“እንዳቅሜ አዋጣለሁ! እንደ ህመሜ እታከማለሁ!”

0
103

ጤና መድኅን አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ አባሉ ወይም ቤተሰቦቹ የጤና መታወክ ሲያጋጥማቸው የህክምና ወጫቸውን  የሚሸፈንበት መንገድ እንደሆነ በሀገሪቱ የጤና ፖሊሲ ላይ ተመላክቷል:: አገልግሎቱ በአማራ ክልል በ2003 ዓ.ም መጀመሩ ያታወሳል::

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ  ወይዘሮ ፋሲካ ወርቁ አንዷ ናቸው:: ወይዘሮ ፋሲካ እንደነገሩን  በባሕር ዳር ከተማ በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል እና በሀናን ጤና ጣቢያ ቤተሰቦቻቸው በተለይም ልጆቻቸው የጤና እክል ሲያጋጥማቸው ቀድመው በከፈሉት አነስተኛ መዋጮ  ያሳክሟቸዋል::

ወይዘሮዋ የማኅብረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አባል ከሆኑ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል:: በዓመት በሚከፍሉት 1ሺህ 300 ብር  መዋጮም  ከቀላል እስከ ከባድ ሕክምናዎችን እንዳገኙ ነግረውናል:: የጤና መድኅን አባል በመሆናቸው  በግል ተቋማት ያወጡት የነበረውን ከፍተኛ ገንዘብም ቀንሶላቸዋል::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሕክምና ባገኙበት ተቋም የታዘዙላቸውን መድኃኒቶች በመንግሥት መድኃኒት ቤቶች ባለመኖራቸው ለከፍተኛ ውጪ መዳረጋቸውን ጠቁመዋል:: የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሉት አንዳንድ ጊዜ በተቋማቱ ከመድኃኒቶች ባለፈ “የዕጅ ጓንት የለም ከውጭ  ግዙ” የተባሉበት ጊዜም አለ:: ከዚህ ባለፈ ግን የማኅብረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ክፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ጉድለቶቹ  እንዲሟሉ ጠይቀዋል፤  ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የጤና መድኅን አባል ቢሆን ተጠቃሚ እንደሚሆንም መክረዋል::

ሌላዋ አስተያየት የሰጠችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ወጣት ቃልኪዳን ሁነኛው ናት::  እሷን ጨምሮ ሦስት ቤተሰቦቿ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ናቸው:: ወጣቷ      እንደገለጸችው እሷና ቤተሰቦቿ የጤና እክል ሲያጋጥማቸው ማንኛውንም ሕክምና በመንግሥት የጤና ተቋማት ያገኛሉ:: አልጋ ይዞ ተኝቶ እስከመታከም ድረስ አገልግሎቱን እያገኙ ነው::

ቃልኪዳን እንደምትለው  በተለይ በግል ተቋማት አልጋ ይዞ ለመታከም የሚጠየቀው ገንዘብ ከአቅማቸው በላይ ነበር:: ሆኖም የጤና መድኅን አገልግሎት ገንዘብ ባይኖራቸውም ሳይቸገሩ በወቅቱ ታክመው እንዲድኑ አስችሏቸዋል:: ነገር ግን አንዳንዴ በጤና ተቋማቱ የሕክምና መሣሪያዎች ስለሚበላሹ በግል የሕክምና ተቋማት በመሄድ ለአልትራ ሳውንድ እና ለራጅ ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጡ እንደተገደዱ ጠቁማለች::

እኛም ተጠቃሚዎች የጠቀሷቸውን አንዳንድ  ችግሮች እና አጠቃላይ የክልሉ የጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ  ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ  በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ቢሮ የመድኃኒት እና ሕክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከአቶ ዘለቀ አበጀጋር ቆይታ አድርገናል::

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ   ተጠቃሚዎች ያነሱት የጤና መድኅን አገልግሎት ቅሬታ ተገቢ ነው:: ሆኖም በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮው የተቻለውን እያደረገ ነው:: ለሁሉም ዜጎች ሁሉን አቀፍ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግም ቀደም ሲል በመኪና ይመጣ የነበረው መድኃኒት አሁን  ባለው የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ   በካርጎ አውሮፕላን ወደ ክልሉ እየገባ  ነው::

የክልሉ ጤና ቢሮ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በገመገመበት ወቅት  እንዳስታወቀው በሥድስት ወሩ ውስጥ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎችን በክልሉ አሰራጭቷል::

የአብክመ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ በበኩላቸው  በስድስት ወራት ቢሮው መሠራት ይገባቸዋል ያላቸውን ተግባራት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል:: በተለይም በሕክምና ግብአት አቅርቦት፣ የፋርማሲ አገልግሎት፣ የሕክምና መሣሪያ ጥገና፣ የመረጃ ሥርዓት… በመሳሰሉት ተግባራት ላይ ባለሙያዎች በችግር ውስጥም ሆነው የግንኙነት ሰንሰለታቸውን በማጠናከር መሰረታዊ ተግባራትን ማከናወን መቻላቸውን ተናግረዋል::

ምክትል ኃላፊው አክለውም የአቅርቦት ስርጭት ፣የፋርማሲ አገልግሎት፣ የሕክምና መሣሪያ ጥገና፣ የመረጃ ሥርዓት በመሳሰሉት የኅብረተሰቡን ጤና ሊያስጠብቁ በሚችሉ የአሠራር ሥርአቶች ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ አየሠራ ያለ መሆኑን ተናግረዋል::

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሀብት አስተዳደር እና አሰባሰብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አበባው እንደገለጹት በክልሉ የጤና መድኅን የተጀመረው በ2003 ዓ.ም ነው:: ያኔ ለሙከራ  በሁለት ወረዳዎች የተጀመረው አገልግሎት አሁን ላይ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች እና ዞኖች ተግባራዊ እየሆነ ነው:: በዚህም ዜጐች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ::

የጤና መድኅን ሥራ ለሕብረተሰቡ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ አዲስ አባላትን ማፍራት እና ለነባር አባላት የእድሳት ሥራዎች እየተሠሩ ነው:: በተያዘው የበጀት ዓመትም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን አባዎራዎችን እና እማዋራዎችን አባል ለማድረግ ታቅዷል:: በዚህም አየተሠሩ ባሉ የአባልነት ማፍሪያ ሥራዎች የስድስት ወሩ አፈጻጸም 50 በመቶ ደርሷል:: አቶ አዲሱ እንደገለጹት የአባልነት ክፍያ የሚፈጸመው በሦስት ምድብ ሲሆን ዝቅተኛ፣መካከለኛ እና የተሻለ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ በመመደብ ነው::

ከአንድ ወር በፊት የአማራ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የጥር ወር የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት የንቅናቄ አፈጻጸም መድረክ በተካሄደ ወቅት የአማራ ክልል ምክትል  ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ.ር) እንደተናገሩት ደግሞ ለሁሉም ዜጎች ሁሉን አቀፍ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች አንዱ ዜጎች ፍትኃዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ  መደረጉ ነው ብለዋል::

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 24  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here