እጅ ያልሰጡ እጆች

0
32

ወጣት ባዘዘው ሙሉቀን የተወለደው በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ አካባቢ ነው:: እናቱ በ16 ዓመቷ ትዳር ይዛ ነበር:: ሆኖም ትዳር በመሰረተች በሁለት ወሩ በቤተሰብ ምክንያት ትዳራቸው ፈረሰ::

በዚህ ጊዜ ታዲያ ባዘዘው ሙሉቀንን ነፍሰ ጡር ነበረች:: ታዲያ ከተወለደ ጀምሮ  እስከ አራት ዓመቱ እናቱ ብቻዋን ነበር ያሳደገችው::  በኋላም ከአያቶቹ ጋር ትታው ሁለተኛ ባል አገባች:: ከሁለተኛ ባለቤቷ ጋር ትዳር ከመሰረቱ በኋላ አያቶቹ ጋር የተወችውን ባዘዘውን ከእንጀራ አባቱ ጋር ለማሳደግ ተስማምተው እናቱ ይዛው ሄደች::

ይሁንና ከአካባቢው ማሕበረሰብ እና ከእንጀራ አባቱ ጋር ሊላመድ ባለመቻሉ ብቻውን መሆንን ያዘወትር ነበር::

ከዕለታት በአንደኛው ቀን እናቱ ውኃ ቀድታ እስክትመለስ  ባዘዘው ሳይፈልግ አስገድዳ ጎረቤት ጋር  እንዲቆይ ትታው ሄደች:: ሆኖም ይህ ሁኔታ እንግዳ የሆነበት ባዘዘው የእናቱን እግር ተከትሎ እናቱን ፍለጋ ወጣ:: በማያውቀው ቀዬ እናቱን ቢፈልግም  ሊያገኛት አልቻለም:: በጠፋ በሦስተኛው ቀንም ቤተክርስቲያን  እንደጠፋ ተለፈፈ፤ በፍለጋም ተገኘ::

ሆኖም ምን እንዳጋጠመው ሳይታወቅ ከዛፍ ስር እግሮቹ ተሳስረው መንቀሳቀስ አልችል ብሎ ነበር:: ለአንድ ዓመትም ምንም መንቀሳቀስ በማይችልበት ሁኔታ           ቆየ:: ከዚያም ቆሞ እንደ እኩዮቹ ይቦርቅ የነበረ ልጅ በጉልበቱ ዳዴ ማለት ጀመረ::

ባዘዘው አደጋው እንደተከሰተ ሰሞን የአካባቢው ማሕበረሰብ ለአካል ጉዳት የነበረው አመለካከት የተዛባ ስለነበር ብዙ አስቀያሚ ነገሮችን ይናገሩ እንደነበር ያስታውሳል:: እናቱም ከዚህ ቅስም ሰባሪ ንግግር ልጇን ለማዳን ስትል ሁለተኛ ትዳሯን ፈታች፣ ብቻዋንም ማሳደግ  እንደ ጀመረች ባለታሪካችን ባዘዘው ይናገራል:: ከዚያም ልጇንም እንደልጁ የሚያሳድግ ሰው አገኘች እና ድጋሚ ትዳር መሰረተች::

ሦስተኛ ባሏን ስታገባ ባዘዘው የሰባት ዓመት ልጅ ነበር:: ይህኛው ባሏ ለባዘዘው ጥሩ አባት ሆነ፤ ሽመና ይሠራ ስለነበርም አብሮ ሥራውን እንዲለምድ ያበረታታው ነበር:: ይሁንና  ሁለተኛ የእንጀራ አባቱ አንድ  ወንድ እና አንድ ሴት ልጆችን እንደወለዱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዬ::

አባታቸው እንደሞተ ሕይዎት ከባድ ሆነበት:: እናቱ ብቻዋን አረቄ እያወጣች ልጆቿን ማሳደግ ስላልቻለችም ባዘዘው በ13 ዓመቱ የጀመረውን ትምህርቱን ሦስተኛ ክፍል እንደደረሰ ለማቋረጥ ተገደደ::

ከዚያም የባሕል አልባሳት የእጅ ጥልፍ መጥለፍን ተማረ፤ ትምህርቱንም በነጻ እንደሰለጠነ (ሰብዓዊነት ያሸነፋት አሰልጣኝ) ነው ባዘዘው የነገረን:: በዚህ ሥራም በቀን ከ100 እስከ 150 ብር እያገኘ ቤተሰቡን ማስተዳደር ጀመረ::

ከዚያም  የተሻለ ሕይዎት ፍለጋ ጥልፍ እየጠለፈ ካጠራቀመው ገንዘብ 140 ብር በመያዝ ወደ አዲስ አበባ አቀና:: መናኸሪያ ውስጥ ደግሞ ለትራንስፖርት ይሁንህ በሚል 150 ብር ድጋፍ አገኘ::

አዲስ አበበባ ለሁለት ቀናት አደባባይ ላይ ካደረ በኋላም “ሁኔታዬ ስላሳዘነው አንድ ልበ ቀና ሰው ሊረዳኝ ወሰነ” ሲል ያስታውሳል:: በመሆኑም ወደ አንድ ሆቴል ወስዶ ከጥበቃው ጋር ማደሪያ እንዲዘጋጅለት እና ከሆቴል የተረፈ ምግብ (ቡሌ) እንዲመገብ አመቻቸለት::

ባዘዘው ወደ አዲሰ አበባ ሲመጣ ሰው በሰጠው 150 ብር ማስቲካ  እና ሶፍት  በመግዛት የተጠጋበት ሆቴል አካባቢ መሸጥ ጀመረ::  ወረቱ እየሰፋ ሲመጣም የሞባይል ባትሪዎችን መሸጥ ጀመረ፤ ለአንድ ዓመት በዚህ ሁኔታ ከቆየ በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢው ያጠራቀመውን 19 ሺህ ብር ይዞ ተመለሰ:: በ17 ሺህ ብርም ከመኖሪያ ቀየው ላይ የጭቃ ቤት ገዝቶ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተደራጅቶ የጌጠኛ (ኮብል) ድንጋይ ማምረት እና ማንጠፍ ጀመረ::

ሆኖም ከባልደረቦቹ ጋር መግባባት ባለመቻሉ ሥራውን ለማቆም ተገደደ:: በምንም ነገር እጅ የማይሰጠው ባዘዘው ግን ከበፊቱ ሥራው የ7 ሺህ ብር ወረት ነበረውና በፍጥነት የሕጻናት ጫማን መሸጥ ጀመረ:: ነገር ግን ይህም ሥራ አልተሳካለትም:: የሚሠራበት ቦታ ተወረሰ፤ በዚህ ጊዜ ሰዎች ያለበትን ችግር በመመልከት ለምንድን ነው የምትለፋው? አንተ እኮ ቤተክርስቲያን አካባቢ ተቀምጠህ ብትለምን ሳትለፋ፣ ሳትደክም ብዙ ገንዘብ ታገኛለህ የሚል ምክር እና አስተያየት በየጊዜው ይደርሱት እንደነበር ያስታውሳል::

ይሁንና ባዘዘው የሰው ልጅ ሙሉ አካል እያለው እንዴት ሠርቶ አይበላም፤ አያድግም፤ የሚል ጠንካራ አመለካከት ስለነበረው ባሕር ዳር ለአንተ አይነት የአካል ጉዳተኞች ለሥራ ተስማሚ ናት፤ የሚል ምክር ሲሰማ ከሦስት ዓመት የአዲስ አበባ ቆይታ በኋላ ወደ ባሕር ዳር ተመለሰ:: ጊዜውም 2006 ዓ.ም ነበር:: አሮጌው መናኸሪያ አካባቢ ሶፍት፣ የእጅ አምባር ቀለበት፣ የጆሮ ጌጣ ጌጦችን እና ማስቲካ (ሱቅ በደረቴ) ጀመረ:: ሱቅ በደረቴውም ወገቡ ላይ ችግር ስለፈጠረበት ጋሪ በመግዛት ሥራውን አሰፋ፤  ቀስ በቀስም ካልሲዎችን፣ የውስጥ ሱሪዎችን መሸጥ ጀመረ::

በ2012 ዓ.ም ጥንካሬውን የምታደንቅለት ከጎኑ ሆና አይዞህ የምትለው ሴት አገኘ እና ትዳር መሠረተ:: በአሁኑ ጊዜም የሁለት ልጆች አባት ሆኗል::

ሠርቶ ማግኜት እየተቻለ መረዳት እንደሞት ይቆጠራል የሚል ዕምት ያለው ባዘዘው በርካታ ሥራዎችን ሞክሯል:: መጽሐፍ ተረክቦ ያከፋፍልም ነበር:: እንዲሁም መንግሥት እንደማንኛውም ሥራ አጥ ወጣት በሰጠው ሦስት በሁለት ስፋት ያላት ኮንቴይነር  ሽሮ ቤት በመክፈት ከባለቤቱ ጋር ይሰሠራ ነበር:: ባለቤቱ በወሊድ ምክንያት ሽሮ ቤቱን ማስቀጠል ስላልቻለች አሁን ላይ ቢያቆመውም ከእንጨት የተሠሩ ኩርሲዎችን እና ጠረጴዛዎችን በብድር እያመጣ በመሸጥ ይተዳደርበታል:: የጋሪ ላይ ንግዱም እንደቀጠለ ነው::

አካል ጉዳተኛነቱ ሳይበግረው ጋሪውን እየገፋ በባሕር ዳር ከተማ ዋና መንገዶች ላይ፣ ሰው የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ይታትራል::

ባዘዘው “ለአካል ጉዳኞች ከእርዳታ ይልቅ ብድር ነው የሚያስፈልገው:: ምክንያቱም ሕይዎትን ሊለውጥ የሚችል ብድር ነው:: ተበዳሪው  እዳውን ለመክፈል ሲል ጠንክሮ ይሠራል:: በእርዳታ የተጠመደ ግን ራሱን ሊያሻሽል አይችልም፤ የጠባቂነት መንፈስን ነው የሚያዳብረው:: ስለዚህ ለጋሽ ድርጅቶችም ይሁኑ  መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ከእርዳታ ይልቅ ብድር መስጠት ላይ ቢያተኩሩ መልካም ነው” ይላል::

ባዘዘው በመጨረሻም “መንግሥት ከወለድ ነጻ የሆነ ብድር ለአካል ጉዳተኞች ቢያመቻችልን መልካም ነው” የሚል መልዕክትም አስተላልፏል::

ባዘዘው ብዙዎች በረባ እና በልረባ ምክንያት “ሥራ የለኝም” በሚል ቤት ውስጥ እና አልባሌ ቦታዎች በሚያሳልፉበት ጊዜ ሥራን አክብሮ እና ወዶ የሚሠራ አካል ጉዳተኛ ልጅ ነው:: የሚመለከተው መንግሥታዊ አካልም ሆነ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ባዘዘውን እና መሰል ታታሪ ልጆችን ልታበረቷቷቸው ይገባል፤ የሚለው መልዕክት የጽሑፋችን ማሳረጊያ ነው::

አጋዥ

ሔለን ኬለር

 

በአ.አ.አ ሰኔ 27/1880 በአሜሪካ አላባማ በተባለች በትንሽ የገጠር ከተማ ውስጥ ተወለደች፡፡ ጨቅላ እያለች መስማት እና ማየትን ጨምሮ ሙሉ አካል የነበራት ልጅ ነበረች፡፡ ሆኖም በአንድ ዓመት ከሰባት ወሯ በደረሰባት የአዕምሮ ትኩሳት ዕይታዋን እና የመስማት ችሎታዋን አጣች፡፡

ይህ አካል ጉዳተኝነት ቢያጋጥማትም የመጀመሪያዋ መስማትና ማየት የተሳናት በአርት ባችለር ዲግሪ ማግኘት የቻለች ምሁር ለመሆን በቅታለች፡፡

ሔለን ኬለር ምናልባት አማካኙ ሰው ከሚያነባቸው መጻሕፍት አንድ መቶ እጥፍ ያነበበች፣ ዐሥራ ሁለት የራሷን መጻሕፍት የጻፈች፣ የራሷን የሕይወት ታሪክ የተመለከተ ፊልም የሠራች ታታሪም ናት፡፡

ስቴፈን ሀውኪንግስ

የመጠቀ አዕምሮ ያለው እንግሊዛዊው ስቴፈን በፊዚክስ እና በሕዋ ሳይንስ በርካታ ሥራዎችን ለዓለም አበርክቷል፡፡

ሃውኪንግ በ22 ዓመቱ /እ.አ.አ በ1963/ በደረሰበት አካላዊ እንቅስቃሴ መገደብ /የጭንቅላት ሞተር ነርቭ/ በሽታ ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ መኖር እንደማይችል ተነግሮት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ1985 እ.አ.አ የመናገር ችግር ገጥሞትም ነበር፡

ይሁን እንጅ ስቴፈን በገጠመው የጤና ችግር ሳይደናገጥ እና ሐኪሞች ከምርመራ በኋላ በነገሩት ሕክምና ውጤት ተስፋ ሳይቆርጥ እስከ ሕልፈቱ በዊልቸር በመንቀሳቀስ እና ለሱ ተብሎ በተሠራ ኮምፒውተር በመታገዝ በርካታ የምርምር ውጤቶችን ለዓለም አበርክቷል፡፡ 14 ትላልቅ ሽልማቶችም ተበርክተውለታል፡፡

ምንጭ፡-/worldcrutches.com/famous

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here