እጃቸዉ ያልተባረከላቸዉ

0
187

በእግር ኳስ ስፖርት ግብ ጠባቂዎች እና ተከላካዮች በመጀመሪያው የሜዳ ክፍል የሚገኙ ሲሆን ሚናቸውም መረባቸውን አለማስደፈር ነው። ከተከላካዮቹ የበለጠ ግን የግብ በሩን የመጠበቅ ተግባር እና ኃላፊነት የግብ ጠባቂዎቹ መሆኑ ይታወቃል። ግብ ጠባቂ ስህተቱ የሚጎላ፣ ጀግንነቱ ደግሞ የሚረሳ ነው። በግብ ጠባቂው እና በመረቡ መካከል ቀጭን መስመር ብቻ በመኖሩ ቦታው ይቅርታ የሌለው ነው ሲሉ ብዙዎቹ ይገልጹታል። ምክንያቱም ስህተቱ በጭራሽ የማይታረም በመሆኑ ነው።

ግብ ጠባቂ ከሌሎች የበለጠ ትልቅ ኃላፊነትም የተሸከመ ነው፣ የግብ በሩን ከመጠበቅ ባለፈ የተከላካይ ክፍሉን የማደራጀት ኃላፊነትም ይኖርበታል። እርሱ በጥሩ መንገድ ኳስን ካስጀመረ ኳስን መስርቶ ለሚጫወት ቡድን ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በአጠቃላይ ግብ ጠባቂዎች የስኬትም፣  የውድቀትም መነሻ ለመሆን ቅርብ ናቸው ይባላል። በዚህ ወሳኙ የሜዳ ክፍል ኳስ እና መረብ እንዳይገናኝ የግብ በሩን የሚጠብቁት ግብ ጠባቂዎች ተገቢውን ክብር እያገኙ እንዳልሆነ ግን አያጠያይቅም።

ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ ግን ጫናቸውን  በደንብ የተረዱ አንድ አንድ ክለቦች እና አሰልጣኞች ለግብ ጠባቂዎች የተለየ ትኩረት እና ክብር ያላቸው እንዳሉ መዘንጋት የለብንም።  የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን “ማጥቃት ጨዋታዎችን አሸናፊ ያደርጋል፣ መከላከል ደግሞ ዋንጫን አሸናፊ ያደርጋል” ይላሉ።

የኋላ ክፍሉን አስተዋጽኦ በደንብ የተረዱት ስኮትላንዳዊ አሰልጣኝ በእርሳቸው ዘመን ፒተር ሽማይክል፣ ኢድዊን ቫን ደር ሳር እና ዴቪድ ዲሃያን የመሳሰሉ ግብ ጣባቂዎች ከፍ ያለ ክብር ይሰጣቸው  እንደነበር ታሪክ ያወሳል። በአጠቃላይ በእግር ኳስ ታሪክ በርካታ ስመ ጥር ጀግና ግብ ጠባቂዎች ታይተው አልፈዋል፤አሁንም እየታዩ ነው።

ከቀደሙት ግብ ጠባቂዎች መካከል  ተገቢውን ክብር የተሰጠው ግን ሩሲያዊው የቀድሞ ግብ ጠባቂ ሌቭ ያሺን ብቻ ነው። ያሺን በአንድ ክለብ ብቻ ነበር ተጫውቶ ያለፈው። በዳይናሞ ሞስኮ በተጫወተባቸው 20 ዓመታት ውስጥ ክለቡ በርካታ ዋንጫዎችን እንዲያነሳ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል። ይህ ብቻ አይደለም 150 ፍጹም ቅጣት ምቶችን ማዳኑን የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል። በእግር ኳሱ ታሪክ ዓለም ካያቸው ግብ ጠባቂዎች መካከል ያሺንን የሚወዳደር እንደሌለም ይነገርለታል።

ሌቭ ያሺን እስካሁን ድረስ ባሎንዶርን ያነሳ ብቸኛው ግብ ጠባቂ ጭምር ነው። “ጥቁር ሸረሪት” ተብሎ የሚጠራው ያሺን በ1963 እ.አ.አ የባሎንዶርን ሽልማት ያገኘበት ወቅት ነው። ላለፉት 61 ዓመታትም ይህን ክብረ ወሰን የሚጋራ ግብ ጠባቂ አልተገኘም። የዓለም የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ ይህን ታላቅ ግብ ጠባቂ ለመዘከር በእርሱ ስም ሽልማት አዘጋጅቶ በየዓመቱ እየሰጠ ይገኛል። እ.አ.አ ከ1994 ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት በየዓመቱ ምርጥ የውድድር ጊዜ ለሚያሳልፉ ግብ ጠባቂዎች “የያሺን ዋንጫ” እየተበረከተላቸው ነው።

ጀርመናዊው የቀድሞ ግብ ጠባቂ ኦሊቨር ካህን በዓለማችን ከታዩ ምርጥ ግብ ጠባቂዎች መካከል ሌላኛው ነው። ኦሊቨር ካህን በባየርን ሙኒክ ቤት በቆየባቸው 14 ዓመታት አስደናቂ ጊዜን ማሳለፉ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ያስታውሳል። ከባቫሪያኑ ክለብ ጋርም ያላሳካው ክብር የለም። ካህን ምንም እንኳ በ2002 እ.አ.አ ከጀርመን ጋር የዓለም ዋንጫውን ባያነሳም ሀገሩ ፍጻሜ ድረስ እንድትጓዝ ትልቁን አስተዋጽኦ አድርጓል።

የቀድሞው ጀርመናዊ ግብ ጠባቂ በወቅቱ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች እንደነበረም አይዘነጋም። የእግር ኳስ ቤተሰቡም ባሎንዶር ይገባቸው ነበር  ብሎ ከሚያስባቸው ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ነው ኦሊቨር ካህን። ነገር ግን ባሎንዶርን ሳያገኝ በ2001 እና በ2002 እ.አ.አ በተከታታይ 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።

ሌላኛው የቀድሞ ስፔናዊ ግብ ጠባቂ ኢከር ካሲያስም ከምርጥ ግብ ጠባቂዎች ተርታ የሚሰለፍ ነው። ለ16 ዓመታት ባንጸባረቀበት  ሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ከኃያሉ ክለብ ሪያል ማድሪድ ጋር ያላሳካው ክብር አልነበረም። ከሀገሩ ስፔን ጋርም የዓለም እና የአውሮፓ ዋንጫን አሳክቷል።

ጣሊያናዊዎቹ  ጂያሉንጂ ቡፎን እና ዲኖ ዞፍ፣ የቼክ ሪፐብሊኩ ፒተር ቼክ፣ ዴንማርካዊው ፒተር ሽማይክል እና ኔዘርላንዳዊው ኢድዋን ቫን ደር ሳርን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እነዚህ ግብ ጠባቂዎች በዘመናቸው አስደናቂ ገድልን ፈጽመዋል። በንስር ዓይናቸው ግብ የሚሆኑ ኳሶችን አድነዋል። ክለባቸውን፣ ቡድናቸውን ተሸክመው ከጉድ አውጥተዋል፣ ለክብርም አብቅተዋል። ነገር ግን እነዚህ ግብ ጠባቂዎች በዘመናቸው ተገቢውን ክብር እንዳልተሰጣቸው ብዙዎቹ የሚስማሙበት ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለግብ ጠባቂዎች የሚሰጠው ትኩረት፣ ክብር እና ተፈላጊነታቸው  እየጨመረ መጥቷል።  በዘመናዊ እግር ኳስ የግብ ጠባቂዎቹ ሚና መጎልበቱ እና ሥራቸውም በመብዛቱ ነው ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣው። አሁን ላይ የግብ ጠባቂዎቹ የዝውውር ዋጋ እና ደሞዛቸው በእጅጉ ጨምሯል።

ለአብነት በ2018 እ.አ.አ ቼልሲ ለኬፓ አሪዛብላጋ 71 ሚሊዮን ፓውንድ፣  በተመሳሳይ ዓመት ሊቨርፑል ለአሊሰን ቤከር 65 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ሲያደርግ፣ ማንቸስተር ዩናይትድም ባሳለፍነው የክረምት ወር ለአንድሬ ኦናና 44 ሚሊዮን ማውጣቱ የሚታወስ ነው።

አሰልጣኞችም ግብ ጠባቂዎችን ለቡድን ግንባታ መሰረት አድርገው እየተመለከቷቸው ይገኛሉ። የግብ በሩን ከመጠበቅ ባሻገር ለቡድን ግንባታ ወሳኝ በመሆናቸው በእግራቸውም እንዲጫወቱ እያበረታቷቸው ነው። አጫጭር ቅብብሎችን መጫወት እና ዓላማ ያላቸው  ኳሶችን ወደ ታጋጣሚ የግብ ክልል የበለጠ ማስጠጋት እንዲችሉ ኃላፊነት ይሰጧቸዋል። በእግራቸው የሚጫወቱት እነዚህ ግብ ጠባቂዎች ደግሞ ዘመኑ የሚፈልገውን የእግር ኳስ ክህሎት የያዙ በመሆናቸው ዘመናዊ ናቸው ተበሎ ይታመናል::

ዘመናዊ ግብ ጠባቂ በሁለት እግሮቹ ኳስን የሚጫወት በጭንቅላቱ ኳሱን የሚያጸዳ ቀልጣፋ እና ፈጣን መሆን እንዳለበት የአሰልጣኞች ድምጽ ድረ ገጽ  መረጃ ያመለክታል ። ለዘመናዊ ግብ ጠባቂዎች መንገዱን የጠረገው ደግሞ ጀርመናዊው ማኑኤል ኑዬር ነው።የባየር ሙኒኩ ግብ ጠባቂ በእግሮቹም ሆነ በእጆቹ በጥሩ መልኩ ይጫወታል። ተጋጣሚ ቡድንን በመልሶ ማጥቃት ከጥቅም ውጪ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት ባየር ሙኒክ ማኑኤል ኑዬርን ትልቁ መሳሪያው አድርጎ ሲጠቀም መቆየቱ አይዘነጋም።

የ35 ዓመቱ ግብ ጠባቂ በ423 የቡንደስ ሊጋ ጨዋታዎች 197 ጊዜ ግብ ሳይቆጠርበት ከሜዳ ወጥቷል። አሁን ላይ በአውሮፓ  አምስቱ ታላላቅ ሊጎች የእርሱን ፈለግ ተከትለው በእግራቸው ጭምር የሚጫወቱ ግብ ጠባቂዎች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል። እነዚህ ግብ ጠባቂዎችም በታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች በብርሃን እየተፈለጉ ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት 44 ሚሊዮን ፓውንድ ገንዘብ በማውጣት አንድሬ ኦናናን ማስፈረሙ ይታወሳል። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዲሃያን በእግሩ አይጫወትም (ኋላ ቀር) ነው በማለት ነበር በኦናና የተኩት::

የባርሰሎናው ግብ ጠባቂ ማርክ አድሬ ቴር ስቴግንም ሌላኛው ዘመኑ የሚፈልገው ግብ ጠባቂ ነው። ቡድኑ ኳስን መስርቶ ሲጫወት ከሳጥን ውጪ ለባርሰሎና ተጨማሪ 11ኛ ተጫዋች ይሆናል። ጀርመናዊው ግብ ጠባቂ ኳስን በእግሩ የተካነ በመሆኑ ብዙ ቅብብሎችን ከሳጥን ውጪ ማድረግ ያስደስተዋል። በፍጥነትም አደገኛ ቅብብሎችን ማድረግ ይችላል።

ብራዚላዊው ግብ ጠባቂ ኤደርሰን ሞራኤስም ኳስን በእግሩ በመጫወት ልዩ እና ብቁ ሲሆን የተለየም እይታ አለው። ኤደርሰን ከአጭር ቅብብሎች በተጨማሪ ረጅም ቅብብሎችንም በማድረግ ይታወቃል። የሊቨርፑሉ ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከርም ቀዮቹ ኳስን መስርተው ሲጫወቱ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሰው ነው። በርካታ ግብ የሆኑ ኳሶችንም በቀጥታ አቀብሏል። ለአብነት ሙሀመድ ሳላህ ከአሊሰን ቤከር በተላከለት ኳስ በተደጋጋሚ  ኳስና መረብን አገናኝቷል።  ልክ እንደ ማንቸስተር ሲቲው ግብ ጠባቂ ከሳጥን ውጪ በእግሩ ብዙ ቅብብሎችን ባያደርግም ጨዋታዎች ከኋላ እንዲጀመሩ ግን ያደርጋል። በተመሳሳይ የሪያል ማድሪዱ ቲቦ ኮርትዋ፣ የአል ሀሊው ኢዱዋርድ ሜንዲ፣ የፓሪሰን ዥርማው ጂያሉንጂ ዶናሮማ፣ የሪያል ቢትሱ ክላውዲዮ ብራቮ ከዘመኑ ጋር የተዋሀዱ ዘመናዊ ግብ ጠባቂዎች መሆናቸውን  መረጃዎች ያመለክታሉ።

ግብ ጠባቂዎች በእግር ኳሱ ዓለም የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ቢወጡም በሽልማትም ሆነ በጥቅማ ጥቅም ከግብ አስቆጣሪዎች ጋር ተፎካካሪ ሆነው አይታዩም፤ለእጆቻቸው የተሰጣቸው ክብርም አነስተኛ መሆኑን በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል::የብዙ እግር ኳሳዊ ዋንጫዎች የስኬት ሚስጥር የሆኑት ግብ ጠባቂዎች ተገቢውን ክብር ማግኘት እስካልቻሉ ድረስ ተተኪዎችን ማፍራቱ ላይም ሥጋት ይፈጥራል::

የአሰልጣኞች ድምጽ ድረ ገጽን፣ፉት ቦል ኢንሳይደርን እና ቢቢሲ ሰፖርትን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here