ጂት ኩንዶ የተለያዩ የማርሻል አርት አይነቶች ድብልቅ ውጤት ነው። ጂት ማለት መከላከል ሲሆን ኩንዶ ደግሞ ማጥቃት ማለት ነው። ብሩስ ሊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ወቅት ጓደኞቹን ሰብስቦ በማሰራት ስፖርቱን የፈጠረው ሲሆን ከሀገሩ ቻይና ግን ውግዘት ደረሶበት እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። በኋላ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ እና ስመ ጥር ሰፖርት መሆን ችሏል። ስፖርቱም ወደ ፊልሙ ዓለም እንዲገባ እና ተወዳጅ እንዲሆን አድረጎታል።
የጂት ኩንዶ ማርሻል ጥበቦች ከሁሉም አይነቶች የተለያዩ ስልቶች እና ትምህርቶች ተለቅመዉ ተካተውበታል። በዚህም ተቀናቃኝ የሚያውቀውን እና የሚችለውን በማወቅ፤ ከተቀናቃኝ በልጦ መገኘትን ያስተምራል። በተወሰነ መርህ እና ሕግ ብቻ መታጠርንም አይፈቅድም። በዚህ መሠረት በጂት ኩንዶ ጥበብ ከወገብ በታች ይሄን ያክል በመቶ፣ ከወገብ በላይ ይሄን ያክል በመቶ መጠቀም የሚል ህግ የለም፤ በነጻነት ማስኬድ ይቻላል። ምቶች፣ አርቶች (ጥበቦች) እና የሰርከስ አይነቶችም እንዲሁ ወሰን የላቸውም፤ ይህም ሰልጣኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ያስችላቸዋል።
የጂት ኩንዶ መሰረታዊ መመሪያዎች ቀላልነት (simplicity)፣ ቀጥተኛነት (directness) እና ነጻነት (freedom) ናቸው። “ቅርጽ የሌለው ቅርጽ” ሲልም የስፖርቱ ጀማሪ ብሩስ ሊ ይገልጸዋል። ቴክኒኮቹ እና ፍልስፍናዎቹ በእውነተኛ ፍልሚያዎች እና በፈታኝ የህይወት ገጠመኞች ውስጥ ቢተገበሩ ውጤታማ እንደሚያደርጉ ያስረዳል።
አሁን ላይ ስፖርቱ በኢትዮጵያ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በስፋት ይዘወተራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን እየተዘወተረ ይገኛል። የጂት ኩንዶ ማርሻል ጥበብ ስፖርት፤ በሀገራችን የስፖርት ማህበራት ደንብ እና ሕግ አልወጣለትም። በስፖርት ኢንቨስትመንት ፈቃድ ላይ ከተዘረዘሩት ስፖርቶች ውስጥ የጂት ኩንዶ ስፖርት የለም። ዘርፉ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም አይታወቅም።
በተጨማሪም በስፖርት ኢንቨስትመንት ፈቃድ ላይ በተዘረዘሩት ስፖርቶች ላይም የጂት ኩንዶ ስፖርት አልተካተተም። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ሌሎቹ ክልሎች ስፖርቱ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ቦታዎች እየተዘወተረ ይገኛል። በቦርና መካነ ሰላም፣ ለጋምቦ፣ መሀል ሳይንት፣ አማራ ሳይንት እና ኮምቦልቻን በመሳሰሉት የጂት ኩንዶ ጥበቦች ስልጠና እየተሰጡ ናቸው። የጂት ኩንዶ ጥበቦች ክለቡ በ2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ውድድር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና በመሳተፍ የብር ሜዳሊያን አስመዝግቧል።
የጂት ኩንዶ ማርሻል ጥበቦች በአማራ ክልል መሰጠት የተጀመረው በ2011 ዓ.ም ነው። በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ የሚገኘው የሳዳም የጂት ኩንዶ ስፖርት ክለብ ነው በክልሉ ዘርፉን ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው። የአካባቢው ማህበረሰብ እና የከተማ አስተዳደሩ የስፖርት ጽ/ቤት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገላቸው መሆኑን አሰልጣኙ ማስተር ሳዳም ሀብታሙ ከአሚኮ በኵር ስፖርት ዝግጅት ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል። የስፖርት ክለቡ እስካሁን ከ300 በላይ ሰልጣኞችን አፍርቷል። ከእነዚህ ውስጥ 61ዱ በዳን እና በጥቁር ቀበቶ ለአሰልጣኝነት በቅተዋል።
ምንም እንኳ ስፖርቱ በአማራ ክልል እንግዳ ቢሆንም ተቀባይነትን ግን አግኝቷል። ስፖርቱ ተሳታፊዎችን በአዕምሮ እና በአካል ብቃት ቀልጣፋ እና ንቁ ያደርጋቸዋል። ጥንካሬንም የሚጨምር በመሆኑ የሰልጣኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህ ደግሞ የማዝወተሪያ ስፍራ እጥረት ችግር እንደ ፈጠረባቸው ማስተር ሳዳም ተናግሯል። እንደ አሰልጣኙ ገለጻ “ስልጠና የምንሰጠው በቀበሌ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ነው። አዳራሹ የቀበሌ በመሆኑ እኛ በምንፈልገው ወቅት አናገኘውም። ስብሰባ ካላቸው እኛ ስልጠናችንን ለማቋረጥ እንገደዳለን”። ሲል ተደምጧል። እናም የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው አሰልጣኙ ጠይቋል።
የጂት ኩንዶ የማርሻል ጥበቦች በሁሉም የማህበረሰብ ክፍል እንዲሰርጽ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እና የአካባቢው ባለሀብቶች እንዲደግፏቸው ጠይቋል። የሱፍ ኑሪዬ በሳዳም ጂት ኩንዶ ማርሻል ጥበቦች ክለብ ስልጠናውን እየተከታተለ ይገኛል። ሰልጣኙ ባለፉት አምስት ዓመታት በስልጠናው አልፏል። ታዲያ የወሰደው ስልጠና በአዕምሮ፣ በአካል ብቃት እና በስነ ምግባር የተሻለ ሰው እንዲሆን እንዳገዘው ይመሰክራል። ታዲያ የጂት ኩንዶ የማርሻል ጥበቦች የቤት ውስጥ ስፖርት በመሆኑ የማዝወተሪያ ስፍራ ችግር እንዳለባቸው ተናግሯል። ችግራቸውም መፍትሄ እንዲሰጣቸው ይጠይቃል።
የስፖርቱ ተሳታፊ የሱፍ ኑርዬ በቀጣይ የጂት ኩንዶ ማርሻል ጥበቦች ክለብ በማቋቋም፤ በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ስኬታማ የሚሆኑ ሰልጣኞችን የማፍራት ዕቅድ እንዳለው በቆይታችን ነግሮናል። ስፖርቱን በሌሎችም የአማራ ክልል ከተሞች ለማስፋፋት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ የተናገረው ማስተር ሳዳም “ማህበር” ለመመስረት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ይህን ለማድረግ ግን መጀመሪያ ከዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ እና ከክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ፈቃድ እና እውቅና ማግኝት ይኖርበታል።
ከዚህ በፊት በ2014 ዓ.ም ልክ እንደ ጥቂት ባህላዊ ስፖርቶች እውቅና ባይሰጣቸውም ስፖርቱ እንዲስፋፋ ታስቦ እውቅና ተሰጥቷቸው እንደነበር በአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የሰፖርት ፋሲሊቲ እና የማዝወተሪያ ስፍራ ዳይሬክተር አቶ ባንተአምላክ ተናግሯል። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን የደቡብ ወሎ ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ስፖርቱ ለምን አገልግሎት እና ለምን አላማ እንደሚውል አላውቅም በማለቱ እንዲታገድ ተደርጓል።
በዞኑ ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ ዓላማ የስፖርት ማዝወተሪያ ሥፍራ ተፈቅዶላቸው በሌላ ህገወጥ ሥራ ተሰማርተው መገኘታቸው አይዘነጋም። ታዲያ የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምንም እንኳ የጂቲ ኩንዶ ማርሻል ጥበቦች በሀገራችን እንደ ስፖርት ባይመዘገብ እና እውቅና ባይሰጠውም በሌሎቹ ክልሎች እየተዘወተረ በመሆኑ ስፖርቱ እንዲስፋፋ ይፈልጋል።
ለሳዳም የጂት ኩንዶ የማርሻል ጥበቦች ክለብ ፈቃድ ለመስጠትም የዞኑ የስፖርት መምሪያ የስፖርቱን ምንነት መርምሮ ለክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ማሳወቅ እንዳለበት አቶ ባንተአምላክ ተናግሯል። አሊያ ደግሞ ስፖርቱ እንዲመዘገብ የኢትዮጵያን የስፖርት ማህበራትን መጠየቅ ይገባል ብለዋል። ስፖርቱ በስልጠና እና ውድድር ወቅት በሰዎች ላይ አደጋ እና ተጽእኖ የማይፈጥር ከሆነ ስፖርቱ ሊስፋፋና ደንብ ወጥቶለት ሊዘወተር ይችላል። አሊያ ግን በኢትዮጵያ የስፖርት ማህበራት ያልተመዘገበን ስፖርት እንዲስፋፋ ማድረግ ተጠያቂም ያደርጋል ነው የተባለው።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም