“እንደ ሰው እንሁን”

0
76

የምኖርበት ግቢ ውስጥ ሁለት የአራት እና የሦስት ዓመት ሕጻናት ሴት ልጆች አሉ። አብረው ሲጫዎቱ፣ ሲሳሳቁ፣ በአሻንጉሊት እና እቃቃ ጨዋታ ድክም ብሏቸው ወደ ቤታቸው ገብተው ይተኛሉ።

ከእንቅልፍ በኋላ አንደኛዋ ስትመለስ አዲስ ልብስ ለብስሳ ትመጣለች። ያን ጊዜ አንደኛዋ እሪ ብላ እያለቀሰች ወደ እናቷ ትሮጣለች። “ለእኔም እንደ ሶስና ቀሚስ ግዡልኝ?” ብላ ስቅስቅ ትላለች። እናት ታባብላለች። አልቅሳ ብስኩት ተገዝቶላት በማባበያ ዝም ትላለች።

 

ከሳምንታት በኋላ ደግሞ ባለፈው ስታለቅስ የነበረችው ሕጻን አዲስ ጫማ ተገዝቶላት እሱን ለብሳ ለጓደኛዋ ልታሳያት እየሮጠች ቤቷ ስትሄድ “አውልቂው እሱን ጫማ ያስጠላብሻል” ትላታለች በቁጣ ፊት።  በዚህ ጊዜ “ጫማሽ አያምርም አለችኝ” ብላ እያለቀሰች ወደ እናቷ ትሮጣለች።

 

በዚህ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ አድገናል። አሁንም ቢሆን አብዛኛው ከንጽጽር እና ምቀኝነት የመንጋ አስተሳሰብ አልወጣም። አንደ ተኩላ በራሳችን ፈለግ መጓዝ እስካልጀመርን ጊዜ ድረስ  ውስጣችን አንደ ልጆች ለቅሶ እና ቅናት ያለበት ይሆናል። የምናድገው ይህንን አስተሳሰብ ይዘን ነው። በለጋ እድሜያችን ክፉ የንጽጽር ዘር በቅሎብናል። በራሳችን መንገድ መድመቅ እና መፍካት እንድንችል ሆነን አላደግንም። “እንደ ሃገሩ መምሰል፤ እንደሰው መሆን” በሚሉ የመመሳሰል ልምምዶች ውስጥ ነው ያደግነው። የእኛ ስኬት በዙሪያችን ባሉ ሰዎች ስንፍና እና ጉብዝና ነው እየተመዘነ ያለው። ሰዎች ስላደረጉት ብቻ ብዙ ነገሮችን እናደርጋለን። ደግሞ በጣም ብዙ ወጪዎችን አውጥተን የማይጠቅሙን ነገሮች ላይ ገንዘብ እናባክናለን። ይህ ድርጊት ውስጡ ሲመረመር “ከማን አንሳለሁ” የሚል የቅናት ስሜት ነው። ቤታችን፣ አዕምሯችን፣ አካባቢያችን፣ መስሪያ ቤታችን በማይጠቅሙን ሰውን ለመምሰል በተገዙ እቃዎች እና መመሪያዎች ጥራዝ ሞልቷል።

 

“የማህበራዊ ንጽጽር ንድፈ ሃሳብ” እ.አ.አ 1954 በስነ ልቦና ባለሙያ ሌዎን ፋስቲንገር ይፋ የተደረገ ሐሳብ ነው።

ይህ ንድፈ ሐሳብ “ሰዎች በተደጋጋሚ ራሳቸውን የሚገመግሙት የሌሎች ሰዎችን ሳቢነት፣ ሀብት፣ እውቀት እና ስኬት በማየት ነው” ይላል።

ይህ ጥናት ሰዎች በንጽጽር ሕግ መሰረት ለመሻሻል መነሳሳት ያገኛሉ፤ ወይም ደግሞ ጥልቅ የሆነ ርካታ ማጣት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ጥፋተኝነት፣ ከንቱነት እና አጥፊ የሆኑ ባህሪያት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። መዋሸት እና  የአመጋገብ መዛባት ሊገጥማቸውም  ይችላል ይላል።

 

ንጽጽር ከሚበልጡን እና ከምንበልጣቸው ሰዎች ጋር ይደረጋል። ጥናቶች እንደሚሉት ወደ ላይ ከማነጻጸር ይልቅ ወደ ታች ማነጻጸር ይሻላል። ከእኛ  ከሚበልጡ ሰዎች ጋር ራሳችንን ካወዳደርን የማነስ እና የትንሽነት ስሜት ሊሰማን ነው። በአንጻሩ ከምንበልጣቸው ሰዎች ጋር ራሳችንን ካነጻጸርን ስለራሳችን መልካም ነገር እንዲሰማን ልናደርግ እንችላለን።

 

ይሁን እንጂ ሁለቱም ንጽጽሮች የራሳቸው ችግሮች አሉባቸው ሲሉ የስነ ልቦና ምሁራን ይገልጻሉ። ወደ ላይ ራሳችንን ስናነጻጽር ደህንነት ማጣት እና ቅናት ይፈጠርብናል። ከታችኞቹ ጋር ራሳችንን ስናነጻጽር ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን እና ጉራ እንዲሁም ድንቁርና ሊጋባብን ይችላል። በብዛት ግን የተለመደው ራሳችንን ከሚበልጡን ሰዎች ጋር ማነጻጸር ነው።

 

26ኛ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ንጽጽርን “የደስታ ጠላት ነው” ብለው ገልጸውት ነበር።  በ2008 እ.አ.አ የወጣ ጥናት የሰው ልጆች 12 በመቶ የሚሆኑት ሐሳቦቻቸው ከሌላ ሰው ጋር በማነጻጸር የሚያሰላስሏቸው እንደሆኑ ጠቅሷል። ይህ ውጤትም ከአንድ ቀን ውስጥ 2 ሰዓት ያህሉን ራሳችንን በማነጻጸር ጊዜያችንን እንደምናሳልፍ የሚያመላክት ነው። የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ደግሞ ይህንን ጉዳይ በጣም እያባባሰው ቀጥሏል።

 

በሕንድ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በአማካይ እያንዳንዱ ሰው ሶስት ሰዓታትን ያሳልፋል። ይህም የስራ ሰዓታቸውን 18 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ነው። 90 በመቶ የሚሆኑት የፌስቡክ፣ ኤክስ እና ኢንስታግራም ልጥፎች የሌሎችን ሰዎች አኗኗር እና ሕይወት የሚመለከቱ ናቸው። ይህን ማየታቸው ደግሞ ተመልካቾች በሕይወታቸው ካላቸው ይልቅ የጎደላቸውን እንዲመለከቱ በማድረግ የከንቱነት ስሜት ያሳድርባቸዋል። በዚህ ስሌት ሕንዳዊያን  በየቀን ውሏቸው ውስጥ 30 በመቶ ያህሉን ጊዜ በተስፋ ማጣት እና ከንቱነት ያሳልፉታል ማለት ነው።

 

ንጽጽር በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን የድባቴ እና ጭንቀት ምክንያት ሆኗል። “እንደ እሱ ወይም እንደ እሷ በለበስሁ ነበር፤ ሰውነቴ እንደ እሱ (ሷ) እንዲሆን ብቻ ነው የምመኘው፤ መድረኩን እንደ እሱ ብውረገረግበት ምንኛ በታደልሁ፤ ሕዝብ ፊት እንደ እሷ በራስ መተማመን ብራመድ እንዴት ደስ ባለኝ፤ እንደ እገሊት (ሌ) ሀብታም ብሆን እና ሌሎች መሰል የንጽጽር ሐሳቦችን መስማት በየቀን ውሏችን የሚያጋጥመን ጉዳይ ነው። የዚህ ንግግር ስነልቦናዊ መልእክቱ “እኔ በራሴ ብቁ አይደለሁም” የሚል ነው። የገንዘብ እጥረት፣ የችሎታ ማነስ፣ የተሰጥኦ አለመኖር፣ ወዳጅ አለመኖር፣ ጓደኛ ማጣት፣ ደንበኛ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማጣት ነው ይህንን የሚያስደርገን።

 

ይህን ተከትሎ የቅናት ስሜት፣ ጭንቀት፣ ረዳት አልባነት፣ ዋጋ ቢስነት፣ ድብርት እና ሌሎች አሉታዊ ስሜቶች በሕይወታችን ይከሰታሉ።

አሜሪካዊው ፅሐፊ ጆይስ ማየር “ራስህን ከሌሎች ጋር ማነጻጸርህን አቁም። አንተ ልዩ ፍጥረት ነህ። ሁላችንም ልዩ ነን። ይህ ደግሞ ደስ የሚል ነገር ነው” ይላል። ንጽጽር በተመሳሳይ ነገር ያምራል። ሰዎች ግን ምንም የሚያመሳስል ነገር የላቸውም። ንጽጽሩም በዚህ ሁኔታ ፍትሐዊ አይሆንም። ትንሽ አቅማችንን ከብዙ አቅም ጋር ማወዳደራችን ፍትሐዊ አይሆንም። ሁሉም ሰው የተለየ አቅም እና ስጦታ እያለው በልዩነቱ መኖር ሲችል ንጽጽር ተገቢ አይደለም የሚለውን ሐሳብ ነው ጆይስ የተናገረው። ሁሉም ሰው ወደ ምድር የመጣበት የሕይወት ዓላማ አለው። የተላከበትን ሰርቶ መመለስ ሲገባው ሌላን ሰው በመምሰል ሳይሰራ ይቀራል።

 

የንጽጽር ትልቁ ችግሩ ማለቂያ የሌለው ፉክክር ውስጥ የሚጥል ወጥመድ መሆኑ ነው። የትኛውንም ያህል በስኬት ብንገፋበት ሁልጊዜ ከፍታው ጫፍ ለመድረስ ቀና ብለን የምናያቸው ሰዎች አይታጡም። ካለን ይልቅ በጎደለን፣ ካደረግነው ይልቅ ባላደረግነው ጉዳይ ላይ እንድናተኩር ያደርገናል። የሰዎችን ማረጋገጫ እንድንፈልግ ያደርገናል። ባይሳካልንስ ብለን እንፈራለን። ሰዎች ባስቀመጡን መስፈሪያ  ለመሙላት ስንል ምንም አለመሞከርን እንመርጣለን።

 

እውቁ የስነ ልቦና ባለሙያ ጆርዳን ፒተርሰን ዘ ቲዌልቭ ሩልስ ኦፍ ላይፍ በሚለው መጽሐፉ በአራተኛው ሕጉ ላይ “ሰዎች አሁን ካሉበት ሁኔታ ሳይሆን አንተ ትናንት ከነበርህበት ጋር አነጻጽር” ይላል። በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ሰዎች በተደጋጋሚ የንጽጽር ወጥመድ ውስጥ ይወድቃሉ። ጆርዳን የሚለው ሌሎች ከደረሱበትን የስኬት ሕይወት ይልቅ  አንተ የተጓዝህበትን መንገድ ለካው፣ አስተውለው ነው። በየቀኑ እድገትህን፣ መሻሻልህል እና ስኬትህን መዝነው ይላል።

ጆርዳን የሰው ልጆች በሕይወታቸው ውስጥ ተመሳሳይ መስመር የላቸውም፤ ሁሉም የግሉን ፈለግ ይዞ መጓዝ አለበት ይላል። በዚህም ሌሎችን ለመምሰል ከመሞከር ይልቅ ትናንት ምን ዐይነት ሰው ነበርሁ፤ ዛሬስ የት ላይ ነኝ፤ ነገስ አቅጣጫዬ እንዴት ነው ብለህ ገምግም ነው የሚለን። ሰው በየዕለቱ ራሱን ማሻሻል ላይ እንጂ ከሰዎች ጋር ንጽጽር ውስጥ መግባት የለበትም ብሏል በመጽሐፉ።

 

በአንድ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጭ በሚሊዮን ወይም በቢሊዮን የሚቆጠር ሰው ተመልካች ዘንድ መድረስ ይቻላል። በጣም በብዙ የሚበልጡን ሰዎች ይኖራሉ።

ጀማሪው ዘፋኝ ከዝነኛው፣ ጀማሪው ነጋዴ ከቢሊየነሩ ጋር፣ ጀማሪው አርቲስት ከዓለም አቀፍ አርቲስቶች ጋር፣ አንድ መጽሐፍ የጻፈው ልጅ  ከዝነኛው ደራሲ ጋር ራሱን ማወዳደሩ አይደለም ክፋቱ። እሱን አይቶ አልደርስበትም፣ አልችልም፣ እሱ’ኮ የረዱት ሰዎች አሉ እና ሌሎች መሰል አሉታዊ ሐሳቦችን ማንጸባረቁ ነው።

 

ራስን ከሰዎች ጋር  ማነጻጸር አንድም የቅናት ምልክት ነው። ሁለትም  አቅመ ቢስነትን በራስ አንደበት መመስከሪያ ነው። ሰዎች የደረሱበት ጥግ ለመድረስ የመቧጠጥ ምኞት ነው። ንጽጽር እልህ ውስጥ ይከታል። ለራሳችን ያለንን ግምት እና ችሎታ ያወርዳል። ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል።

ሁሉም ሰው የራሱ ስጦታ ኖሮት ተፈጥሯል። በአኗኗርም ይሁን በተፈጥሮ አንዱ ከሌላው ተመሳሳይ አይደለም። በመንታዎች መካከል እንኳን ልዩነቶች አሉ። ፈጣሪ ለሰው ልጆች ያዘጋጀላቸው ምድራዊ ጸጋ አለ። ያንን ጸጋ ከመጠቀም ይልቅ የሰዎችን ጸጋ ለማግኘት መሞከር ያጎድላል፣ ያሳንሳል እንጂ ከፍ አያደርግም።

 

አኗኗራችን በመንጋነት ነው። ሰዎች የለበሱትን፣ የገዙትን፣ ያደረጉትን፣ የጀመሩትን፣ የተማሩትን፣ የሚያቅዱትን ማድረግ እንፈልጋለን። በራሳችን ጥረት አዲስ መንገድ ለመፈለግ የምናደርገው ሙከራ በጣም ደካማ ነው። ማርታ ካገባች ሜሮንም ማግባት አለባት የሚል የፉክክር መንፈስ ያለበት ማህበረሰብ ውስጥ አድገናል።

የጎረቤት ሰዎች ለፋሲካ በግ ከገዙ እኛም በግ እንግዛ የሚል የመመሳሰል መንጋነት ውስጥ አድገናል። እንግዲህ ጥቅሙን እና ጉዳቱን አውቀን በልዩነት መኖር እንጀምር። ከጎደለን ይልቅ ባለን ነገር እንደሰት፣ እንስራ፣ እናመስግን የሚለው የዘርፉ ምሁራን ምክረ ሐሳብ ነው።

 

“ውሽማዋን አይታ ባሏን ጠላችው” እንዲሉ አበው አሁን ባለንበት ዘመን ማህበራዊ ሚዲያን የሚያይ ሰው የሌሎችን አኗኗር ተመልክቶ  ከራሱ ጋር ይጣላል። ይህ ከራስ ጋር ጠበኝነት ደግሞ አጥፊ ነው። ካስተዋልነው እና ከተጠቀምንበት ውስጣችን ያለው ብዙ ነው። ሌሎች የደመቁ መስለው የታዩን የተሰጣቸውን በመጠቀማቸው ነው። ባለን ብናውቅበትስ?።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here