እየሩሳሌም

0
65

በመካከለኛው ምስራቅ ክልል የተለያየ ባህል፣ እምነት፣ ታሪክ መሰረት በሆነው የፍልስጥኤም ምድር ውስጥ የተቆረቆረችው እስራኤል ከዓለም እድሜ ጠገብ ሀገራት አንዷ ናት። እስራኤል ስትነሳ ወደ አእምሮ ቀድሞ የሚመጣው እየሩሳሌም የሚለው ስም ነው። በእብራይስጥ ቋንቋ የሩሻሎም ሲሆን ሰላም የሚል ትርጓሜ አለው። እናም ይህችን ታሪክ ጠገብ የእየሩሳሌም ከተማ ለማስጎብኘት የሽርሽር አምዳችን ምርጫ ሆናለች።

የእየሩሳሌምን ታሪክ በቀላሉና በጥቂት ቃላት ብቻ ጠቅለል አድርጎ ለመግለፅ አዳጋች ነው። የቅሬተአካል ቁፋሮ ምርምር ባለሙያዎች እንደሚሰጡት ግመታ በከተማው የመጀመሪያ ሰፈራ የተካሄደው በ4500 ዓመተ ዐለም ገደማ ነበር፤ ይሁን እንጂ እየሩሳሌም የአይሁድ ግዛተ መንግሥት ዋና መዲና የሆነችው በ1002 ዓመተ ዓለም በንጉሥ ዳዊት ዘመን ነበር። በዘመኑ የዳዊት ከተማ ትባል ነበር። ይህም ማለት የአይሁድ ሕዝብ  ያለምንም መቆራረጥ ለ3000 ዓመታት ያህል በእየሩሳሌም ከተማ ኖረዋል ማለት ነው።

እየሩሳሌም በተለያዩ የውጭ ኃይላት ተገዝታለች። ፋርሳውያንን ፣ ሮማውያንን፣ ኦቶማን ቱርኮችን፣ እና የእንግሊዝ ግዛተ መንግሥትን ጨምሮ ከ40 በላይ ወረራዎችን አስተናግዳለች። እየሩሳሌምን ለመያዝም ከ100 በላይ ጦርነቶች መደረጋቸውን ታሪክ ያስረዳል። ከዚህ የተነሳ እየሩሳሌም የተለያዩ ባህሎችን ተፅእኖ ያስተናገደች የታሪክ፣ የባህል እና የእምነት መዘክር ናት። በወራሪዎች እየተገፋች እየሩሳሌም እየፈረሰች የተሰራችባቸው ብዙ አጋጣሚዎችም አልፈዋል።

እየሩሳሌም የምትታወቅበት የመጀመሪያው ታላቁ ቤተ መቅደስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን በ10ኛው ዓመተ ዓለም አጋማሽ ላይ ሲገነባ እስከ 150ሺ ሰራተኞች ተሳትፈው ነበር። ይሁን እንጂ በወረራ ምክንያት ፈርሶ ሁለተኛው ቤተመቅደስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ6ኛው ክፍለ ዘመን እንደገና ተገነባ እና እስከ 70 ዓመተ ዓለም ድረስ ቆይቷል። በሮማውያን ወራሪዎች የአይሁድ ከተሞች በወደሙበት ወቅት ከእየሩሳሌም ብቸኛው የተረፈው የከተማዋ ምእራባዊው ግድግዳ ሲሆን እስካሁን ቆሞም በቱሪስቶች እየተጎበኘ ይገኛል።

አይሁዳውያን በግንብ የተከበበችውን እየሩሳሌምን ጨምሮ ከተሞቻቸው ስለወደሙ፤ እስራኤላውያን ወደ አውሮፓ ተሰድደው ለ2000 ዓመታት ያህል በሰው ሀገር ለመኖር ተገድደዋል። ነገር ግን ለታሪክ ምስክር የቀረው ብቸኛው ምልክት የምእራቡ የእየሩሳሌም የግምብ ክፍል  በስደት ለነበሩት እስራኤላውያን የተስፋ እና የህብረት ምንጭ ሆነላቸው።

በፈራረሰችው እየሩሳሌም የቀሩት አይሁዶችም በተረፈው ግምብ  ዙሪያ ኑሯቸውን መስርተው ማንነታቸውን እና እምነታቸውን ጠብቀው ሲኖሩ በውጭ ሀገራት የተሰደዱት ደግሞ የመሰባሰብና ወደ እየሩሳሌም የመመለስ ህልም በልባቸው ተክሎ በተስፋ የመኖር ፅናት ሆነላቸው። እየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ዋነኛው የቱሪስት መስእብም ይኸው ነው።

እየሩሳሌም ከተማ ከተማ በግንብ የታጠረች ከተማ ናት። የግምብ ቅጥሯ 2.5 ማይል ርዝመት፣ 40 ጫማ ቁመት እና ስምንት ጫማ ውፍረት አለው። በእየሩሳሌም የግምብ ቅጥር ላይ 34 የመጠበቂያ ማማዎች ያሉ ሲሆን ለትራፊክ ሲባል ሰባት መግቢያዎች አሏት።  እየሩሳሌም አብርሃማዊ ሀይማኖቶች የሚባሉት የአይሁድ፣ ክርስትና እና የእስልምና ሀይማኖቶች ቅዱስ ስፍራ ስትሆን በየዓመቱ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይጎበኛታል። ከ50 በላይ ቤተክርስትያኖች፣ 33 መስጅዶች እና 300 የአይሁድ ምኩራቦችን ይዛለች።  ከ60 በላይ ሙዚየሞች ይገኙባታል።

እየሩሳሌም አስደናቂ ከተማ ናት። ውብ የሆነ ባህል፣ ታሪክ፣ ኪነ ሕንፃ እና ከሁሉም በበለጠ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ የታወቁ መዳረሻዎች ያላት እና ዓለም ካሏት ድንቆች አንዷ የግድ መታየት ያለባት ግሩም ስፍራ ናት። በዓለም ጥንታዊ ከተማ እንደመሆኗ ከሁሉም የዓለም መዓዘናት በርካታ ጥንታዊ እና ዘመናዊ ባህሎችን ያቀፈ ታሪክ የሞላባት ከተማ ስለሆነች ለጎበኛት ሁሉ ልዩ ተመክሮ ትሰጣለች፣ እየሩሳሌም። እየሩሳሌም የአይሁድ፣ የክርስትያኖች እና የሙስሊም ቅዱስ ስፍራ ናት። ብዙዎቹ ወደ ዚህች ከተማ ቅዱሳን ስፍራዎችን ለማየት ሀይማኖታዊ ጉዞ እንደሚያደርጉ እና ከዚህ በፊት አይተው የማያውቁትን ሕያው እምነትን ይቋደሳሉ።

አሮጌዋ ከተማ

አሮጌዋ የእየሩሳሌም ከተማ ከዘፍጥረት ልትቀድም እንደምትችል ይነገርላታል። መፅሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ላይ እንደተገለፀው፣ በአሮጌዋ ከተማ እምብርት ላይ ያዬው የቤተመቅደሱ ተራራ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብርሃም ልጁን ይስሀቅን ሊሰዋበት ከነበረው ስፍራ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። ከ2000 ዓመታት በፊት የነበሩት የአይሁድ ቤተመቅደሶች መፅሐፍ ቅዱሳዊ ስፍራዎች ማእከል ነበረች። ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ የሁለተኛው ቤተመቅደስ ምእራባዊ የቅጥር ግድግዳ ብቻ ተርፎ ቆሞ ይገኛል። በዚሁ ስፍራ ያለው ሌላ ታሪካዊ ስፍራ እየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለበት የሚታሰብበት ጎልጎልታ አሁን በቤተክርስትያኑ ውስጥ ቅዱስ የመቃብር ስፍራ ሆኖ ተቀድሷል። የአለቱ ጉልላት በእስልምና ካሉ የተቀደሱ ስፍራዎች አንዱ የሆነ ሙሃመድ ወደ ጀነት ያረገበት እና ሌሎች አስገራሚ ስፍራዎች ያሉበት ነው። በእየሩሳሌም ካሉ ታሪካዊ ከተሞች ጥቂቶቹን እነሆ።

የተረፈው ግድግዳ

ምእራባዊው ግድግዳ ለአይሁዳውያን እጅግ ዋነኝ ስፍራ ነው። በእየሩሳሌም ካሉት እጅግ ዋነኛው ታሪካዊ ስፍራ ምእራባዊው ግንብ ነው። ይህ አይሁዶች ለመፀለይ እና ለመሰባሰብ የሚመጡበት ቅዱስ ስፍራ ነው። አካባቢውን ለረጅም ዘመናት ቅኝ ከገዙት ከኦቶማን ቱርኮች ዘመን ጀምሮ የአይሁድ ሕዝብ መንፈሳዊ ጉዞ የሚያደርጉበት ቅዱስ ስፍራ ነው። በእያንዳንዱ ዓመት አያሌ ሕዝብ እየመጣ ይጎበኘዋል። ምእራባዊው ግድግዳ  ሁለተኛው ቤተመቅደስ ሲፈርስ የተረፈው ብቸኛ የከተማዋ ቅጥር አምዱ አካል ነው። በሌላ በኩል የለቅሶ ግድግዳ ይሉታል ምክንያቱም አይሁዳውያን በ70 ዓመተ ዓለም ላይ ለፈረሰው ግንብ የለቅሶ እንጉርጉሮ የሚያደርጉበት ስፍራ በመሆኑ ነው። በእብራይስጥም ኮቴል ይሉታል።

የዳዊት ከተማ

የዳዊት ከተማ የሀገሪቱ ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሰው ይጎበኘዋል። እንደ አንድ ወሳኝ የአርኪዮሎጂ ስፍራ ዛሬ ለጎበኘው ሁሉ ጥንታዊቷን እየሩሳሌምን የሚገልጥ ድንቅ ስፍራ ነው። በእየሩሳሌም እጅግ ገናና ከሆኑት የቱሪስት መስእቦች አንዱ የሆነው የዳዊት ከተማ በርካታ መስእቦችን ይዟል።

የቅዱስ መቃብሩ ቤተክርስትያን

ይህ እየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ስፍራ የተገነባ በክርስትያኖች መንደር ያለ ቤተክርስትያን ነው። የተገነባው ንጉሥ ታላቁ ኮንስታንቲን በ4ኛው ክፍለ ዘመን ክርስትናን ከተቀበለ እና የሮማ ግዛተ መንግሥት ብሔራዊ ሀይማኖት ካደረገው በኋላ ነበር። ከመላው ዓለም ለክርስትያኖች መንፈሳዊ ጉዞ የሚያደርጉበት ቅዱስ ስፍራ ነው። ቤተክርስቲያኑ ውስጣዊ ክፍሉ በአስደናቂ ሀይማኖታዊ ስእሎች የተሞላ ውብ የኪነ ሕንፃ ቅርፅ ያለው ነው።

የድንጋይ ጉልላት

የድንጋይ ጉልላቱ የእስልምና ሶስተኛው ቅዱስ ስፍራ ነው። እንዲሁም ለአይሁድ እና ለክርስቲያኖችም እንዲሁ ወሳኝ ስፍራ ነው። እስላማዊ ትውፊት ይህን ስፍራ ነብዩ ሙሃመድ ወደ ሰማይ ያረጉበት ስፍራ እንደሆነ ይጠቁማል። ሙስሊም ያልሆኑ ጎብኝዎች በሙስሊሞች የመጎብኛ ሰዓት መግባት አይፈቀድላቸውም። ነገር ግን ሙስሊም ያልሆኑ በሚጎበኙበት ሰዓት እንዲገቡ እና በቤተመቅደሱ ተራራን እንዲጎበኙ ይፈቀዳል። ይህ ስፍራ በሌላ መልኩ በአይሁድ ትውፊት መሰረት የሞሬ ተራራ ይባላል። ይኸውም አብርሀም ልጁን ይስሀቅን አይኑን ሸፍኖ ለእግዚአብሔር መስዋእት ሊያደርገው ሳለ መልአኩ ገብርኤል መጥቶ እንዲተው ያዘዘበት ስፍራ ነው። እንዲሁም ንጉሥ ሰሎሞን ለቃል ኪዳኑ ታቦት የመጀመሪያውን ቤተመቅደስ የገነባበት ስፍራ ነው ይባላል።

የዳዊት ማማ

የዳዊት ማማ ወይም ደግሞ የመጠበቂያ ምሽግ የሚባል ሲጆን ከጃፋ መግቢያ በር ቀጥሎ ይገኛል። አሁን የሚታየው ህንፃ በመካከለኛው ዘመን እንደተገነባ ይነገራል። ይሁን እንጂ ከመነሻው የተገነባው በ1ኛው ክፍለ ዘመን፤ በንጉሥ ሔሮድ ን ቤምእራብ በኩል መግቢያ እንዲሆን ታስቦ የተገነባ ነበር።

በአጠቃላይ ታሪካዊቷ እየሩሳሌም ከተማ ከመላው ዓለም እየመጡ ሰዎች የሚጎበኟቸው ከላይ ከገለፅናቸው የሚበዙ ታሪካዊ እና ሀይማኖታዊ ስፍራዎችን የያዘች አስገራሚ ስፍራ ናት። ኢትዮጵያውያንም እየሩሳሌምን በሕይወት ዘመን ቢያንስ አንዴ ሂደው ለመጎብኘት የሚመኟት ነበረች። ነገር ግን የሕዝቡን በጉዞ የሚደርስበትን እንግልት ለመቀነስ ንጉሥ ላሊበላ በእየሩሳሌም አምሳል ላሊበላን እዚሁ በኢትዮጵያ በመገንባቱ እዚያ ድረስ የመሄዱ ነገር ሙሉ በሙሉ ባይባልም፤ እንደቀረ ታሪክ ያስረዳል። መልካም የልደት በዓል እየተመኘን አበቃን።

አጭር እውነታ

እስራኤል

የተቆረቆረችው ፡ 1948 ዓ.ም- ነው፡፡

ዋና ከተማ፡ ኢየሩሳሌም (በአለም አቀፍ ደረጃ ክርክር ያለባት) ቢሆንም

መገኛ አካባቢ፡ መካከለኛው ምስራቅ

ህዝብ፡ ከ9 ሚሊዮን በላይ

ቋንቋ፡ ዕብራይስጥ (Hebrew)፣ አረብኛ፡፡

ሀይማኖት፡ የአይሁድ ሀይማኖት ዋና ነው፣ ክርስቲያንና ክርስትና ሙስሊም ከስልምና የሞት ባህር (Dead Sea)፡ በዓለም ዝቅተኛው የመሬት ስፍራ

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የታህሣስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here