ክሮሺያዊው ቪቶሚር ማሪች ሦስት ሜትር ጥልቀት ባለው ውኃ የተሞላ ገንዳ ውስጥ ሰጥሞ ያለ መተንፈሻ መሣሪያ እገዛ ወደ ውስጥ ስቦ በገባው ኦክስጂን ብቻ 29 ደቂቃ በመቆየት ለክብረወሰን መብቃቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገፅ ከሳምንት በፊት አስነብቧል፡፡
ድረ ገጹ እንዳስነበበው አብዛኛዎቹ ሰዎች ከጥቂቶች በስተቀር በውኃ ውስጥ ያለመተንፈሻ መርጃ መሣሪያ ለሰኮንዶች ቢበዛ ጥቂት ደቂቃ ነው መቆየት የሚችሉት፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ክሮሺያዊው ነፃ ጠላቂ ወጣት ቪቶሚር ማሪቺ ግን ተገቢውን ስልጠና እና ልምምድ በማድረግ ትንፋሹን ተቆጣጥሮ 29 ደቂቃ በመቆየት አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል፡፡
ቀደም ብሎ ክብረ ወሰን ሆኖ የተመዘገበው 24 ደቂቃ የውኃ ውስጥ ቆይታ ሲሆን ቪቶሚር ማሪች ግን አምስት ደቂቃ አብላጫ ቆይቶ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችሏል፡፡
ቪቶሚር ማሪች ለዚህ ስኬት ለመብቃት ያላሰለሰ ስልጠና እና ልምምድ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል፡፡ ያለ መተንፈሻ መርጃ መሳሪያ አንዴ ስቦ በገባው ኦክስጂን 29 ደቂቃ መቆየት እጅግ ፈታኝ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ወደ ውስጥ የሚገባ ዓየር በሌለበት አንዴ ስቦ ባስገባው ኦክስጂን 29 ደቂቃ መቆየት ደረቱ እና የውስጥ የመተንፈሻ አካሉ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደነበረው ገልጿል- ወጣቱ፡፡
ትንፋሹን አምቆ ሲቆይ በደም ውስጥ የሚንሸራሸረው የኦክስጂን መጠን እያነሰ የካርቦንዳይ ኦክሳይድ መጠን ይጨምራል፤ በዚያን ጊዜ የመተንፈሻ ጡንቻዎች ከቁጥጥር ውጪ ሆነው ወደ ውጪ ለመተንፈስም ሆነ ወደ ውስጥ መሳብን እንደሚያስገድዱ ነው ያረጋገጠው፡፡ ይህንን ማድረግ አለመቻል ደግሞ ህልፈትን እንደሚያስከትል ነው ያሰመረበት- ጠላቂው ቪቶሚር፡፡
ነፃ ውኃ ጠላቂዎች በአካላዊም ሆነ በስነ ልቦና ቅድመ ዝግጅት እና ልምምድ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የጠቆመው ቪቶሚር በመመሰጥ (ኮንሰንትሬሽን)ል የኦክስጂን ፍላጐት እንዳይጨምር ፍርሃት እና ጭንቀትን መቆጣጠር፤ አእምሮን ማረጋጋት፣ ኦክስጂን የመጠቀም ፍጥነትን መቀነስ ዋነኞቹ ስልቶች መሆናቸውን ነው በማደማደሚያነት ያሰመረባቸው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም