በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች ዘመናዊ ከያኒነትን የሚሹት የውጭውን ዓለም ሙዚቃ በማስመሰል ነው:: አንዳንዶች ደግሞ የሀገራችን የሙዚቃ ቅኝት በሆኑት አንቺ ሆዬ፣ ባቲ፣ ትዝታ እና አምባሰል በመዝፈን ኢትዮጵያዊ ቀለም እና ለዛን ይፈጥራሉ። ክራር፣ መሰንቆ፣ ከበሮ እና ዋሽንትም ለምን እንደተሰሩ ያሳዩናል።
አስቻለው ፈጠነ (አርዲ) ኢትዮጵያዊ ለዛ ባላቸው ሙዚቃዎቹ ወደ አድማጭ ጆሮ ከቀረበ ሰነባብቷል:: እናትዋ ጐንደር እና ካሲናው ጐጃም ደግሞ የአቀንቃኙን ሥራዎች አዳምጠን ጉሮሮህ ይባርክ ያልንባቸው ዘፈኖቹ ናቸው፤ እነሆ አሁን ደግሞ ከሙሉ አልበሙ ጋር ወደ አድማጮቹ ይበልጥ ቀርቧል::
አስቻለው ሲዘፍን ኢትዮጵያዊ ሆኖ ብቻ አይደለም፤ የኢትዮጵያ የሆኑትን ብዙ ነገሮች በማስተዋወቅ ጭምር እንጂ:: በአስቻለው ሙዚቃዎች ውስጥ የባሕል ሙዚቃ መሣሪያዎች ቦታቸው ከፍ ያለ ነው:: ድምፃዊው ከባሕል ሙዚቃዎቻችን በተጨማሪ በዘፈኑ ውስጥ በገለፀው አካባቢ ያሉ እሴቶች ሲያስተዋውቅም አሳጐብኚ እንጂ ዘፋኝ አይመስለም::
እናትዋ ጐንደር እና ካሲናው ጐጃም የተባሉት የአስቻለው ሙዚቃዎች ወደ ሁለቱም አካባቢዎች በምናብ የሚወስዱን ብቻ ሳይሆኑ አካባቢዎቹን እና ሙዚቃ እንደዚህ በውስጡ ብዙ ቁም ነገሮችን ሲይዝ ደስ የሚል ብቻ ሳይሆን ይበል የሚያሰኝም ነው:: እስኪ እኔም አስቻለው ፈጠነ በቅርቡ ከለቀቀው አልበሙ ውስጥ “እንገር ወሎ” የሚለው ሥራውን በወፍ በረር ለመቃኘት ልሞክር::
”ከመቃብር በላይ ስም ይቀራል ብሎ
ፍቀርና ጀግንነት ያውቅበታል ወሎ”
ወሎ በእርግጥም የቆነጃጅት ሀገር ብቻ ሳይሆን የፍቅርም ሀገር ነው:: ‘ስም ከመቃብር በላይ ይውላል’ እንዲሉም ወሎዬዎች አንድም በፍቅር ወይ ደግሞ በጀግንነት ስማቸውን ከመቃብር በላይ አስቀምጠውልን አልፈዋል::
“ወሎ ልበ ሰፊ መተኛ ድንኳን
አበጋር ይፈራል እንኳን አምላኩን”
የአስቻለው ሙዚቃዎች ሙዚቃ ብቻ ሳይሆኑ ታሪክ ጠቃሽ እና ትውፊትን አስታዋሾች ናቸው ላልኩበት አስተያየቴ አንደኛው ማሳያ ይሄው ስንኝ ነው። ወሎ ውስጥ አበጋር የሚባሉት የሀገር ሽማግልዎች ደም የሚያደርቁ አንቱ የተባሉ አስታራቂዎች ናቸው:: አበጋሮች ጋር ቀርቦ አለመታረቅ እና ቂምን እስከወዲያኛው አለመተው በወሎዬዎች ዘንድ አይታሰብም:: በእርግጥም የወሎ ሰው እንኳንስ አምላኩን የሀገር ሽማግሌዎችን ወይም አበጋሮችን ጭምር የሚፈራ ነው::
“የራስ አሊ ሀገር የመሩ ጓንጓል ይሾማል ይቀባል አቡን ይመስል”
ወሎ ሲነሳ የግዛቱ አስተዳዳሪ የነበሩትን እነ ራስ አሊን አለማንሳት መሳሳት ነው፤ አስቻለው ግን አልተሳሳተም፤ ንቡር ጠቃሽ ሆኖ ራስ አሊን እና የፌሩ ጓንጉልን በሙዚቃው አስታውሶናል::
“ሐሊማ ብላችሁ እስኪ ስሟን ጥሩ
መነን አይደለም ወይ የጁ ስልጣን ክብሩ፣
እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ የምወድሽዋ
እንዴነሽ እንዴት ነሽ መገን አንገትዋ፣
የአገር ዋርካ ልኩ ሀገር መንግሥት
ጠቅልል ሰውነቱ አማራ ሳይንት”
የሙሲሊም እና የክርስቲያኑ ባሕል ተዘንቆ ሰውነት ብቻ ከፍ ብሎ በሚታይባት ወሎ ውስጥ ሐሊማም ሆነች እቴጌ መነን፣ የጁም ሆነ አማራ ሳይንት፣ ወሎ ውስጥ ከፍ ብሎ የሚደመጠው ፍቅር ብቻ ነው፤ ይለናል አስቻለው ፈጠነ::
”አንኮበር ወንዝ ላይ አንድ ፀሐይ ወጥታ
መቄት ታየኝ አሉ ብልህ መሪ መርጣ፣
አገር ክተት ብለው በአዋጅ ሲማማሉ
መቶ ከትቶ አደረ ጃማ ወረኢሉ”
አስቻለው በዚህ ሙዚቃው ወሎን በየአቅጣጫው ማስተዋወቁ ብቻ ሳይሆን ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረርችበት ወቅት ወሎ ለአድዋ ድል መገኘት ምን ያህል ሚና እንደነበራትም እያስታወሰን ነው:: አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ክተት ብለው የጠሩት ወሎ ወረኢሉ ላይ መሆኑን ታሪክ መዝግቦታል፤ አስቻለውም ታሪኩን ዘፍኖታል::
‘‘እንዴት ነሽ እነዴት ነሽ የምወድሽዋ
እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ የኔ ሰለውላዋ፣
አንቺ ሆዬ ለኔ ብለሽ ከመጣሽ
በትዝታ አምባሰል ባቲን ቃኝተሽ”
የምወድሽዋ እና የምወድህዋ ወለዬዎች በፍቅር አቆላምጠው የሚጠሩበት ነው:: አንቺ ሆዬ፣ ትዝታ፣ አምባሰል እና ባቲ ደግሞ የኢትዮጵያ አራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች ናቸው:: ይሄንን ታዲያ ሙዚቃ ወይስ የታሪክ ሰነድ እንበለው?
‘‘አደስ ተቀብታ የኔ ሰለውላዋ
የተነደፈ ጥጥ እንገር ነው ገላዋ
መገን አንገትዋ የምወድሽዋ
አርሂቡ በይኛ የኔ ሰለውላዋ፣ ፈረንጅ ገባ ደሴ ቁንጅናሽን ዓይቶ
ላብሽን አንቆርቆሮ ሊያሰራው ነው ሽቶ”
አደስ መቀባት፣ በወይባ መታጠንም ሆነ በሌሎች ባሕላዊ ነገሮች መቆነዳጀት የወሎ ሴቶች መለያ ነው። በተፈጥሮ ውበታቸው ላይ የሚጨምሩት ሰው ሠራሽ ውበት የወሎ ሴቶችን ከውብም በላይ ውብ ያደርጋቸዋል:: የወለዬ ጠረን ከፈረንሳይ ሽቶ የሚያስንቅ ስለመሆኑ አስቻለው ነገሮናል:: ለዚያም ነው ፈረንጆች ከወለዬዋ ላብ ሽቶ መሥራትን የተመኙት::
‘‘አይጠየፍ ሆኖ ይታያል አንገትሽ
ለዳናው ተስዬ እጅሽን ልሳምሽ፣
ጡቷ የራያ ቀንድ ዓይኗ ኮለምላማ
በሌላ አይምጡ እንጂ በይህ በይህማ፣
ሌላኛ ነው መልኳ ጤነኛ ሚሰብር
የምሬን ወድጃት ሐዋን እስከጇ አምባር፣
ሳልደርስ አላማጣ ሳልረግጠው ደጅሽን
ከወንዙ ጠጥቼ አወኩት ጣምሽን”
የአስቻለው ፈጠነ “እንገር ወሎ” ዘፈን፣ ዘፈን ብቻ አይደለም ያልኳችሁ ከላይ የቀረቡትን ስንኞች ስታደምጧቸው ነው፤ የአይጠየፍ ተራራ፣ ስለት የሚቀበሉባቸው ዳናዎች፣ የራያ ቆንጆ፣ የእጅ አምባር እና አላማጣ በወሎ ውስጥ የሚታወቁ ቦታዎች እና የአካባቢው እሴቶች ናቸው:: እነዚህን ከወሎ ቱባ ትውፊቶች የተቀነጨቡ የወሎ መገለጫዎች እያደመጥን ወሎን በምናብ አለማየት ወይም ወሎን ለማየት አለመመኘት አንችልም::
‘‘ሀገርን በፍቅር እንዲህ ሲገልፀው
በጦቢያ ታረቁ ጓንጉል እና አፄው፣
ዋግም ሹም አይጣ የመክሊቱ ሞገስ
ዳና ኸሚስ ታድሮ ሮሐ ይቀደ፣
ላኮመልዛም ብሄድ አልደረስም ሰቆጣ
የራስ ኃይሉን አንገት ከሮም ሳላመጣ”
ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት ሲባል ይቅር መባባሉ የዛሬ ብቻ ሳይሆን በአፄው እና በጓንጉል ዘመን የነበረ ትውፊታችን እንደሆነ አስቻለው ነግሮናል፤ በታላላቅ ሹሞቿ የምትታወቀው ዋግ በንጉሥ ላሊበላ የታነጸው የሮሐ ቤተመቅደስ ዛሬም ድረስ የለምን የሚያስደምም ድንቅ ቅርሳችን ነው:: ይህ ቅርስ ኢትዮጵያ የነበሯትን ቀደምት ስልጣኔ እየመሰከረ ትውልዱን ለራሱ አሻራ የሚያተጋ ህያው ምልክት ነው::
በሰቆጣ ከተማ ውስጥ በስማቸው በርካታ ነገሮች የተሰየሙላቸው ራስ ኃይሉ ለሀገር ክብር ሲሉ አንገታቸው የተቀላ መሆኑን ታሪክ ነጋሪው ሙዚቀኛ አስቻለው ታሪካቸውን በአንድ ስንኝ ይተርክልናል::
‘‘መገን ቅኔ መገን ዜማ
ጃኖ እና መንዙማ”
ኢትዮጵያችን አዛን እና ቅዳሴ ባንድ ላይ የሚሰሙባት ድነቅ ሀገር ናት ጃኖ እና መንዙማም እንዲሁ:: በኢትዮጵያ ውስጥ የሀይማኖት መቻቻል ሳይሆን ዝንቅነት ጐልቶ ይታያል:: በተለይ በወሎ ውስጥ ከሰዎች የስም አሰያየም አንስቶ ያንዱን ሀይማኖት ሌላኛው ማክበሩ በጣም የተለመደ መልካም እሴት ነው:: አስቻለውም በእንገር ወሎ ዘፈኑ ይሄንኑ አስቃኝቶናል::
‘‘እንገር ወሎ
አርሂቡ መጋሎ”
በእርግጥም የወሎዎች ፍቅር በእንገር ይመሰላል፤ መጀመሪያ ቀምሶ ነው፣ እስከመጨረሻው የምንወደው ነው:: አስቻለው ፈጠነ በእንገር ወሎ ዘፈኑ እኔ ከተረዳሁትም በበለጠ መልዕክቶችን አስተላልፏል፤ የእኔ መረዳት ግን በዚሁ ልክ ብቻ በመሆኑ ከያኒውን እና በሙዚቃው ውስጥ የተሳተፉትን ባለሙያዎች በሙሉ ይቅርታ እየጠየኩኝ በድጋሚ ጉሮሮህ ይባረከ! የሚል ምርቃቴን ይድረስህ ብያለሁ::
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም