እንደ እሳት የሚፋጀዉ ዙፋን

0
146

በእግር ኳስ ስፖርት የአሰልጣኞች ሥራ ትልቁ እና አድካሚው ሙያ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። ሁሌም አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ፣ ከተፎካካሪዎቹ በላይ ሆኖ ለመገኘት በርካታ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን ያሳልፋሉ። ተጫዋቾችንም በሚፈልጉት መንገድ ይቀርጻሉ፤ያበቃሉ። ለእግር ኳሱ መንኩሰው ሀሳባቸውን ስለ እግር ኳስ ብቻም ያደርጋሉ።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን እግር ኳስ ተለዋዋጭ እና ፉክክር የበዛበት በመሆኑ የአሰልጣኞችን ሥራ አክብዶታል። በየጊዜው ተለዋዋጭ በሆነው በዚህ ሙያ ስኬታማ የሆኑ አሰልጣኞች ዕድለኛ ያስብላቸዋል። ያልተሳካላቸውን ደግሞ ሲባክኑ እና ሲባዝኑ ማየት የተለመደ ነው። ይህም ሥራቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ ወይም ተገፍተው እንዲወጡ ያደርጋቸዋል።

የአሰልጣኞች የትናንት እና የዛሬ ስኬት ለነገ ዋስትና አይሆናቸውም። ታዲያ ክለቦች አሰልጣኞችን ሲቀጥሩ ውጤትን መሰረት አድርገው በመሆኑ፤ ውጤት ማምጣት ያልቻሉ አስልጣኞችን አይታገሱም። በዘመናዊ እግር ኳስ  አሰልጣኞች በክለቦች ያላቸው የቆይታ እርዝማኔ እያጠረ መጥቷል። ከሌሎች የአውሮፓ ሊጎች በተለየ በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች የአሰልጣኞች ስንብት ይበዛል። በተለይ ፉክክሩ ጠንካራ በሆነበት እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባሉ ሊጎች የአሰልጣኞች የቆይታ ጊዜ አጭር መሆኑን የዋን ፉትቦል መረጃ ያመለክታል። ይህም አሰልጣኞችን ሁሌም በቀጭን መንገድ በስጋት የሚጓዙ ባለሙያዎች አድርጓቸዋል።

በ2024/25 የውድድር ዘመን በአምስቱ ታላላቅ ሊጎች በርካታ አሰልጣኞች ተሰናብተዋል። አስደናቂ ፉክክር በሚታይበት በእንግሊዝ  ፕሪሚየር ሊግ ብቻ እስካሁን ስድስት አሰልጣኞች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል። በዘንድሮው ዓመት የመጀመሪያው ተሰናባች አሰልጣኝ ኔዘርላንዳዊው ኤሪክ ቴን ሀግ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ቴን ሀግን በወርሃ ጥቅምት ማሰናበቱ የሚታወስ ነው።

ስቴቭ ኩፐር ከሌስተር ሲቲ፣ ጋሪ ኦኔል ከወልቨር አምፕተን፣ ሩዜል ማርቲን ከሳውዝ አምፕተን፣ ጁሊያን ሉፕቴጌ ከዌስትሀም እና ሲያን ዲያች ከኤቨርተን እስካሁን ከሥራቸው የተሰናበቱ አሰልጣኞች ናቸው። አምና በፕሪሚየር ሊጉ በአጠቃላይ በውድድር ዘመኑ ሦስት አሰልጣኞች ብቻ ነበር የተሰናበቱት። ዘንድሮ ገና በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የተሰናባች አሰልጣኞች ብዛት ስድስት ደርሷል።

ከስፔን ላሊጋ ደግሞ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አራት አሰልጣኞች ተስናብተዋል። ላስፓልማስ ለአሰልጣኝ ሊዊስ ካርሪዮን የስንብት ደብዳቤ የሰጠ የመጀመሪያው የላሊጋ ክለብ ነው። ፓውሎ ፔዛላኖ ከሪያል ቫላዶሊ፣ ሊዊስ ጋርሺያ ከዲቦርቲቮ አላቬዝ እና ሩበን ባራጅ ከቫሌንሺያ እስካሁን ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ባሳለፍነው ዓመት በላሊጋው 11 አሰልጣኞች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው የሚታወስ ነው።

በጣሊያን ሴሪኤ ስድስት አሰልጣኞች ከሥራቸው ሲነሱ ሮማ አሰልጣኝ ዳንኤል ዲ ሮሲን  ከስታዲዮ ኦሎምፒክ ገፍቶ በማስወጣት ቀዳሚ ክለብ ነው። ሊቼ ሉካ ጎቴን፣ ሮማ ኢቫን ጁሪክን፣ ጄኖዋ አልቤርቶ ጊላርድኖን፣ ሞንዛ አሌሳንድሮ ኔስታን እና ኤስሚላን ፓውሎ ፎንሴካን አሰናብተዋል። በጣሊያን ሴሪ ኤ የያዝነው የውድድር ዘመን ሲጀምር አምስት ክለቦች ብቻ ነበሩ ነባር አሰልጣኞቻቸውን ይዘው የቀጠሉ። በድምሩ 14 የሴሪ ኤ አሰልጣኞች ባለፈው ዓመት ከሥራቸው መነሳታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል። የኔፕልሱ ክለብ ናፖሊ ብቻ አምና ሦስት አሰልጣኞችን ቀያይሯል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የቦቹአም አሰልጣኝ ፒተር ዘይድለር በውድድር ዓመቱ ከኃላፊነቱ የተነሳ የመጀመሪያው አሰልጣኝ ሲሆን ሆፈኒም ፔሌግሪኖ ማታራዞን፣ ዩኒየን በርሊን ቦ ስቬንስን እና በቅርቡ ደግሞ ቦርሲያ ዶርትመንድ ኑሪ ሳሂንን ከሥራቸው ማንሳቱ አይዘነጋም። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ስምንት አሰልጣኞች የስንብት ደብዳቤ ሲደርሳቸው ኦግስበርግ  ሁለት አሰልጣኞችን በማስናበት ብቸኛ ክለብ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

በፈረንሳይ ሊግ አንድ እስካሁን ሦስት አሰልጣኞች ተሰናብተዋል። ሞንቴፕሌር አሰልጣኝ ሚሼል ዴር ዛካሪን ከኃላፊነቱ ያነሳ የመጀመሪያ የፈረንሳይ ክለብ ነው። ሬንስ ጁሊያን ስቲፋንን፣ ሴንት ኢቲን ኦሊቨር ዳል ኦሊጉን ከኅላፊነታቸው አንስተዋል። አምና በፈረንሳይ ሊግ አንድም ስምንት አሰልጣኞች ከአሰልጣኝነት መንበር መነሳታቸውን የዋን ፉትቦል መረጃ ያስነብባል።

በየዓመቱ አዲስ የውድድር ዘመን ሲጀመር ለእግር ኳስ አሰልጣኞች ደስታ፣ ብሩህ ተስፋ እና ሁሌም የይቻላል ስሜት የሚፈጠርበት ወቅት ነው። ቀስ በቀስ ግን ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም የሚፈጠረው ጫና  አሰልጣኞች በክለቦች ያላቸውን ቆይታ እንዲያጥር ያደርገዋል። የእንግሊዝ የአሰልጣኞች ማህበር እንደሚለው ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኞች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ነው ከሥራቸው የሚሰናበቱት። አማካይ በክለቦች የሚኖራቸው የጊዜ ቆይታም አንድ ዓመት ከሰባት ወራት እንደሆነ ያስረዳል።

እንደ ኦፕታ አናሊስት መረጃ በአሰልጣኞች ስንብት ታሪክ በፍጥነት የተሰናበተው የቀድሞው አሰልጣኝ ሌሮይ ሮዘኒየር ነው። የቀድሞው አሰልጣኝ አሁን ላይ በእንግሊዝ ስድስተኛ ሊግ የሚሳተፈው ቶርኳይ ዩናይትድ ክለብን ለማሰልጠን ውል ከፈረመ ከዐስር ደቂቃ በኋላ ውሉ ተቀዶ ከኃላፊነቱ ተሰናብቷል። ይህም በእግር ኳስ ታሪክ በፍጥነት ከሥራው የተሰናበተ አሰልጣኝ አድርጎታል።

ክሪስታል ፓላስ ፍራንክ ዲቦርን እና ዴቭ ባሴትን በቀጠራቸው በአራተኛ ቀናቸው በማሰናበት በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ቀዳሚ ሆኗል። አሰልጣኝ ክርስቲያን ግሮስ ከቶትንሀም ሆትስፐርስ በ21 ቀን፣ ሩድ ጉሌት ከኒውካስትል ዩናይትድ በተመሳሳይ 21 ቀን፣ ግራም ሱነስ ከብላክበርን ሮቨርስ በ23 ቀን፣ ስኮት ፓርከር ከበርንማውዝ በ25 ቀን፣ ቶማስ ቱህል ከቸልሲ በ33 ቀን፣ ግራም ፖተር ከብራይተን ሆብ አልቢዮን በ34 ቀን እና ሆዜ ሞሪንሆ ከቸልሲ በ39 ቀን ፈጣን የስንብት ደብዳቤ ከደረሳቸው አሰልጣኞች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ከአውሮፓ አምስቱ ታላላቅ ሊጎች መካከል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለአሰልጣኞች ምቾት የሚሰጥ ቦታ አይደለም። በአንድ የውድድር ዘመን ብቻ 14 አሰልጣኞች ተሰናብተዋል። ይህም በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። በ2022/ 23 እ.አ.አ የውድድር ዘመን 14 አሰልጣኞች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

ቶማስ ቱህል ከቸልሲ፣ ቡሩኖ ላዥ ከወልቭስ፣ ስቴቨን ጄራርድ ከአስቶንቪላ እና አንቶኒዮ ኮንቴ ከቶትንሀም ለአብነት ስራቸውን ያጡ አሰልጣኞች ናቸው። እ.አ.አ በ2013/14፣ በ2017/18፣ በ2021/22 የውድድር ዘመን ዐስር አሰልጣኞች ከዙፋናቸው መነሳታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል። እ.አ.አ በ1994/95 ፣ 2004 /05 እና 2008/09 የውድድር ዘመን ደግሞ ዘጠኝ አሰልጣኞች ተሰናብተዋል።

በዘመናዊ እግር ኳስ ከአሰልጣኞች የሚፈለገው የጨዋታ እንቅስቃሴ እና ውጤት ካልተገኘ ደጋፊዎችን ትዕግስት አልባ በማድረግ የክለቡ ኃላፊዎች በአሰልጣኞች ላይ እንዲጨክኑ እያደረጋቸው ነው። በዚህ ምክንያት በአሰልጣኝነት ህይወታቸው በተደጋጋሚ ከሥራቸው የተሰናበቱ በርካታ አሰልጣኞች አሉ። አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒየሪ እ.አ.አ በ2015 16 የውድድር ዘመን ከሌስተር ሲቲ ጋር ዋንጫ አሳክቷል። ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦችንም አሰልጥኗል።

አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒየሪ በአሰልጣኝነት  ህይወቱ ስምንት ጊዜ የስንብት  ደብዳቤ የደረሰው ቀዳሚው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ነው። ቸልሲ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ኢንተርሚላን፣ ቫሌንሺያ እና ሮማን የመሳሰሉት የነበራቸውን ውል በማቋረጥ ከኃላፊነቱ አንስተውታል። ዝነኛው እና ስኬታማው ሌላኛው ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲም በአሰልጣኝነት ህይወቱ ከአምስት የተለያዩ ክለቦች የስንብት ደብዳቤ ደርሶታል።

ጁቬንቱስ፣ ኤስሚላን፣ ቸልሲ፣ ሪያል ማድሪድ እና ባየርሙኒክ ካርሎ አንቸሎቲን ያሰናበቱት ክለቦች ናቸው። በተመሳሳይ የፕሪሚየር ሊጉ አንጋፋው አሰልጣኝ ሮይ ሁድሰን፣ አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ እና አሰልጣኝ ሳም አላርዳይስ በአሰልጣኝነት ህይወታቸው በተመሳሳይ አምስት ጊዜ በተለያዩ ክለቦች የስንብት ደብዳቤ ደርሷቸዋል።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here