ ዘመን ባስቆጠረው የዘመናዊ ኦሎምፒክ ታሪክ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ከስቴዲየም ወጥቶ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ስፖርተኞች እና እንግዶች በረዥሙ የሴይን ወንዝ በመንሸራሸር ዝግጅቱን ሲያደምቁ ታይተዋል። የመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ደግሞ በስታዲዩ ደ ፍራንስ ነው የተከናወነው። በዚህ የኦሎምፒክ ውድድር ከ206 ሀገራት የተውጣጡ ከአስር ሺህ 700 በላይ ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፈዋል። ለዚህ ግዙፍ የስፖርት መድረክ ዝግጅት ፈረንሳይ ከዘጠኝ ቢሊዮን ዮሮ በላይ ወጪ ማድረጓን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል።
ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የኢማኑኤል ማክሮን አስተዳደር የፀጥታ ስጋት አለብኝ በማለት ጥበቃውን ለማጠናከር ከጎረቤት ሀገራት ጭምር የፖሊስ ሠራዊት ወደ ፈረንሳይ አስገብቷል። በአጠቃላይ ከ45 ሺህ በላይ የፖሊስ ሠራዊት መድቦ ሥራው ሲሰራ እንደ ነበር መረጃዎች አመልክተዋል። ቀደም ብሎ የሰው አልባ አውሮፕላን( ድሮን) ጥቃት ስጋት እንዳለበት የገለጽው የፈረንሳይ መንግስት ከወዳጆቹ እንግሊዝ፣ኳታር፣ ቤልጂየም፣ ካናዳ፣ ብራዚል፣ ጣሊያን፣ ፖርቱጋል እና ከመሳሰሉት 40 ሀገራት የፖሊስ ሠራዊት በማስመጣት ጥበቃውን አጠናክሯል።
የተፈራው የፀጥታ ስጋት ሳይደርስ የኦሎምፒክ ውድድሩ በሰላም መጠናቀቁን ዘጋርዲያን አስነብቧል። ያ ማለት ግን ስፖርተኞች እና እንግዶች የፓሪስ ቆይታቸው ያማረ ነበር ማለት እንዳልሆነ መረጃው ያስነብባል። እንዲያውም በቆይታቸው ተማረው እና ተከፍተው ነው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ተብሏል።
የመኝታ ክፍሎች ንፁህ አለመሆን፣ በቂ የመኝታ ክፍል አለመኖር፣ የአየር ማቀዝቀዣ አለመኖር፣ የመጸዳጃ ቤት ቁጥር እና ጥራት አነስተኛ መሆን ስፖርተኞች ሲማረሩባቸው የነበሩ ችግሮች ናቸው። ዘጋርዲያን ይዞት በወጣው ጽሁፍ አንዳንድ ስፖርተኞች ከማረፊያ ክፍላቸው ይልቅ ስቴዲየም ውስጥ ጨርቅ አንጥፈው ይተኙ እንደነበር በምስል አስደግፎ አስነብቧል።
በቂ ምግብ አለመኖርም ለ15 ቀናት የነበረ ሌላኛው ችግር ነበር። የሚቀርበው ምግብ ቢሆን የጥራት ጉድለት እንደነበረበት አትሌቶችን ጠቅሶ መረጃው አስነበቧል። እንግሊዝን የመሳሰሉ ሀገራት ከእነዚህ ችግሮች ለመሸሽ ከኦሎምፒክ መንደሩ በመራቅ የራሳቸውን ምግብ በማጓጓዝ እና ምግብ አብሳይ (ሼፍ) በመቅጠር አትሌቶቻቸውን መግበዋል።
የኦሎምፒክ መንደሩ በቂ የአየር ማቀዝቀዣ እንደሌለው ቀደም ብሎ መነገሩ አይዘነጋም። ይህንን የተረዱት ሀብታሞቹ ሀገራት ካናዳ፣ ታላቋ ብሪታኒያ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ዴንማርክ እና ጃፓንን የመሳሰሉት የራሳቸውን አየር ማቀዝቀዣ በማዘጋጀት ለአትሌቶቻቸው አቅርበዋል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ድሀ ሀገራት ደፍረው ቅሬታ ባያቀርቡም። ዩጋንዳ ግን መፍትሄ ባታገኝም በአየር ማቀዝቀዣዎች መበደሏን በመግለጽ ቅሬታ አቅርባ ነበር።
በፓሪስ ኦሎምፒክ በርካታ አትሌቶች ታመዋል። ለአብነት በአንድ የስፖርት ዓይነት ብቻ አራት ስፖርተኞቿ የታመሙባት ቤልጂየም ሌላ ስፖርተኛ መተካት ባለመቻሏ ከውድድሩ ራሷን አግልላለች። ሌላው የፓሪስ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ሰይጣን የጎበኘው እንደነበር በቀጥታ ስርጭቱ ተመልክተናል፤ ብዙ ጋዜጦችም ዘግበውታል።
ቢሊዮኖች በቀጥታ የቴሌቭዥን መስኮት በተከታተሉት የኦሎምፒክ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት የክርስትና እምነትን እና ፈጣሪን የሚፃረር ሰይጣናዊ ድርጊት ተከናውኖ ተመልክተናል። ይህን ሰይጣናዊ ድርጊትም የኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ የክርስትና እምነት ተቋማት ማውገዛቸው አይዘነጋም።
33ኛው ኦሎምፒያድ አዳዲስ ስፖርቶችም የተዋወቁበት ነበር። የኦሎምፒክ ፎርሙላ አንድ፣ የኦሎምፒክ ታንኳ ውድድር፣ የስኬት ቦርዲንግ ውድድር፣ ተራራ መውጣት፣ በቡጢ ውድድር አዲስ የሴቶች ክብደት መጨመር እና የመሳሰሉት ውድድሮች በፓሪሱ መድረክ ተሞክረዋል። የ2024ቱ የፓሪሱ ኦሎምፒክ ምንም እንኳ እንከኑ የበዛ ቢሆንም በድራማዊ ክስተት የታጀበ፣ አዳዲስ የኦሎምፒክ ጀግኖች የተፈጠሩበት እና ብዙ ክብረ ወሰኖች የተመዘገቡበት ሆኖ ነው ያለፈው።
ኢትዮጵያ ከ24 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን ወርቅ ያገኘችበት እና በ800 ሜትር ደግሞ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ውስጥ የገባችበት ሆኖ ነው የተጠናቀቀው። ሲሞን ባይልስ ለሦስተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የኦሎምፒክ ውድድር በሜዳሊያ የተንቆጠቆጠችበት ነበር።
አልጀሪያዊቷ ቡጢኛ ኢማኔ ክህሊፍ ጣሊያናዊቷን ተጋጣሚ አንጀሊያ ካሬርና ላይ ከባድ ምት በማሳረፍ በቅጽበት ከውድድሩ ውጪ አድርጋታለች። በቡጢኛዋ ኢማኔ ክህሊፍ የጾታ ጉዳይ ውዝግብ ተነስቶ እንደነበር አይዘነጋም። ዘግይቶም ቢሆን ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ምላሽ ሰጥቷል። ሰርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች የመጨረሻውን የኦሎምፒክ ውድድር ነው ያደረገው። ሰርቢያዊው ኮከብ በአራት የኦሎምፒክ መድረኮች ያሸነፈ አምስተኛው የሜዳ ቴኒስ ሰው መሆን ችሏል።
በመድረኩ አዳዲስ ጀግና አትሌቶችንም ተመልክተናል። ፈረንሳዊው ዋናተኛ ሊዮን ማርቻንድ በአንድ መድረክ አራት የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ የመጀመሪያው ፈረንሳዊ ስፖርተኛ ለመሆን በቅቷል። የ22 ዓመቱ ዋናተኛ በኦሎምፒክ ታሪክ ከአሜሪካውያኖች ማይክል ፍሊፕስ እና ማርክ ስፒዝ ቀጥሎ ገና ከወዲሁ ሦስተኛው የዘርፉ ድንቅ ስፖርተኛ መሆኑን አስመስክሯል።
ለኔዘርላንድስ የምትወዳደረው አትሌት ሲፋን ሀሰን በሦስት ርቀቶች በመወዳደር ሜዳሊያ ያስመዘገበች አትሌት ሆናለች። አትሌቷ በአምስት እና ዐስር ሺህ ሜትር ነሐስ እና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች። እ.አ.አ በ1952 በሄልሲንኪ ኦሎምፒክ ቼክ ሪፐፕሊካዊው የረዥም ርቀት ሯጩ ኤሚሊ ዛቶፔክ በሦስት ርቀቶች ተወዳድሮ ካሸነፈ በኋላ፤ ሲፋን በአንድ የኦሎምፒክ መድረክ ሦስት ሜዳሊያ ያሳካች የመጀመሪያዋ አትሌት መሆን ችላለች።
በፓሪሱ ኦሎምፒያድ 31 የዓለም ክብረ ወሰኖች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል ሦስቱ በአጭር ርቀት ሲሆን ኢትዮጵያዊው የማራቶን ሯጩ ታምራት ቶላም ክብረ ወሰን ካስመዘገቡ አትሌቶች መካከል ይገኝበታል። በአጠቃላይ የተመዘገቡት ክብረ ወሰኖች ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጋር ሲነፃፀር በዘጠኝ ይበልጣሉ። ከአራት ዓመታት በፊት በተደረገው 32ኛው ኦሎምፒያድ 22 ክብረ ወሰኖች መመዝገባቸው የሚታወስ ነው። ከስምንት ዓመታት በፊት በሪዮ በተደረገው ኦሎምፒያድ ደግሞ 28 ክብረ ወሰኖች ተሻሽለዋል።
በመም እና በሜዳ ተግባራት እንደተለመደው የአሜሪካውያን ስፖርተኞች የበላይነት የታየበት ነበር። አሜሪካ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሆና ነው ያጠናቀቀችው። 40 ወርቅ፣ 44 ብር እና 42 ነሐስ በድምሩ 126 ሜዳሊያ በመሰብሰብ ውድድሩን ጨርሳለች። ልዕለ ኃያሏ ሀገር ባለፉት ስምንት የኦሎምፒክ መድረክ በሰባቱ በበላይነት ነው ያጠናቀቀችው።
ባለፉት ተከታታይ አራት ዓመታት ደግሞ እርሷን የሚበልጣት ሀገር አልተገኝም። ቻይና በ40 ወርቅ፣ በ27 ብር እና በ24 ነሐስ በድምሩ በ91 ሜዳሊያ ሁለተኛ እና ጃፓን ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አውስትራሊያ እና ፈረንሳይ አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል። ሀገራችን ደግሞ ከዓለም 47ኛ ደረጃ እና ከአፍሪካ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የሩሲያ በውድድሩ አለመሳተፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ትልቅ ለውጥ አሳይቷል። ይሁን እንጂ 15 ሩሲያውያን እና 17 ቤላሩሲያውያን ስፖርተኞች በግላቸው መወዳደራቸውን መረጃዎች አስነብበዋል። ዶሚኒካ፣ ሴንት ሉቺያ፣ ኬፕቨርዴ እና አልባኒያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል።
ቦትስዋና እና ጓቲማላም በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያቸውን የወርቅ ሜዳሊያ አሳክተዋል። የስደተኞች የኦሎምፒክ ቡድንም ለመጀመሪያ ጊዜ በቡጢ ስፖርት የነሐስ ሜዳሊያ አሸንፏል። 34ኛው ኦሎምፒያድ ከአራት ዓመታት በኋላ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ የሚደረግ ይሆናል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም