እየተነቃቃ ያለዉ የቅርጫት ኳስ ቡድን

0
150

የቅርጫት ኳስ ስፖርት ከሌሎች ስፖርቶች አንጻር ሲታይ አነስተኛ የማዝወተሪያ ስፍራ፣ አነስተኛ በጀት እና  የሰው ኃይል የሚፈልግ የስፖርት ዘርፍ ነው። ታዲያ ይህ ዘርፉ በቀደሙት ጊዜያት በባሕር ዳር ከተማ በስፋት ይዘወተር እንደነበር የሚታወስ ነው።

አሁን ላይ በከተማው የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ እየተስፋፋ ቢመጣም  ስፖርቱ ግን  ተቀዛቅዟል። በከተማው ብቸኛ የሆነው የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ክለብ ቀደም ባሉት ጊዜያት በከተማው የነበረውን ድምቀት ለመመለስ እየተጋ ይገኛል።

በ1993 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅርጫት ኳስ ፕሮጀክት በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች መጀመሩን ታሪክ ያስታውሰናል። ባሕር ዳር ከተማም የዚህ መርሀ ግብር አካል በመሆኗ በከተማው  የቅርጫት ኳስ ፕሮጀክት በሁለቱም ጾታዎች ተቋቁሟል።  ከ13 ዓመት በታች የሆኑ 15 ታዳጊዎች ይዞ ነው የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሮጀክት የተጀመረው።

በወቅቱ ባሕር ዳር ልዩ ዞን የላብ መተኪያ 150 ብር፣ ፕሮጀክቱን ያስጀመረው አካል ደግሞ የስፖርት ትጥቅ፣ ቁሳቁስ እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ የሴቶች ቅርጫት ኳስ እንዲነቃቃ አሻራ አሳርፏል። ከሁለት ዓመታት የስልጠና ጊዜ በኋላ ማለትም ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮጀክቱ በክልሉ እና በተለያዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ጀምረዋል።

በተሳተፉባቸው መድረኮችም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ለአብነት በ1995 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ በተካሄደው ከ15 ዓመት በታች የፕሮጀክቶች ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ አሸንፈዋል። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ተሳትፈው ሻምፒዮን ሆነዋል።

ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እነዚህ የፕሮጀክት ተጫዋቾች ወደ አዋቂዎች ተሸጋግረው በተለያዩ ውድድሮች መሳተፍ ጀመሩ። ምንም እንኳ በክለብ ደረጃ ተቋቁሞ ውጤታማ የነበረ ቢሆንም በባለቤትነት ይዞ የሚደግፋቸው ተቋም ግን አልነበረም። ተጫዋቾችም ውድድር ብቻ ሲኖር በቀን ውሎ አበል እየተወዳደሩ እስከ 2008 ዓ.ም ቆይተዋል።

ክለቡ በ2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የከተሞች ዋንጫ (City Cup) ውድድር ላይ ባሕር ዳር ከተማን ወክሎ በመሳተፍ ዋንጫ ማሳካት ችለዋል። ከአንድ ዓመት በኋላ በድሬድዋ በተካሄደው በዚሁ መድረክ የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ክለብ ዋንጫውን ማንሳቱ የሚታወስ ነው። በዚህ ዓመት በአማራ ክልል መዲና በሆነችው ባሕር ዳር ከተማ በተደረገው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታም ማሸነፋቸው አይዘነጋም።

በ2007 ዓ.ም ደግሞ አርባ ምንጭ ላይ በተከናወነው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና ላይም የባሕር ዳር ሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን ነበር ያሸነፈው። በ2009 ዓ.ም የአማራ መንገድና ህንፃ ዲዛይን ቁጥጥር ድርጅት ክለቡን በባለቤትነት በመያዝ እስከ 2014 ዓ.ም አስተዳድሮታል። የቅርጫት ኳስ ቡድኑ ችግር በመጠኑም ቢሆን ተቀርፏል።

ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ ስፖርት ክለብ በባለቤትነት ይዞ እያስተዳደራቸው ይገኛል። አሁን ላይ የስፖርት ክለቡ አቅሙ በፈቀደው ድጋፍ እና ክትትል እያደረገላቸው መሆኑን የክለቡ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር በለጠ ፀጋ ከአሚኮ በኵር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ለተጫዋቾች ወርሃዊ ክፍያ ጨምሮ አስፈላጊው የስፖርት ቁሳቁስ እየተሟላልን ነውም ብለዋል- አሰልጣኙ።

ለተጫዋቾች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው የተናገሩት አሰልጣኙ ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ግን አሁንም ከሌሎች የሀገራችን የቅርጫት ኳስ ክለቦች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች እንዲኮበልሉ አድርጓል። ዘርፉን የሚቀላቀሉ ተተኪዎችም በብቃት እንዳይወጡ፣ በሴቶች ቅርጫት ኳስ የታዳጊ ፕሮጀክቶች እንዳይስፋፋ አድርጓል ነው የተባለው።

የባሕር ዳር ከተማ የሴቶች ቅርጫት ኳስ ቡድን ባሳለፍነው ዓመት ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው አይዘነጋም። ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በዚህ በባሕር ዳር ከተማ ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። “ከመስከረም ጀምሮ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ቅድመ ዝግጅት ስናደርግ ነው የቆየነው፤ በቴክኒክ በታክቲክ እና በአካል ብቃት ጥሩ ሆነን ለመቅረብ ተዘጋጅተናል፤ አሁንም እየተዘጋጀን ነው። ባለፈው ዓመት የነበሩብንን ክፍተቶች ዘንድሮ በሚገባ አስተካክለን ጠንካራ እና የተሻለ ክለብ ለመሆን እየሠራን ነው” ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል።

ጥሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ የተናገረችው የክለቡ ተጫዋች ፍሬህይወት ሲሳይ ናት። ተጫዋቿ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ በዋንጫ ታጅበው እንደሚያጠናቅቁም እምነትን አሳድራለች።

“አነስተኛም ቢሆን አሁን ላይ ወርሃዊ ክፍያ እና ጥቅማጥቅም እናገኛለን፤ ይህ ደግሞ ያበረታታል። ጠንክረን በመሥራት ሻምፒዮን የመሆን ዕቅድ አለን” ብላለች።  ኢንስትራክተር በለጠ ፀጋም ፕሪሚየር ሉጉን በበላይነት በመጨረስ በአፍሪካ መድረክ ለመሳተፍ ዕቅድ እንዳላቸው ነግረውናል።

በኢትዮጵያ ሴቶች የቅርጫት ኳስ  ፕሪሚየር ሊግ ስድስት ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን አማራ ክልልን ወክለው ፋሲል ከነማ እና ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሴቶች ቅርጫት ኳስ  ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል። ውድድሩ ታህሳስ ስድስት እንደሚጀምር አወዳዳሪው አካል አሳውቋል።።

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here