ወንጀል የሰው ልጆች በሕይወት ዘመናቸው ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ከወንጀል አፈጻፀም ድርጊቶች አንዱ በሆነው እጅ ከፍንጅ ዙሪያ የፌዴራል አቃቢ ሕግ እና አቢሲኒያ ሎው በድረ ገጻቸው ያወጡትን መረጃ መሰረት አድርገን ለንባብ አዘጋጅተናል፡፡
እጅ ከፍንጅ የሚለው ቃል ትርጉም በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀው አማርኛ መዝገበ ቃላት ”አንድ ሰው ወንጀል በመፈፀም ላይ እንዳለ የመያዝ ሁኔታ ነው” በማለት አስፍሮታል:: እጅ ከፍንጅ ወንጀል ማለት ወንጀሉ እየተፈጸመ ያለ ወይም እንደ ተፈጸመ ወዲያውኑ ከሆነ ወይም ከተፈጸመበት ቅርብ ጊዜ እንደሆነ ይገልጻል:: ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሰው ከተሰረቀው ንብረት ጋር ከተገኘ ወይም ወንጀል ለመፈጸም ከሚያግዝ መሣርያ ጋር ከተያዘ ወይም ወንጀሉን ስለመፈጸሙ ከሚያረጋግጥ ማስረጃ ጋር ከተያዘ እጅ ከፍንጅ ወንጀል መሆኑን መረጃው አስፍሯል::
የእጅ ከፍንጅ አፈጻፀምን በተመለከተ በ1954 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በሰጠው ትርጉምም እጅ ከፍንጅ ማለት ወንጀል አድራጊው ወንጀሉን ለመሥራት ሲሞክር ወይም ወንጀሉን እንደፈጸመ ወዲያውኑ ሲያዝ ነው፡፡
ሌላው ወንጀል አድራጊው የወንጀሉን ተግባር ከፈፀመ በኋላ ወዲያውኑ ሲሸሽ ምስክሮቹ ወይም ሕዝቡ የተከታተሉት ወይም የሕዝብ ጩኸት እና እሪታ የተሰማ እንደሆነ ወንጀሉ እጅ ከፍንጅ እንደተፈፀመ እንደሚቆጠር የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አስፍሯል፡፡ ስለሆነም በሕጉ መሰረት አንድ ተጠርጣሪ አንድ ወንጀል ለመሥራት ሲሞክር፣ ሲሠራ ወይም ከፈፀመ በኋላ በቦታው ከተያዘ እጅ ከፍንጅ መሆኑን ሕጉ አስፍሯል፡፡
ወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በቁጥር 19 እንዳሰፈረው ደግሞ አንድ ወንጀል እጅ ከፍንጅ ተብሎ ሊጠቀስ የሚቻለው ወንጀሉ በተሠራበት ቦታ ወዲያውኑ ፖሊስ ከተጠራ እና ወንጀሉ ሲፈፀም ወይም እንደተፈፀመ ወንጀሉ ከተሠራበት ቦታ ላይ የድረሱልኝ እሪታ የተሰማ እንደሆነ ነው፡፡ ተጠርጣሪው ሲሸሽ በመከታተል የሕዝብ ጩኸት ከተሰማ፣ ወደ ቦታው ፖሊስ ወዲያውኑ ከተጠራ ወይም ተጠርጣሪውን ባይከታተሉትም በወንጀሉ ቦታ የድረሱልኝ እሪታ ከተሰማ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደ እጅ ከፍንጅ ወንጀል ይቆጠራል::
የወንጀል ምርመራ የሚጀምረው እንደዚህ ያለው ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ፍርድ ቤት የሚሰጠው የመያዣ ትዕዛዝ ሳይኖር በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 49 እና በተከታዮቹ ቁጥሮች መሰረት ወንጀለኛውን ለመያዝ ይቻላል:: በመሆኑም የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች በተፈፀሙ ጊዜ የግል አቤቱታ የማያስፈልጋቸው ከሆነ ምርመራ እና ተጠሪጣሪን መያዝ በአንድ ላይ ይጀምራል::
በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 50 በተገለፀው መሰረት ማንኛውም ሰው ወይም የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ የእጅ ከፍንጅ ወይም መሰል ወንጀል ከፈፀመ በቁጥር 19 እና 20 በተመለከተው መሰረት ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ ይቻላል::
በሌላ በኩል በሌሎች ሕጎች የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች ሠርተው በሕጉ በተለየ ሁኔታ የተቀመጠ ነገር ካልተሟላ በስተቀር ተጠርጣሪን መያዝ የማይቻልበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54 ንኡስ አንቀጽ ስድስት እንደሚገልፀው ማንኛውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈፀም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም::
በዚሁ ሕግ አንቀጽ 63 ንኡስ አንቀጽ ሁለት መሰረት ማንኛውም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈፅም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም፡፡
በመርህ ደረጃ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 32 በተጠቀሰው መሰረት ማንኛውም መርማሪ ፖሊስ ወይም የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ በፍርድ ቤት የተሰጠ የብርበራ ማዘዣ ካልያዘ በቀር መበርበር አይችልም:: ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ያለብርበራ ማዘዣ መበርበር የሚፈቀድለት ወንጀለኛውን እጅ ከፍንጅ ሲከታተሉትና ከቤት ውስጥ ሲገባ ወይም ወንጀል የሠራበትን ነገር ከቤት ውስጥ ያስቀመጠ ሲሆን ይበረበራል፡፡ በተከሰሰበት ወንጀል ወይም ወንጀል ሠርቷል ተብሎ በተጠረጠረበት ነገር ማስረጃ የሚሆን በሰውነቱ ደብቋል የሚያሰኝ በቂ ምክንያት ካለ የተያዘውን ሰው መፈተሽ ይቻላል:: እጅ ከፍንጅ ወይም መሰል ወንጀል እንደተፈፀመ በመከታተል ሰውነቱንም ሆነ ንብረቱ የተቀመጠበትን ቦታ መበርበርም ይቻላል፡፡
የእጅ ከፍንጅ ወንጀል በክስ ሂደት
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ በ109 ንኡስ አንቀጽ አንድ እንደሰፈረው አቃቤ ሕግ የፖሊስ ምርመራ መዝገብ በደረሰው በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት እንዳለበት ይገለፃል፡፡
የኢ.ፌዲ.ሪ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ መሰረት በማንኛውም የወንጀል ክስ ጉዳይ የተሟላ ማስረጃ እስከቀረበ ድረስ ማንኛውም የወንጀል ክርክር በተቀላጠፈ ሥነ ሥርዓት ሊመራ ይችላል::
የእጅ ከፍንጅ የሚቀርቡ ጉዳዮች በፖሊሲ በግልፅ የመወሰን ስልጣን የአቃቤ ሕግ እንደሆነ ይገለፃል፡፡ አቃቤ ሕግ በማስረጃ ይዘታቸው ውስብስብነት የሌላቸው የእጅ ከፍንጅ እና ሌሎች ወንጀሎችን የተፋጠነ ፍትሕ እንዲሰጥ ያግዘዋል:: ይህንም ሲወስኑ የወንጀሉን አጠቃላይ ባሕርይ፣ የማስረጃዎችን ይዘት እና ብቃት እንዲሁም የተጠርጣሪውን እና የተጎጂውን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል::
እጅ ከፍንጅ ችሎት ከሌላው የሚለየው በዕለቱ ሥራ መቀጠሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል በሕግ የተደነገገ፣ ማስረጃው የቅርብ የሆነ እና የወንጀል ምርመራው ፣ የክስና የፍርድ ሂደቱ የተፋጠነ በመሆኑ በተሻለ ሆኔታ ፍትሕን ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም