‘‘እንኳን ደስ አላችሁ!’’

0
148

በሀምሌ የመጀመሪያው ሳምንት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ፔዳ ግቢ/ ከወትሮው በተለዬ ደምቆ ሰንብቷል:: ምክንያቱ ደግሞ ዩኒቨርሲቲው  በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን  8 ሺህ 52 ተማሪዎች ሀምሌ 27/2016 ዓ.ም የሚያስመርቅበት ዕለት መሆኑ ነው። በዕለቱም በዩኒቨርሲቲው ግቢ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ  ተመራቂዎች እና  አስመራቂዎች በተባለው ሰዓት ባይገኙም ቀስ በቀስ  ተሟሉ::

በዕለቱም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ! መልዕክት ካሰሙ በኋላ  ባሰሙት ንግግር  በትምህርት ዘመኑ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ተማሪዎች ውስጥ መውጫ ፈተናውን  በአማካይ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል:: የመውጫ ፈተና ከተሰጡባቸው 78 የትምህርት ክፍሎች መካከል 38ቱ የትምህርት ክፍሎች ሁሉንም 16ቱ ደግሞ በእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ተማሪ ብቻ ሲቀር አሳልፈዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ብዙ ያልተነካ ሃብት እና ዕድል  ለመጠቀም አዲስ ትውልድ እና አዲስ ኀይል ያስፈልጋታል ፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  ለዚህ ትክክለኛው ቦታ  እንደሆነ ነው ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር ያሰሙት።

በዕለቱ በከፍተኛ ውጤት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ሽልማት ተሰጥቷቸዋል:: ከእነዚህም መካከል ኤሊያስ አሸኔ በአካውንቲንግ እና በፋይናንስ የትምህርት ዘርፍ 3 ነጥብ 99 በማምጣት የሜዳሊያ እና የዋንጫ ተሸላሚው ለመሆን በቅቷል:: ኤሊያስ እና አቻዎቹ  ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደገቡ ኮሮና በመከሰቱ በአግባቡ መማር ያልቻሉበት ወቅት  እንደ ነበር ያስታውሳል:: በተቻለ  መጠን ግን በአግበቡ በመረዳዳት ለመለወጥ ጥረት ያደርግ ነበር::

ኤሊያስ እንደሚለው እያንዳንዱ ሰው የራሱ የማንበብ ልምድ አለው ፤  በተቻለው መጠንም ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ የአቅሙን ሊሞክር እንደሚገባ ይመክራል::

በመጨረሻው የትምህርት ዓመት በአግባቡ የመማር ዕድል ማግኘት መቻሉን ፣ የመምህራኑ እገዛ መልካም እንደነበር    እንዲሁም ጥረቱን የደገፈው የፈጣሪ አጋዥነት ለስኬት እንዳበቃው ኤሊያስ ገልጿል። ወላጆች ልጆቻቸው ለውጤት እንዲበቁ ለማድረግ መልካም ስብዕና እንዲኖር አድርገው ማሳደግ እንደሚገባ  ኤሊያስ ያምናል:: እርሱ ላገኘው ውጤትም ቤተሰቦቹን አመስግኗል::

በቀጣይም ደግሞ በተማረበት የትምህርት መስክ ሀገሩን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑንም  የገለፀልን ኤሊያስ  ሁሉም ሰው ለመሥራት እና ለመለወጥ ጥረት ካደረገ ስኬታማ መሆን እንደሚችልም ነው የተናገረው።

ከአዲስ አበባ የመጡት የኤሊያስ ወላጅ እናት ወ/ሮ ፍሬዘውድ ያዴታ ስለልጃቸው በሰጡት አስተያየት “ኤልያስ ከልጅነቱ ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ ነበር:: ባሕር ዳር ሲመደብ ደስ ቢለኝም በመካከል በተፈጠረ የሰላም መደፍረስ መጨረሻ ዓመት በተለይ ጥር ወር ላይ ልጄ ቅር!  ብዬ ለምኜው ነበር:: አሁን ግን ላስቀርበት የነበረውን ማዕረግ ሳስብ ልጄን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ::  አራት ዓመት በጥሩ ሁኔታ አልፎ ላገኘው ከፍተኛ ማዕረግ  እና ለነበረው ነገር የባሕር ዳርን ሕዝብ እና ዩኒቨርሲቲው ምስጋና ይድረሳቸው!” በማለት ነበር::

ሌላዋ በሳይኮሎጅ ትምህርት መስክ በማዕረግ የተመረቀችው ሕሊና ቢተው በበኩሏ  ለምን እንደሆነ ባታውቅም ከልጅነቷ ጀምሮ ሳይኮሎጂ የማጥናት ህልም ነበራት:: ህልሟን እውን ለማድረግም በብርታት ማጥናቷ እና ጊዜዋን በአግባቡ መጠቀሟ እንደረዳት ተናገራለች።

ሕሊና እንደምትለው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደገባች ኮሮና  እና በክልሉ በተከሰተው ጦርነት በትምህርታቸው መስተጓጎል ቢገጥማቸውም  በጥድፊያ ማጠናቀቅ ችለዋል:: ከዚህም ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ስኬታማ ውጤት ለማምጣት እንደሚቻል ተገንዝበናል የምትለው ሕሊና 3 ነጥብ 9 በማምጣት በትምህርት ክፍሏ እና በሴቶች አጠቃላይ የፍተኛ ውጤት ባለቤት በመሆን የሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆኗን በቅታለች።

መምህራን ሲያደርጉላቸው የነበረው ድጋፍ የሚደነቅ እንደነበርም ያነሳችው ሕሊና ተማሪዎች እንደ እርሷ በማዕረግ ለመመረቅ ለጊዜ እና ለዓላማ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ምክሯን አስተላልፋለች። ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር አስቀድመው ማሰብ፣ ችግር ሲገጥም ደግሞ በጽናት ማለፍ  አስፈላጊ መሆኑንም ታምናለች።

ሕሊና በተመረቀችበት የትምህርት መስክ ሀገሯን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኗንም  እና በተመረቀችበት  በሥነ ልቦናው ዘርፍ የራሷን አስተዋጽኦ ለማበርከት ጥረት እንደምታደርግም ነው የገለፀችው።

ሀገር በቀል ዕውቀት በሆነው በግዕዝ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ በከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚው መሪጌታ አብርሐም ዓለማየሁ ናቸው:: መሪጌታ እንዳሉት ከልጅነታቸው ጀምሮ የቤተክህነት ትምህርትን ሲማሩ ቆይተዋል:: በዘመናዊ የትምህርት መስክ  ራሳቸውን ለመፈተን ገብተው ሜዳሊያ ጭምር በመሸለም ለመመረቅ እንደበቁ ነው የሚናገሩት::

ግዕዝ ከሀገራችን ውጭ በሌሎች እንደ ጀርመን በመሳሰሉ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርትነት የሚሰጥ በመሆኑ ትምህርቱን በከፍተኛ የመማር ጉጉት እና ፍላጎት ለማጥናት እንደፈለጉ ነው የተናገሩት:: ለስኬታቸው ምክንያት ደግሞ ለጊዜ ልዩ ትርጉም መስጠት እና ከፋፍሎ መጠቀም እንደሆነ ነው መሪጌታ አብርሐም የጠቆሙት:: ለአብነት በጥናት ወቅት ስልክ እንኳን ቢደወል የማንሳት ልምድ እንደሌላቸውም ነው የገለፁልን::

መሪጌታ አብርሐም  እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ከስልክ ጋር ተያይዞ ጊዜን የማባከን ችግር እንዳለ መታዘባቸውን እና ወጣቱ በተቻለ መጠን ለሁሉም ጊዜን ከፋፍሎ  መሥጠት እና የ”እችላለሁ!” መንፈስን ማሳደር ለውጤት ያበቃል:: መሪጌታ አብርሐም  አካል ጉዳተኝነታቸው  ከስኬት እንዳላስቀራቸው እና  ሌሎች አካል ጉዳተኞችም  ሁልጊዜም ”እንችላለን!” የሚል መንፈስ በውስጣቸው ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል:: “አካል ጉዳተኞች ይከብደናል ብለው  አስቀድመው መሸነፍ  የለባቸውም” በማለትም አስገንዝበዋል::

በቀጣ በተማሩበት ዘርፍ ለሀገራቸው አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም መሪጌታ አብርሐም  ቃል ገብተዋል::  መንግሥትም አካል ጉዳተኞችን በቴክኖሎጅም ጭምር መደገፍ እንደሚገባው ጠይቀዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here