እኛስ…?

0
279

ጊዜው እ.አ.አ ጥቅምት 2ቀን 2022፤ ድርጊቱ የተፈፀመው ደግሞ በአሜሪካ ኦርላንዶ ዲሲ ግዛት ነው:: ነገሩ እንዲህ ነው፦ ፍሎሪዳ ፖለቲክስ ዶት ኮም፣ ፋክስ 13 ኒውስ ዶት ኮም እና ሌሎችም በምስል እና በድምጽ የተቀዳውን መረጃ እንዳጋሩት በኦርላንዶ  መንገድ ላይ የአካባቢውን ተሽከርካሪዎች ፍሰት እና የሰዎችን ደህንነት ለመቆጣጠር በሥራ ላይ የነበረችው የራሽያ ተወላጅ  ጁሊያ ቤስኪን የተባለች የትራፊክ ፖሊስ ከፍጥነት በላይ እያሽከረከሩ የሚመጡ ግለሰብ ተመለከተች:: ልታስቆማቸው ምልክት አሳየች:: ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ እንዲቆሙ በተጋጋሚ ምልክት አሳየቻቸው::

ከቆይታ በኋላ የሁሉም የበላይ ለሆነው ሕግ ሳይወዱ ቆሙ:: ፖሊሷ ወዲያው እንዳስቆመቻቸው ማንነቷን ተናግራ ይህንኑ የሚያረጋግጥላትን መለያዋን /ባጇን/ አሳየቻቸው:: እንደ ማንኛውም ነዋሪ  በደረቷ ላይ ባለው መቅጃ  ድምጻቸው እና ምስላቸው እየተቀረፀ ስለመሆኑም ፈጥና ነገረቻቸው:: የማስቆሟ ምክንያትም በአካባቢው ከተፈቀደው የፍጥነት  ወሰን በላይ ሲያሽከረክሩ እና በተደጋጋሚ ስልካቸውንም ሲነካኩ ማየቷ እንደ ነበር ስልካቸውን በጣቷ እየጠቆመች አብራራችላቸው::

ይህን ጊዜ ባለሥልጣኑ “እንዴት ተደፈርሁ! እንዴት በአንዲት ተራ ሴት እንድቆም ተጠየቅሁ!” በሚል አካኋን “ጣትሽን ወደ እኔ አትጠቁሚ!” በሚል ንቀት ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት:: እርሷም ጣቷን አቅጣጫ ለመጠቆም እንደሆነ ነገረቻቸው፤ “ለመሆኑ ማን እንደሆንሁ ታውቂያለሽ!? ባታውቂኝ ነው እንጂ ብታውቂኝ ኖሮ ደፍረሽ ለማስቆም አትሞክሪም ነበር!” ሲሉ በምፀት መለሱላት:: እርሷ ግን ታውቃቸዋለች፤ “አዎ በትክክል አውቅዎታለሁ!” በማለት ቆፍጠን ብላ መለሰችላቸው::

ማርቲን ሀይድ  የተባሉት  የኮንግረስ አባል በትራፊክ ፖሊሷ  እንዲቆሙ የተጠየቁት በሰዓት 40 ማይል በሚያስኬድ መንገድ ላይ 57 ማይል እየከነፉ እና ስልካቸውን እየነካኩ መልእክት እየተላላኩ   ስለነበር ነው:: ፖሊሷ ስልካቸውን መነካካት ትተው መንጃ ፈቃዳቸውን  እንዲሰጧት ጠየቀቻቸው:: “ለመሆኑ ማን እንደሆንሁ ታውቂያለች” ሲሉ በድጋሚ በንቀት ጠየቋት፤ “አዎ አንድ የአሜሪካ ነዋሪ ነዎት፣ አሁን ደግሞ ሕግን ጥሰዋልና መንጃ ፈቃድዎትን ቢሰጡኝ መልካም ነው!?” በማለት በትህትና ጠየቀቻቸው:: እርሳቸውም የግዳቸውን መንጃ ፈቃዳቸውን እያጉረመረሙ አቀበሏት፤ የኢንሹራንስ ወረቀትም እንዲሰጧት ቀጥላ ጠየቀች፤ የኢንሹራንሱን ወረቀት ግን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም፤ ደግማ እንዲሰጧት ትብብራቸውን ጠየቀቻቸው::

እርሳቸው ግን የተጠየቁትን ከመስጠት ይልቅ ዛቻቸውን ቀጠሉ:: “እዚህ ከኔ ጋር እንድትነጋገሪ የሚያደርግሽ ስደተኝነትሽ ነው:: ተሰደሽ ነው የመጣሽው! ካንች ጋር አልነጋገርም በአስቸኳይ ተቆጣጣሪሽን /ሱፐርቫይዘርሽን/ ጥሪልኝ! ተቆጣጣሪሽ በአስቸኳይ እንዲመጣና ከእርሱ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ!” ሲሉ ጮሁባት::

የተባለው ተቆጣጣሪ እስኪመጣም በካሜራ እየተቀረፁ በሀገሪቱ ያለውን የፖሊስ አዛዥ፣ ከንቲባውን እና የከተማዋን አስተዳዳሪ ስልክ በመደወል ካሉበት ድረስ እንዲመጡ አዘዙ:: እሷም በጥንካሬዋ እንደቆመች ባለሥልጣኑን መንገድ ላይ አስቁማ ጠበቀች:: ከመኪናቸው ወርደው ከወዲያ ወዲህ እየተንጐራደዱ “ከኮንግረሱ አባል ጋር እንደዚህ ፊት ለፊት ማውራትሽ እንዴት ዋጋ እንደሚያስከፍልሽ አሳይሻለሁ!” በማለት ዛቻቸውን ቀጠሉ:: ስልካቸውን አንስተውም ለባለሥልጣናት እንደደወሉና እንደሚመጡ ገለፁላት::

እሷ ምን ግዷ፤ የአሜሪካ ነዋሪዎች ሕግ ከማን በላይ መሆኑን ለመግለጽ “ይህ አሜሪካ ነው!” እንደሚሉት ሕግ አስከባሪዋም በጥንካሬዋ ፀንታ “አሁንም ለደህንነትዎ ሲሉ መኪና ውስጥ ገብተው ይቀመጡ፤ አለያ ከመንገድ በላይ ተሻግረው ከሚታይ ቦታ ይቀመጡልኝ! አለዛ ግን ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነኝ!”   በማለት  ልክ እንደማንኛውም ሕግ እንደጣሰ የአሜሪካ ዜጋ ወይም  ሕግ እንደጣሰ የአሜሪካ ነዋሪ  አሳወቀቻቸው::

በዚህ ሁኔታ የተጠሩት ሁሉ ከቦታው እስኪደርሱ በመጠባበቅ ላይ እያሉ  “የምጽፍብዎት ሦስት ተከታታይ ቅጣቶችን ነው:: ከፍጥነት በላይ በማሸከርከር እና ስልክ በመነካካት ሲሆን ለሕግ አካላት ባለመተባበር በሚለውም ጨምሬ እቀጣዎታለሁ” ስትልም ነገረቻቸው:: ወዲያውኑም ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር እና እያሽከረከሩ መልዕክት በመጻፍ እንዲሁም የመንጃ ፈቃድ ለመስጠት ባለመተባበር በሚል ሦስቱን ጥፋታቸውን አከታትላ አሰፈረች:: ይህን የተመለከቱት ባለሥልጣን  “ቆይ ይህን ሥራሽን ባላሳጣሽ!” ሲሉ ዛቱባት:: ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረችው ጠንካራዋ የፖሊስ አባል ስምንተኛ ዓመቷን እንደማትቀጥል እየዛቱ ነገሯት:: “አስባርርሻለሁ!” አሏት::

በዚህ በሁለቱ ክርክር መሀል አንድ የፖሊስ አባል በአካባቢው ደርሶ ምን እንደተፈጠረ ጠየቀ:: “ለባለሥልጣን አክብሮት ስለማትሰጥ እንደምትባረር ንገራት! አባርራታለሁ! ማን እንደሆንሁ አታውቅም! ለ25 ዓመታት ተከብሬ በኖርሁበት ከተማ እንዲህ ያለ ውርደት ተዋርጀ አላውቅም! የገዛ ልጄም የፖሊስ አባል ነው:: እንዲህ ያለ ውርደት እና ክብር አጥቸ አላውቅም! እንዴት የኮንግረስ አባል ሆኜ ልቀጣ ይገባልን?” ሱሉ ለፖሊስ አባሉ ደረሰብኝ ያሉትን በደል በንዴት አስረዱት::

የፖሊሷ አለቃ /ሱፐርቫይዘር/ ደግሞ በፍጥነት ከቦታው ላይ ደርሰ::  ጉዳዩን ለማጣራት እርሳቸው ወደቆሙበት ሲሄድ “ይሄውልህ ክብሬ በከፍተኛ ሁኔታ ተነክቷል! ተዋርጃለሁ! በኖርሁበት ከተማ እንድቀጣ ተደርጌያለሁ! አንተነህ አለቃዋ!?” ሲሉ ጠየቁት::

“አዎ ጌታዬ ይረጋጉ! ይቀመጡ!  መጉላላት እንደደረሰበዎት ይገባኛል:: ከፖሊሷ ደረት ላይ እንደሚመለከቱት ካሜራ አለ:: ሁሉም ንግግራችሁ ተቀድቷል:: የዚህን የቪዲዮ ቅጅ አይተን ጥፋቱ የእርሷ ከሆነ ጥፋቱን ለእርስዎ አሳውቀን በቢሮ ደረጃ እንቀጣታለን:: ጥፋቱ የእርስዎ ከሆነ ደግሞ እንደማንኛውም የአሜሪካ ነዋሪ እርስዎም ቅጣቱን ይቀበላሉ” ይላቸዋል::

ንዴታቸው ጨመረ፤ “የ150 ሺህ ዶላር መኪና እኮ ነው የምነዳው! ከ25 ዓመት በላይ ኖሬ በተከበርሁበት፤ ተመርጨ እያስተዳደርሁ ባለሁበት ከተማ በፍጹም ይህ ሊሆን አይችልም” በማለት  መለሱለት::

ጉዳዩም በባለሙያዎች ተመረመረ፤ ውጤቱ ግን ባለሥልጣኑ ሲናገሩት ከነበረው በተቃራኒው ነበር:: ሲያንቋሽሿት እና ሲያመናጭቋት የነበረው እርሳቸው መሆናቸውን የቪዲዮ ቅጅው አሳዬ:: አንገታቸውን በሀፍረት እንዲደፉ አደረጋቸው:: የሳራሶታ ፖሊስ ጽ/ቤትም ሥራዋን ከተቀመጠላት ዝንፍ ሳታደርግ የፈፀመችውን ጠንካራዋን የፖሊስ አባላቸውን እንደሚደግፉ እና ውጤቱም በትክክል እርሳቸውን እንደሚያስቀጣ መሰከሩ::

የማይቀረው ቅጣት የተጻፈላቸው ባለሥልጣኑ ከቅጣቱ ባሻገር ፖሊሷን ይቅርታ እንዲጠይቋት በዚህም ደግሞ በማህበራዊ ድረ ገጽ በግዛቲቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ወጥተው ሕዝቡን ይቅርታ እንዲጠየቁ ተበየነባቸው:: “ከሳምንት በፊት” አሉ ባለሥልጣኑ፤ ስብር ባለ ቅስም “በሀገሬው መገናኛ ብዙኃን በቴሌቪዥን እየታየሁ በመኪናዬ ፍጥነት ሳቢያ በሳራሶታ  ውስጥ በትራፊክ እንድቆም በተገደድሁበት ወቅት ፖሊስ መኮንኗን ክብር የጐደለው፣ ያልተገባ… የተናገርሁ አስፀያፊ ሰው ነበርሁ!” ሲሉ በራሳቸው አንደበት ገለፁ::

“ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ላይ በሁሉም በቪዲዮ በብዛት ተሠራጭቷል:: ስለባህሪዬ ብዙ አስተያየት ተሰጥቶኛል:: አሁንም በማንም ላይ ማሳበብ አልፈልግም:: ጥፋተኛ እና  ቆሻሻ ሰው ነኝ” ሲሉ ነበር ራሳቸውን በድጋሚ የገለፁት::

“ብዙዎች ይህን ሳደርግ የመጀመሪያዬ እንዳልሆነ የጻፉብኝንም ተመልክቻለሁ:: ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ነገር አድርጌ ከሆነ ይህ የመጨረሻ መማሪያየ ነው:: ቁጡ ሰው ነኝ:: ያ ደግሞ ፈጽሞ ሊሠራ አይችልም:: ትክክል አይደለሁም፤ ላስተካክል ይገባል:: የፖሊስ አባሏንም በግል ይቅርታ ጠይቄያታለሁ:: አሁን ደግሞ እንደማኀበረሰብ የከተማዋን ነዋሪ፣ የሀገሪቱን ሕዝብ በሙሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ! ይቅርታ! ከዚህ በኋላ የምላችሁ ባህሪዬን ማስተካከል እና ማሳየት፣ እናንተንም ማኩራት እፈልጋለሁ:: ላደረስሁት በደል ሙሉ በሙሉ ስብር ብየ ይቅርታ እጠይቃለሁ!” ሲሉ ማርቲን ሀይድ ደጋግመው ይቅርታ ጠየቁ::

በሥልጣናቸው መመካታቸው እና ስደተኞችን በሚያገል የዘረኝነት ንግግራቸው የተበሳጩ ብዙ ብዙ ብለዋል:: ባለሥልጣኑ በስተመጨረሻ ኩምሽሽ፣ እፍር ብለው በማህበራዊ ገጻቸው ባሰራጩት ጽሑፍ “ምን አይነት ቆሻሻ ሰው ነኝ!” ሲሉም ነው ስብራታቸውን የገለፁት:: ይህን ስብራታቸውን ያዩ አሜሪካዊያንም “ሕግ የሚከበርባት አሜሪካ ናት፤ ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም” ሲሉ እንደገሰጿቸው መረጃው አስነብቧል::

ጠንካራዋ ፖሊስ ማንኛውም የአሜሪካ ዜጋ እና ነዋሪ የሀገሪቱን የትራፊክ ሕግ አክብሮ እንዲንቀሳቀስ የተጣለባትን ኃላፊነት ይወጣ ዘንድ የአካባቢው ከፍተኛ ባለሥልጣን /የኮንግረስ አባል/ መኪናቸውን ከተወሰነው ፍጥነት በላይ እያሽከረከሩ እና  የእጅ ስልካቸውን /ሞባይላቸውን/ እየነካኩ ስታይ አስቁማ እንዲቀጡ አድርጋለች:: ሥልጣን ከሕግ በላይ እንዳልሆነም ፖሊሷ አሳውቃለች:: እኛስ ስንቶቻችን ነን    ለባለሥልጣን፣ ለዘመድ፣ ለንዋይ…ሳንገዛ የተጣለብንን ኃላፊነት የምንወጣ?

(ሙሉ አብይ)

በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here