እንፍጠን!

0
104

በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም እጦት በክልሉ ሕዝብ ማሕበራዊ እንቅስቃሴ፣ በልማት እና በመልካም አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ የፀጥታው አለመረጋጋት ክልሉን በትምህርት፣ በጤና፣ በምጣኔ ሀብት… ወደ ኋላ እንዲቀር እያደረገ ነው፡፡ በተለይም ትምህርት ላይ ያሳደረው ጫና ጎልቶ በመውጣቱ የህፃናትን የነገ ተስፋ ያደበዘዘ እንዲሁም የክልሉን የተማረ የሰው ኃይል ተወዳዳሪነት ሊያደናቅፍ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኗል፡፡

የተከሰተውን  የሰላም መደፍረስ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ወገኖች በሚፈጥሩት የመንገድ መዝጋት ርምጃ በምርት እና በግብአት አቅርቦት እንዲሁም ሥርጭት ዙሪያ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ልማቱንም ሲያስተጓጉል ቆይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም  ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ወገኖች ሕይዎት ላይ የከፋ ችግር እያስከተለ ይገኛል፡፡ በተለይም በህንፃ ግንባታዎች እና በሌሎች ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲቀንስ፣ በሕዝብ ላይም ቀላል የማይባል ሰብአዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱን፣ ሕዝቡ ከልማቱ እንዲነጠል በማድረግ ድህነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ማስጓጎሉን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በሰሞኑ የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ አውስተዋል፡፡

በመሆኑም  የሰላም እጦቱ በክልሉ ሕዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ያሳደረገውን ተጽዕኖ ለመቀልበስ ክልሉ ይታወቅበት ወደ ነበረው የሰላም ሁኔታ ለመመለስ እየተከናወነ ያለው የሰላም መልሶ ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ ክልሉ ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስም ሕዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ተደጋጋሚ ውይይቶችን እንዲያካሂድ ማድረግ፣ ታጣቂ ኃይሎችም ሰላማዊ መንገድን ብቻ ምርጫቸው በማድረግ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ በማሳሰብ ድርድር  እንዲደረግ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ችግሩ ሙሉ በሙሉ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ሰላምን ለማስፈን በተሠሩ በርካታ ሥራዎች አማካኝነት በክልሉ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም እየተገኘ ነው፡፡ ይህንን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል እና ክልሉ ይታወቅበት ወደነበረው የሰላም ቀጣና ለመመለስም ሕዝቡ እና መንግሥት ተናበው ሊተገብሩት የሚገባ አሁናዊ ተግባር ነው፡፡ የክልሉ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የሁሉንም ትብብር እና ድጋፍ የሚጠይቅ ቢሆንም በተለይም ደግሞ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እና የሌሎችንም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ርብርብ እና ድጋፍ አብዝቶ ይጠይቃል፡፡

በየጊዜው እየተፈጠሩ ሕዝቡን እረፍት እየነሱ ያሉ የሰላም እና የደኅንነት መናጋቶች ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ገዥ ትርክት መፍጠር እንደ መውጫ መንገድ ተደርጎ እየተሠራ ያለው ሥራ ሊበረታታ የሚገባው ቁልፍ ተግባር ነው፡፡ በሀገራችን የነበሩ እና ያለፉ የታሪክ እጥፋቶችን በማረም ለብሔራዊ አንድነት ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ እየተሠራበት በመሆኑ ይህ ጅምር ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲሁም እየተፈጠሩ ያሉ ሰው ሠራሽ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መተማመንን መሠረት ባደረገ መልኩ እና በአካታችነት መርህ ሀገራዊ መፍትሄ ለማምጣት ጥረት እያደረገ የሚገኜው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የጀመረውን ሥራ እውን እንዲያደርግ ማገዝ የወቅቱ ቁልፍ ተግባር ነው፡፡

በመሆኑም በሀገራችን ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ አካላት በሙሉ እና ነፍጥ አንግበው በጫካ የሚገኙ ወኖቻችን ጥያቄዎቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቅረብ ወደ ቀደመ ሰላማችን፣ አንድነታችን፣ ኃያልነታችን እና ክብራችን መመለስ መሥራት ጊዜው አሁን ነውና እንፍጠን!

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here